Saturday, 20 July 2013 10:26

“ገና ትከስላለህ፣ ትደብናለህ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ብርዱ እንዴት ይዟችኋልሳ! ምን ይገርምሀል አትሉኝም..ይቺ በየመሀሉ የምትወጣው ድብን የምታደርግ ጸሀይ፡፡ “በረደን!” “አንዘፈዘፈን!” ስንል…አለ አይደል…ሌላ በኩል ጸሀዩዋ… “ገና ታራለህ ትደብናለህ፣ ታዲያ ምን… ትሆናለህ!” የምትለን ይመስላል፡፡ የሰዉ “ታራለህ፣ ትደብናለህ…” አልበቃ ያለን ይመስል!… ስሙኝማ…በኮሚኒስቶቹ ዘመን ነው አሉ… እዛችው የፈረደባት ሩስያ ውስጥ፡፡ እናማ… ለኮሚኒስት ምሁራን አምስት ያልተጻፉ መመሪያዎች ነበሩ አሉ፤ መጀመሪያ ነገር አታስብ፣ ካሰብክ ደግሞ አትናገር፣ ካሰብክና ከተናገርክ አትጻፍ፣ ካሰብክ፣ ከተናገርክና ከጻፍክ ደግሞ አትፈርም፣ ካሰብክ፣ ከተናገርክ፣ ከጻፍክና ከፈረምክ ግን ወዮልህ! እናላችሁ…ዘንድሮ በየቦታው “…ከፈረምክ ግን ወዮልህ!” የተባለ ይመስል አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ስሙኝማ…የሆነ ሰው መታወቂያ ለማውጣት አንድ አገልግሎት መስጫ ይሄድላችኋል፡፡

እዛም ሲደርስ ኮምፒዩተሩ አጠገብ ያለችው ‘ትንሽዬ ልጅ’…አለ አይደል… “ኮምፒዩተሩ አይሠራም…” ትለዋለች፡፡ እሱም አየት ሲያደርግ ኮምፒዩተሩ ፏ እንዳለ ነው፡፡ ሌሎች መታወቂያ ፈላጊዎችም “ኮምፒዩተሩ አይሠራም…” ተብለው ግራ ተጋብተው ቆመዋል፡፡ እናማ…ሰውየው “ይኸው በርቶ ይሠራ የለ እንዴ?” ይላታል፡፡ እሷም ምን ብትል ጥሩ ነው… “አይ፣ አሁን መታወቂያ መሥራት አይቻልማ…” ትለውና “አወቃለሁ ካልክ ለምን አንተ አትሞክርም“” ትለዋለች፡፡ ነገርዬዋ የሹፈት መሆኗ ነው…አጅሬ አልሆን ብሎት ‘ሲንደፋደፍ’ ከጓደኞቿ ጋር ‘ሙድ ሊይዙበት!’ ቂ…ቂ…ቂ… እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ አለችኝማ…ምን የሚል አባባል አለ መሰላችሁ…“ሁሉም ነገር በተበላሸበት ሰዓት ፈገግ የሚል ሰው ችግሩን ማን ላይ እንደሚላክክ አስቦ ወስኗል ማለት ነው፡፡” እና ነገርዬው ሁሉ ሲበላሽ…አለ አይደል… ቲማቲም እንኳን በአቅሟ ሀያ ምናምን ብር ስትገባ ፈገግ የምንል ሰዎች የቲማቲሙን መወደድ ማን ላይ እንደምናላክክ አስበንበታል ማለት ነው፡፡

