Saturday, 13 July 2013 10:41

ታሪካዊቷ የትግራይ ምድር

Written by  ገ.ኃ
Rate this item
(3 votes)

“…ግብጽ በነዚያ ጥንታዊ ዘመናት በኢትዮጵያውያን አገዛዝ (የበላይነት) ሥር ነበረች፡፡ ሳይክሎፒዲያ በሚለው ቢቢላካል ሊትሬቸር (ሥነ-ጽሑፍ) ውስጥ እንደተጠቀሰው፤ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ለግብጽ ነገሥታትና የንግሥናው ቤተሰቦች የተሰጠ ስም እንደነበር ይመሰክራል፡፡ በእርግጥም በነዚያ ዘመናት ኢትዮጵያ ግብጽን ገዝታለች…

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር “ሕያው የጥበብ ጉዞ” በሚል መርሐ ግብር የተለያዩ ጉዞዎችን የቅርቡ ጉዞ “የአባይ ዘመን ሕያው የጥበብ ጉዞ፤ ወደ ቅዱስ ያሬድና ፈላስፋው ዘርአያዕቆብ ሀገር” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ አንዱ ተጓዥ በመሆን የትግራይን ምድር ከረገጥኩ በኋላ ጉብኝቱ ሲጀመር ማንነትን የመፈለግ ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡ በመሠረቱ በዓለም ላይ የማንነትን ምንጭ ወይም ሥር ፈልጐ በአስተማማኝ ሁኔታ እንደማግኘት የተለየ ውስጣዊ ጥንካሬ የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ የማንነት ጥያቄ ደግሞ በሥጋ፣ በደምና በአጥንት የሚገደብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከወገን፣ ከሀገር፣ ከሥልጣኔና ከመንፈሳዊ ሀብት የሚቀዳና ውስጣዊ ስሜትና መንፈስን በማረስረስ ልዩ ጥንካሬን የሚያጐናጽፍ ኃይል እንጂ፡፡ ቻርለስ ኮሪያ የተባለ አንድ ተመራማሪ ስለማንነት ፍለጋ በተነተነው ጽሑፉ፤ “ማንነት የተገኘ ወይም የተጨበጠ አካል ሳይሆን ሂደት ነው፡፡ ማንነት በታሪክ ሂደት ውስጥ ከሥልጣኔ ጋር በጥብቅ ተሳስሮ የሚገኝ ሲሆን፤ ይኸው ጥብቅ ትስስር የዚያን ዘመን ስልጣኔ እና ማንነትን ያመለክታል…” ሲል ይገልፃል፡፡

ይህም ማንነት ከሥልጣኔ ጋር በጥቅም መተሳሰሩን ጠቋሚ ነው፡፡ የትግራይ ምድር ሜዳ፣ ዳገት፣ ተራራና ሸንተረር ገጹም ሆነ ከርሰ ምድሩ በጥንታዊ የሥልጣኔ ታሪክና ቅርስ የታጨቀ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህን ምድር ገና ተፈልቅቆ? ያላለቀ እንቡጥ እሸት እንደሚመስል በሕሊናዬ ስየዋለሁ፡፡ እነዚህ የጥንታዊ አባቶቻችንና እናቶቻችን የሥልጣኔ አሻራዎች፣ የማንነቴ አሻራና ማኅተም መሆናቸውን ሳስብ ደግሞ ልዩ የመንፈስ ጥንካሬና ትልቅነት ተሰማኝ፡፡ ጥልቅና ጥብቅ የሆነ ውስጣዊ ጥንካሬ ያጐናፀፉኝ ጥንታዊ የሥልጣኔ ታሪክና ቅርሶች እንዲሁ በአጭርና በተራ አገላለጽ የሚተረኩ አይመስለኝም፡፡ ይሁንና የማንነቴ ፈለግና የእውነተኛ የታሪክ ምንጮቼ በመሆናቸው በራሴ የግንዛቤ መንገድ ለአንባቢዎቼ በአጭሩ አጋራለሁ፡፡ ሀ. ጥንታዊው የድንጋይ ሥነ - ሕንፃና የማነፅ ስልጣኔ የጥንታዊና የገናና ሥልጣኔዎችን ደረጃ በማያሻማ መንገድ ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ውስጥ የድንጋይ ሥነ - ሕንፃና ጠረባ እንዲሁም በተጠረቡት ድንጋዮች ላይ የተቀረፁ ጽሑፎችና ሥዕሎች ዋንኞቹ እንደሆኑ ተደጋግሞ የተወሳ ጉዳይ ነው፡፡ በድንጋይ የተጠበቡት ጥንታውያን ለእድገትና ለስልጣኔ ይሰጡት ስለነበረው ከፍተኛና ክቡር ዋጋ በዓለማችን በተለያዩ አህጉራት በተደረጉ በጥናቶችና በመጻሕፍት በስፋት ተዘክረዋል፡፡

