Print this page
Saturday, 19 November 2011 14:04

ኢህአዴግ፣ ከ20 ዓመት በኋላ እራሥን ስለመውደድ ፍልስፍና ሲያቀነቅን …

Written by  ናርዶስ ጂ.
Rate this item
(0 votes)

አቶ ልደቱም በ”መድሎት” መጽሐፋቸው ፍልስፍናውን በአፅንኦት ተችተውታል …
- ፍልስፍናው፣ ጥቂት ለማይባሉት አባላቱም የእግር እሣት የሆነባቸው ይመስላል …
“ፍልስፍና” ስል፣ የብዙ አሠራሮች መርህ ማለቴ ነው፤ ወይም ለአፈፃፀም ጣጣችን ማስኬጃ የሚሆን ከብዙ የኑሮ ልምዶች በብልሃት ተጨምቆ የሚወጣ “የአኗኗር መመሪያ” በሚል መረዳት ይቻላል፡ እናም፣ በመርህ ደረጃ ገደብ ያለፈ ሊባል ስለሚችለው የራስ መውደድ ልክፍት ማሣያዎችና የፍልስፍናውን ኢህአዴጋዊ መገለጫዎች ባጭሩ ላቅርብ፡፡

ኢህአዴግ እንደ ሃገር አስተዳዳሪ መንግስትነቱና እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅትነቱ፣ የሚሰብከው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና የሚፈፅመው ተጨባጭ ተግባር ለየቅል ይሆኑበታል በሚል በተደጋጋሚ ተተችቷል፡፡ በራሡ የውስጥ ግምገማውና በራሡ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በመንግስት የመረጃ ማሰራጫዎች ሣይቀር እራሡን ሲወቅስም ታይቷል፡፡ ፖሊሲዎቹ ሁሉ የሃገራችንን ችግሮች እንደሚፈቱ፣ ግን የአፈፃፀም ችግሮች በየጊዜው እግር ከወርች ጠፍረው እንዳሠሩት በራሡ ልሣን ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ “ዘቅጫለሁ … በስብሼያለሁ” በማለት ራሱን በይፋ እስከ መሣደብ የደረሠባቸው ወቅቶች ነበሩ፡፡  
ይህን ራስን የመገምገም “ብቃቱን” እንደ ጠንካራ ጐን፣ በዋናዎቹ “የፖለቲካ መነኮሳቱ” ቡራኬ አሰጥቶበታል፤ አንዳንድ ያልበሠሉ ካድሬዎቹ “የታላላቅ መነኮሳቱን” ቡራኬ ገለባብጠው እያስተጋቡ እንደየአቅማቸው አስተንትነዋል፡፡ “ኢህአዴግ እራሡን የሚገመግምና የተንሻፈፈውን አመራሩን የሚያስተካክል ጠንካራ ድርጅት ነው” በማለት ባልተረዱት መድረክ ላይ ሣይቀር እየደሠኮሩ፣ ይኩራራሉ፡፡ በጅምላ አስተሣሠብ፣ በስሜት የሚናጡ አንዳንድ ወገኖችም ኢህአዴግ ራሡን የመገምገም ብቃቱ ሣይገባቸዉ ጭምር በአድናቆት ሢጮሁ ተሠምቷል፡፡
የሠከነ የፖለቲካ ፍልስፍና የሚያራምዱ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ፣ “የኢህአዴግ ግምገማ፣ የተሣሣቱ የፍልስፍና ዛፎችንና ችግኞቹን ከስሩ መንግሎ ከማስወገድ ይልቅ፣ ግንዳቸው ላይ ይቆርጣቸዋል፤ ውለው ሢያድሩ የተቆረጡት ግንዶች፣ የተለያየ መጠንና ጥንካሬ ያላቸው ብዙ የተሣሣቱ ፍልስፍናዎችን ያበቅላሉ፤ ብዙ የችግር ቅርንጫፎች ችፍግግ ብለው ይወጡባቸዋል፡፡ ግምገማው፣ እራሥ ወዳዳዊ ፍልስፍናውን ወይም የፖለቲካ መርሁን ደፍሮ ስለማይተቸው፣ የኋላ ኋላ የችግሩን ግንድ ትቶ የተወሠኑት ቅርንጫፎቹን ብቻ ይዳስሳል፡፡ ሥለዚህ፣ ስር ነቀል ለውጥ የማያመጣ የይስሙላ ተግባር ሆኗል - የራስ ግምገማው” በማለት ይሞግታሉ፡፡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ፣ ኢህአዴግ፣ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሢገመገምና እንደ አንድ የሃገር አስተዳዳሪ መንግስት ሢመዘን ውጤቶቹ በጣም የተራራቁ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ከመንግስትነቱ ይልቅ፣ ፖለቲካዊ ድርጅነቱን አግዝፎ ለመትከል በመጣጣሩ፣ በአንዳንድ አርቆ አስተዋይ አባላቱ ሳይቀር ይተቻል፡፡ ይሄው ድርጅታዊ ትጋቱ፣ እውነተኛ ግምገማ እንዳያደርግ፣ ሃገራዊ ሃላፊነቱን፣ ከድርጅታዊ ህልውናው ነጥሎ አሳንሶ እንዲመለከት አድርጐታል ይባላል፡፡ ለዚህ ነው የችግሩን ግንድ ወገቡ ላይ በመቁረጥ የይስሙላ መፍትሄ ፈላጊ በሚያስመስለው ግምገማው፣ ችግሮቹን አብዝቶ፣ የተሣሣቱ ፍልስፍናዎቹንና ቅርንጫፋቸውን አራብቶ ከፈርጀ ብዙ ችግሮች ጋር በተደጋጋሚ ፊት ለፊት ሢጋፈጥ የሚታየው፡፡
የቅርብ ጊዜ ምሣሌዎችን ብናነሣ እንኳ፣ 50 ከመቶ በላይ እያሻቀበ ባለው የገንዘብ ግሽበት ጦስ ሣቢያ ለተከሠተው ከልክ ያለፈ የኑሮ ውድነት የወሠደውን መፍትሄ አይተናል፡፡ የችግሩን ግንድ ወገቡ ላይ በመቁረጥ መፍትሔ ለማምጣት በተንቀሣቀሠበት አቅጣጫ፣ የዋጋ ተመን ማውጣትና “ስግብግብ” ያላቸውን ነጋዴዎች መቆጣጠር ጀመረ፡፡ ውጤቱ ግን ሸቀጦችን ከጣራ በላይ እንዲወደዱ ከማድረግ አልፎ ለአይን እንኳን እንዲጠፉ ነበር የሆኑት፡፡
ራቅ ያለ ምሣሌ እናንሣ ቢባል ለኢትዮ ኤርትራ የፖለቲካ ድርጅቶቹ መሪዎች ግብታዊ ተግዳሮትና ግጭት የተወሠደውን መፍትሔ ማውሳት ይቻላል፡፡ ሁለት ወንድማማች ህዝቦችን ወደ ደም መፍሰስ ያስገባ ብሎም፣ ወገኖች ከተወለዱበት፣ ካደጉበትና ከኖሩበት ሃገር ለቀው እንዲወጡ ያደረገና በትውልዶች ላይ የማያባራ ፍጅት እንዲፈጥር የሚያነሣሡ ሁነቶች እንዲከሠቱ ያደረገ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ መፍትሔው፣ ከችግሩ የበለጠ ችግር ፈጣሪ የሆነበት ብዙ አጋጣሚዎችን ኢህአዴግ አሣይቶናል፤ በአንዳንድ ሀጢያቶች ላይ ንስሃ ለመግባት ቢሞክርም፡፡ ለምሣሌ፣ ከሃገር እንዲወጡ የተደረጉ “ኤርትራዊያን” ወገኖች እንዲመለሡና ሃብት ንብረታቸው እንዲያስተዳድሩ ተደርጓል፡፡ ከዚህም አልፎ፣ በተለያየ ምክንያት ኤርትራን የለቀቁ፣ ከሻቢያ መንግስት ሸሽተው የመጡ ወገኖች በየደረጃው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሣይቀር ገብተው እንዲማሩ በማድረግ የዘመናት መርቃዥ ቁስሎችን ለማድረቅ የሚደረገው ጥናት በበጐነቱ ይጠቀሣል፡፡
