Print this page
Saturday, 20 July 2013 10:37

የሁለት ታላላቅ ሳይንቲስቶች ወግ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(7 votes)

“ሥራውን በሌሎች አሠራው፤ ምስጋናውን ግን አንተ ውሰድ”

ስመ ጥሩው ፈረንሳዊ ጦረኛ መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት፣ “ድል የአይታክቴ ሰዎች ናት” ሲል መናገሩን ታሪክ መዝግቦለታል፡፡ ልክ እንደ ናፖሊዮን ሁሉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍራንክሊን ሩዝቬልትም “ከስኬት የሚያግደን ነገር በገሃዱ አለም የሚያጋጥመን እንቅፋት አይደለም፡፡ ይልቁንስ በአዕምሮአችን ውስጥ ስለ ችሎታችን ያለን የጥርጣሬ ሃሳብ ነው” በማለት እንደተናገሩ እስከ ዛሬ ድረስ ይጠቀስላቸዋል፡፡ የእነዚህ ታዋቂ መሪዎች ንግግር የያዘው መልእክት ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም - ቀላልና ግልጽ ነው፡፡ ንግግሮቹ የሰው ልጅ ልቡ ያሰበበት ቦታ ለመድረስና ከፍተኛ ስኬትን ለመጐናፀፍ፣ በከፍተኛ የራስ መተማመን ስሜት ያለመታከት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት የሚያስገነዝቡ አባባሎች ናቸው፡፡

እንደ አብዛኛው የአለማችን ህብረተሰቦች፣ ይህን መልዕክት ለኮንጐ (ዛየር) ሰዎች ቢነግሯቸው፣ ሀሰት ነው ብለው አይከራከሩም፡፡ ነገር ግን “ኤሊ፣ ዝሆንና ጉማሬ” የተሰኘውን የሀገራቸውን እድሜ ጠገብ ተረት በመተረክ ከተጠቀሰው መልዕክት በተጨማሪ የሰውን ልጅ ወደ አለመው ግብ አድርሶ ስኬትን የሚያጐናጽፍ አንድ ሌላ ዘዴ ወይም መንገድ እንደሚያውቁ ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ተረቱ የሚተርከው፣ እሱ መስራት የሚገባውን ስራ፣ ዝሆንና ጉማሬን በማሰራት ያለመውን ግብ መምታትና ስኬትን መጐናፀፍ ስለቻለው ኤሊ ነው፡፡ ኮንጐአውያን በዚህ ተረት አማካኝነት የሚያስተላልፉት የስኬት ዘዴ ወይም መንገድ “ለስኬትህ የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ ሌሎች እንዲሰሩልህ አድርግ፡፡ ስኬቱን ግን አንተው ብቻ ተጐናፀፍ” የሚል ነው፡፡ ይህን ግልጽ ለማድረግ የቀረበው ማብራሪያ ደግሞ እንዲህ ይላል - “አላማና እቅድህን ከግቡ ለማድረስ የሌሎች ሰዎችን ጥበብና ችሎታ፣ ክህሎትና ጉልበት ሳታመነታ ተጠቀም፡፡ ይህን ማድረግህ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነውን ጊዜህንና ጉልበትህን መቆጠብ ብቻ ሳይሆን አማልዕክቶች ብቻ እንዳላቸው አይነት ጥራትና ፍጥነት እንዲኖርህ ያደርግሃል፡፡