ይሁንና፤ ይህንን ከፍተኛ ጥበብ እንደ ኢትዮጵያውያኑ በድንቅ ሁኔታ፣ በጥልቅና በጥብቅ የሥልጣኔ መወራረስ ሂደት ለዓለም ያበረከተ ወይም ያስተማረ መኖሩን ግን እጠራጠራለሁ፡፡ በድንጋይ ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ጥንታዊውን ጥበብና ሥልጣኔ ከኢትዮጵያውያኑ እጅ አውጥቶ ለሌሎች ለመስጠት እጅግ በርካታ ጥናቶች ቢጐርፉም ማስረጃ ቢስ ፍሬከርስኪ እየሆኑ መምጣታቸው ደግሞ የተሻለ መረጃን ለማበርከት የተነሳሽነት ኃይል ይሰጣል፡፡ አብዛኞቹ በድንጋይ ቅርፅ ላይ የተደረጉ ጥናቶች በግብፆች ፒራሚዶች ላይ ያነጣጥራሉ፡፡ ይሁንና ጉዳይን በተሻለ የሚያዩና ከሕሊናቸው የታረቁ ወገኖች፣ ይህ ጥንታዊ የሥልጣኔ ምንጭ የሆነው የድንጋይ ሥነ - ጥበብ ኢትዮጵያውያኑ ለዓለም ያበረከቱትና ፒራሚድም ጭምር በእነርሱ የተጠረበና የታነፀ መሆኑን ያለማወላወል ይመሰክራሉ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በቅርቡ በእጄ የገባ አንድ መጽሐፍ ያሠፈረውን በጥቂቱም ቢሆን ልጥቀስላችሁ፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ “Wonderful Ethiopians of the Ancient cushite Empire” (የጥንታውያኑ ኩሻይት ግዛት ድንቅ ኢትዮጵያውያን የሚል ነው፡፡) ፀሐፊው ደሩሲላ ዱንጂ ሃውስተን ይባላል፡፡ ይኸኛው መጽሐፉ ቅጽ 2 ሲሆን ቀደም ሲል በተመሳሳይ ቅጽ 1 እንደፃፈ ተገልጿአል፡፡

መጽሐፉ በ2007 እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በአሜሪካ የታተመ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 13 ላይ፡- “…ታሪካችን በጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን የኩሻይት አገዛዝ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ አገዛዙ ያለማቋረጥ ሦስት ክፍለ አህጉራትን በማካለል ለሦስት ሺህ ዓመታት ዘልቋል፡፡ …” በማለት ያወሳና በመቀጠልም በገጽ 21-22 እንዲህ ይላል፡፡ “…በቅርቡ ከግብጽ ምድር በቁፋሮ በተገኘው አስደናቂ ነገር ተደምመናል፡፡ የግብጽን የፊት ታሪክ የሳይንስ መነጽር ብንመለከት፣ በጥንቱ (አሮጌው) የሰው ዘር አጀማመር ወቅት ቅኝ ተገዥ ነበረች፡፡ የዚህ ሁሉ ድንቅ ሀብት ምንጭ ኢትዮጵያ የነበረች ሲሆን ግብጽ ለሮምና ለግሪክ እንዳስተላለፈች አሳምራ ታውቃለች…” ይለናል፡፡ በዚህ እሳቤ መሠረት በአሁኑ ጊዜ በቁፋሮ የሚገኙ ቅርሶች በተለይም በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የጥንታዊ ኢትዮጰያውያኑን አሻራ እንደሚያመለክቱ በሰፊው ይወሳል፡፡ በዚሁ ከላይ በገለጽኩት መጽሐፍ ውስጥ የኩሻይት ግዛት በትሮይም ተዘርግቶ እንደነበር ያስረግጥና ራሳቸውን ለመከላከል ከፍተኛ ጦርነት ያካሂዱ እንደነበር፣ ይህም ጦርነት የግብጽ ግጭት እየተባለ እንደሚታወቅ ያትታል፡፡ በመቀጠልም “…ግብጽ በነዚያ ጥንታዊ ዘመናት በኢትዮጵያውያን አገዛዝ (የበላይነት) ሥር ነበረች፡፡