ኢህአዴግ ከ20 ዓመት በኋላም ወደ ድርጅታዊ ማንነቱ ባተኮረ መልኩ እራሥን ብቻ አብዝቶ የመውደድ ፍልስፍና ማቀንቀኑን የሚጠቁሙ የተለያዩ ተግባራትን በማን አለብኝነት ሢያከናውን ታይቷል፡፡ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ፋይዳቸው ይልቅ፣ በፖለቲካ ድርጅቱ ያላቸው ታማኝነት ብቻውን መመዘኛ እየሆነ፣ የአቅም ችግር ያለባቸው ካድሬዎችን በተለያዩ የህዝብ መገልገያ ቁልፍ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ሢያስቀምጥ ታይቷል፡፡ ህዝብ ተበደልን፣ ተሠቃየን ሢል “ጆሮ ዳባ ልበስ” የሚለው ኢህአዴግ፤ በሌሎች አባላቱ ጭምር ችግሩ ገፍቶ ከመጣ፣ አንዳንድ “ልብ አድርቅ” የሚባሉ ካድሬዎቹን ከአንድ ሃላፊነት ቦታ አንስቶ በአብዛኛው ከፍ ወዳለ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ አዛውሮ እንዲሠሩ ያደረገበት ብዙ አጋጣሚዎች (በተለየ በየክልሎቹ) እንዳሉ ይነገራል፡፡
በድርጅታዊ ጉዳይ ላይ ቅንጣት ስህተት ሢገኝበት፣ ወይም በሰሞኑ በኢህአዴግ በራሱ አገላለጽ፣ “ወደ መንግስት ሥራ አድልተሃል” በሚል ከሃላፊነት ያለ ርህራሄ ሢመነጥቅ ደግሞ “ጨካኝ” ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምንም በህዝብ የሚወደድ የሥራ መሪ ቢሆን፣ በድርጅታዊ ጉዳይ ላይ ቀልድ የለም - ከድርጅታዊ ተግባር ትንሽ ዘንበል ካለ ከሃላፊነት ወንበሩ ያሽቀነጥረዋል፡፡
ለዚህ ነው፣ ዛሬም ከ20 ዓመት ሀገር የመምራት የሽምግልና እድሜው ላይ (ድርጅቱ በራሡ በርግጥ “ገና ሠርቼ ያልረካው ወጣት ነኝ፤ ገና ወደፊት ገደብ ለማይደረግባቸው አመታት የማስተዳደር ሚና ያለኝ “አውራ ፓርቲ” ነኝ ማለቱን ሣንዘነጋ) በተቀመጡበት የሀላፊነት ቦታ ላይ በትምህርት አይነታቸው፣ በሙያ ደረጃቸውም ሆነ በአጠቃላይ ብቃታቸው ምንም የማይገጥሙ (የማይመጣጠኑ) የተለያዩ የድርጅቱን ቀኖና ብቻ የሚያነበንቡ አንዳንድ “ጅምር ምሁራን” ካድሬዎቹን እየሾመብን፣ እየሠየመብን የምናየው፡፡ አንዳንድ ወገኖች እንደውም፣ ”ዶክተሩ ሲዘፍን ዘፋኙ ቀዶ ጥገና ሲያደርግ የሚታይበት” የስራና ሠራተኞች (ካድሬዎች) ጥምረትን ኢህአዴግ አሁንም እየገፋበት እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡
እንዲህ አይነት እጅ እግር የሌለው የሥራና የካድሬዎች ጥምረትን ኢህአዴግ ለምን ተግባራዊ እንደሚያደርገው ግን ብዙዎች ከምንጩ መረጃ ሢሠጡ አይታይም፡፡ ጉዳዩ ግን፣ መሠረቱን ከሣተ የራስ መውደድ ፍልስፍና ከማቀንቀን የሚመጣ ግትር የፖለቲካ ፓርቲ አካሂያድ መሆኑን ማስተንተን የሚቻል ይመስለኛል፤ ከሃገር ህልውና ይልቅ የፓርቲን ህልውና ከማስቀደም ጭፍን ፍልስፍና የመጣ ማን አለብኝነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስዬ አብርሃ፣ ቀደም ሲል በኢህአዴግ ውስጥ ከነበራቸው አድራጊ ፈጣሪነት አንፃር ያሉትን ሁሉ “ትክክለኛ ነው” ብሎ ማመን የሚከብድበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የዋስ መብታቸው ተነስቶ ወደ ወህኒ እንዲወርዱ የተደረጉት በሠሩት ሙስና ሣይሆን ከፖለቲካ ድርጅቱ (“ከህውሃት-ኢህአዴግ”) ቡድናዊ አመራርና አስተሣሠብ በማፈንገጣቸው እንደሆነ የተናገሩት ሁኔታ፣ ከጅርጅታዊ ህልውናው ጋር ተያይዞ የኢህአዴግን ቀልድ አያውቄነት የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡
ከፍተኛ ትምህርታቸውን በውጭ ሃገር በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው፣ “መድሎት” በሚለው መጽሐፋቸው፣ የኢህአዴግን ፅንፈኛ የራስ መውደድ ፍልስፍና አቀንቃኝነት ለማጋለጥ ሞክረዋል፡፡ አቶ ልደቱ፣ ኢህአዴግ በሃገሪቱ ላይ ከተከሠቱት ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለና ጠንካራ መሆኑን ይመሰራክሉ፡፡ ኢህአዴግ ዋና መሪዎቹንና አባላቱን በአንድ ማስተሣሠር የሚችል፣ ከ97ቱ ቅንጅትም ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ የመሪዎች መከባበርና መደማመጥ የሚታይበት፣ በብዙ መመዘኛዎቹ ጠንካራ የሚባል ድርጅታዊ መሠረት የገነባ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንደውም፣ ኢትዮጵያዊያን አብሮ መሥራት አይችሉም የሚለውን አባባል ተረት ያደረገ፣ ተጋግዘውና አብረው የሚሠሩ መሪዎችን ማፍራት የቻለ ጠንካራ ፓርቲ ነው” በማለት ያደንቁታል፡፡ ኢህአዴግን ከድርጅታዊ አቋሙና ማንነቱ ጋር አያይዘው ባነሡት ክፍል መጨረሻ ላይ የሠነዘሩት ሀሣብ ግን “ፅንፈኛ ራስን የመውደድ ልክፍት” ያልነውን አቋሙን ቀጥ ብለን እንድንመረምር ያነቃል፤ “ኢህአዴግ ድርጅታዊ አቋሙ ጠንካራ ቢሆንም፣ ለሀገር የማያስብ ፓርቲ ነው” ብለዋል፡፡
እዚህ ላይ፣ ከምንመገበው ምግብ ሣይቀር፣ ከመንጋጋችን ላይ መንጭቆ የሠበሠበውን ግብር ደመወዝ እየከፈለ፣ እኛ በምንገለገልባቸው የሃላፊነት ቦታዎች ላይ እንደፈለገው የሚሾም የሚሽረው ኢህአዴግ፣ የመንግስት ሠራተኞች የሆኑ አባላቱን “ወደ መንግስት ስራ አድልተሃል” በማለት ማገማገሙን ያየ ወይም የሰማ፣ ከሃገር ህልውና ይልቅ የድርጅት ህልውና እንደሚያስቀድም ቅንጣት ባይጠራጠር አይገርምም፡፡