ቂ…ቂ…ቂ… ታዲያላችሁ…ሰውየው የተወሰነች ደቂቃ ተቀምጦ የአራት ሰዎች መታወቂያ ሠራላችሁና አረፈው! ለካስ ትንሽዬዋ ልጅ ገና መታወቂያ እንዴት እንደሚሠራ አታውቅም ኖሯል! ስሙኝማ…የምር ግን…እንዲህ አይነት ነገሮች ብዙ ቦታ የተለመዱ እየሆኑ ነው፡፡ ምናልባትም ልጆቹ ለታጩበት ሥራ በቂ ‘ኦሪዬንቴሽን’ ስላላገኙም ይሆን ወይም መጀመሪያም ‘ምደባዎቹ’ ችግር ስላለባቸው…አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየበዙ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ‘ሜይንስትሪም ሚዲያ’ የምንለው እዚህ ችግር ላይ ጊዜ ሰጥቶ…“ኧረ መላ በሉ…” አይነት ነገር አለማለቱ ያስገርማል፡፡ ይቺን ስሙኝማ…አንዱ ሌላውን እንዲህ ብሎ ይጠይቀዋል…“በሶቪየት ህብረት ውስጥ ልክ እንደ አሜሪካ አይነት የንግግር ነጻነት አለ?” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፣ “በመርህ ደረጃ አዎ፤ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ ኋይት ሀውስ ፊት ለፊት ሆነህ ‘ሬጋን ይውደም!’ እያልክ ብትጮህ ምንም አይነት ቅጣት አይደርስብህም፡፡

ሞስኮ ውስጥ በቀዩ አደባባይ ቆመህ ‘ሬጋን ይውደም!’ እያልክ ብትጮህም ምንም ቅጣት አይደርስብህም፡፡” እናማ…በራሳችን የሆነ ‘ቀይ አደባባይ’ ቆመን…“በሰዎች ምደባ፣ ችሎታና ስነ ምግባር ይቅደሙ!” የምንልበት ጊዜ እየናፈቀን ነው፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንደው ነገረ ሥራችን ሲታይ…አለ አይደል… ከጊዜ በኋላ አዲስ አበባ ምን ልትባል የምትችል መሰላችሁ…“የገጠር አካባቢዎች ወደ ከተማነት እንደሚለወጡ ሁሉ፣ ከተማዎችም ወደ ገጠርነት እንደሚለወጡ ምሳሌ የሆነች…” በየቢሮው፣ በየገበያው፣ በየመንገዱ…የምናሳያቸው ባህሪያት አንዴ ‘ጓድ’ ሌኒን… “አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ” ያለው አይነት ነገር ይሆናል፡፡ ስሙኝማ… ‘ጓድ’ ሌኒንን ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንድ አስተማሪ ልጆቹን ሰብስቦ በአንድ መናፈሻ ውስጥ እያዘዋወራቸው ነው፡፡ ልጆቹ ደግሞ የከተማ ልጆች ስለሆኑ አንድም አይነት እንስሳ አይተው አያወቁም፡፡

እናማ… የሆነ ጥንቸል ብቅ አለ፡፡ አስተማሪውም ወደ ጥንቸሉ እያመለከተ “ይሄ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ አንድም አወቃለሁ የሚል ልጅ አልተገኘም፡፡ አስተማሪውም “እንግዲያው እኔ ልጠቁማችሁ” አላቸው፡፡ “በብዙ በምናነባቸው ታሪኮች ውስጥ ይገኛል፣ ብዙ መዝሙሮች ተዘምረውለታል፡ ዜማዎች ተዚመውለታል፡፡ አሁንስ አወቃችሁ?” አላቸው፡፡ ይሄን ጊዜ አንድ ልጅ ጥንቸሉን ቸብ፣ ቸብ እያደረገ ምን አለ መሰላችሁ… “እኔ እኮ መልክህ እንዲህ እንደሆነ አላውቅም ነበር፣ አያቴ ሌኒን…” ብሎት አረፈው፡፡ መዝሙርና ዜማ ማብዛት አንዳንዴ እንዲህ ያደርጋል! እናላችሁ…በየቦታው ያልሆኑትን ‘መስሎ መቅረብ’ በዝቷል፡ የሀብታም ቤት ግንብ የሚያካክል ወንበር ላይ የተቀመጠው ሁሉ ለ‘በርጩማ የሚበቃ’ ያህል የሥራ ችሎታ ላይኖረው ይችላል፡፡ ግን…አለ አይደል…‘ጊዜው’ ሆነና ወንበሩ ላይ እየተሽከረከረ… (እየተሽከረከሩ በዛው ‘ዞሮባቸው’ የቀሩ ልብ እየተባለ…) “ለእግሬ ውሀ አምጡ…” ለማለት የሚዳዳው… በድምር ሳይሆን በብዛት እየተበራከተ ይመስላል፡፡ ‘ኩኩሉው’ የሚል በዝቶ “ነግቷል!” የሚል የጠፋበት አገር እየመሰለ ነው፡፡