ሳይክሎፒዲያ በሚለው ቢቢላካል ሊትሬቸር (ሥነ-ጽሑፍ) ውስጥ እንደተጠቀሰው፤ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ለግብጽ ነገሥታትና የንግሥናው ቤተሰቦች የተሰጠ ስም እንደነበር ይመሰክራል፡፡ በእርግጥም በነዚያ ዘመናት ኢትዮጵያ ግብጽን ገዝታለች…” በማለት ትንተናውን ይቀጥላል መጽሐፉ፡፡ (ገጽ 28) ከላይ የጠቃቀስኳቸውን አባባሎች ለማስፈር ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት፤ በጥንታዊው የሥልጣኔ ዘመን በድንጋይ ሥነ ሕንፃና ጠረባ የተጠበቡት ኢትዮጵያውኑ፣ ፒራሚድንም ጭምር ራሳቸው እንዳነጿቸው ያለምንም ይሉኝታ መግለጽ እንደሚገባኝ ስላመንኩበት ነው፡፡ እንዲያውም በትግራይ ክልል ገጽና ከርሰምድር የተጐዘጐዙትን የተራቀቁ የሥነ ሕንፃና የጥርብ ድንጋይ አስደናቂነት ዓለም በራሱ ህሊና ፊት ቆሞ የሚያዋውጥበት ጊዜው ደርሷል፤ የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ “ዳቬንቺ ኮድ” በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ደራሲ ዳን ብራውን፤ በቅርቡ “The Lost Symbol” ወይም “የጠፋው ምልክት” በሚል ርዕስ ትልቅ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ መጽሐፉ በጥንታዊው ሥልጣኔ ዘመን የነበረውን ባሕረ ዕውቀት ከድንጋይ መጥረብ ሥነ - ሕንፃ ጥበብ ጋር በማቆራኘት ያስነብበናል፡፡

ተደብቆ ወደጠፋውና ወደከፍተኛው ባሕረ ዕውቀት የመሸጋገሪያው ቁልፍ ምልክት የት እንደሚገኝ በብርቱ ሁኔታ የሚያፈላልገው መጽሐፍ፤ ዋነኛ ጠቋሚ ካርታ ወይም ኮምፓስ ተገኘ የሚለው በፒራሚድ ቅርጽ በተጠረበ ትንሽዬ የጥቁር ድንጋይ ቁጭራ ላይ ነው፡፡ አካሄዱም የድንጋይ ሥነ - ሕንፃና ጠረባ ጥበብ ከፍተኛው ደረጃ የደረሰው በግብፁ ፒራሚድ ላይ እንደሆነ አንድምታ ሰጪ ነው፡፡ የዳን ብራውን የታላቁ ባሕረ ዕውቀት መሸጋገሪያ ምልክት የማፈላለግ ጥረት የሚያበቃው፣ ካፒቶል በተሰኘው የአሜሪካ ሕንፃ መሠረት ሥር በረጅም ርቀት እንደተቀበረ በማመላከት ነው፡፡ መጽሐፉ ልብ ወለድ ቢሆንም ከትግራይ ምድር ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ ተዘርቶ የሚገኘውን በድንጋይ የመጠበብ ጥንታዊ የሥልጣኔ ባሕረ ዕውቀት ዳን ብራውን ልብ ቢለው ኖሮ፣ የታላቁ ባሕረ ዕውቀት የመሸጋገሪያ ምልክቱ በሀገሬ ተራሮች በአንዱ ግርጌ ተቀብሮ እንደሚገኝ በሚያማልለው ውብ አተራረኩ ይገልፀው እንደነበር ሳስብ አግራሞት ያስፈግገኛል፡፡ ለነገሩ የኢትዮጵያውያን ሥልጣኔ ሰማይ ጠቀስ እንደነበር የአክሱማውያኑን አስደናቂ ሥራዎች በብርቱ ማጤን ብቻ የሚበቃ ይመስለኛል፡፡

