Saturday, 13 July 2013 10:28

ሽቅብ መቧጠጥ፣ ቁልቁል መንደርደር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንደ ሰሞኑ ሆኖ ነው ክረምቱ የሚዘለቀው! በበጋ ‘ሲጠብሰን’ ኖሮ በክረምቱ ‘ሲያንዘፈዝፈን’ ሊከርም ነው ማለት ነው! ዕድሜ ለአገር በቀሏ ዳግም አረቄ…ማን ይሞኛል! (ወዳጄ፣ ይመችሽማ!) ስሙኝማ… እዚቹ እኛዋ አገር ለምንድነው በጥሩ የተጀመረ ነገር እንዳማረበት የማይቀጥለው? የምር እኮ…ግርም ይላችኋል፡፡ ሁሉም ነገር በመጀመሪያ ምን አለፋችሁ… “እስከ ዛሬ የት ነበራችሁ?” የሚያሰኝ አይነት አሪፍ ይሆናል፡፡ “ጉዱ ጠዋት ነው…” እንደሚባለው ጉዱ የሚመጣው በኋላ ነው፡፡ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስሙኝማ፣ ማታ ልዕልት ዲያናን የምታስንቅ ቆንጆ የነበረችው እንትናዬው ጠዋት ላይ ‘ያለብቃት ማረጋገጫ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) የተሞነጫጨረች የቀለም ቅብ ስትሆንበት “ጉዱ ያለው ጠዋት ነው…” ቢል አይፈረድበትም፡፡

እኔ የምለው…ማታ በታየችውና ጠዋት በምትታየው ‘ያችው እንትናዬ’ ያለው ‘የውበት መለያያት’…አለ አይደል… “የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ በአንድ ምሽት አራት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ወደ ኋላ መሄድ ጀመረ እንዴ!” የሚል ጥያቄ የፈጠረባቸው እንትናዎች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ እናላችሁ…ለምሳሌ የሆነ አዲስ ሬስቱራንት ነው እንበል፡፡ ታዲያላችሁ…የሚቀርብላችሁ ተጋሚኖ የገባበት ቅመም ብዛት ዝርዝር ሁለት ገጽ የሚሞላና “እንኳንስ እዚህ ቤት እግር ጣለኝ!” የሚያሰኝ ይሆናል፡፡ ገና እዛው እያላችሁ…በሞባይል የፈቃደኝነት ‘ሎቢዪንግ’ ሥራ ትጀምራላችሁ፡፡ “የእኔ ጌታ ቅመሰውና ሁለተኛ ሥጋ በዞረበት አትዞርም ነው የምልህ!” እናማ… የምግቡ ጣዕም አንድ ሦስት፣ አራት ሳምንት እንዲሁ ይቆያል፡፡ ወር ምናምን ገደማ የተወሰኑ ወዳጆች ሰብሰብ አድርጋችሁ ትመጣላችሁ፡፡

እናማ… ምን ቢገጥማችሁ ጥሩ ነው… ነገርዬዋ፣ አይደለም ያ ሁሉ ቅመም ሊጨመርባት ጨዉ እንኳን ተቆጥቦ የገባባት፣ እንደ ዓባይ ግንድ ይዛ ባትዞርም ማደሪያ አጥታ የምትንከራተት ከውሀ የቀጠነች (እንክት አድርጎ ነዋ!) ‘ፈሰሴ’ ትቀርብላችኋለች፡፡ (ልክ ገና ብርጭቆው አፍ ሳይደርስ ተወርውሮ እንደሚፈስ ነገር…ቂ…ቂ!) የምር… ቤቱ ሲከፈት ከመወፈሯ የተነሳ “ኧረ ጭልፋው እንዳይሰበር!” ያሰኘች ሹሮ ‘ሆድ ብሷት’ በአርማታ ብትገድቧት እንኳን ሰርጋ ማለፍ ትችላላች… (ዕድሜ ለ‘ትራንስፓረንት’ እንጀራ!) አንዳንዴ… ሹሮዋ ከመጥቆሯ የተነሳ ከአሻሮ ጋር ‘ሪሚክስ’ የተደረገች ይመስላል፡፡ እና…ያኔ ሲከፈት “ሆዴ!” “አንጀቴ!” ሲሉ የነበሩት ባለቤትየዋ ይቺ ሹሮ ጣእሟ ምናምን ቢባሉ “አይ እንግዲህ…መብላት ካልጣማችሁ ሌላ ቦታ መሄድ ትችላላችሁ…” አይነት የትኩስ ባለገንዘብ መልስ ይሰጧችኋል፡፡ ደግሞላችሁ…የሆነ መሥሪያ ቤት አለላችሁ፡፡