ይህም ሌሎች ሰዎች ጨርሶ የሌላቸውን ልዩ ግርማ ሞገስ ያጐናጽፍሃል፣ የማታ ማታም ስራውን የሰሩልህ ሰዎች ወዲያውኑ ሲረሱ፣ አንተ ግን ሁሌም እየታወስክና ስምህ በስኬት እየተጠራ ትኖራለህ፡፡ እናም ሌሎች ሰዎች ላንተ ሊሰሩልህ የሚችሉትን ስራ አንተ በፍፁም አትስራ፡፡” ይህ የስኬት መንገድና ማብራሪያው ከመጀመሪያዎቹ የናፖሊዮንና የሩዝቬልት መንገዶች ጋር ሲነፃፀር፣ የስነምግባር ክርክር እንደሚያስነሳ ቅንጣት አያጠራጥርም፡፡ የዚያኑ ያህልም ሰዎች ስኬትን ለመጐናፀፍ ባደረጉት ጥረት ውስጥ ይህኛውንም ዘዴ በመጠቀም የተመኙትን ስኬት መጐናፀፍ እንደቻሉ ጨርሶ መካድ አይቻልም፡፡ በአለማችን በተለያየ የሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ስኬትን በመቀዳጀት ታላቅ ዝናና ፀጋ የተጐናፀፉ ሰዎች፣ የህይወት ታሪክ የተፃፈበትን መዝገብ በጥሞና ብንመረምር፣ በአንዱ ወይም በሌላኛው ምዕራፍ ውስጥ ኮንጐአውያን በተረታቸው በጠቀሱት የስኬት ጐዳና የተጓዙ በርካቶች እንዳሉ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ አለማችን ከቶማስ ኤዲሰን የበለጠ እጅግ በርካታ የፈጠራ ውጤቶችን ሊያበረክትላት የቻለ ሌላ የፈጠራ ባለሙያ እስከዛሬ ድረስ ጨርሶ አላገኘችም፡፡ የካቲት 11 ቀን 1847 ዓ.ም በኦሀዮ ግዛት የተወለደው አሜሪካዊው ቶማስ አልቫ ኤዲሰን፣ በህይወት በቆየበት ሰማኒያ አራት አመታት ውስጥ አንድ ሺ ዘጠና ሶስት የፈጠራ ውጤቶችን የፈጠራ መብት (Patent) በስሙ በማስመዝገብ፣ የአለምን ሬከርድ እስካሁንም ድረስ የጨበጠ የፈጠራ ሰው ነው፡፡

በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ስኬትንና አለማቀፋዊ ዝናን መጐናፀፍ ችሏል፡፡ በስሙ ያስመዘገባቸውን እነዚያን ሁሉ የፈጠራ ውጤቶች በስራ ላይ እንዲውሉ ባያደርግ ኖሮ፣ አለማችን የዛሬዋን አለም እንደማትሆን መገመት አያዳግትም፡፡ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ አምፑልን እሱ ባይሰራው ኖሮ፣ የአዳምን ዘር ማን ከኩራዝ ጭስ ይገላግለው እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በአለማችን የመጀመሪያ የሆነውን የኢንዱስትሪ ምርምር ላቦራቶሪ ያቋቋመውም ቶማስ ኤዲሰን ነበር፡፡ በ1880ዎቹ አመታት ሰርብያውያን “እንዲያው መጨረሻውን ሳያሳየን አይግደለን” እያሉ ለአምላካቸው ስለት የሚቋጥሩለት እንደ ኒኮላ ቴስላ ያለ ወጣት ሳይንቲስት አልነበራቸውም፡፡ ያኔ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰርቢያውያን፣ ወጣቱ ኒኮላ ቴስላ ድንቅ የፈጠራ ውጤቶችን በመስራት፣ እነሱንና ሀገራቸውን በድፍን አለሙ ዘንድ ለዝንተ አለም ሲያስጠራ ይኖራል ብለው በእጅጉ ይተማመኑበት ነበር፡፡ ሰርቢያውያን ኒኮላ ቴስላን እንዲህ ቢተማመኑበት በእርግጥም እውነታቸውን ነበር፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቄስ ከነበሩት አባቱና የቤት እመቤት ከሆኑት እናቱ ሰኔ 10 ቀን 1856 ዓ.ም በዛሬዋ ክሮኤሽያ ውስጥ የተወለደው ቴስላ፤ የላቀ አስተሳሰብና ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ ባለቤት መሆኑን ያስመሰከረው ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነው፡፡ ኒኮላ ቴስላ ከዚህ በተጨማሪም ቀላል የማይባል የግጥም ችሎታ ነበረው፡፡

