Saturday, 20 July 2013 11:50

ወይሳና ወቀሳ - በ”መልክአ ስብሃት”

Written by  ከኃይለጊዮርጊስ ማሞ
Rate this item
(3 votes)

ከአዘጋጁ በደራሲና ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገላጋይ ሃሳብ ጠንሳሽነትና አርታኢነት፣ 30 የጥበብ ባለሙያዎች በደራሲ ስብሐት ገ/እግዚብሄር ህይወትና የድርሰት ሥራዎች ዙርያ የፃፉትን ፅሁፎች የያዘ “መልክአ ስብሃት” የተሰኘ መፅሃፍ ባለፈው ሰኞ በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ተመርቋል፡፡ በመፅሃፉ ላይ አስተያየት ወይም ሂስ በቅርቡ እንደምናስነብብ እየገለፅን እስከዛው ግን ለቅምሻ ያህል ተከታዮቹን ፅሁፎች ቀንጭበን አቅርበናል፡፡ መንደርደሪያ “I a Senior Citizen, Lost in their `golden` world of youth, Not sure how or why I strayed this way.” Sebhat G/Egziabher ይህንን ከላይ ያሰፈርኩትን አባባል ጋሽ ስብሃት የእርሱ ትሁን ወይም ከዘመናት ንባቡ ከአንዱ (ነገር ግን ከየት እንዳገኘው ከዘነጋው) የቆነጠረው ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን የዛሬ ሁለት ዓመት ህይወት በምድር ካዘጋጀችልን ዕጣ ፈንታ በአንዱ መንገድ አገናኝታን፣ ለጥቂት ወራት በተደጋጋሚ እየተገናኘን ከትዝታዎቹ ሲያወጋኝ በነበረበት ወቅት ድንገት በብጣሽ ወረቀት ከትቦ ከእጄ እንዳስቀመጣት ትዝ ይለኛል፡፡

ዛሬም እንደ ቁም ፀሐፊ በጥንቃቄና በሥርዓት ፊደላቱን ሰድሮ ያስቀመጠበትን ቁራጭ ወረቀት አልፎ አልፎ ስመለከት፣ የስብሃትን የእድሜ ምሽት ጥያቄ ይዞ ከእኔ ጋር የመቀመጧን ሚስጥር ለማወቅ መሻቴ አልቀረም፡፡ ሰሞኑን የእኛ ማህበረሰብ ለአዛውንቱ (ለዕድሜ አንጋፋው ትውልድ) የሚሰጠውን ስፍራና ክብር ለስብሃት የሰጠው በቀብሩ ሥነ - ሥርዓት ላይ ብቻ ነው የሚል ስሜት ሳያድርብኝ አልቀረም፡፡ እርግጥ ነው እሱም በዘመኑ ይህን ሥፍራና ክብር አስቦትም ሆነ ተመኝቶት እንደማያውቅ በእነዚያ ጥቂት ወራቶች ውስጥ ካወጋኝ የውስጡ ሃቅ እና እምነት በሚገባ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ለዚህም ነበር “እኔ የማህበረሰቡ አዛውንት፤ በእነሱ ወርቃማ የወጣትነት ዓለም የጠፋሁ፤ እንዴት እና ለምን በዚህ መንገድ እንደባከንኩ እርግጠኛ አይደለሁም” በማለት የተነፈሰው፡፡

በተደጋጋሚና በየመድረኩ የሞትን ያህል እርጅናን እንደሚፈራ ሲናገር የኖረው ስብሃት፤ እርጅናን ሳያያት እንደሞተ በእሱ ልብ ውስጥ የነበረው እሳት ሲፈጀው የኖረው የትውልዱ ቀዝቃዛ ልብ ምስክር ነው፡፡ ወደ ቦታህ ተመለስ በማለት ስብሃት ከተለያየ አቅጣጫ ለዓመታት ሲሰነዘርበት የኖረውን “ታላቅ ቁጣ” “በታናሽ ምፀት” ሲመልስ መኖሩን ዛሬ ላይ ቆመን ስናስብም የከሳሾቹን መብከንከን “በዳኛ ትዕግስት” እየተመለከትኩ ኖሬያለሁ (ዜን፤ ቅጽ 1 ቁጥር 3) የማለቱን አባባል በቅጡ እንድንረዳው የሚያግዘን ይሆናል፡፡ ስብሃት የማንም ቁጣ ደንታ የሚሰጠው ሰው አለመሆኑን በየመድረኩ ተጠይቆ ይሰጣቸው ከነበሩ ምላሾች መገመት ይቻላል፡፡ ለነገሩ ስብሃት እንኳን በሩቁና በስነጽሑፍ ስራዎቹም የሚያውቁት ቀርቶ አብረውት ለመኖር እድሉን ያገኙት ውስጣዊ ማንነቱን ብሎም እምነቱን ተረድተውት ነበር ብሎ ለመገመት ያስቸግራል፡፡ በማንኛውም መልኩ ቢሆን ስብሃት በማህበረሰቡ የተሰጠውን ስፍራ ግድ ሳይል፣ በራሱ ስፍራ ህይወትን አጣጥሟት አልፏል፡፡ ምስጋናም ሆነ ነቀፋ ለእሱ በህይወትም ቆሞ ግድ አልሰጡት፤ ከዚህ በኋላም አያስጨንቁትም፡፡