በቃ “አዲስ የሥራ መንፈስ…” ምናምን ይባልና…ሰዉ ሁሉ ‘በአንድ እንትን፣ እንትን ካላልን’ አይነት ፍቅር ውስጥ ይገባል፡፡ የቢሮ ሠራተኞቹን ተዉአቸው… ዘበኛው እንኳን ሰላምታ ሲሰጣችሁ በጣም ከማንጎንበሱ የተነሳ “ይሄ ሰውዬ በተጓዳኝነት ሊስትሮነት ይሠራል እንዴ!” ያሰኛል፡፡ ወር የምትመላለሱበት ጉዳይ በአሥራ አምስት ደቂቃ ያልቅላችኋል፡፡ (ስሙኝማ…እዚህ አገር አንድ ሰሞን ቢ.ፒ.አር. የሚባል ነገር እንደነበረ የሚያስታውስ ዘጋቢ ፊልም ይሠራልንማ! ርዕሱም ‘እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር…’ እንዲሆን ይኸው ሀሳብ አዋጣን፡፡) እናላችሁ…ገና የመጀመሪያው ወር ሳይጋመስ ምን ይሆናል መሰላችሁ…ዘበኛው የመጥረጊያ ስባሪውን እያወዛወዘ “ጌታው ወዴት ነው!” ማለት ይጀመራል፡፡ “ሥራ አስኪያጁ ዘንድ ነው!” ትላላችሁ፡፡ ከዚያ ምን ይል መሰላችሁ…“ቀጠሮ ከሌለህ መግባት አትችልም፡፡”

ቢሮ ውስጥም ከአሥራ አምስት ቀን በፊት ሳቅና ፈገግታ ገጽታቸው ላይ የተነቀሰላቸው የሚመስሉ ተላላኪዎች፣ ፀሀፊዎች ምናምን ቁርሳቸውን ጆግ ሙሉ፣ ጆግ ሙሉ እንቆቆ የጠጡ ይመስል ይኮሳተሩባችኋል፡፡ በዛች በሁለት ሳምንት ምናምን ምን ተፈጠረ! ዘንድሮ አይደለም በሁለት ሳምንት በሁለት ሰዓት እንኳን የሚመጣው ለውጥ ምን ነው ለደጋጉም ነገር እንዲህ በፈጠንን ያሰኛችኋል! ቦሶችን ልብ ብላችሁልኛል…ገና ሲሾሙ ሠራተኛውን ይሰበስቡና ምን ይሉ መሰላችሁ…“ሁላችንም በአዲስ መንፈስ ተያይዘን ይህን ድርጅት ማሳደግ አለብን፡፡ ማንኛውም ሠራተኛ ሊያናግረኝ ከፈለገ ቢሮዬ ምን ጊዜም ክፍት ነው፡፡” እናላችሁ…ዊክኤንዱ ላይ አዲሱ ቦስ የአዲስ ቦስነቱን ጠበል ሲጎነጫጭ ይከርምና ሰኞ ይመጣል፡፡ ጸሀፊ ሆዬ በውስጥ ስልክ… “የንብረት ክፍል ሀላፊዋ ልታናግርዎ ትፈልጋለች…” ትላለች፤ “ሥራ ላይ ነው በያት፡፡” ማክሰኞ ደግሞ ዋናው ትእዛዝ ይመጣል…“ማንንም ሰው ያለቀጠሮ እንዳታስገቢ፣ ቀጠሮ ከመስጠትሽ በፊት ደግሞ እኔን ማስፈቀድ ይኖርብሻል...” አለቀ፡፡ ወደ ስልጣን የሚደረገው ሽግግር ተጠናቀቀ ማለት ነው፡፡ ከዚያማ… ጸሀፊዋ በራሷ ተነሳሽነት “ዛሬ እንግዳ አያናገሩም…” ማለት ትጀምራለች፡፡