ኦስትሪያ ግራዝ ከተማ ከሚገኘው የቴክኒክ ዩኒቨርሲቲና ፕራግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኢንጂነሪንግ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ የ “Rotating Magnetic field” ን ግኝት በማግኘት የፈጠራ ባለቤትነቱን በስሙ በማስመዝገብ፣የፈጠራ ችሎታውን አሀዱ ብሎ ለመላው አለም ማሳየት ችሏል፡፡ በመቀጠልም ባለ ሶስት ፌዝ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ሲስተም፣ የኤሌክትሪክ ሞተሮችና፣ ትራንስፎርመሮችን በመስራት ሰርቢያውያንን አጀብ አስባላቸው፡፡ በአለምአቀፉ የኤዲሰን ኩባንያ የፓሪስ ቅርንጫፍ ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ከጀመረበት ከ1882 ዓ.ም ጀምሮ አብረውት ይሰሩ የነበሩ ባልደረቦቹም ቴስላ ልዩ የሆነ የአስተሳሰብና የፈጠራ ችሎታ እንዳለው በግልጽ ይመሰክሩለት ነበር፡፡ በተለይ ይሰራበት የነበረው የኤዲሰን ኩባንያ የፓሪስ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጁና የቶማስ ኤዲሰን የቅርብ ጓደኛ የነበሩት ቻርለስ ባችለር፣ የወጣቱ ሰርቢያዊ ሳይንቲስት የኒኮላ ቴስላ የምር አድናቂ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ቻርለስ ባችለር፣ ቴስላ ሙሉ ችሎታውን አውጥቶ ለመጠቀም በወቅቱ አውሮፓ የምትመች ቦታ አይደለችም ብለው ያምኑ ነበር፡፡ እናም ፓሪስን ለቆ ለሳይንቲስቶችና ለፈጠራ ባለሙያዎች በእጅጉ የምትመች ሀገር ናት ወደሚሏት አሜሪካ ለመሄድ ፈቃደኛ ከሆነ፣ ከቶማስ ኤዲሰን ጋር እንዲገናኝና የፈጠራና የምርምር ስራዎቹን እውን እንዲያደርግ የሚያስፈልገውን እገዛ ሁሉ እንዲያገኝ እንደሚያደርጉለት ደጋግመው ቃል ይገቡለት ነበር፡፡

ኒኮላ ቴስላም በ1883 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ቻርለስ ባችለር የፃፉለትን ደብዳቤ ተቀብሎ፣ የእድል እጣ ፈንታውን ለመሞከር በመወሰን ወደ አሜሪካ አቀና፡፡ ሰርቢያውያን ብዙ ነገር እንደሚሰራላቸው የተማመኑበት ወጣቱ ሳይንቲስታቸው ፈረንሳይን ለቆ አሜሪካ የመግባቱን ዜና ሲሰሙ፣ ልጃቸው ከእንግዲህ በኋላ የአሜሪካ እንጂ የእነሱ ልጅ እንደማይሆን በመገመት ልባቸው በሀዘን ተሰበረ፡፡ ፀጉረ ልውጡ ሰርቢያዊ ወጣት ሳይንቲስት ኒኮላ ቴስላም ለወራት እጅግ አሰልቺ የሆነ የመርከብ ጉዞ ካደረገ በኋላ በ1884 ዓ.ም መባቻ ላይ አሜሪካ ኒውዮርክ ደርሶ ከዝነኛው የፈጠራ ሰው ከቶማስ ኤዲሰን ጋር ተገናኘ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አንድን ሰው በአስተማማኝና በማያዳግም ሁኔታ ለማስተዋወቅ ቁንጅናንና ዝናን የሚያስንቅ የማስታወቂያ ዘዴ እስከዛሬ ድረስም ጨርሶ አልተፈጠረም፡፡ ኒኮላ ቴስላም ይህንን በሚገባ ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት በአካል አይቶት ከማያውቀው ቶማስ ኤዲሰን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ “ለመሆኑ አንተ ማነህ?” ብሎ መጠየቅ አልፈለገም፡፡ ጓደኛው ቻርለስ ባችለር፣ ከዚህ በፊት ከላከለት የተለያዩ መረጃዎች የኒኮላ ቴስላን ማንነት በሚገባ የተረዳው ቶማስ ኤዲሰንም ስለጉዞው ሁኔታ ካቀረበለት አንዳንድ ተራ ጥያቄዎች በቀር ሌላ አላስቸገረውም፡፡ ወዲያውኑም ኒኮላ ቴስላ፣ ቻርለስ ባችለር ጽፈው የሰጡትን ደብዳቤ ለኤዲሰን ሰጠው፡፡ ኤዲሰን ደብዳቤውን አንብቦ ከጨረሰ በኋላ የቴስላን ጀርባ በእጁ መታ መታ በማድረግ፣ በዲናሞ ላይ የሚያደርገውን ምርምር ጠንክሮ እንዲገፋበት ካበረታታው በኋላ ማናቸውንም አይነት እርዳታ ከፈለገ፣ ያለ አንዳች ማመንታት እንደሚያደርግለት አስረዳው፡፡ ቶማስ ኤዲሰን፣ ዘመናዊ ዲናሞ ለመስራት አስቦ የጀመረውና ከሶስት አመት በላይ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሊሳካለት ባለመቻሉ ተስፋ ቆርጦ ያቆመው ትልቅ የፈጠራ ፕሮጀክት ነበረው፡፡

