Saturday, 06 July 2013 13:36

ፍርሐት

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(4 votes)

                      እያነበበ ነበር የቆየው እስከ ምሽቱ አራት ሰአት ድረስ፡፡ መፅሐፍ በህይወት ዘመኑ ከሶስት የበለጠ አንብቦ አያውቅም፡፡ ሶስተኛውን ሊጨርስ ትንሽ ነው የቀረው፡፡ ሦስት ሰአታት ማንበብ ቢቀጥል ይጨርሰዋል፡፡ ዝናቡ ድንገት ሲቆም ፀጥታ በቤቱ ውስጥ እና ዙሪያ ሰፈነ፡፡ ከጫጫታ ለመራቅ ብሎ ነው ከሳምንት በፊት እዚህ አገር ቂጥ፣ ጫካ መሐል ገና ጭቃው ያልደረቀ ቤት በ600 ብር የተከራየው፡፡ ከጫካው በታች ወንዝ አለ፡፡ ፀጥታው ለምን ድንገት እንደረበሸው ሊገባው አልቻለም፡፡ መፅሐፉን አጥፎ በሰላ ጆሮው ማድመጥ ያዘ፡፡ የቤቱ ጣሪያ ላይ የባህር ዛፍ ቅጠል ይራገፍና ይንገዋለላል፡፡ ደስ የማይል ስሜት ተሰማው፡፡

መፅሐፉን ዘርግቶ ማንበብ ቀጠለ፡፡ ከአረቄ ለመራቅ ሲል ነበር ከድሮ ሰፈሩ ወጥቶ ጫካ የገባው፡፡ ያሸፈተው የአረቄ ሱስ … ከፋኖ ጫካው እየጠራ፣ ሲያስወጣው ቁርጥ ውሳኔ ወሰነ። የዛሬዋን እለት ከቤት ንቅንቅ ሳይል እንደሚውል ለራሱ ማለ፡፡ አረቄው ሲጠራው አልሰማም ብሎ መፅሐፉን አይኑ ላይ ከልሎ፣ ሲያነብ - ሲያነብ። በማያስቀው ታሪክ ሲስቅ … ባልገባው ጥልቀት ሲዘፈቅ … “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ይላል የመፅሐፉ አርዕስት፡፡ ዋናው ነገር መፅሐፉን አንብቦ መጨረሱ ብቻ ነው፡፡ ከዋናው ነገር በላይ ደግሞ በመፅሐፉ የአረቄውን በል-በልታ አሻፈረኝ ብሎ መተኛት፡፡ ተሳክቶለታል፡፡ ከምሽቱ አራት ሰአት ሞልቷል፡፡ “አረቄ ሱስ የለውም ማለት ነው” ሲል ቆየ፤ ከምሽቱ አንድ ሰአት ጀምሮ፡፡ መፅሐፉ ላይ ያሉ የተወሰኑ አረፍተ ነገሮችን ያዋሰው ሰው ነገ ቢያወራው በወሬው እንዲሳተፍ ይዟል፡፡ ሸምድዷል፡፡ ለወሬ ያህል፡፡ ከወሬ ጃንጥላ ውጭ መሆን ያስፈራዋል፡፡

መፅሐፉ ስለምን እንደሆነ ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡ ስለ መክሸፍ ነው፤ እሱ ዛሬ በመፅሐፉ አማካኝነት የአረቄ ሱሱን ማክሸፍ ችሏል። ስለ “መክሸፍ” በማንበብ “ማክሸፍ” ይቻላል፡፡ ፀጥታው ረበሸው፡፡ ንባቡን መቀጠል አልቻለም። “ፍሬ ነገሩ ኢጣልያኖች በአርባ አመት ጊዜ ውስጥ በጣም ተለውጠው፣ ተሻሽለው፣ በልፅገውና ጠንክረው …” ብሎ ሊቀጥል ሲዳዳ… ጆሮው ከውጭ የሆነ ነገር ያሰማውና ወደ ውጭ ይጠራዋል፡፡ የልቡን ምት እያደመጠ ከበስተውጭ ያለውን በአልጋው ውስጥ ሆኖ እየተንጎራደደ መመርመር ጀመረ፡፡ ፀጥታውን አልወደደውም፡፡ ወደ መፅሐፉ ተመልሶ “ወኔና ጀግንነት ብቻውን እንደማያዋጣ …” ብሎ ሊቀጥል ሲል በመፅሐፉ አናት ላይ በጨረፍታ በሚታየው የእይታው ክልል … አንድ ነገር ውልብ አለበት፡፡ መፅሐፉን አስቀመጠ፡፡ በተጠንቀቅ፡፡ የፍርሐት ዛር ወረደ፡፡ አድብቶ ሲያደምጥ ምንም የለም፡፡ አልጋውን በእጁ ለመነቅነቅ ሞከረ፡፡ ምናልባት … ሹክሹክታው በአልጋው መወዛወዝ የመጣ ሊሆን ይችላል፤ ብሎ ስለተመኘ፡፡ ድምፅም መፍጠር ስለፈለገ ነው፡፡ ፀጥተው ረብሾታል፡፡

