Saturday, 13 July 2013 10:49

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

Written by  በኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(1 Vote)

ተናጋሪዋ ምድር

 የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ ሰኔ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ለጥበብ ተገዦት እንዳለፉት ሁለት ቀናት የወከባ ዕለት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የዕለቱ መርሐ ግብር መቀሌንና አካባቢዋን መጐብኘት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከክልሉ መንግሥት ባገኘው ሙሉ ድጋፍ ያዘጋጀው “የዓባይ ዘመን ሕያው የጥበብ ጉዞ ፫ ወደ ቅዱስ ያሬድና ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ሀገር” ከተጀመረ ሶስተኛ ቀኑ መሆኑ ነው፡፡ በ19ኛው መቶ ክፍለዘመን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የነበረችው መቀሌ ንፁህ ናት፡፡ አሰስ ገሰስ አይበዛባትም፤ እንደ ሌሎች የሀገራችን ከተሞች የዕድገት ጉዞዋን ተያይዛዋለች፡፡ አዳዲስ ህንጻዎችና ዘመናዊ ጐዳናዎች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ናቸው፡፡

መጀመያ የጐበኘነው የሰማዕታትን ሀውልት ነው፡፡ በመቀሌ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ የተገነባው የትግራይ ሰማዕታት ሀውልት የተመሠረተው ከፍ ካለ ቦታ ላይ ስለሆነ በየትኛውም የከተማዋ አቅጣጫ ሆኖ መመልከት ይቻላል፡፡ ቦታው ሃውልት ብቻ ሳይሆን ሙዚዬም፣ 2500 ሰዎችን በአንዴ ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ አዳራሽ፣ መዝናኛ ክበብና ሌሎችም የተሟሉለት ባለ ዘርፈ ብዙ ማዕከል ነው፡፡ በሙዚየሙ ውስጥ ህወሓት ካለፈው መንግሥት ጋር ባካሄዳቸው መራራ ውጊያዎች ያጋጠሙ እጅግ ዘግናኝ ትውስታዎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ የጦር ሜዳ መገናኛ ሬዲዮኖች፣ አልባሳት፣ ጽሑፎችና ስዕሎች ይገኛሉ፡፡ በተለይ የፎቶግራፍ ክፍሉ የተሸከመው ብዙ አሰቃቂ ትዝታዎችን ሲሆን “አደራ ይህ ነገር ከዚህ በኋላ እንዳይደገም” የሚል የአደራ ቃል የሚያስተላልፍ ይመስላል፡፡

የጦርነትን ዘግናኝ ባህርይም ያስታውሳል፡፡ ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ አራት እህትና ወንድሞች፣ አባትና ልጆቹ፣ ወይም ከሚወደው ቤተሰቡ አንዱ ወድቆ ሌላው በተአምር የተረፈ ሊገኝ ይችላል፡፡ ጦርነቱን አሰቃቂ የሚያደርገው ደግሞ ከባዕድ ወራሪ ጋር ሳይሆን የአንዲት አገር ልጆች ጐራ ለይተው፣ መደብ አደርጅተው የፈፀሙት ውጊያ መሆኑን ሳስበው አፌን ሬት ሬት አለኝ፡፡ ቀጥሎ የጐበኘነው ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥለው “ተክለ ጊዮርጊስ” በሚል የዘውድ ስም ነግሠው የነበሩትን ዋግሹም ጐበዜን በጦርነት አሸንፈው የነገሡት የአፄ ዮሐንስ 4ኛን ቤተመንግሥት ነው፡፡ ቤተመንግሥቱ ከተሰራ ከ138 ዓመት በላይ ቢሆነውም ዛሬም አልተዛባም፡፡ ጥንታዊ ውበቱን ጠብቆ “ህንፃ በእኛ ጊዜ ቀረ” የሚል ይመስላል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶባቸው ገና ሳይመረቁ እንደ አክርማ መሰንጠቅ የሚጀምሩ ህንፃዎች በገፍ በሚገኙባት ሀገር እንደ አፄ ዮሐንስ ቤተመንግሥት ያለ ጠንካራ ህንፃ ማየት በእጅጉ ያስደንቃል፡፡ ቤተመንግሥቱ እየታደሰ በመሆኑ፡፡