ለ. የትግራይ ተራሮች ሕያው ምስክርነት የትግራይን ታሪካዊ ምድር የረገጠ ማንም ቢሆን በተራሮቹ አሰላለፍ ወይም አቋቋም ከልብ መመሰጡ አይቀሬ ነው፡፡ ተራሮቹ በላያቸውና በጥጋ ጥጋቸው ወይም በአሸጋጋሪያቸው ከጥንት ጀምሮ የተፈራረቁትን በርካታ ኩነቶች ሕያው ሆነው ታዝበዋል፡፡ ከሰው መፈጠርና ከዘመን መቆጠር አንስቶ የተከናወኑ ተግባራትን ሁሉ ከመታዘብ ባሻገር ምናልባትም በጥጋ ጥጋቸው የትየለሌ የታሪክ ሀብት ተቀብሮባቸዋል፡፡ እነዚህን የትግራይ ተራሮች በተመስጦ ሲመለከቷቸው አፍ አውጥተው የሚያነጋግሩ ታላላቅና አዛውንት ዜጐችን ይመስላሉ፡፡ በእርግጥም በጥልቅ ልቦና ከቀረቧቸው እጅግ የበዛ ወግ እንዳላቸው አስባለሁ፡፡ ሀብትና አቅም በእጅጉ የሚጠይቅ ነው እንጂ፣ የተራሮቹ አናት፣ ወገብና ግርጌ ቢቆፈር ደግሞ እንደተለመደው ዓለምን የሚያስደንቁና የሚያስደምሙ የጥንታዊ ሥልጣኔአችን መረጃዎች ብቅ ማለታቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ኃያል ተራሮች ለረጅም ዘመናት በርካታ ጦርነቶችን ታዝበዋል፡፡

የቅርብ ጊዜያቱን ለመጥቀስ እንኳ የአድዋንና የማይጨውን ጦርነቶች ማንሳት ይቻላል፡፡ በተለይ የአድዋን ጦርነት ያስተናገዱትን ተራሮች በርቀትም ሆነ በቅርበት አተኩረው ካዩዋቸው አሁንም ድረስ በድሉ ተጀንነው መቆማቸውን ልብ ይላሉ፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ግርማቸው ገዝፎ ፍፁም በተመስጦና በትህትና የቆሙ የዓድዋ ተራሮች፣ በጦርነቱ ዋዜማ ምን ተመካክረው ይሆን? የሚል ጥያቄ ራሴን በራሴ ጠየቅሁ፡፡ እናም፤ ለቅጽበት ምናቤ ወደዚያው ዘመን ነጐደ፡፡ በጦርነቱ ዋዜማ ከሁሉም የዓድዋ ተራራዎች በሃያል ግርማ ሞገሱ ተገማሽሮና ልቆ የሚታየው የሶሎዳ ተራራ ሁሉንም ታናናሾቹንና ሊስተካከሉትም የከጀሉትን ተራሮች በጦርነቱ ዋዜማ ምሽት አንገቱን አስግጐ ጠራቸው፡፡ ሁሉም “አቤት ወዲ ማሬ” በማለት መለሱለት፡፡ “ነገ የሀገሬ ልጆች የሚፋለሙትን እብሪተኛ የጠላት ጦር በያላችሁበት በቡጢ አቅምሱት፡፡ ለወሬ ነጋሪት እንዳይተርፍ ጀግኖቼ!” ሲል አወጀላቸው፡፡ በፈገግታ ተቀበሉት፡፡ በጦርነቱም ዕለት በጧት በተሳሳተ መረጃ “በውሸት ኪዳነምሕረት” ተራራ ጥግ የሠፈረው ቀዳሚ የኢጣሊያ ባታሌዮን ጦር የምሽግ ስህተት መፈፀሙ ተነገረው፡፡