በክፍሉ ውስጥ ያሉትን እቃዎች በጥንቃቄ ቃኘ። ምን አልባት፤ ውልብ ያለው አይጥ ከሆነ … እንደገና ሲንቀሳቀስ እጅ ከፍንጅ ለማየት እንዲችል፡፡ አይጥ ከሆነ፤ ብዙ ተደብቆ መቆየት አይችልም፡፡ ሲቆረቁር ከቆይታ በኋላ ይሰማዋል፡፡ ወይ ጥግ ጥጉን እንደ አይነ ስውር … ግርግዳውን እየታከከ ሲሄድ ያየዋል፡፡ ብዙ ጠበቀ አፍጥጦ፡፡ ሁሉንም መስማት እና ማየት እንዲችል አይኑን ሁሉም ቦታ እንደ ብይ በተነው፡፡ ጆሮውን ደግሞ በኩኩሉ ጨዋታ እንደተደበቁ ህፃናት በየስርቻው አስደፈጣቸው፡፡ ምንም የለም፡፡ “ሙዚቃ ለምን አልከፍትም?” አለ ጮክ ብሎ። ከአልጋው ወርዶ ወደ ሬዲዮኑ ግን ማምራት አስፈራው፡፡ በእሱ እና በሬዲዮኑ መሀል ያለውን ፀጥታ እንዴት ይሻገረዋል? አረቄ ባለመጠጣቴ ምክንያት የተፈጠረ ፍርሐት ነው፤ ብሎ ገና ከማሰቡ … ከውጭ ሳቅ የሰማ መሰለው፡፡ ልክ ከበሩ ደፍ ስር፡፡ የሆነ ሰው የሱን ሀሳብ ሲያደምጥ ቆይቶ ድንገት በመጨረሻው ሀሳብ ሳቁ ያመለጠው ነው የሚመስለው፡፡ ጭንቅላቱን ወዘወዘ፤ ራሱን ከፍዘት ለማንቃት። ተነስቶ ወደ በሩ ሄደ፡፡ በሩን ከፈተ፡፡ ንፋስ እና ቅዝቃዜ አንድ ላይ አሸማቀቁት፡፡ ሸሚዙን እየቆለፈ በግማሽ ሰውነቱ ወደ ውጭ ብቅ አለ፡፡ ዙሪያውን ተመለከተ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች ትዝ አሉት፡፡

የታንክ አፈ ሙዝን … በጎራዴ ለመቁረጥ የሚሞክሩት … በሙከራቸው ላይ ሲሞቱ የተመለከቱት ደግሞ ከኋላ እየፎከሩ የሟቾቹን ሙከራ በሞታቸው ለመድገም የሚንደረደሩት …፡፡ ማን ይሄንን ታሪክ በሬዲዮ ሲተርክ እንደሰማ ለማስታወስ እየጣረ ወደ ደጅ ራቅ ብሎ ወጥቶ ለመንጐራደድ ራሱን አደፋፈረ፡፡ ታች ማዶ ያለው ወንዝ አይታይም፡፡ ለነገሩ ወንዝ ተባለ እንጂ በቁሻሻ ፌስታል የተሞላ የድቡልቡል ድንጋዮች ክምችት ነው፡፡ ወንዝ መፍሰሻውን ፈርቷል፡፡ ደርቋል፡፡ ከሽፏል፡፡ መጥፎ መንፈሶች ከወንዝ አካባቢ ይመጣሉ፤ ብሎ ስለሚያምን ነው ታቹ ያስፈራው፡፡ ጤናማ ምሽት ነው፡፡ ሰማዩም፤ መሬቱም፣ ዛፉም … የአፈሩ ሽታም መሬቱም … ሀገሩም ከእግሩ ስር አሉ፡፡ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ እየተመለሰ ከኋላው የሆነ ጥላ ከበደው፡፡ በፍጥነት ዞሮ አየ፡፡ በጨለማ ውስጥ ጥላ የለም፡፡ ግን ይሄንን ማወቁ የልቡን ቅዝቃዜ አልቀየረለትም፡፡ ደግሞ ጥላው በእግሩ የቆመ መስሎ ተሰማው፤ በአይኑ ባያየውም፡፡ በሩን ዘግቶ ውስጥ ገባ፣ በፍጥነት (የሆነ ነገር ሸሚዙን ይዞ ሳይጐትተው በፊት) ወደ አልጋው እየሄደ ድንገት ደርቆ ቀረ፡፡ ሽምቅቅ፡፡ አልጋው ስር ሁለት ጫማዎች አሉ፡፡ ጫማዎቹ የእሱ አይደሉም፡፡ እና ታዲያ ምን የሚያስፈራ ነገር አለው? የልቡ ምት የጆሮውን ታምቡር ሊሰነጥቀው ነው፡፡ ጫማ ሳይሆን እግር ያየ ነው የመሰለው፡፡ ትላንት ማታ፤ እሱ ከተማ ሄዶ አረቄ ሲጠጣ፣ አማኑኤል ደውሎ የቤቱን ቁልፍ እንዲሰጠው ሲጠይቀው ትዝ አለው፡፡ በስካሩ መሃል… ቁልፍ በሩ ስር መልሶ እንዳስቀመጠ ነግሮታልም፡፡

