Saturday, 13 July 2013 10:29

በ“ጋምካ” መታገድ ተጓዦች እየተጉላሉ ነው

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(6 votes)

ባለፉት 11 ወራት 190ሺ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳውዲና ኩዌት ሄደዋል

ወደ ሳውዲ አረቢያ እና ኩዌት ለስራ ለሚሄዱ ተጓዦች የጤና ምርመራ ለማድረግ ውክልና የተሰጣቸው 8 የህክምና ተቋማት የመሰረቱት ማህበር (ጋምካ) በዚህ ሳምንት በመታገዱ ተጓዦ፣ እየጉላሉ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በቦሌ እና በቂርቆስ ክ/ከተሞች የንግድ ፈቃድ የተሰረዘበት ጋምካ፣ “የውጪ ንግድ ረዳት ኮሚሽን ኤጀንት” በሚል ዘርፍ ከንግድ ሚኒስቴር ያወጣው ፈቃድ ደግሞ ሰሞኑን ታግዶበታል፡፡ ሳዑዲ አረቢያና ኩዌትን ጨምሮ ከገልፍ አገራት በኩል እውቅና የተሰጣቸው 8 የጤና ተቋማት በማህበራቸው (በጋምካ) በኩል ካልሆነ በቀር፣ በተናጠል ለተጓዦች የጤና ምርመራ ማረጋገጫ ወረቀት ማዘጋጀት ስለማይችሉ ተጓዦች እየተጉላሉ ነው፡፡ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመሄድ ለበርካታ ወራት የፓስፖርት፣ የኤጀንሲ፣ የቪዛ ጉዳያቸውን ሲያስፈጽሙ የከረሙ በርካታ ሴቶች፣ ድንገት ጋምካ በመዘጋቱ ግራ ተጋብተው በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ደጃፍ ተሰብስበው ጥያቄ ሲያቀርቡ ሰንብተዋል፡፡

ከደሴ የመጣችው ሉባባ ሁሴን፣ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመሄድ ከሶስት ወር በፊት የጤና ምርመራ ብታደርግም ቪዛ ስለዘገየባት የምርመራው ውጤት ጊዜው አልፎበት እንደተቃጠለባት ትናገራለች፡፡ ከበርካታ የመንደሯ ልጆች ጋር፣ መርካቶ አቅራቢያ አሜሪካን ግቢ በሚባለው አካባቢ በደባልነት ቤት ተከራይተው ጉዳያቸውን እንደሚከታተሉ ሉባባ ገልፃ፣ ቪዛ ዘግይቶ ጉዞዋ ስለተጓተተ ቤተሰቦቼ ተጨንቀዋል ብላለች፡፡ “በጣም ነው የጨነኝ፣ ቶሎ ተመርምሬ ካልሄድኩ ቪዛ ይቃጠልብኛል” የምትለው ሉባባ፣ ትሄዳለች ብለው ለሚጠብቋት ቤተሰቦቿ ችግሯን ለመንገር መሳቀቋን ገልፃለች፡፡ የጋምካ የአገልግሎት አሰጣጥ በበርካታ ችግሮች የተሞላ ነው የሚሉት የአስሊ ኤጀንሲ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አንሷር መሐመድ፣ ይሁን እንጂ ጋምካ ሲታገድ መንግስት አማራጭ ስላላስቀመጠ ኤጀንሲዎችና ተጓዦች ለእንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ጋምካን የመሰረቱ የጤና ተቋማት በአገር ውስጥ የመንግስት አካላት ተመዝግበው የሚሰሩ ክሊኒኮች ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ ማህበራቸው ከገልፍ አገራት የውክልና እውቅና ተሰጥቶታል፡፡

ይሁንና፣ ጋምካ ለተጓዦች የሚሰጠው የጤና ምርመራ ውጤት ላይ በተደጋጋሚ ስህተቶች እንደሚከሰቱ አቶ አንሷር ይገልፃሉ፡፡ በጋምካ ምርመራ የጤና ችግር አለባችሁ የተባሉ ተጓዦች ሌላ ቦታ ሲመረመሩ ጤነኞች ሆነው ተገኝተዋል የሚሉት አቶ አንሷር፤ በጋምካ የጤና ችግር የለባችሁም ተብለው ወደ አረብ አገራት የተላኩ አንዳንድ ተጓዦች ደግሞ እዛ ተመርምረው ውጤታቸው ትክክለኛ አለመሆኑ ተነግሯቸው ተመልሰዋል ብለዋል። በተሳሳተ የጤና ምርመራ ሳቢያ የሚንገላቱ ዜጐች በኛ በኤጀንሲዎች ላይ አቤቱታ ያቀርባሉ፤ የትራንስፖርት እና የደሞዝ ወጪዎችን ለመሸፈን ስለምንገደድ ኪሳራ ይደርስብናል ብለዋል አቶ አንሷር፡፡ አንዲት ተጓዥ ለምርመራ ከሶስት መቶ ብር በላይ ማውጣት እንደሌለባት አቶ አንሷር ገልፀው፤ ጋምካ ግን ስምንት መቶ ሃምሳ ብር ሲያስከፍል ጠያቂ የለውም ብለዋል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባ ፍቃድ ተጠባባቂ ዳሬክተር አቶ ደሬሳ ሆቱ፣ መጀመሪያውኑ ለጋምካ የተሰጠው ፈቃድ ላይ ክፍተት አለ ይላሉ፡፡ ጋምካ “የጽሕፈት አገልግሎት እሰጣለሁ” ብሎ ከቦሌና ከቂርቆስ ክ/ከተሞች ፍቃድ አውጥቶ እንደነበር አቶ ደሬሳ ጠቅሰው፤ የጋምካ አገልግሎት ከዚህ ውጭ ነው ተብሎ እንደተሰረዘበት አስታውሰዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ህዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ፣ የጋምካ አገልግሎት “የውጪ ንግድ ረዳት ኮሚሽን ኤጀንት” በሚል ዘርፍ እንደሚካተትና በዚሁ ዘርፍ ፈቃድ እንዲሰጠው የሚጠይቅ ነው፡፡ በደብዳቤ መሰረት ንግድ ሚኒስቴር ለጋምካ ፈቃድ መስጠቱን የገለፁት አቶ ደሬሳ፣ ጋምካ እውቅና ከተሰጣቸው የውጭ አካላት ጋር የተፈራረመውን የኮሚሽን ኤጀንትነት ህጋዊ ውል ማቅረብ እንሚደጠበቅበት ጠቅሰዋል፡፡ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በበኩሉ፤ ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም፤ የጤና ጉዳይ ክትትል አናደርግም በማለት የህዝቡ ግንኙነት ምክትል ዳሬክተር ወ/ሮ እመቤት ሙሉ ይናገራሉ፡፡ ባሳለፍነው አስራ አንድ ወራት ብቻ በህጋዊ መንገድ ወደ ሳውዲ አረቢያና ኩዌት የተጓዙ ዜጐች ብዛት 190ሺህ እንደሚደርስ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

Read 17194 times