ስለዚህ ፕሮጀክት ባሰበ ቁጥርም ከልቡ ይቆጭ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ እውቀት ያለው ኒኮላ ቴስላን በምርምር ስራው እንዲገፋበት ቀድሞ ያበረታታውም፣ አቅቶት የተወውን ዲናሞ አሻሽሎ ሊሠራው ይችላል ብሎ በማሰቡ ነበር፡፡ ይህ ሃሳቡና እቅዱ እንዲሳካ ከሁሉ በፊት ምን ማድረግ እንዳለበት በሚገባ የተረዳው ኤዲሰን፤ ኒኮላ ቴስላ ፈቃደኛ ከሆነ በዓለም አቀፉ የኤዲሰን ኩባንያ ዋና መስሪያ ቤት በሳይንቲስትነት ተቀጥሮ መስራት እንደሚችል ግብዣውን በትህትና አቀረበለት፡፡ ቴስላም ኤዲሰን ያቀረበለትን ይህን የስራ ጥያቄ ለአፍታም እንኳ ሳያመነታ ወዲያውኑ ተቀበለ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ቴስላ ሊያመነታ የሚችልበት አንዳችም ምክንያት አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም ከፈረንሳይ ፓሪስ ተነስቶ አሜሪካ ኒውዮርክ ሲገባ፤ በኪሱ ውስጥ የነበረው አራት ሳንቲም፣ መርከብ ውስጥ በጉዞ ላይ እያለ የፃፋቸው የተወሰኑ ግጥሞችና በአየር ላይ የሚበር ማሽን ለመስራት አስቦ የሂሳብ ቀመርና ስሌት የሰራባቸው ቁርጥራጭ ወረቀቶች ብቻ ነበር፡፡ ቴስላ ከተቀጠረ በኋላ የኤዲሰን “የግል ቤተ መቅደስ” እየተባለ በሰራተኞቹ ዘንድ በሚጠራው ልዩ ወርክሾፕ ውስጥ ከኤዲሰን ጋር መስራት ጀመረ፡፡ ከእለታት ባንዱ ቀንም በወርክሾፑ አንድ ጥግ ላይ የተቀመጠ ጥንታዊ አሰራር ያለው ዲናሞ ተመለከተ፡፡

ዲናሞው ኤዲሰን በዘመናዊ ሁኔታ አሻሽሎ ለመስራት ፈልጐ፤ ከሶስት አመት በላይ ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር በተስፋ መቁረጥ የተወው ዲናሞ ነበር፡፡ ቴስላ ዲናሞውን አንስቶ እያገላበጠ አሰራሩን በደንብ መፈተሽ እንደጀመረ ድንገት ከኤዲሰን ጋር ተገጣጠሙ፡፡ ቴስላ በዲሞው ላይ ያሳየውን ከፍተኛ ትኩረት በሚገባ ያስተዋለው ኤዲሰን፤ “ስሪቱን ላሻሽለው ፈልጌ በጊዜ ማጣት ምክንያት ብዙም ትኩረት ያልሰጠሁት ዲናሞ ነው፡፡ የሚረባ ነገር ስላልሆነ አንተ በራስህ ምርምር ላይ አተኩር እንጂ ለዚህ ጊዜህን ልታጠፋበት አይገባም፡፡” ብሎት መልስ ሳይጠብቅ ወደ ቢሮው አመራ፡፡ ቴስላ ግን ኤዲሰንን ተከትሎት ሄደና “ቶማስ አንዴ አዳምጠኝ፡፡ ምን መሰለህ-- ዲናሞው የማይረባ ነው አይባልም፡፡ እኔ በዘመናዊ መልክ አሻሽዬ ልሰራው እችላለሁ፡፡” አለው፤ እርግጠኝነት በተሞላው ስሜት፡፡ የኤዲሰን ልብ በደስታ ዘለለ፡፡ ያጠመደው ወጥመድ በቀላሉ ያዘለት፡፡ እርሱ መስራት ያልቻለውን ስራ አሁን ሌላ ሰው ሊሠራለት ነው፡፡

