Saturday, 13 July 2013 10:45

“TOWER IN THE SKY” በምሁራን ዕይታ!

Written by 
Rate this item
(12 votes)

“ግፈኞችን ስተታገል አንተም ወደ ግፈኞች አውሬ እንዳትቀየር ተጠንቀቅ”

“ታወር ኢን ዘ ስካይ” ይላል በቀድሞዋ የኢህአፓ አባል ህይወት ተፈራ የተፃፈው መፅሀፍ፡፡ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ መተማመን፣ መካከድ እንዲሁም ግራ መጋባት ነፍስ ዘርተው የተተረኩበት መፅሃፉ፤ ኢህአፓ “አንጃ” በሚል ፍረጃ ህይወቱን በቀጠፈው ጌታቸው ማሩ መነሻነት የወቅቱን ሁኔታና የዚያን ዘመን ትውልድ ወለል አድርጐ ያሳየናል፡፡ ከየጌታቸው ማሩ ጓደኞች አንዱን “It remains a paradox to me that someone who believed so strongly in negotiation has been killed” (በውይይት ፅኑ እምነት የነበረው ሰው መገደሉ እንቆቅልሽ ነው እንደማለት ነው) የሚል ምላሽ እንደሰጣት የገለፀችው ህይወት ተፈራ፡፡ መፅሃፉን የፃፍኩበትም ምክንያትም ይኸው ነው ትላለች፡፡

“አንድ ሰው እንወያይ፣ የማያስፈልግ መስዋእትነት አንክፈል፣ ህይወት እናድን፣ ሃሳቤ ለመላው አባላት ይቅረብና የትግሉን አቅጣጫ እነሱ ይወስኑ ስላለ ለምን ይገደላል? ይህ ላለፉት በርካታ አመታት በውስጤ ሲብላላና መልስ ሳላገኝለት የቆየ ጥያቄ ነው” ብላለች፡፡ እስር ቤት እያለች ጀምሮ ታሪኩን ለመፃፍ ፍላጐት እንደነበራት ፀሃፊዋ አስታውሳ በተለያዩ ምክንያቶች ግን ሳልፅፈው ቀረሁ፤ በነዚህ ረጅም አመታት ግን ለራሴ የገባሁትን ኃላፊነት ባለመወጣቴ ከህሊናዬ ጋር ስጣላ ቆይቼ በመጨረሻ ከራሴ የተረከብኩትን ይሄን ከባድ ኃላፊነት ልወጣ በመብቃቴ ከፍተኛ የህሊና እረፍት ይሰማኛል ብላለች - መፅሃፉ ለህትመት በመብቃቱ፡፡ ጌታቸው ማሩ በተማሪዎች ንቅናቄ የማይናቅ ቦታ የነበረውና ከድርጅቱ መስራች አባላት አንዱ ሆኖ በአመራር ደረጃ ላይ የቆየ ቢሆንም ወደዚች ምድር መጥቶ እንደማያውቅ ተቆጥሮ መቆየቱን ሳይ ይቆጮኝ ስለነበር ጥብቅና ልቆምለት፣ ስሙን ላነሳት፣ ካለጊዜው በተዘጋው ልሳኑ ልናገርለት፣ ጉዳቱን ለመላው ኢትዮጵያዊ እና ለአለም ህዝብ ሁሉ ላሳውቅለት በመወሰኔ እነሆ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” ፅፌያለሁ ብላለች - ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመፅሃፉ ላይ በተደረገው ውይይት ንግግር ያቀረበችው ህይወት ተፈራ፡፡