በፍጥነት ወደ “ትክክለኛው የኪዳነ ምሕረት” ተራራ ገሠገሠ፤ ቀደሚ ባታሊዮኑ፡፡ ተሰባስቦ ያለመውን ምሽግ እንኳን በአግባቡ ሳይዝ፣ ለሀገራቸው ከልብ በቆሙት በነአወሎም የስለላ መረብ ተተብትቦ አበሳውን ማየት ጀመረ፡፡ በአጭር ጊዜ፤ ቀዳሚው ባታሊዮን የኪዳነምህረት ተራራ አካባቢ ድባቅ ተመትቶ ድል በኢትዮጵያውያኑ ተበሰረ፡፡ የዓድዋ ተራሮች በአግራሞት ፈገጉ፡፡ ባለድሎቹ እያቅራሩና እየፎከሩ በተራሮቹ ጥጋ ጥግ፣ ቀጥሎ ወደመሸገው የጣሊያን ጦር ተረማመዱ፡፡ ተራሮቹ በጀግኖቹ ቀረርቶና ፉከራ ተመስጠው የራሳቸውን የገደል ማሚቶ ከዳር እስከዳር አስተጋቡ፡፡ በተኩሱ መግነን፣ በጐራዴና ጦሩ መፋጨት፣ በጀግኖቹ ቀረርቶና ፉከራ መጋጋል የተነሳ… በመላው የዓድዋ ተራሮች ሠፈር ልብን የሚያርድና ወኔን የሚሰልብ የድምጽ ወጀብ ናኘ፡፡ የአውሮጳ በረዶ ያደነዘውና ያደነገዘው የኢጣሊያ ሠራዊት ጭንቅላቱ ዞረ፤ ጆሮውም ደነቆረ፡፡ “የሀበሻ አገር ተራራም ይፎክራል እንዴ? ምን ጉድ ነው!” ብሎ ሳይጨርስ… ደረቱ በጦር ተፈጥርቆ፣ አንገቱ በጐራዴ ተቀንጥሶ፣ ጭንቅላቱ በድንጋይ ጥበብ በተካኑ እጆች በሚወረወር የጥቁር አለት አሎሎ እየተፈጠፈጠ፤ የጣሊያን ሠራዊት በዓድዋ ዝነኛ ተራሮች ግርጌ ተረፈረፈ፡፡ የመጨረሻው የድል አውድማም በማርያም ሸዊት ተራራ ግርጌ ተሰተረ፡፡

የኢጣሊያ ሠራዊትም በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች ክንድ በሚገባ ተበራየ፡፡ አበቃ፡፡ እነዚህ የዓድዋ ዙሪያ ተራሮችና ሌሎችም በትግራይ ምድር ተሰድረው የሚታዩት ሁሉ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የማንነትና የታሪኩ ሁነኛ አምዶች ናቸው፡፡ በመሠረቱ በማይጨው ጦርነት ወቅትም ቢሆን የአካባቢው ተራሮች ወገንን በማገዝ በእጅጉ ተግዘዋል፡፡ ያልተሳካላቸው ጉዳይ ቢኖር አፈር በጥብጦ፣ ቅጠል ቀጥቅጦ መርዝ በመቀመም የጠላትን አውድ በጢስ ማፈን ብቻ ነበር፡፡ ድንቆቹ የሰሜን ተራሮች፤ ለድርሰት፣ ለፊልም፣ ለቴአትርና በአጠቃላይም ለባህል ዕድገታችን ከሚሰጡት ሠፊ የግብዓት ልግስና ባሻገር፣ የእያንዳንዳችንን የማንነትና የታሪክ ሀውልት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ በውስጣቸው አምቀው፣ በታማኝነት የሚጠብቁትንም ጥንታዊ የታሪክ ቅርስ ለትውልዱ ለማውረስ ዝግጁ በመሆን በእኔነት ስሜት ይጠብቃሉ፡፡ ዛሬ፣ የትግራይ ገበሬ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የጥንቱ አባቶች ጥበባዊና የጀግንነት እጆች ተራቁተው የነበሩ በርካታ ተራሮችን በደን እየለበሱ ናቸው፡፡ ተራሮቹ በልጆቻቸው ተፈጥሮን የመንከባከብ ታላቅ ወኔ እየተደመሙ፣ የተፈጥሮን ፀጋ እንደ በርኖስ ተጐናፅፈው ይበልጥ በግርማ ሞገስ ገዝፈዋል፡፡ አርአያነቱ ለመላው ኢትዮጵያውያን እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