በእሱ አገላለጽ ሳስቀምጠው “ምናልባት ስም የሚባለው ነገር ከሞት በኋላ ሳይሰማኝ የሚኖር ነገር ይሆን እንዴ? ለምንድነው ሰው ሁሉ ለታሪክ የሚጨነቀው? ጃንሆይ ለታሪካቸው ሲጨነቁ ይገርመኝ ነበር፡፡ ስም ከመቃብር በላይ ይውላል ሲባል እኔ እዚህ የለሁ፤ ዋለ አልዋለ ስሜን ጠሩኝ አልጠሩኝ ምኔም አይደል፡፡” (ኢሜጅ፤ ቅጽ 1 ቁጥር 1 ሚያዚያ 1998 ዓ.ም) ለእሱ ስም ማለት በአካላችን ላይ እየበቀለ፣ ነገር ግን ሲቆረጥ እንደማይሰማን ጥፍርና ፀጉራችን ነው፡፡ ከእኛ ውስጥ ሲወጣም ቆርጠን የምንጥለው ትርፍና አላስፈላጊ ኮተት፡፡ ይህን ኮተት ነው እንግዲህ በፈርጁ ሸክፈን በማንሳት የስብሃትን የቀደመ ህይወት የምንዘክረው፡፡ …

                                         ***

ሚካኤል ሽፈራው …ዘነበ ወላ የስብሐትን ህይወት በዘከረበት መጽሐፉ ላይ የስብሐትን የድህነት ህይወት አንስቶ እንዲህ ባለ ድህነት ሲኖር ያየነው አንድ ሰው ማህተመ ጋንዲ ብቻ መሆኑን ያወሳል፡፡ ዘነበ ወላ እንዳለው በእርግጥ ማህተመ ጋንዲን ከሚገልፁት ማንነቶቹ አንዱ በገዛ ፈቃዱ የመረጠው የድህነት ህይወት ነው፡፡ ጋንዲ ይህን ህይወት የመረጠው የሃሳብና የእምነት ነጻነቱን ለመጠበቅ፣ ሁሉም ነገር በጁ ሳለ ከሁሉም የፈቃድ እስራቶች ራሱን ነፃ ለማድረግ ብቻ ነው፡፡ ጋንዲ እንደኛ ስብሐት በብዙ የሥጋ ፈቃድ ትብታቦች ታስሮ፣ ዘወትር በኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የሚኖር ያለፈቃድ የደኸየ ነዳይ በመሆኑ አልነበረም፡፡ ስብሐትን ስናውቀው ለዕለት ጉርስ አረቄና እጸ ፋርስ ሲኖረው የሚያካፍል፣ ሳይኖረው የሚካፈል ዘወትር ከኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ወጥቶ የማያውቅ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ የስብሃትና የጋንዲ ድህነት በእጅጉ የተለያዩ ናቸው፡፡ ጋንዲ ገንዘብን በማፍራትም ሆነ በማስተዳደር በኩል በዲሲፕሊኑ የሚተካከለው አልነበረም፡፡