በውስጡ የነበሩት ቅርሳቅርሶች ጊዜያዊ መጠለያ ተሰርቶላቸው እየተጐበኙ ናቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከማህዲስቶችና ከግብጾች ጋር የተዋጉባቸው ልዩ ልዩ የውሃ መትረየሶች፣ መድፎች፣ በልዩ ጥበብ የተሰራ የንጉሡ ዙፋን፣ የንጉሡ ሽጉጥ፣ አልቢን ጠመንጃ፣ የበቅሎና የፈረስ ኮርቻ፣ አልጋ፣ 138 ዓመት እድሜ ያለው የንጉሱ የሜዳ አልጋ፣ (በ1928 ዓ.ም “ወርሰጌ” በተባለ ቦታ ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ከፍተኛ ውድቀት በጣሊያኖች ላይ ደርሶ ነበር፡፡) ከዚያ ቦታ ላይ የተገኘ ከነሐስ የተሰራ የፋሽሽቱ ሙሶሎኒ ሀውልት፣ በርካታ መስቀሎችና የብራና መጻሕፍት፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተሳሉ ሃይማኖታዊ ስዕሎች፣ የክብር አልባሳትና የወግ ዕቃዎች፣ ሙዚየሙን አጣበውት ይገኛሉ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የጐበኘነው መሥፍን ኢንደስትሪያልን ነው፡፡

ኩባንያው ከተመሠረተ አስራ ዘጠኝ ዓመት የሞላው ሲሆን 1500 ሰራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ አስር ማሽንሾፕ ያለው መስፍን ኢንደስትሪያል፤ የባቡርና የስኳር ፋብሪካ ሃዲዶችን፣ የስኳር ፕሮጀክት ጋኖችን፣ የተሳቢ ዕቃዎችን ወዘተ ሙሉ በሙሉ አገር ውስጥ ያመርታል፡፡ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሰማው የኳኳታ ድምጽ “አገሬ ሆይ ንቂ” የሚል የደወል ድምጽ ይመስላል፡፡ መስፍን ኢንደስትሪያልን ስንጐበኝ በህሊናዬ የመጣው ከዛሬ 145 ዓመት በፊት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋፋት የላይ አቋቁመውት የነበረው የብረት ማቅለጫና የመድፎች ማምረቻ ነው፡፡ የያኔዎቹ አባቶቻችን ከጐናቸው ቢሰለፉ ኖሮ ሀገራችን ዛሬ በኢንዱስትሪ የመጠቀች ትሆን ነበር ብዬም አሰብሁ፡፡ ሆኖም እንደመስፍን ኢንደስትሪያል ያሉትን ተቋማት በብዛት መገንባት ከቻልን ዛሬም ጊዜው አልረፈደም፡፡

ያለጥርጥር ማደግ እንችላለን የሚል ተስፋ ይፈነጥቃል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን አቅም በማዳበር ወደተሻለና ደርዝ ወዳለው ተቋምነት ለማሸጋገር እንዲረዳ ታስቦ በ33 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለው የኢንዱስትሪ መንደርም በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ በርካታ ወጣቶችን ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ለመሳብና ብቁ የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማግኘት ትክክለኛው መስመር ይህ ይመስለኛል፡፡ ከምሳ በኋላ በአራተኛነት የጐበኘነው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው እንዳ ኢየሱስ ግቢ ስንደርስ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ክንደያና ሌሎች ኃላፊዎች የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” አቀባበል አድርገውልናል፡፡ ግቢውን እየተዘዋወርን በርካታ ህንፃዎችን ጐብኝተናል፡፡ የዩኒቨርስቲው ዋና ግቢ የተመሠረተው በ1888 ጣሊያኖች መሽገውበት በነበረውና በኋላም በእቴጌ ጣይቱ መላ በውሃ ጥም ብቻ በተፈቱበት ታሪካዊ ቦታ ላይ ነው፡፡ ቀደም ሲል “መቀሌ ንፁህ ናት” ብዬ ነበር፡፡