እናላችሁ…የከተማዋን የህንጻ መስታወቶች አንጋጠን እያየን… ራሳችንን በመስታወት ማየት የረሳን ሰዎች ቁጥራችን እንደ ችግሮቻችን ቁጥር እያሻቀበ ያለበት ዘመን እየሆነ ነው፡፡ ስሙኝማ…ይቺን ነገር ከዚህ በፊት አውርተናት ነበር መሰለኝ፡፡ እሱዬው ለአንድ ምግብ ከጠቅላይ ግምጃ ቤት ይወሰድ የነበረው በዓመት የሚከፈል የሦስት ወር ደሞዝ የሚጠየቅባቸው ቤቶች… ‘ገርሉካውን’ ይዞ ይገባል፡፡ ሜኑ ይቀርብለታል፡፡ ‘ኳንተም ፊዚክስ’ ምናምን ያጠና ይመስል በተመስጦ ሲያይ ይቆይና ምን ይላል መሰላችሁ…“ይኸው ብቻ ነው?” ይላል፡፡ ሜኑው እኮ ሁለት ገጽ ተኩል ጥቅጥቅ ያለ ነው! “ይኸው ነው…” ብለው ይመልሱለታል፡፡

ከዛ ምን ቢያዝ ጥሩ ነው፡፡ “አንድ የጾም በያይነቱ…” ይልና ወደ ‘ገርሉካው’ ዘወር ብሎ “አንድ ይበቃል አይደል! በልተን ካነሰ ብንጨምር አይሻልም…” ይላታል፡፡ከዛ ደግሞ አጠገቡ የቆመውን አስተናጋጅ ‘አጨብጭቦ ይጠራና’ ቂ…ቂ…ቂ…ምን ይላል መሰላችሁ…“የሚጠጣ ምን አለ?” የመጠጥ አይነት ይዘረዝርለታል፡፡ ወደ እንትናዬዋ ዘወር ይልና “ውሀ ይሻለናል አይደል…” ይልና ለአስተናጋጁ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ውሀ በጆግ አምጣልን፡፡” ‘ኧረ እባካችሁ’ ማስመሰልም አይነት አለው! እናማ… በየቢሮው፣ በየመንገዱ፣ በአገልግሎት መስጫ…ምናምን ቦታዎች የማስመሰል ‘እርፍና’…አለ አይደል…እየበዛ ሲሄድ ጥሩ አይደለም፡፡

አንዱ ጓደኛውን ምን ብሎ ይጠይቀዋል መሰላችሁ…“በካፒታሊስት ተረትና በማርክሲስት ተረት መካካል ያለው ልዩነት ምንድነው?” ጓደኝዬውም ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“የካፒታሊስት ተረት ‘ከዕለታት አንድ ቀን…ነበር…’ ብሎ ይጀምራል፡፡ የማርክሲስት ተረት ደግሞ… ‘ከዕለታት አንድ ቀን…ሊኖር ይችላል…’ ብሎ ይጀምራል፡፡ እና… የዘንድሮ ነገረ ሥራችን ላይ… “ከዕለታት አንድ ቀን…” የነበረው ሁሉ እየጠፋ እርግጠኛ ስላልሆንበት ‘ከዕለታት አንድ ቀን’ እያወራን ነው፡፡ እናማ…በዚህ የግብር መክፈያ ወቅት በየቦታው የምናያቸው “ገና ትከስላለህ፣ ትደብናለህ…” አይነት አገልግሎት አሰጣጦች…አለ አይደል… የሚመለከታቸው ክፍሎች (ያሉ ስለሚመስለን…) ይመልከቷቸውማ! ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 3506 times