ሐ. የፍልስፍናና የሃይማኖት ትውፊት ውርስ የኢትዮጵያውያን የፍልስፍናና የሃይማኖት አስተሳሰቦች ምድሪቱ የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ አንድምታ ጋር በጥብቅ ይተሳሰራል፤ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሰው፤ ራሱን ወደ ከፍተኛና የተወሳሰቡ ግንኙነቶች (በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካና በባሕላዊ) እያሳደገ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ የፍልስፍናውና የሃይማኖቱም እሳቤዎችና ተግባራት ከዚሁ የመነጩ ናቸው፡፡ በአክሱማይቱ የሥልጣኔ ዘመን የነበረውን ሥርዓተ ማኅበር መሠረት በማድረግ ታላላቅ የአስተሳሰብ መዘውር የሆኑ የፍልስፍና ሀሳቦች ፈንጥቀዋል፡፡ ፈላስፋው ዘርአያዕቆብና ቅዱስ ያሬድን የመሳሰሉ ሰዎች የመነሳታቸውም ጉዳይ ከዚሁ አቢይ ሁኔታ ጋር ሊተሳሰር ይችላል፡፡ ከጊዜው ማሕበረሰብ አስተሳሰብ አኳያ የተፈለሰፉት ሀሳቦች ከፍ ያሉ እና የሚደነቁ እንደነበሩ አይጠረጠርም፡፡ በመሆኑም፤ ይህ የአገራችን ክፍል ለአዳዲስ አስተሳሰቦች መፍለቅ ከፍተኛ መነሻ እንደነበር በአጭሩ መመስከር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የኦሪታዊው የምኩራብና የቤተመቅደስ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በዚሁ የትግራይ ታሪካዊ ምድር ቅሪታቸው በቁፋሮ እየወጡ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ረገድ ለየትኛውም ሃይማኖት መነሳትና መስፋፋት አካባቢው በቀዳሚነት የሚነሳ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በምኩራቦችና በቤተ መቅደሶች ይከናወኑ የነበሩ መስዋዕት የማቅረብ ወይም የመንፃት ሥርዓቶች ከዚሁ ታሪካዊ ምድር እየተጀመሩ ወደየአካባቢው ሀገሮች ስለመሰራጨታቸው፣ አሁን አሁን እየተገኙ ያሉት መረጃዎች አስተማማኝ ፍንጭ እየሰጡ ይመስለኛል፡፡ የሚቀረው ጉዳይ ሌሎች በቁፋሮ ሊደረስባቸው የሚችሉ ታሪካዊ ቅርሶችን እያደኑ የነበረውን የመረጃ ክፍተት በመሙላት የተቀናበረና የተደራጀ መረጃ ዓለም እንዲያገኝ በጽናት መሥራት ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም የትግራይ ምድር በሀዲላት ዘመንም የክርስትናንና የእስልምናን እምነት በመምረጥ ትውፊታቸው በፀና አለት ላይ እንዲቆም ያደረገች ናት፡፡ ይኸኛው ድርጊት ለታሪክም ሆነ ለመረጃ የራቀ ስላልሆነ ምንም የሚያከራክር ሀሳብ የለውም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ኢትዮጵያውያን የፍልስፍናና የሃይማኖታቸው ጥንታዊነት በታሪክና በመረጃ ይረጋገጥ ዘንድ የትግራይ ምድር የቅድሚያውን ኃላፊነት እንደሚወስድ በማስረገጥ መገንዘብ ይኖርብናል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ዱንጂ ሃውስተን ቀደም ሲል በጠቀስኩት መጽሐፋቸው ውስጥ ያሰፈሩት ሀሳብ እጅግ የሚያስደምም ነው፡፡ “ኢትዮጵያውያን ምናልባትም ጥንታዊና ታላቅ ዝርያ ናቸው፡፡