በመፅሃፉ ላይ ባለፈው ሰኞ በተካሄደው ምሁራዊ ውይይት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ ዶ/ር ጌታቸው ሳህለማርያም፣ አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና አቶ ወልደልዑል ካሳ በመፅሀፉ ላይ ያላቸውን እይታ ያቀረቡ ሲሆን ውይይቱን የመሩት ፕሮፌሰር ማስረሻ ነበሩ፡፡ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ፤ መፅሃፉን ከታሪካዊ ዳራው በመነሳት ከአራት ዋና ዋና ኩነቶች ጋር በማያያዝ አጭር ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡ 1962 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ስፍራ እንደነበረው እንዲሁም የመንግሥት ታጋሽነት፣ የተማሪዎች አይበገሬነት የታየበትና በመጨረሻም ኢህአፓ ህቡዕ የገባበት ዘመን መሆኑን ያስታወሱት ምሁሩ፤ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጥያቄ እያየለ መምጣቱን እየጐለበተ የጥናት ክበቦች መጀመራቸውን፣ በመጨረሻም በተማሪዎች ንቀናቄ ውስጥ መከፋፈል እንዲሁም ስም የመለጣጠፍና ኢህአፓ “አንጃ” እና “ዋና” በሚል ለሁለት የተከፈለበትን ሁኔታ ቃኝተዋል፡፡ በእውነት ላይ የተመሰረቱና ውበት የተላበሱ መፃህፍት መፃፍ የሚችሉት የቀድሞ የኢህአፓ አባላት ብቻ እንደሆኑ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፤ ብእሩ የኛ ነው በማለት የህይወት ተፈራን መፅሃፍ አወድሰዋል፡፡

ስለአብዮት አይነቶች፣ አብዮት መቼ እና እንዴት እንደሚፈነዳ ከመፅሃፉ ጋር አያይዘው ትንተና ያቀረቡት ፕሮፌሰሩ፤ መፅሃፉ ላይ በተጠቀሰው የሌኒን “It is possible to predict the time and progress of revolution. It is governed by its own more or less mysterious laws.” የሚል አባባል መነሻነት 45 አመት በፊት የማላደርገው ነገር ግን ዛሬ ላይ ተሳስቷል የምለው አባባል ነው ብለዋል፡፡ “ለዚህ ደግሞ ምክንያቴ የሰውን ልጅ ባህርይ መተንበይ ስለማይቻልና የማይታዩ ታሪካዊ ሁነቶች ስለሆኑ ነው በማለት በማስረጃ አስደግፈው አብራርተዋል፡፡ የአረብ እስራኤል ጦርነት ባይኖር እና የነዳጅ ማእቀብ ባይደረግ ለአብዮቱ ወሳኝ አስተዋፅኦ የነበረውን የታክሲ ሾፌሮች የስራ ማቆም አድማ ማየት አይቻልም ነበር፡፡ ይህን ታሪካዊ ሁነት ደግሞ ማንም ግምት ውስጥ ሊያስገባው አይችልም” በማለት፡፡ ፀሐፊዋም በዚህ ሃሳብ ትስማማለች፡፡

“We didn’t see it coming it caught us by surprise...” (ሲመጣ ስላለየነው በአግራሞት ተዋጥን እንደማለት) ስትል ገልፃለች፡፡ አብዮቶች ነፃነት ያመጣሉ? በሚል ላነሱት ሃሳብ የጆርጅ በርናርድ ሾውን “አብዮቶች የጭካኔን ቀንበር አቅልለው አያውቁም፣ ከአንድ ትከሻ ወደሌላ ያስተላልፋሉ እንጂ” አባባል የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን አብዮት ጭካኔውን አስተላልፎ አያውቅም፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ እንደተደላደለ ነው ብለዋል፡፡ ይህቺ አለም በሰቆቃ፣ በረሀብ እና በነፃነት ጥያቄ እያለች አብዮት አይቀሬ እና ግዴታ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ገብሩ፤ “ወደፊት የሚመጣው የወጣቱ ትውልድ አብዮት ኢትዮጵያ” ጨምሮ በሕዝባዊ አመፅ ሊሆን ይችላል?” በማለት ታዳሚውን ከጠየቁ በኋላ “ዝምታችሁ መልሱን ነግሮኛል” ሲሉ ራሳቸው መልሱን ሰጥተዋል፡፡ ትውስታ (Memoir) እንደ አንድ የስነፅሁፍ ዘርፍ እንዴት እንደሚታየ ያብራሩት ዶ/ር ጌታቸው ሳህለማርያም በበኩላቸው ስለዛ ዘመን እና ትውልድ የተፃፉ መፃህፍት ተችተዋል፡፡ “ከደሙ ንፁህ ነኝ በሚል ተፎካካሪ ድምፆችን ጨፍልቀው፣ አመልካች ጣታቸውን ወደፊት ቀስረው እውነት ያለችው እኛ ጋ ነው የሚሉና በእውነት ስም እውነትን በወገናዊ አተያያቸው ሊያጣምሟት የሞከሩ ናቸው” ብለዋል፡፡ “ታወር ኢን ዘ ስካይ” ግን በወገናዊነት ተጀምሮ ከወገናዊነት በላይ ያደገ፣ ስለዛ ትውልድ ገድል እንድናወራው ሳይሆን እንድንጠይቀውና ራሳችንን በጥብቅ እንድንመረምረው የሚያስገድደን መፅሀፍ ነው ሲሉ እይታቸወን አንፀባርቀዋል - ዶ/ር ጌታቸው፡፡

