Saturday, 20 July 2013 10:08

“አንድነት” በህዝብ ጥያቄ በ16 ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍና ስብሰባ እጠራለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

ባለፈው ሳምንት በጐንደርና በደሴ ሠላማዊ ሰልፍ ያካሄደው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ተመሳሳይ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ከበርካታ ከተሞች የህዝብ ጥያቄ እንደቀረበለት በመጥቀስ በ16 ከተሞች የተቃውሞ ሰልፉንና ህዝባዊ ስብሰባዎች ለማካሄድ እንደወሰነ ገለፁ፡፡ በአዲስ አበባ ሐምሌ 28 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ታቅዶ እንደነበር የተናገሩት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ ከጐንደርና ከደሴ የተቃውሞ ሰልፍ ጋር ተመሳሳይ ሰልፍ ለማካሄድ ከተለያዩ የኦሮሚያና የደቡብ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የህዝብ ጥያቄ ስለቀረበለት ፓርቲው አዲስ ፕሮግራም ለማውጣት እንደወሰነ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባውን ለማዘግየትና መስከረም 5 ቀን 2006 ለማድረግ እንደታሰበ ነግረውናል፡፡

በደቡብ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ እና በሀረሪ ክልሎች ተከታታይ ሠላማዊ ሠልፎችና የአደባባይ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ፓርቲው ወስኗል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የአዲስ አበባው ሰላማዊ ሰልፍ ወደ መስከረም ተራዝሟል ብለዋል፡፡ ይሁንና ፓርቲው በአዲስ አበባ በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት የአደባባይ ወይም የአዳራሽ ስብሰባዎችን ይጠራል ተብሏል፡፡ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ሐሙስ እለት ተወያይቶ መርሃግብር እንዳዘጋጀ አቶ ዳንኤል ጠቅሰው፤ በ16 ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ህዝባዊ ስብሰባ የሚካሄደው ከሐምሌ 28 ጀምሮ ነው ተብሏል፡፡ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭና በባህርዳር ሠላማዊ ሰልፍ በሚካሄድበት በዚሁ እለት፣ በወላይታና በመቀሌ የአደባባይ ስብሰባ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል፡፡ ነሐሴ 12 ቀን፣ በወሊሶ፣ በናዝሬት፣ በፍቼ እና በባሌ ሠላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ አቶ ዳንኤል ጠቅሰው፤ ነሐሴ 26 በድሬዳዋ እና በጋምቤላ የአደባባይ ስብሰባ እንዲሁም በአሶሳ ሰላማዊ ሰልፍ ይኖራል ብለዋል፡፡

በአምቦ፣ በሃዋሳ እና በደብረ ማርቆስ ከተሞችም ነሐሴ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚዘጋጁ ፓርቲው ገልጿል፡፡ የሠላማዊ ሰልፎቹና የአደባባይ ስብሰባዎቹ ዋና ዋና ትኩረቶች፣ የፀረ ሽብር አዋጁ ይሰረዝ፣ የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ይቀረፍ፣ የንግዱ ማህበረሰብ ላይ ያለው ጫና ይቃለል፣ የዜጐች መፈናቀል ይቁም የሚሉ ናቸው ብለዋል - አቶ ዳንኤል፡፡ በደሴና በጐንደር ሰልፎች ላይ ህብረተሰቡ የራሱን ችግሮችም በመፈክር መግለፁን አቶ ዳንኤል ጠቅሰው፤ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች መቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው የሰላማዊ ሰልፍና የህዝባዊ ስብሰባ ንቅናቄ መስከረም 5 ቀን በአዲስ አበባ በሚካሄደው መርሃ ግብር እንደሚጠናቀቅ ከገለፁ በኋላ ፣ መስከረም 30 በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የሚመረጡ አዳዲስ አመራሮች ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ ይወስናሉ ብለዋል - አቶ ዳንኤል፡፡

Read 24041 times