ወደ መጠፋፋት አያመሩም፡፡ ሌሎች ዝርያዎች በቂም በቀል ተቀያይመው ወይም ተጣልተው ሲጠፋፉ፣ ኢትዮጵያኑ ግን ገለል ብለው ፊታቸውን ደስታ ወደሚያመነጩላቸው አበቦች ይመልሳሉ፡፡ የሕይወት ጉዟቸውንም ይቀጥላሉ፡፡ ገጽ 17 …” እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያውያን አብሮነት፣ መተባበርና አንድነት ከጥንት ጀምሮ ሲሸጋገር የመጣ ታሪክና ትውፊት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ልዩ ከሆነ የህይወትና የእምነት ፍልስፍናዎች የሚመነጭ አስተሳሰብ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ መ. ተፈጥሮን የመግራት ምሳሌነት በሕብረተሰብ የእድገት ሂደት ውስጥ በአፍሪካ አለፍ ሲልም በዓለም ደረጃ የእርሻን ተግባር በመጀመር ረገድ ትግራይና አካባቢው ይጠቀሳል፡፡ ለብዙ ሺህ ዓመታትም የእርሻ ተግባር በዚሁ አካባቢ ተከናውኗል፡፡ ይኸው የሀገራችን ጥንታዊ የሥልጣኔ አውታር፣ የባሕረ-ነጋሽን ግዛት ተግኖ የሚገኝ በመሆኑ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከውጭ ለሚሠነዘሩ ግጭቶች ቅርብ መሆኑ ይታወሳል፡፡ የግጭቶቹ ሁኔታዎችና ምክንያቶች በእጅጉ ቢለያዩም ከውስጥ የሚነሱትም አተካሮዎች ወደ ጦርነት እያመሩ በትግራይና አካባቢዋ እጅግ በርካታ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ በተጠቀሱትና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች የሕዝቡ አሠፋፈርና ኑሮ ሲመሰቃቀል ቆይቷል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ለአፈር መሸርሸር፣ መደህየት ምክኒያት ሆነዋል፡፡ በተለይም ጋራዎቹና ቁልቁለታማዎቹ መሬቶች ለዘመናት በእጅጉ መጐዳታቸው እሙን ነው፡፡

ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ በዋናነት ትግራይንና ወሎን በሚያካልለው የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው መሬት ለምነቱን ከማጣቱም ባሻገር ጠልን ወይም እርጥበትን የመሳብ አቅሙን አጣ፡፡ በዚህም ምክንያት አካባቢው ለድርቅና ለረሃብ ተጋላጭ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይኸው የተጋላጭነት ሂደት እየቀጠለና እያደገ ሄዶ፣ ሀገራችን በዓለም ፊት የረሃብና የጉስቁልና ተምሳሌት ሆና እንደነበር ለሚያስታውስ ሁሉ የሚያስቆጭ ጉዳይ ነው፡፡ በጥንታዊ ሥልጣኔ ምንጭነት በታሪካዊ ሀብቶች ባለ ፀጋ የሆነው የትግራይና የወሎ ሕዝብ፣ በአዲሱና በአሁኑ ትውልድ ወቅት ለተደጋጋሚ የድርቅና የረሃብ ተጋላጭ ላለመሆን የአባቶቹን የፈጠራና የጀግንነት ውርስ ተላብሶ ታሪክ ለመቀየር እየማሰነ መሆኑን በዚህ ታላቅ ጉዞ መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ጥረቱ ቀደም ሲል እርቃናቸውን ቀርተው በድርቅ ሳቢያ በከፍተኛ ጠኔ ህዝብ ያሸለበባቸው እንደነበሩ ሊታሰብና አሁን የደንና የአረንጓዴነት ፀጋ ተጐናፍጸው ሲታዩ ቀልብን የሚሰበስብና የሚያስደንቅ ነው፡፡

(የ1987 ድርቅና የረሃብ እልቂትን ያስታውሷል) በትግራይ በገጹና በከርሰ ምድሩ ውስጥ ያሉት ታሪካዊ ሐብቶች እንዲከበሩ እንዲሁም በተለይ የተፈጥሮን ሚዛን ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረት የበለጠ መጠናከር አለበት፡፡ የቅርሶች አያያዝና አጠባበቅ ይበልጥ ተጠናክሮ ለቱሪዝም ፍሰት መበራከት የሚበጁ የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት መከናወን አለባቸው፡፡ ወደየቅርቦቹ ለመድረስና ቀልብን ገዝቶ ጉብኝቶችን ማጣጣም ይቻል ዘንድ መሠረተ ልማቶቹ አቅም በፈቀደ መሠረት እንዲጠናከሩ መረባረብ ተገቢ መሆኑን ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡

Read 2045 times