“በዚህ መፅሀፍ በቀዳሚት ትኩስነት (ለፍቅር፣ ለእውቀት፣ ለትግል)፣ ቀጥሎ የወጣቱን የመረረ ትግል እና መስዋእትነት፤ በተለይ በአገሪቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፣ ከመሃል እስከ ድንበር በደርግና በታጠቁ ድርጅቶች፤ የተማገደውን ወጣት እያንዳንዱ ድርጅት በውስጡ የጫረው ምህረት የሌለው ትንቅንቅ እንዲሁም ግንባሮች እና ድርጅቶች እርስ በርስ የተራረዱበትን አውዳሚው እልቂት - መኢሶን ከኢህአፓ፣ ኢህአፓ ከህወሓት፣ ህወሓት ከኢዲዩ፣ ሰደድ ከመኢሶን፣ ሻዕቢያ ከጀብሀ፣ ጀብሀ ከህወሓት” ፍንትው አድርጐ ያሳያል የሉት ምሁሩ፤ በዚህ ትግል አሸናፊና ተሸናፊ ነበር ለማለት እንደሚከብድ ገልፀዋል፡፡ “በሰብአዊነት ሚዛን ከለካነው ሁላችንም ተሸናፊዎች ነን፡፡ ይህን የተሸናፊነት ምክንያት የፌሬድሪክ ኒቼ አባባል ይገልፀው ይሆናል፡፡ “ግፈኞችን ስትታገል አንተም ወደ ግፈኛ አውሬ እንዳትቀየር ተጠንቀቅ” ብሎ ነበር ብለዋል፡፡ “ታወር ኢን ዘ ስካይ”ን ሲያገላብጥ ያገኘሁት ወጣት፤ ስለመፅሐፉ ምን እንደተሰማው ስጠይቀው “ለመሆኑ ያ ትውልድ ኢትዮጵያን ያውቃታል? አይመስለኝም” አለኝ - ያሉት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ የትውልዱ ትልቁ ችግር ጥያቄዎችን የሚመዘውም መልሱን የሚፈልገውም ከመፃህፍት ከፅሁፍ ነበር ይላሉ፡፡