ይህ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ለኤዲሰን በጣም አስፈላጊና አስደሳች ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ እቅዱ እስከ መጨረሻው ድረስ ግቡን መምታት ስላለበት፣ የተሰማውን ከፍተኛ የደስታ ስሜት በውስጡ አፍኖ በመያዝ፣ አሁንም ምንም አይነት ትኩረት እንዳልሰጠው በሚያሳይ ሁኔታ “እየውልህ ቴስላ--- እንደ እኔ ከሆነ በዚህ ውዳቂ ዲናሞ ላይ ምንም አይነት ጊዜህንም ሆነ ጉልበትህን ባታባክን እመርጣለሁ፡፡ ግዴለም ይሁን ብለህ ከገፋህበትና አሻሽለህ ከሰራኸው ግን የሃምሳ ሺ ዶላር ሽልማት እሰጥሃለሁ፡፡ የፈጠራ መብት ባለቤትነት መብቱንም ትወስዳለህ፡፡” አለው፡፡ ቴስላ እንዲህ ያለ ታላቅ ሽልማት (የያኔው ሃምሳ ሺ ዶላር በዛሬው ተመን ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር ይበልጣል) ይዘጋጅልኛል ብሎ ጨርሶ ያልገመተው ነገር ስነለበር፣ በደስታ እየፈነጠዘ ወደ ወርክሾፑ ተመለሰ፡፡ ቶማስ ኤዲሰን፤ ቴስላ ከቢሮው እንደወጣ እግሮቹን ጠረጴዛው ላይ ዘርግቶ ወደ ኋላው ተለጥጦ ቁጭ አለና፣ በከፍተኛ የእርካታ ስሜት በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ቴስላ ዲናሞውን እንደሚያሻሽለው እርግጠኛ ስለነበር “ከሶስት አመት በላይ ደክሜ መና ቀርቼበት የነበረውን ትልቅ ፕሮጀክቴን ያለ አንዳች ተጨማሪ ጊዜና ድካም፣ ከቦርሳ ቢወድቁ እንኳ በማይታወቁ ጥቂት ዶላሮች ብቻ ማሳካት መቻል በእውነቱ በጣም፣ እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡” አለና ለብቻው ፈገግ አለ፡፡ ኒኮላ ቴስላ የተዘጋጀለት ሽልማት ከተነገረው በኋላ፣ በቀን አስራ ስምንት ሰአት እየሰራ፣ ለአንድ አመት ያህል የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ፣ ዲናሞውን በላቀና በዘመናዊ ሁኔታ አሻሽሎ ለመስራት ቻለ፡፡

ወዲያውኑም የተዘጋጀለትን የሃምሳ ሺ ዶላር ሽልማት ለመቀበል በከፍተኛ የእርካታና የአሸናፊነት ስሜት ተሞልቶ፣ የስኬት ዜናውን ለኤዲሰን አበሰረው፡፡ ኤዲሰን ምንም እንኳ በእርግጠኝነት የጠበቀው ቢሆንም የስኬቱን ብስራት እንደሰማ፣ ቴስላን በአድናቆት አቅፎ ወደ ላይ አነሳውና “ብራቮ!ብራቮ!ብራቮ ቴስላ! እጅግ የሚያስደንቅ ነገር ነው የሰራኸው፡፡ ስለዚህ የአንድ መቶ ሃምሳ ዶላር የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግልህ ለሰራተኛ አስተዳዳሪው አሁኑኑ ትዕዛዝ እሰጥልሃለሁ” አለው፡፡ ቴስላ ይህን የደመወዝ ጭማሪ እንደ ሌላ ሽልማት ወይም ተጨማሪ ልዩ ማበረታቻ እንደተደረገለት በመቁጠር በከፍተኛ የደስታ ስሜት የኤዲሰንን ቀኝ እጅ በሁለት እጆቹ ጥብቅ አድርጐ ያዘና “ቶማስ! በጣም አመሰግናለሁ! በእውነት በጣም አመሰግንሃለሁ! አንተ መልካም ሰው ነህ! የሃምሳ ሺ ዶላር ሽልማቱ በራሱ እኮ ማንም በቀላሉ የማያገኘው ትልቅ ሽልማት ነው፡፡ በዚህ ላይ የአንድ መቶ ሃምሳ ዶላር የደመወዝ ጭማሪ ሲታከልበት ዋው! ይህ መቼም ህልም ህልም የሚመስል በጣም ድንቅ ነገር ነው፡፡” አለው፡፡ “ኦህ! ሽልማቱ? ሃምሳ ሺ ዶላሩ?” ኤዲሰን ከት ብሎ ሳቀ፡፡