ግን የዩኒቨርሲቲውን እንዳ ኢየሱስ ግቢ አይጨምርም፡፡ በሰፊው በተንጣለለው ግቢው ውስጥ ስንዘዋወር መጥፎ የሽንት ቤት ጠረን አስቸግሮን እንደነበር መሸሸግ አይቻልም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን የሚያስተናግደው ዩኒቨርሲቲው በዚህ ላይም ትኩረት ቢሰጥና ቢሰራ መልካም ይመስለኛል፡፡ የአይደር ሆስፒታል ደግሞ በተቃራኒው እጅግ የፀዳ ነው፡፡ ሆስፒታሉ 500 አልጋዎች አሉት፤ እጅግ በርካታ ህሙማንን በየዕለቱ ያስተናግዳል፡፡ የሚተዳደረውም በዩኒቨርስቲው ሥር ነው፡፡ ዋናው ግቢ ከአይደር ሆስፒታል መማር ያለበት ብዙ ነገር አለ፡ አይደር ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅም ነው፡፡ የኮሌዱ ዲን ዶ/ር ዘሪሁን አበበ በአርአያነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ወጣት ምሁር ናቸው፡፡ የኮሌጁን ቤተመጻሕፍት በዘመናዊ መንገድ አደራጅተውታል፡፡ ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከሚመለከታቸው የውጭ አካላት ጋር ያላቸው የሰመረ ግንኙነት ኮሌጁን በፋና ወጊነት እንዲጠቀስ አድርጐታል፡ ሆስፒታሉ የኩላሊት ማጠቢያ (ዲያሌሲስ) ማሽን ያስገባ፣ የካንሰር ህክምና ማዕከል ያቋቋመና በአገልግሎት ዋጋውም ቢሆን አዲስ አበባ ካሉት የመንግሥት ሆስፒታሎች በእጅጉ የተሻለ መሆኑን ተረድተናል፡፡ የተማሪ አያያዝ፣ የባለሙያን ፍልሰት ለመግታት ሳይሆን ለማስቀረት የሚጠቀሙበት ዘዴም እጅግ የሚገርም ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ዶ/ር ዘሪሁን እንደ ሌሎች ሀኪሞቻችን የገቡትን መሃላ አፍርሰው በወገናቸው ወይም በሰው ልጅ አይነግዱም፡፡

ሃሳቤን ግልጽ ላድርገው፤ በከተማችን እንደምናያቸው በርካታ ሃኪሞች ከሆስፒታሉ ዙሪያ ክሊኒክ አቋቁመው ህመምተኛውን በሰበብ አስባቡ አይሰልቡም፡፡ እናም “ምናለ እንደእሳቸው ያሉ የሞራል ባለፀጋዎች በበዙልን!” ብዬ ከልቤ ተመኘሁ፡፡ ሀገር የምታድገው እንዲህ አይነት ከንዋይ አምልኮ የፀዱ ወጣት ምሑራን ሲኖሯት ነዋ! ጊዜው እየመሸ ነው፡፡ የዕለቱ መርሃ ግብር የሚጠናቀቀው በሰማዕታት ሃውልት በሚደረገው የኪነጥበብ ምሽት ስለሆነ መፍጠን አለብን፡፡ ስለሆነም ዶ/ር ዘሪሁንንም ሆነ ባልደረቦቻቸውን አመስግነን ወደ ዝግጅቱ ቦታ አመራን፡፡ የትግራይ ከያንያን ማህበር አባላት፣ የጥበብ ተጓዦችና የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪዎች በተገኙበት የጥበብ ምሽት በትግራይ ሰማዕታት ሀውልት ውስጥ በሚገኘው የተንጣለለ አዳራሽ ማካሄድ ቀጣዩ ተግባር ነበር፡፡ ስለሆነም የትግርኛና ኩናምኛ ባህላዊ ዘፈኖችና ግጥም በ”ማኅበር ከየንቲ ትግራይ” የቀረበ ሲሆን፤ “ዘርዓ ያዕቆብና የፍልሥፍናው መሠረቶች” በሚል ርዕስ አቶ አበረ አዳሙ ከኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፣ “የትግርኛ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ በወፍ በረር ምልከታ” በሚል ርዕስ ደግሞ አቶ ጌታሁን መሰለ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡ የዕለቱ መርሃ ግብር የተጠናቀቀው የክልሉ መንግሥት ባዘጋጀው የራት ግብዣ ነው፡፡ በራት ግብዣው ላይ የጥበብ ተጓዦች ከማህበር ከየንቲ ትግራይ አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ የማድረግ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ግጥሞች፣ ዘፈኖችና ገጠመኞችም ቀርበዋል፡፡ ሆኖም በጊዜ መተኛትና ከንጋቱ 11፡00 ላይ መነሳት የግድ ይል ነበር፤ ሆነም፡፡ የጥበብ ተጓዦች አራተኛ ቀናቸውን “ሀ” ብለው የጀመሩት “አድ አካውህ” የተባለውን መካነ ቅርስ ነው፡፡ ሆኖም የጥንታዊውንና ታሪካዊውን የነጋሽ መስጊድ ጉብኝት ላስቀድምና ወደ ተነሳሁበት ልመለስ፡፡ መስጊዱ መስጊድ ብቻ አይደለም፡፡ ከሌሎች መስጊዶች በተለየ በርካታ መቃብሮችም አሉበት፡፡