ይህን እውነት ማስተባበል ይከብዳል፡፡ ምናልባትም የዛ ትውልድ ድክመትና ውድቀት አንዱ ምክንያት ለራስ ባእድ፣ ለጥቅስ ታማኝ የመሆኑ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ የትውልዱ ጥንካሬ ደግሞ የቁሳዊ ሃብትና የስልጣን ተገዢ አለመሆኑ ነው” ሲሉ ያስረዱት ምሁሩ፤ ስለ ህዝባዊው ድል እየዘመረ እንደ ጭድ የረገፈ፤ እኩልነት፣ ነፃነትንና ፍትህን ለማንገስ የነበረውን ህልም ለመተግበር ማንንም ሳይጠብቅ የታገለና የተሰዋ ነው ብለዋል፡፡ ምሁሩ ሌላው ያነሱት ነጥብ በመባነንና ራስን በመፈለግ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ ፀሃፊዋ ውጣ ውረድ ከበዛው የትግል ተመክሮዋ ተነስታ Crowd mentality ወይም ስለጅምላ ስሪተ ህሊና ትገልኀለች፤ ፈላስፋው ዘርያዕቆብ “የልማድ እስረኞች ከመመርመር ይልቅ የሰሙትን ማመን የሚመርጡ ናቸው” ይላል፡፡ ጅምላ ስልተ ህሊና ከምክንያታዊና ሂሳዊ እውቀት ይልቅ ቡድኑን የሚገዙ እምነቶች የሚስተጋቡበት ስሪት ነው፡፡ ጅምላ መንገድም መዳረሻም ነው፡፡ ደራሲዋ የታሪኩን ጉዞ የደመደመችው በራሷ ላይ ያመጣችውን ለውጥ በመግለፅ ነው፡፡ ወደ ጅምላው ስሪተ ህሊና ለመደባለቅ መንገዱ ቀላል እና ግፊቱ ፈርጁ ብዙ ነው፡፡ የእድሜ እኩዮች ጫና፤ እውቅና የማግኘት ጉጉት፣ መጠጊያና መከታ ፍለጋ፤ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆን፤ በዘር መጓተት እና ሌሎችም፡፡

የመለያያው መንገድ ግን ቀላል አይደለም፡፡ ከጀማው ለመለየት የሚወስደው ጉዞ በአደጋ የታጠረ ነው፡፡ መገፋትን፣ መሳደድን፣ መገደልን፣ እንደ ከሀዲ መቆጠርን ያስከትላል፡፡ ከነዚህ አደጋዎች ውስጥ ራስን ቀና አድርጐ ለመውጣት ጠንካራ ሞራል፣ በራስ መተማመንና ሰፊና ጥልቅ የሆነ የእውቀት ስንቅን ይጠይቃል፡፡ የጅምላው አባላት ለጅምላው አላማ ከሚኖራቸው ታማኝነት ይልቅ ለመንጋው ያላቸው ተገዢት እጅግ የጠነከረ ነው፡፡ ትልቁ ቁምነገር አላማው ሳይሆን መለዮው ነው፡፡ ለዚህም ነው ከውጪ ጠላት ይልቅ መለዮውን ያጐድፋል ተብሎ የተጠረጠረውና በከሀዲነት የተፈረጀው የጌታቸው ማሩ እጣ ሞት የሆነው” ደራሲዋ በግል ነፃነትና በግለኝነት መሃል ያሰመረችው መስመር የደበዘዘውም ለዚህ ነው፡፡ ህይወት ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን ያልተጠየቁ ጥያቄዎችን አንግባ በህይወት መንገድ ረጅም ጉዞ ተጉዛ ትልቅ ማህበራዊ አንደምታ ያለው መፅሀፍ ይዛ መጥታለች፡፡ በዚህ ዘመን ለነበሩ ሌሎች ተዋናዮችም ይህን የመሰለ ድፍረት እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡ ያኔ ነው የአገራችን የፖለቲካ ዲስኮርስ ከዛ ትውልድ ጥላ ተላቆ እፎይታ የሚያገኘው፤ ይህ ትውልድ ካለፈው ትውልድ ተምሮ የወደፊት ራእዩን ከቂምና ከጥላቻ ውጪ መንደፍና እውን ማድረግ የሚችለው” ብለዋል - ምሁሩ፡፡

የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ደግሞ መፅሀፉን በኤግዚስቴንሺያሊዝም መነፅር የተነተኑ የተራኪዋ አቀራረብ ከግል ህይወት ተመክሮዋ በመነሳት ሰፋ ወዳለው የአብዮትና ርዕዮተ ዓለም ዳሰሳ የሚሸጋገርና በመጨረሻ እስር ቤት ባለችበት ወቅት ግለሰቡ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው በመደምደሟ ከኤግዚስቴንሺያሊስት ጋር ትዛመዳለች ብለዋል፡፡ መፅሃፉ የሰው ልጅ እጣ ፈንታ አንዴ ተበይኖ ያልተቀመጠና በምርጫ የሚወሰን መሆኑንና ምርጫው በፍርሃት እና በመርበድበድ የተሞላ እንደሆነም ያሳያል ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ በእምነት የተጠቀጠቀ ነው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ህይወት ጌታቸው፣ ማሩ መገደሉን ስትሰማ “የአሁኑን ሳይሆን የወደፊቱን ማየት ጀመርኩ፣ እውነት ነው ፓርቲው ልታገልልትና ልሞትለት የምፈልገው አይነት አልሆነም ነገር ግን ትግሉ ከሁሉም በላይ ነው” የሚል ሃሳብ እንደተፈጠረባት ጠቅሰዋል፡፡ የወጣቶቹ እምነትና ፅናት Indestructible እንደነበር ሲያስረዱም፤ “እነዛ ወጣቶች በሞት ጠርዝ ላይ የቆሙ ቢሆንም በአንድ ትልቅ ተስፋ የተሞሉ እና ጉዞ ላይ እንዳሉ ይታወቃቸው ነበር፡፡

በውስጣቸው ያለው ያለመበገርና ያለመሸርሸር ፅናት በፈታኝ ወቅት እንኳን አልከዳቸውም ብለዋል፡፡ አምበሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል በበኩላቸው፤ ከደራሲዋ ጋር የነበራቸውን ቅርበትና አብረው የቆዩ መሆናቸውን በመጥቀስ መፅሀፉን በዛ መነሻ ቃኝተውታል፡፡ ንግግራቸውን ሲጀምሩም፤ “ይህ ውይይት በዶ/ር እሸቱ ጮሌ አዳራሽ በመከናወኑ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ታዋቂው ምሁር እንደኛ እስረኛ ነበር፡፡ ስለመፅሀፍ መፃፍ ስናወራ ያጋጠመውን አጫውቶኝ ያውቃል፡፡ አራተኛ ክፍለ ጦር በጠዋት መጥተው የያዛችሁትን አስቀምጣችሁ ውጡ ተባሉ፡፡ ለአሰሳ የመጡ መስሎት በሁለት ደብተር የፃፈውን በጋቢው ስር ሸጉጦ ወደ መፀዳጃ ቤት በመሮጥ ቀድዶ ውሃ አፈሰሰበት፡፡ እንዳሰበው ሳይሆን የዛን እለት ጃንሜዳ ወስደው ፈቷቸው፡፡ በአራተኛ ቀን እቃቸውን ለመውሰድ ሲመለሱ እቃቸውን በሙሉ እንደተውት ሲያገኙት ቢናደድም እንደገና እንደማይፅፈው ሲያስብ በሀዘን ተዋጠ፡፡ ይህ የብዙ እስረኞች እጣ ነበር” ብለዋል፡፡ መፅሃፉ በእስር ዘመናችን እንወያይባቸው በነበሩና በማውቃቸው ጉዳዮች የተሞላ ቢሆንም ደጋግሜ አንብቤዋለሁ ያሉት አምባሳደሯ፤ “በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አጥንትና ስጋ አልብሳ፣ እስትንፋስ ዘርታ ነው ያቀረበችው፡፡