በከፍተኛ የሃገር ሃብት፣ በህዝብ ገንዘብ የሚማሩትን አባላቱን፣ በድንገት የከፍተኛ ትምህርታችሁን አቋርጣችሁ የ2005ቱን የአዲስ አበባ ምርጫ እንዳሸንፍ፣ የፖለቲካ ሥራ ሥሩ፣ አባላት አፍሩ፣ ህዝብ የማሣመን ሥራ ፈፅሙ …” ብሎ በረዶ ሲያፈላባቸው ያየ ወይም የሰማ “እግዚኦ! ገደብ ያለፈ እራስን የመውደድ ህመም! እግዚኦ የፖለቲካ ፓርቲ ፍቅር! እግዚኦ ለድርጅት ህልውና መሟሟት!” ማለቱ አይቀርም፡፡ ዘንድሮ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ አባላቱ፣ በዚህ ድንገተኛ ድርጅታዊ ቀጭን ትዕዛዝ በጣም ተደናግጠዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ትምህርታቸውን አቋርጠው ፖለቲካዊ ሥራ ከሠሩ በኋላ ኢህአዴግ ቢሸነፍ እጣ ፈንታችን ምን ይሆን በማለት በሀሣብ ተወጥረዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ የተደረጉበትን ዝርዝር ሁኔታና መመሪያ ሢጠይቁ ምላሽ የሚሠጥ ሀላፊ ማጣታቸው ሁሉ ተሠምቷል፡፡
“ድርጅቱ ከሌለ እኛም የለንም .. ቅድሚያ ለድርጅታችን የሞት ሽረት ትግል በማድረግ መስዋዕትነት መክፈል አለብን” በማለት የማሣመን ሃላፊነት የተሠጣቸው አመራሩም፣ አንዳንዶቹ ከመድረክ ሢወርዱ ያጉተመትሙ ነበር፡፡ በተለይ በትምህርት ላይ የነበሩት ሃላፊዎት ሀዘናቸው፣ በመድረክ ከሚደሠኩሩት ድርጅታዊ አቋማቸው ጋር ፍፁም አይገጥምም፡፡ ቀድሞውኑ ያልገባቸው፣ የአውራ ፓርቲያቸው ፅንፈኛ የራስ መውደድ ፍልስፍና ነበር ማለት ይቻላል፡፡ “አውራ ፓርቲው ኢህአዴግ” እነ ልደቱ እንደመሠከሩት በውድም ይሁን በግድ ድርጅታዊ ህልውናን ማስጠበቅ ለድርድር የማይቀርብ አካሂያዱ ይመስላል፡፡
“ለመንግስት ወይም ለሃገር ሥራ ማድላት”፣ ከሃገር በላይ በራሡ ህልውና ለሚዋደቅ ፓርቲ የሃጢያቶች ሃጢያት ሆኖ ቢታየው ለምን ይገርማል? ደም በመክፈል ጭምር የመጣን ድርጅታዊ የበላይነትና ጥንካሬ፣ “እንደ ቀልድ” መስዋዕትነት ላልከፈሉ ቡድኖች ወይም ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አሣልፎ መስጠት ለኢህአዴግ እስከ መጨረሻው የማይዋጥለት ጉዳይ ሆኖ የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡
እንደ አየን ራንድ “ራስን መውደድ ቅዱስነት ነው” የሚሉ ለግለሰባዊ ማንነታቸው ለቆሙ፣ የራሣቸውን ኑሮ ለመቀየር ለሚፍጨረጨሩ አባላቱ፣ “ለድርጅታችሁ ሥትሉ ትምህርታችሁን አቁሙ” ሲባሉ ምን ይሉ ይሆን? … “መጀመሪያ የራስን መቀመጫ በአለት ላይ መገንባት … በራስ መስዋዕትነት የመጣን ድርጅታዊ ሥልጣንና አቅም ለራስ ብቻ መጠቀም … ቅዱስነት ነው፣ ዓላማ ተኮር የኑሮ ስልት ነው” የሚሉ ብዙ ገልብጦ አንባቢ የፖለቲካ ፓርቲ ምሁራን በበዛባት ሃገር፣ ኢህአዴግ “መጀመሪያ በድርጅታዊ ህልውናዬ!” ማለቱ ምኑ ነው ሃጢያቱ? እኔጃ!

 

Read 2812 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:12