ጋንዲ ገንዘብን ባግባቡ ማስተዳደር አለመቻል ከኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ አልከተተውም፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከሚመጣ የሰብዕና ቀውስ ውስጥ የሚከትት ወደ ታላቁ እውነት በሚወስደው መንገድ ላይ ከሚደነቀሩ ደንቃራዎች አንዱ እንደሆነ ጠንቅቆ የሚያውቅ የዲሲፕሊን ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ነገር ጋንዲ አገሩን በምሳሌነት ለመምራት ሲል ፈቃዱን የወሰነ፣ የገዛ ራሱ ገዥ እንጂ ከቶም ደሃ አልነበረም፡፡ ከዚህም በላይ ጋንዲ ፈቃዱን መወሰኑ እንዲሁ ለልማድ ሳይሆን አስተሳሰብና እምነቱን ነጻ አድርጐ አገሩን ህንድን ከምእተ አመታት ቅኝ ግዛት፣ ራሱን ደግሞ ከስጋዊ ባህሪያት ጨለማና ግዞት ነፃ ለማውጣት ሲል የመረጠውና በፍጹም ዲሲፕሊን የኖረው መንገድ ነበር፡፡ ጋንዲ ከደቡብ አፍሪካ ወደ አገሩ ሲመለስ ያገሩ ሰዎች አዋጥተው የሰጡትን እጅግ ብዙ የሆነ ገንዘብ ላለመለወጥ ሲል በክብር የመለሰ የእምነት ሰው ነው፡፡ በዘመኑ ሁሉ በባህላዊ ልብስና በእፍኝ ሩዝ ለመኖር ሲወስን፣ ላገሩ ሰዎች ፈቃዳችንን ከገዛንና በተመጠነ ህይወት ለመኖር ከወሰንን የሃጢያት ሁሉ ስር ከሆነው ከምኞት ነፃ መሆናችንን እንደ ክርስቶስ ማስተማሩ ነበር፡፡

ይህ መንገዱ ያለመተባበር ፍልስፍና (Non cooperation) አስተሳሰቡ አካልም ነበር፡፡ “እኛ ህንዳውያን ቅኝ ገዢዎቻችን ለፈጠሩልን የህይወት ማደንዘዣ ተገዢዎች በመሆናችን፣ በገዛ አገራችን ለሚያመርቷቸው ምርቶቻቸው፣ ለጨርቆቻቸውና ለጣፋጭ ምግቦቻቸው ምርኮኞች በመሆናችን፣ ለቅኝ ተገዥነታችን ተባባሪዎች ሆነናል” የሚል ነበር የጋንዲ አስተምህሮ፡፡ በዚህም ሰበብ ባለመተባበር ፍልስፍና እንግሊዞቹን በህንድ ለመቆየት የሚያስችላቸው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንዲያጡ ለማስገደድ ሲል ነበር የፈቃድ ውሱንነትን ከመርሆቹ እንደ አንዱ የወሰደው፡፡ ለወንድሜ ለዘነበ ወላና ስብሐትን ከጋንዲ ለሚያነጻጽሩ ሌሎች ወንድሞቼ ምናልባት እነርሱ ራሳቸው የሚያውቋቸውን ጥቂት እውነቶች ስለጋንዲ ልጨምርላቸው፡፡ ማህተመ ጋንዲ በተለይ ስለወሲባዊ ፈቃድ የነበረው እምነትና ዲሲፕሊን ብራህማቻሪ የሆነ ወይንም በመጨረሻዎቹ ዘመናት በጋብቻ ውስጥ ሳለ ከወሲባዊ ግንኙነት ነፃ የሆነ ህይወትን የመረጠና ይህንን መፈፀም የቻለ ታላቅ ሰው ነው፡፡ እውነትን በማጭበርበርና በመጋረድ ረገድ ታላቅ አቅም እንዳለው በማመን በስጋ ፈቃዱ ላይ ታላቅ ስልጣን የተቀዳጀና የፈፀመ፣ በሰው ልጅ ውስጥ እግዚአብሔር የፈጠረውን መለኮታዊ ሃይል መቀስቀስና ማንቃት የቻለ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ ስብሐትን በነዚህ የጋንዲ መርሆችና ባህሪዎች የመመልከቱን እና የመመዘኑን ተግባር ለናንተ ልተው፡፡