ብርሃነ መስቀል እና ጌታቸው በህይወት እያሉ ሊያገናኙን ሞክረው ባይሳካላቸውም እነሱ ካለፉ በኋላ እስር ቤት ተገናኘን፡፡ እስር ቤት እያለሁ የተወለደችው ልጄ ትስስራችንን አጠናከረችው፤ ህፃኗ ከእስር ቤት እንድትወጣና ቤተሰብ እንድትቀላቀል የፈቀድኩትም ህይወት ስትፈታ ነው፡፡ ኑሮን ለመልመድና ለመረጋጋት… ያስቻለቻት እሷ ናት፡፡ መፅሃፉ ቀናነት የተመላው፣ ውይይትና መቻቻል እንዲመጣም ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡ አቶ ወልደልኡል ካሳ ከዩኒቨርሲቲ ወደ አሲምባ፣ ከአሲምባ ወደ አሜሪካን የሄዱ የኢህአፓ አባል ሲሆኑ፤ አሜሪካ በሄዱበት ወቅት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ያስጨነቃቸውም እስር ቤት ያሉ ልጆች ጉዳይ ነበር፡፡ “የታሰሩት ምን ተስፋ ያደርጉ ይሆን? እስር ቤት ተሰብሮ ነፃ እንሆን ይሆን? ጓዶች ቀይ ባንዲራ ይዘው ይመጣሉ ብለው ይጠብቁን ይሆን?” የሚለው ያስጨንቀኝ ነበር ብለዋል፡፡ ከምሁራኑ የመፅሃፍ ዳሰሳ በኋላ በተካሄደው ውይይት የተለየዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የጅምላ ስሪት ህሊና (Crowd mentality) የሚለው ጉዳይ አብዛኞቹን የኢህአፓ አባላት ቱግ እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ አንድ የቀድሞ የኢህአፓ አባል “መንጋ አልነበርንም፤ አውቀን ነው የገባንበት” ሲል ተቃውሞውን የገለፀ ሲሆን የዳሰሳው አቅራቢ ምሁር በሰጡት ምላሽ የጅምላ ስሪተ ህሊና የሚለው ከራሴ ያመጣሁት ሳይሆን የመፅሀፉ ደራሲ ከተጠቀመችበት በመነሳት ነው” ብለዋል፡፡

ያለፈው ትውልድ ጥያቄውንም መልሱንም የሚመዘው ከመፅሀፍት እና ከጥቅሶች ላይ ነው በሚል የቀረበው አስተያየትም የቀድሞ የኢህአፓ አባላት ቅንድብ ያስቆመ ነበር፡፡ የኮምፒዩተር ባለሙያውና የዳሰሳ አቅራቢ የነበሩት አቶ ወልደልዑል ሲመልሱ፤ “መፅሀፍ ላይ የመጣው ኩነኔ አይገባኝም፤ ታድያ ከየት ይምጣ ከመፅሀፍ እንጂ እንደድሮ ዶቃ አይመጣ” ያሉ ሲሆን ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በበኩላቸው፤ “ያ ትውልድ ኢትዮጵያን በደንብ ያውቃታል፡፡ የመሬት ላራሹ ጥያቄ የኢትዮጵያ የገበሬ ጥያቄ እንጂ ከመፅሀፍ ላይ የተወሰደ አይደለም” በማለት መልሰዋል፡፡ ይህ ትውልድ ከራሱ ጋር የሚታረቀው መቼ ነው በሚል ለቀረበው ጥያቄም ፕ/ር ገብሩ ታረቀ “የሃሳብ ልዩነት አለመግባባት ነበር እንጂ አልተጣላም” ብለዋል፡፡

በኢህአዴግ ዘመን የተተከለውን የሰማዕታት ሐውልት በተመለከተ ዶ/ር ዳኛቸው በሰጡት አስተያየት፤ “የኢህአዴግ ፍላጐት የወደቁትን የኢህአፓ ወጣቶችና መኢሶንንም ላለማስቀየም የማቻቻል ሁኔታ ያለበት ነው፡፡ ገና ሲገባ የመንግሥቱ ነዋይ ሀውልት ብሎ ነበር፤ አስራ አምስት ሰው ረሽኖ እንዴት ነው ሰማእት የሆነው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “በአጭር የተቀጨ የረጅም ጉዞ፤ ታሪክ” በሚለው የመኢሶን መፅሃፍ ላይ “እኛን ለምንድን ነው ከፊውዳሎቹ ጋር እየጨመራችሁ የምትገድሉን” በሚል ለደርግ የፃፉት ደብዳቤ መኖሩን የጠቀሱት ዶ/ር ዳኛቸው “ፊውዳል መግደል ስፖርት ነው” ሲሉ ታዳሚውን አስፈግገዋል፡፡ ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ውይይት የተደረገባቸው ቢሆንም የቦታ ውሱንነት ከዚህ በላይ እንዳልቀጥል አስገድዶኛል፡፡

Read 6396 times