Saturday, 13 July 2013 12:15

ለዓለም ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ዝግጅት ግልፅ አይደለም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

                        ከወር በኋላ በራሽያዋ መዲና ሞስኮ ለሚካሄደው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ምርጫ እና ዝግጅት በተመለከተ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ኬንያ ተሳታፊ ቡድኗ ለመምረጥ ባዘጋጀችው ብሄራዊ ሻምፒዮና ላይ ሰሞኑን ከፍተኛ ትኩረት አድርጋ ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በዓለም ሻምፒዮናው በስንት የውድድር መደቦች እንደሚሳተፍ እና ስንት አትሌቶችን እንደሚልክ አለማሳወቁየሚኖረውን ዝግጅት እንዳያስተጓጉል ተሰግቷል፡፡ ከወር በፊት በአሜሪካ ዩጂን በተደረገው የፕሮፈንታይኔ ክላሲክስ ውድድር በ10ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ለዓለም ሻምፒዮናው የሚመረጡ አትሌቶችን ለመለየት ፌደሬሽኑ ተጠቅሞበታል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ከሚጠይቀው ሚኒማ ባሻገር በየውድድር መደቡ ለሁሉቱም ፆታዎች ለእያንዳንዳቸው ሶስት ምርጥ አትሌቶችን ለመመልመል ስለሚከተለው አሰራር ግልፅ መረጃ አለመኖሩ ግን የሚያሳስብ ይሆናል፡፡

በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው የዝግጅት ወቅት ካለባቸው የውድድር መደራረብ አንፃር ብቃታቸው የወደ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ በትልልቅ የዓለም ማራቶን ውድድሮች ያሸነፉ በርካታ ማራቶኒስቶች መኖራቸውም ለምርጫ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው በምታሳትፈው ቡድን ምርጫ ላይ ውስብስብ ችግሮች እንደሚኖሩም ይገመታል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኬንያ የዓለም ሻምፒዮና ተሳታፊ ቡድኗን የምትመርጥበት አይነት ተመሳሳይ ብሄራዊ ሻምፒዮናን በአሰላ ከተማ በሚገኘው አረንጓዴ ስታድዬም ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡ ከ35 በላይ የክልል፤የከተማ መስተዳድሮችን፤ የክለብ እና የብሄራዊ ቡድን ውክልና ያላቸው 1070 አትሌቶችን ያሳተፈው ብሄራዊ ውድድር በጋራድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አብይ ስፖንሰርነት 42ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ነበር፡፡ የመከላከያ አትሌቲክስ ቡድን አጠቃላይ አሸናፊ በሆነበት ብሄራዊ ሻምፒዮናው በ5 የስፖርት አይነቶች ብሄራዊ ሪከርዶች ከመሻሻላቸውም በላይከ1 በላይ የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፉ 5 አትሌቶችም ተገኝተውበታል፡፡

ይሁንና ይህ ብሄራዊ ሻምፒዮና በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ስለሚወክለው ቡድን ምንም የሰጠው ፍንጭ አልነበረም፡፡ በተያያዘ ግን የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመመልመል ዓመታዊ ብሄራዊ ሻምፒዮናውን ዛሬ በናይሮቢ ከተማ በሚገኘው ናያዮ ስታድዬም ያካሂዳል፡፡ ብሄራዊ ሻምፒዮናው ምርጥ እና ልምድ ያላቸው ፤ወጣት እና አዳዲስ አትሌቶችን በዓለም ሻምፒዮናው ቡድን ለማካተት የተዘጋጀ እንደሆነ ሲታወቅ በኬንያ ከፍተኛ ተመልካች የሚያገኝ የአትሌቲክስ ውድድር እንደሆነና ሳፍሪኮም በተባለ የቴሌኮም ኩባንያ በ23ሺ ዶላር የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡ በዚሁ ሻምፒዮና በ10 የአትሌቲክስ ስፖርቶች መሳተፍ እንዲችሉ አስፈላጊውን ሚኒማ ያሟሉ፤ ከሁለት ዓመት በፊት የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆኑ 192 አትሌቶች (132 ወንድ እና 60 ሴት) ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን በየውድድር አይነቱ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት የሚችሉት በቀጥታ ለዓለም ሻምፒዮናው ቡድን የመመረጥ እድል እንዳላቸው ታውቋል፡፡ በብሄራዊ ሻምፒዮናው 3ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች አስቀድሞ በነበራቸው ውጤት ግምገማ ተደርጎ የመመረጥ እድል ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ በብሄራዊ ሻምፒዮናው የተመረጡ አትሌቶች ከአንድ ሳምንት በኋላ በካሳራኒ በሚገኘው የመኖርያ እና የልምምድ ካምፕ በመግባት የመጨረሻ ዝግጅታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ኬንያ ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በመካከለኛ ርቀት፤ በ5ሺ ሜትርና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች እና በማራቶን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የሚበቃ የቡድን ስብስብ እንደሚኖራት ትጠብቃለች፡፡ አይኤኤኤፍ ሰሞኑን እንዳስታወቀው ከ200 አገራት የተወከሉ 2000 አትሌቶች የሚሳተፉበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በመላው ዓለም በሚኖረው የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት በሪከርድነት የሚመዘገብ ተመልካች ያገኛል፡፡ በርካታ የዓለም ክፍሎችን በቴሌቭዥን ስርጭት ለማዳረስ ስምምነቶች መደረጋቸውን የገለፀው ዓለም አቀፉ የአትሌቲክሰ ፌደሬሽኖች ማህበር ለ9 ቀናት የሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮናው በ200 አገራት ሽፋን እንደሚኖረውና የሚያገኘው ድምር ተመልካች እስከ 5 ቢሊዮን እንደሚገመት አስታውቋል፡፡ ከ2 አመት በፊት በደቡብ ኮርያ ዳጉ ተደርጎ በነበረው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኬንያ 47 አትሌቶችን በማሳተፍ በ17 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፤ 6 የብርና 4 የነሐስ) ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃ አግኝታ እንደነበር ሲታወስ፤ ኢትዮጵያ በ34 አትሌቶች ተካፍላ 5 ሜዳልያዎችን (1 የወርቅና 4 የነሐስ) በማግኘት ከዓለም ዘጠነኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ነበረች፡፡ ባላፉት 13 የዓለም ሻምፒዮናዎች ደግሞ ኬንያ በተሳትፎ ታሪኳ በሰበሰበቻቸው 100 ሜዳልያዎች (38 የወርቅ፤ 33 የብርና 29 የነሐስ) ከዓለም በሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትመዘገብ፤ ኢትዮጵያ በ54 ሜዳልያዎች(19 የወርቅ፤ 16 የብርና 19 የነሐስ) 7ኛ ላይ ናት፡፡

Read 3272 times