እሸቴ አሰፋ (እሸቴ ከጃንሜዳ) ስብሃት ሆዬ እንግዲህ አንዳንድ ጊዜ ቡና ቤት ግርግር ካለበት ቦታ ይሄዳል፡፡ ያንንም ቁጭ ብሎ ይቃኛል፡፡ እዚያ ላይ ሞቅ ያለው ሰው ያገኘ ጊዜ ንግግሩን ይከታተለዋል፡፡ “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጠዋል” ነውና ደብቋት አፍኗት የነበረችውን ዕውነት ሲሞቀው ያወልቃታል፤ ያወጣታል፤ ይወረውራታል፡፡ ስብሃት የሚኮረኩረው ያገኘ ጊዜ አባባሉን በማስታወሻ፣ ካልሆነም በአእምሮው ይቀልባታል፡፡ ነከራት ማለት ነው፡፡ ከዚያ ታቆነጉላለች፣ ታብጣለች፣ ያዳብራታል፤ በዝታ ታፈራለች፡፡ የጠጭ ብቻ ሳይሆን ስሜቱን ከነካው የማንንም ቢሆን ያጠነጥነዋል፡፡ አሁን አንድ ጊዜ በመንገድ ሲያልፍ ዓይነስውር ሴት ሲለምኑ ይሰማቸዋል፡፡ የሰው ኮቴ ሲሰሙ “ስጡኝ” በማለት የሚለምኑት ሴትዮ፤ ኮቴ ካልሰሙ ግን “ኤሊን ድንጋይ ያለበስክ አምላክ” እያሉ ለብቻቸው ሲነጋገሩ ይሰማቸዋል፡፡ ተጠግቶ ተከታተላቸው፡፡ በኋላ በዚህ ተንተርሶ “ኤሊን ድንጋይ ያለበስክ” በሚል ርዕስ አጭር ልቦለድ ጻፈ፡፡ አንድ ወቅት ደግሞ የመነን መጽሔት ዋና አዘጋጅ “እባክህ እስቲ በክረምት ውሃ እያንቦጫረቁ እግረኛ ላይ ስለሚከልሱት ዘገባ ጻፍ” ይለዋል፡፡ ስብሃት “ዘገባ ከማቅረብ ይልቅ ይሻላል” ያለውን ልቦለድ ጻፈ፤ “ቦርጨቅ” በሚል ርዕስ፡፡ ደራሲ ስብሃት ብዙ ጽሑፎች በብዙ ምክንያት ጽፏልና ያን ሁሉ መዘርዘር ማወቅም ያዳግታል፡፡ ለማለት የተፈለገው ግን “ብዙ ጊዜ ድንገት ከሚገጥሙት ሁኔታዎች በመነሳት ይጽፋል” ነው፡፡

ጽፎ ሲጨርስ ድርሰቱን ያነበዋል፤ ያን ጊዜ ያልዘራ መስሎ ሲታየው ከፊቱ ዘወር ያደርገዋል፡፡ በድጋሚ እይታው እልቡ ካልደረሰ እርግፍ አድርጐ ይተወዋል፤ ዳግም ላይመለስበት፡፡ ስብሃትን ብዙ ሰው የሚያውቀው በአጫጭር ልቦለዶቹ እንጂ በልቦለዶቹ አይደለም፡፡ እኔ ግን እስካሁን ሁለቱን ነገርኳችሁ፡፡ ከነዚህም ሌላ ከተጀመረ አስራ ሁለት አመት የሆነው ለመጠናቀቅ ትንሽ የሚቀረው ልቦለድ እየጻፈ መሆኑ ይታወቅ፡፡ ለመሆኑ አጫጭር ልቦለድ በመጻፍ ለምን አተኮረ? ስብሃት እንዳለው እኔም ልበልና “የመንደሪን ዛፍ ብርቱካን አፈራ” እንደሚባል ሁሉ፤ አጭር ልቦለድ ፀሐፊውን “ለምን ረጅም አትጽፍም?” የረጅም ደራሲውንም “ለምን አጭር አትጽፍም?” ማለት አይቻልም፡፡ ግን ከዚህ ሌላ፤ ደራሲ ስብሃት በአጭሩ ለመጻፍ ያተኮረበት ምክንያት አለው ለራሱ፡፡ ህብረተሰባችን ካሁን በፊት ብዙ የማንበብ ልምድ አለማካበቱ፤ ተረታተረት ለለመደ ህዝብ ረጅም ነገር ለማንበብ ስለማያስበው ለኛ ሰው የተመቸ ስለሚመስለው ነው፡፡ ሁሉም እንደችሎታው መጻፍ እንዳለበት የሚያምነው ስብሃት ገጣሚም ነው፡፡ እሸቱ ዱብ …ስብሀት “ለማዝናናት” እንደሚጽፍ ሌላ ተልዕኮ እንደሌለውም ተናግሯል፡፡ የተናገረበት መንፈስ ሁነኝ ተብሎ በስነ ጥበብና በሳይንስ መካከል ያለው ልዩነት ላይ መስመር ለማበጀት ሳይሆን ከሱና ከዘመንተኞቹ “ወርቃማ ጊዜያት” ጀምሮ ዛሬ የደረሰውን “የማስተማርና የማዝናናት” ክርክር ለመመለስ ነው፡፡