ከተቀመጠበት ተነስቶ ቴስላን ትከሻውን አቀፈውና “አይ ቴስላ! ለካ እስከዛሬ ድረስ የእኛ የአሜሪካኖች ቀልድ አይገባህምና! ሃምሳ ሺ ዶላር ትሸለማለህ ያልኩህ እኮ የቀልዴን ነበር--- አንተ የእውነቴን መስሎህ ነበር እንዴ? አዬ እንዲያው የሰው ሀገር ሰው መሆን ለካ ችግር ነው አቦ!” አለው፡፡ ኒኮላ ቴስላ ተስፋ አድርጐት የነበረው ነገር እንደ ጉም በኖ እንደጠፋ ገባውና ሃይለኛ የንዴት ስሜት ሰውነቱን ሲወረው ተሰማው፡፡ አፉን ደም ደም አለው፡፡ ነገር ግን ስሜቱን እንደ ምንም ተቆጣጥሮ ከኤዲሰን ቢሮ ወጣና በቀጥታ ወደ ቤቱ አመራ፡፡ ለአስራ አራት ቀናት ስራ ሳይገባ ቤቱ ተቀምጦ ግጥም በመፃፍ የተጐዳ ስሜቱን ለመጠገን ሞከረ፡፡ በአስራ አምስተኛው ቀን ኤዲሰንን በድጋሚ ለማነጋገር ፈልጐ ወደ ቢሮው ሄደ፡፡ ኤዲሰን ቴስላን እንዳየው ወደ እርሱ ተንደርድሮ ሄደና “ቴስላ በደህናህ ነው እንዲህ የጠፋኸው? የሰራተኛ አስተዳዳሪው የአንድ መቶ ሃምሳ ዶላር የደመወዝ ጭማሪ እንደተደረገልህ የሚገልፀውን ደብዳቤ ሊሰጥህና በዚያውም እንኳን ደስ ያለህ ሊልህ ፈልጐ ከየት ያግኝህ? እኔማ ክፉ ነገር አጋጥሞህ እንዳይሆን ብዬ በጣም ሰግቼ ነበር፡፡ ደህና ከሆንክ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡

እንግዲህ ዛሬ በሰላም ከተገናኘን በእውነቱ ለሰራኸው ምርጥ ስራ እንኳን ደስ ያለህ ልልህ እወዳለሁ፣ ይሄውልህ ቴስላ የአሜሪካ የፓተንት ቢሮ አሻሽለህ የሰራኸውን (Induction motor) ዲናሞ ባጭር ጊዜ ውስጥ መርምሮ ፓተንቱን አጽድቆና መዝግቦ ልኮልናል፡፡” አለውና በመስታወት ፍሬም ውስጥ የተቀመጠ የፈጠራ ውጤት ባለቤትነት መብት ሰርቲፊኬት አሳየው፡፡ በፈጠራ ባለቤትነት የተመዘገበው ቶማስ አልቫ ኤዲሰን ብቻ ነበር፡፡ የቴስላ አንጀት በሀዘን ተኮማተረ፣ ጭንቅላቱ በንዴት ክፉኛ ጋለበት፡፡ መላ ሰውነቱ በቁጣ ግሎ እጁ እንደ አንዳች ነገር ተንቀጠቀጠበት፡፡ ግን ሁሉንም ነገር በውስጡ ዋጥ አደረገና አንዲትም ቃል ሳይተነፍስ በመጣበት ሁኔታ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ይህም “ከዝነኛው የፈጠራ ሰው” ቶማስ አልቫ ኤዲሰን ጋር የመጨረሻው ግንኙነቱ ሆነ፡፡ ኒኮላ ቴስላ፣ ሳይንስ በተረጋገጠ እውነት ላይ የሚያተኩር ሙያ ስለሆነ የተቀረውን አለም ከሚያውከው ተራ ፉክክር የራቀ ነው ብሎ የሚያምን ሰው እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ቶማስ ኤዲሰን ደግሞ የቴስላ ተቃራኒ ነበር፡፡ ስራውንና የህይወት ጉዞውን በቅርብ የመረመሩ አጥኝዎች፣ ኤዲሰን ከሳይንሳዊ ሃሳብ አፍላቂነቱና ከፈጠራ ባለሙያነቱ ይልቅ መልካም አጋጣሚዎችን ለይቶ በማወቅና ሌሎች የላቁ ባለሙያዎችን ቀጥሮ የሚፈልገውን ነገር በማሰራት፣ መጠቀምን አሳምሮ የሚያውቅ፣ እሳት የላሰ ነጋዴ ነው ይሉታል፡፡