በተለይ የነቢዩ መሃመድ ተከታዮች ከአሳዳጆቻቸው ሸሽተው የተጠለሉት በዚች ታሪካዊት ቦታ ላይ ነው፡፡ 15 የሚሆኑ የሁለተኛው ስደት ተጓዦች አስከሬን በዚችው ታሪካዊት ቦታ ተቀብሮ በክብር እየተጠበቀ ነው፡፡ ነቢዩ መሃመድ “ሐበሾችን አትንኩ!” የሚል ትዕዛዝ ያስተላለፉትም የኢትዮጵያውያንን ደግነትና እንግዳ አክባሪነት ባወቁበት በዚያን ጊዜ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ አንድ ሙስሊም ጓደኛዬ ያወጋኝ ጨዋታ አስገርሞኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- “ነቢዩ መሐመድ ካልነኳችሁ በቀር ሃበሻን አትንኩ” ያሉት ቀልድ እንዳይመስልህ፡፡ እስኪ ግብጾችን ተመልከት፡፡ ሐበሻን መውጋት አለብን ብለው በፎከሩ በማግስቱ አይደለም እንዴ አላህ እርስበርስ ያባላቸው? እህስ የነቢያችን ቃል ትክክል አይደለም ትላለህ?” ብሎኛል፡፡ ከዚያ በፊት አስቤው ባላውቅም “እውነትምኮ አንድ ነገር አለ፡፡ መቸም ቢሆን ለኢትዮጵያ ጤነኛ አስተሳሰብ ኖሮአቸው የማያውቁት ጋዳፊ በውርደት ተሰናበቱ፤ ሆስኒ ሙባረክም መጨረሻቸው ውርደት ሆነ፣ ሶሪያም በቋፍ ላይ ነች፡፡

እውነትም…” ብያለሁ ለራሴ፡፡ ቀጣዩ ጉዟችን ወደ ውቅሮ ነው፡፡ ከእሷ በፊት ግን ሌላ ምስጢራዊ ቦታ ማየት አለብን፡፡ ቦታው “አዲአካውህ” ይባላል፡፡ “የቋጥኞች አገር” ማለት መሆኑን አቶ ከበደ አማረ ነግረውናል፡፡ ቦታው ከክርስቶስ ልደት 2600 ዓመት በፊት የዳአማት ሥርወመንግሥት ዋና ከተማ የነበረ መሆኑን የጀርመን አርኪዮሎጂስቶች አረጋግጠዋል፡፡ ጀርመናውያኑ ቁፋሮ የጀመሩት ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ መሆኑንም ተረድተናል፡፡ ከአዲ አካውህ በቁፋሮ የተገኙ በርካታ ማስረጃዎች አሉ፤ ቁፋሮው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ትግራይ ምስጢሯን “እነሆ” እያለች ነው፡፡ በሳብኛ ቋንቋ በድንጋይ ላይ የተፃፉ ማስረጃዎች እንደሚነግሩን፤ ቦታው ከየሃ ታሪክ ጋር ግንኙነት ነበረው፡፡ በወቅቱም (ከክ.ልደት 2600 ዓመት በፊት) “አልሙጋህ” ለተባለ ጣኦት መስዋዕት ይቀርብ ነበር፡፡ የጣኦቱ የተወሰነ አካልና መሥዋዕት ይቀርብበት የነበረው ጥርብ ድንጋይ በቁፋሮ ተገኝተዋል፡፡

ቦታው እስካሁን ተጠብቆ የቆየበት ዘዴም የሚደንቅ ነው፡፡ “የዮዲት ጉዲት መቃብር ነው” ተብሎ በአካባቢው ህብረተሰብ የሚታመን ሲሆን “ከተቆፈረ የመዥገር መንጋ አካባቢውን ያጠፋዋል” የሚል ጠንካራ ትውፊት ስለነበረ ማንም ለመንካት ሳይደፍር ቆይቷል፡፡ እንዲያውም በአካባቢው የሚያልፍ ሁሉ መዥገሮች እንዳይመጡበት ድንጋይ እየወረወረ መሄድ የተለመደ ነበር፡፡ አካባቢው ከግብጽ ፈርኦኖች ጋር የተያያዘ ታሪክ ሊኖረው እንደሚችልም ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፤ ማስረጃቸውም “ፍራኦን” የሚባል ቦታ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ ነው፡፡ ዛሬ “ፍረወይኒ” የሚባለው ከተማ ማለት ነው፡፡ ሆኖም አዲአካውህ የምትነግረን ገና ብዙ ምስጢር እንዳለ ተመራማሪዎች እያስረዱ ናቸው፡፡ ቁፋሮውም ምስጢር አሰሳውም ቀጥሏል፡፡ ትግራይ እንደሁ የማትነግረን ምስጢር፣ የማታስተምረን ዕውቀት የለም፡፡ ይህንንም አክሱምና የሃ ላይ ስንደርስ በደንብ እናየዋለን፡፡ ለዛሬ ውቅሮ ከተማ እንደር፡፡

Read 3471 times