ስብሀት ለማዝናናት ሲል እንደ በዓሉ እና ሌሎቹ “ለመልዕክት” አይደለም ማለቱ ነው፡፡ አለማየሁ ገላጋይ “ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ክህሎትና ህይወት” በሚለው መጽሐፉ ላይ ስብሀትና ዳኛቸው ወርቁ የተገናኙበትን አጋጣሚ ሲገልጽ በዚሁ “አርት ለአርት ሲባል” እና “አርት ለመልዕክት” በሚል ክርክር ላይ የጠፋን ሰው ተክቼ መድረክ ላይ እንድገኝ ከተጋበዝኩ በኋላ ነው… ስብሀት ማለቱን አስነብቦናል፡፡ ያኔ ስብሀት ምን አቋም ይዞ እንደተከራከረ ባይገለጽም በዚያው መጽሐፍ ላይ “አርት ለአርትነቱ” የሚል አቋም ያላቸው ሰለሞን ዴሬሳና ስብሀት ብቻ መሆናቸው በመገለፁ፣ ያንን መጽሐፍ ደግሞ ስብሀት ይሁንታውን የሰጠበት እንደሆነ ስለማስብ ይሁነኝ ተብሎ በተያዘ አቋም በስብሀት ምልከታ “ማዝናናት” የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ቢያንስ “የማስተማር” ተቃራኒ መሆኑ ነው፡፡ ለኔ ለአርትነቱና ሁነኝ ተብሎ ለተመረጠ መልዕክት (ትምህርት) እየተባለ በሰፊው በመገናኛ ብዙሃኑ የሚወሳው ሃሳብ ውሃ የሚያነሳ ትርጉም የለውም፡፡ ጽንሰ ሃሳቦቹም ፈጽሞ በማይገልጿቸው ቃሎች እንደተገለፁ አስባለሁ፡፡

“ማዝናናት” ምንድነው? ይህ የትኛውም ለመነበብ የሚጽፍ ደራሲ የማይታለፍ አላማ አይደለም? “ማስተማር”ስ ምን ማለት ነው? ይህ ቃል እንዲወክል ተደርጐ ሰርክ የሚታየው፣ ቀድሞ ታስቦበት የተመረጠ ጭብጥ አለህ እንደማለት ሆኖ፣ ይህንን መንፈስ የያዙ ምላሽ ሲሰጥ ይታያል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ፀሐፊዎቹም ሲመልሱ የኖሩት የሚጽፉበትን ምክንያትና ሂደት (motive and process) ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስብሀትን ላራምደው የምፈልገው ፍልስፍና፣ ልነግረው የምፈልገው መልዕክት የለኝም፡፡ ታሪክ የምነግረው መጫወቻ (fun) ለመስጠት ነው ማለቱ ደካማ ነው ጠንካራ? አሁንም የእሴት ጉዳይ ሆኖ የአንድ ደራሲ አላማ ሊሆን ይችላል፡፡ መፃፍ ለመፃፍ ብቻ ወይም “art for art sake” ይሉት ሀሳብ ግን ሁለት መስመር ላባክን የማልፈልግበት፣ ራሱን እንኳን በቅጡ ለመግለጽ የማይበቃ ሃሳብ ነው፡፡ ምክንያቱም መፃፍ ሲጀምር ውሳኔ ይፈልጋል፡፡ ውሳኔ ደግሞ ምርጫ፡፡ ምርጫ ደግሞ እሴት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ደራሲ ፈጽሞ ረብ የለሹን መምረጥ ይችላል፡፡ ሁሉንም የስነ ጽሑፍ እሳቤዎች ምንም ምክንያት ሳያቀርብ መካድ ይችላል…ለዚያም “art for art sake” የሚል ስም ሊሰጠው ይችላል - ምንም ቢያደርግ ግን ቢያንስ የራሱ እሴቶች እስረኛ መሆኑ አይቀርም፡፡ እኔም ሌሎች ልሰርህ ሊሉኝ በሚችሉት ነፃነቴ ውስጥ ግልጽ ሆነው በሚታዩኝ እሴቶች፣ ስብሀትንና የሱን ናቹራሊዝም (ተፈጥሮአዊነት) እንዲህ አየዋለሁ፡፡…

Read 2512 times