ለነገሩ እሱም ይህን አልደበቀም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በ1889 ዓ.ም ተጠይቆ “አለም አጀብ ያለለትን የሂሳብ ሊቅ መቅጠር እየቻልኩ፣ የግድ የሂሳብ አዋቂ ካልሆንኩ ብዬ ምን ያዳርቀኛል?” በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡ ቶማስ ኤዲሰን የሌሎችን የፈጠራ ውጤት አላግባብ ትወስዳለህ ተብሎ በ1982 ዓ.ም ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው መልስ ግን በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ “በንግድና በኢንዱስትሪ መስክ ሁሉም ሰው ይሰርቃል፤ እኔም ብዙ ነገሮችን ከሌሎች ሰርቄአለሁ፡፡ እንዴት፣ ምንና መቼ መስረቅ እንዳለብኝ ግን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡” ነበር ያለው፡፡ ቶማስ ኤዲሰን እንዲህ ያለ መልስ መስጠቱ አስገራሚ ነው የተባለው፣ ሁሉም ሰው እንደሚሰርቀው እኔም እሰርቃለሁ በማለቱ አይደለም፡፡ ይህንንማ ማን ይክዳል! ይልቁንስ አስገራሚው ነገር ታላቅ ለሆነው ክቡሩና ዝነኝነቱ ሳይጨነቅ፣ እውነቱን አምኖ በራሱ አንደበት ደፍሮ መናገር መቻሉ ነበር፡፡ ዝነኛው የፊዚክስ ሊቅ ሰር አይዛክ ኒውተን፣ ከረጅም ዓመታት በፊት ለተመሳሳይ ጥያቄ የሰጠው መልስም “ዋናው ቁም ነገርና እኔም በተግባር ያደረግሁት፣ ከታላላቅና ድንቅ ጠቢባን ትከሻ ላይ መቆም ነው፡፡” የሚል ነበር፡፡

የሆኖ ሆኖ ቶማስ ኤዲሰን፣ ወጣቱን ሰርቢያዊ ሳይንቲስት ኒኮላ ቴስላን (በ1891 ዓ.ም የአሜሪካን ዜግነት ከተቀበለ በኋላ የሚጠራው ሰርቢያ አሜሪካዊ ወይም ትውልደ ሰርቢያ አሜሪካዊ እየተባለ ነው) እንደምን አድርጐ እንደተጠቀመበትና የማይፈጽመውን ቃል እየገባ “እንዳታለለው” በርካታ አሜሪካዊ ሳይንቲስቶች በሚገባ ያውቁ ነበርና፣ በ1917 ዓ.ም የአሜሪካ የኤሌክትሪክ መሀንዲሶች ተቋም አመታዊው “የኤዲሰን ሜዳሊያ” በወቅቱ የድህነት ኑሮ ይገፋ ለነበረው ኒኮላ ቴስላ እንዲሰጥ በአንድ ድምጽ ወሰነ፡፡ ይህንን ዜና የሰማው ኒኮላ ቴስላም የሚከተለውን ደብዳቤ ለተቋሙ በመፃፍ ሜዳሊያውን እንደማይቀበል አስታወቀ፡፡ “የተቋማችሁ ዋነኛው ህልውና የተመሰረተበትን አዕምሮዬንና የአዕምሮዬን የፈጠራ ውጤቶች እውቅና መስጠት ከልክላችሁኝ እንድራብ ካደረጋችሁኝ በኋላ፣ በተቋማችሁ አባላት ፊት ኮቴ ላይ አንጠልጥዬ እንድንጐራደድ፣ ባዶ ሰውነቴን በሜዳሊያ ለማስጌጥ መወሰናችሁ ከቶ እንደ ምን ያለ ቀልድና ምን የሚሉት ፌዝ ነው?”

Read 5442 times