ስሙኝማ…የምር ግን ብዙ ጊዜ ግርም የሚል ነገር ነው…በተለይ በዚህ ዘመን የሚሾሙ ሰዎች ገና መቀመጫው ‘ሞቅ ማለት’ ሳይጀምር እንደ ባላባት ነገር የሚያደርጋቸው ለምንድነው! (እኔ የምለው…እንትና…‘ዘንድሮም’ ሹመት አመለጠህ ማለት ነው! ነገርዬው እንዴት ነው… የ‘አገልግሎት’ ሲቪ ምናምን አይታይም እንዴ! አሀ… ግራ ሲገባንስ…አንተን የመሰለ በ‘ኢንተርናሲዮናል’ መዝሙር እንባው የሚመጣ አይነት ሰው…ስንቴ ታልፈህ ሊዘለቅ ነው! ሀሳብ አለን…‘እሱኛው መንገድ ካልሆነ’…አለ አይደል… “ተሾመ” የሚለው ቃለ ‘ሲቪህ’ ውስጥ እንዲገባ በሦስት ወር የምናፈርሰው እቁብ መስርተን ሰብሳቢያችን ትሆን እንዴ! ስሙኝማ …እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሹመት ነገር ካነሳን አይቀር ሀሳብ አለን፡፡ ‘ቦተሊካ’…አለ አይደል… ‘ኮምፐልሰሪ’ ይሁንና ከፕሪ ኬጂ ምናምን ጀምሮ ይሰጥልን፡፡ አሀ…ልክ ነዋ! ሹመት እጩ የሚሆነው ሰው ቁጥር ይጨምርልና፡፡ እዚህ አገር የኮሚቴ ሊቀመንበርነት፣ የማህበር መሪነት፣ የዕድር ሰብሳቢነት…ምናምን አሪፉ ነገር ምን መሰላችሁ…አንዴ ከወጣችሁ ትከርማላችሁ፡፡

(ልጄ… የሆነ ነገር ‘ሰብሳቢ’ በመሆን የምትገኘዋ… አለ አይደል… ሬሴፕሽኗ፣ ኮክቴሏ፣ የእራት ግብዋ… ምናምን ቀላል አትምሰላችሁ!) እናማ… ሁሉም ቦታ ሹመት በ‘ተክሊል’ እንደ ተፈጸመ ትዳር “እስከ ሀይወት ፍጻሜ…” ምናምን አይነት ነገር ባይሆን አሪፍ ነው፡፡ እናላችሁ…በደህና ሁኔታ ተጀምሮ በዛው የሚቀጥል ነገር ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡እኔ የምለው…እንግዲህ ክረምቱ እየሰፈረብን አይደል…ይቺን ስሙኝማ፡፡ አውሮፕላን አብራሪው ማረፊያ ቦታው ሲዳረስ ሀይለኛ አውሎ ነፋስ ይፈጠራል፡፡ አውሮፕላኗም ትንገጫገጫለች፡፡ አብራሪው እንደ ምንም ብሎ ግን አውሮፕላኗን እያንገዳገደም ያሳርፋታል፡፡ ወደ መንገደኞች ክፍል ይገባናም መልካም ምኞቱን ይገልጽላቸዋል፡፡ ወደ ማብረሪያ ክፍሉም እየተመለሰ እያለም… አንድ አዛውንት ምን ቢሉት ጥሩ ነው…“ለመሆኑ አንተ አሳርፈሀት ነው ወይስ በፀረ አውሮፕላን ጥይት መትተውን ነው!” አንዳንድ ጊዜ ላይ ዓለም ጫፍ ያለን እየመሰለ አምዘግዝገው ሲጥሉን…“ለመሆኑ አንተ አሳርፈሀት ነው ወይስ በፀረ አውሮፕላን ጥይት መትተውን ነው!” ያስብለናል፡፡

(እንትና ‘መውረድህ የማይቀር’ ከሆነ ቀስ ብለህ፣ ትንፋሽ እየወሰድክ ለመውረድ ያብቃህማ!) ስሙኝማ… ዘንድሮ አንዳንድ ነገሮችን ስናይ…አለ አይደል ‘በሆነ ባልሆነው’… “ኪሳችሁ ያለችዋን ሰባራ ሳንቲም ቁጭ አድርጓት…” አይነት ነገር ስንባል የአያ ጅቦ ተረት ትዝ ይላል፡፡ አያ ጅቦ አህይቱን ከአቅሟ በላይ እህል ምናምን ነገር ተጭና ያያትና ምን ይላል መሰላችሁ…“አንቺም ሲሳይ የተጫንሽውም ሲሳይ፡፡” እናማ…በሥራም ሆነ በሌላ ህይወታችን ነገር ሽቅብ እያስቧጠጠ አስወጥቶ ደህና ቦታ ላይ ካደረሰ በኋላ በራሳችን ችግር ቁልቁል እያንደረደረ ከሚያስወርድ አባዜ ይሰውረንማ! ልቦና ለጎደለን ልቦና ይስጠንማ! በመልካም አስጀምሮ በመልካም የሚያስጨርሰውን ልቦና ይስጠንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2675 times