Saturday, 27 July 2013 13:27

የቀድሞ የመኖሪያ ቤት ማህበራት በአዲሱ መመሪያ እንዲደራጁ ይገደዳሉ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት የህብረት ሥራ ማህበራት፤ የቀድሞዎችም ሆነ አዲሶቹ ማህበራት በአዲሱ መመሪያ እንዲደራጁ ይገደዳሉ ተባለ፡፡ መስተዳድሩ ትላንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የማህበራቱ የአደረጃጀትና የምዝገባ መስፈርት ከ20/80 መስፈርት ጋር ሙሉ ለሙሉ እንደሚመሳሰልም ተናግረዋል፡፡ በመስተዳድሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሺሰማ ገ/ስላሴ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የማህበራቱ አደረጃጀትና ምዝገባ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ የሚለየው ማህበራቱ በራሳቸው ገንዘብ መገንባት መቻላቸውና ለተነሺዎች የካሳ ክፍያ ራሳቸው መክፈላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞዎቹ ማህበራት የተረጋገጡ ጉድለቶች እንደነበሯቸው የጠቆሙት ሃላፊው፤ ከነዚህም ውስጥ በህይወት የሌሉ ሰዎችን በአባልነት መመዝገብ፣ ህገወጥ መሬት እንዲገዙ ማድረግ፣ በተጓደሉ አባላት ምትክ ለሚገቡ አባላት አላስፈላጊ ገንዘብ መቀበል፣ ከግንባታ ፈቃድ ውጭ መገንባትና መሬትን ያለ አግባብ መውረር ይገኙበታል ብለዋል፡፡ ሃላፊው አክለውም፤ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ እንዳማራጭ የቀረበው የማህበራት የቤት ግንባታ መመሪያው ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ በአዲሱ መመሪያ መሠረት መስፈርቱን የሚቀርቡ ማህበራት መመዝገብ እንደሚችሉም ተብራርቷል፡፡ የመደራጃ ቦታዎችን በተመለከተ በመኖሪያ አካባቢ፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በንግድ ቦታዎች አካባቢ መደራጀት የሚቻል ሲሆን ለቀድሞ ማህበራት 16 አባላት፣ ለአዲሶቹ ደግሞ 24 አባላት እንዲያደራጁ መመሪያው ያዝዛል፡፡ ሠራተኛዬ ከደሞዙ ቀስ ብሎ ይከፍላል የሚሉ መስሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን በማህበራት አደራጅተው መገንባት ይችላሉም ተብሏል፡፡

ማህበራት የመነሻ ዲዛይን ከመንግስት የሚቀርብላቸው ሲሆን የከተማዋን ማስተርፕላን በጠበቀ መልኩ የዲዛይን ለውጥ ማድረግ ከፈለጉ የገንዘቡም መጠን እንደሚቀየር የተናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም ናቸው፡፡ አቶ ጌታቸው አክለውም፤ የቤቶቹ የግንባታ ዋጋ ግምትን በሚመለከት የቤቱ ግንባታ ፎቅ ሆኖ ባለ አንድ መኝታ 210ሺ፣ ባለ ሁለት መኝታ 280ሺ እና ባለ ሶስት መኝታ ክፍል 385ሺ ብር ሲሆን የዲዛይን ለውጥ ሲኖር ዋጋው እንደሚያቀያይርና የማጠናቀቂያ (Finishing) ስራን እንደማያካትትም ገልፀዋል፡፡ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በየኤምባሲው ምዝገባ የሚካሄድ ሲሆን በውጭ የሚኖሩና በአገር ቤት ያሉ አባላት ተቀላቅለው መደራጀት እንደማይችሉም ተነግሯል፡፡ መመሪያው ከሀምሌ 15 ጀምሮ ምዝገባ ይካሄዳል ተብሎ እስከዛሬ የቆየው ጠቃሚ ሀሳቦችን እንዲያካትትና መጠነኛ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ የተናገሩት ሀላፊዎቹ፤ ለባከኑት ቀናት ተመጣጣኝ ቀናትን እንጨምራለን፣ ቀኑን ዝግ አላደረግንምም ብለዋል፡፡

ክፍያውን ሙሉ ለሙሉ መፈፀም የሚችሉና በ40/60 ተመዝግበው ወረፋ የሚጠብቁም ወደ ማህበራቱ በመምጣት በ40/60 ላይ ያለውን ወረፋ ቀለል ማድረግ ይችላሉም ተብሏል፡፡ ማህበራቱ የመጀመሪያ ስራቸው ማደራጀትና መመዝገብ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ መስፈርቱን አሟልተው ለመጡ ምዝገባው ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ የማህበራት ማጭበርበሮች እንዳይካሄዱ የአሻራ ምርመራም እንደሚካተት ተገልጿል፡፡ ማህበራት አባሎቻቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሆናቸውን፣ የትም ቦታ ቤት የሌላቸው መሆኑን፣ እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ መሆኑንና 50 በመቶ ቅድሚያ መክፈል የሚችሉ መሆኑን በአፅንኦት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የካሳ ተመንን በተመለከተ በግለሰቦች ሳይሆን በካቢኔ የሚወሠን ስለሆነ ለሙስናም ሆነ ለአድልኦ የተጋለጠ እንደማይሆን ሃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

Read 19464 times