አማን፤ ሴት ጓደኛውን በወንድ ጓደኛው አልጋ አቀባበል ሊያደርግላት ፈልጐ ነው ቁልፍ የጠየቀው። እሱ በአረቄ ሰክሮ ሲመለስ አማንና ሴቲቱ የአቀባበል ስነስርዓቱን አጠናቀው፣ አልጋውን እንደነበረ ወጥረው …ወጥተዋል፡፡ አረቄ የማስረሳት ሀይል አለው፡፡ የአማን ጫማ ሊሆን ይችላል፤ ብሎ ገመተ፡፡ ግን አማኑኤል ምን ተጫምቶ ሄደ? ተጫምቶ የመጣውን በእሱ አልጋ ስር ትቶ? ምናልባት ሚስቱ አዲስ ጫማ ገዝታለት ይሆናል፤ ብሎ ተጽናና። በልቡ ምት የተደፈነው ጆሮውም ተከፈተለት፡፡ ቀልቡም ረጋ አለ፡፡ አልጋው ላይ ወጥቶ ተጋደመ፡፡ “የኔን ጫማ መቼም አድርጐ ሊሄድ አይችልም፤ እኔ አንድ ጫማ ብቻ ነው ያለኝ…” ማሰቡን ቀጥሏል። አልጋው ስር አጐንብሶ ማየት አልፈለግም። ጫማ ብቻ ሳይሆን በጫማው ውስጥ እግር ቢኖረውስ? ምን ነክቶኛል፤ አለ ለራሱ፡፡ ጭንቅላቱን ወዘወዘ፡፡ የሆነ ነገር የግርግዳውን ዙሪያ እየጫረ በቀስታ ሲያልፍ ሰማ፡፡ እየጫረ የሚሄደው ነገር ልክ የሱ በር ጋ ሲደርስ ቆመ፡፡…እየጫረ የመጣው ነገር ዝም አለ፡፡ እሱ አፉን ከፍቶ እየጠበቀው ነው፡፡ በሩን ቢያንኳኳበትስ?...እጀታውን ቢሞክርስ?...አረቄ ማን ተው አለኝ?...እያለ ያስባል፤ ተጨማሪ ድምጽ በጆሮው አስልቶ ጠበቀ፡፡ ውሻ ሊሆን ይችላል… የምሽት ድምፆች በፀጥታው ውስጥ ይጐላሉ…አይደል እ? እ?...ራሱን ጠየቀ፤ ራሱን ለማጽናናት፡፡ በጭንቅላቱ ውስጥ የተፈጠሩ ረብሻዎች እንደሆኑ እርግጠኛ ሆነ፡፡ በራሴ ጭንቅላት ውስጥ የተፈጠሩ ድምፆች መሆናቸውን ማወቁ ራሱ ጤነኝነቴን ይመሰክራል፤ ብሎ ምራቁን ዋጠ፡፡

“የፍርሐቴ ምንጭ ራሴ ነኝ፡፡ ነቅቼበታለሁ። ከተነቃ ከሽፏል፡፡ ከሽፏል!...” አለ ጮክ ብሎ፡፡ እያወራም ልቡ ግን ፍርሐት - ፍርሐት ይለዋል፡፡ ፍርሐቱ ከሱ ውጭ ላለ ሀገር፣ ወይ ነገር ሳይሆን፤ ለራሱ ነው፡፡ ፍርሐቱ ለአሁኗ ሰአት ናት፡፡ “የአሁናን ሰአት ካለፋት ፍርሐቱ እንደሚሸነፍ እርግጠኛ ነው፡፡ ዛሬን ማለፍ ከቻለ ደግሞ ነገ ያን ያህል አያስቸግረውም፤” እያለ የሚያስብ የሆነ ተራኪ ድምጽ በውስጡ አለ፡፡ ልክ እንደ ሬዲዮ ነው ድምፁ የሚተርከው፡፡ ሬዲዮው አልበራም፡፡ “ፍርሐት ከሽፏል” አለ፡፡ ብርድልብሱን ለበሰ፡፡ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የሚለውን መጽሐፍ በእጁ ዳብሶ አልጋው ላይ አጣው፡፡ አልጋው ስር ወድቋል፤ ማለት ነው፡፡ ነገ ጠዋት ያነሳዋል፡፡ ዛሬ ማታውኑ ግዴታ አንብቦ መጨረስ አይጠበቅበትም። የሆነ ሳቅ አሁንም የሰማ መሰለው። ከደጅ፡፡ ግን ብዙም አላስደነገጠውም፡፡ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በደንብ መታዘብ አለበት፡፡ መጽሐፉን አልጋ ስር ፈለገው፡፡ የአማን ጫማ ብቻ ነው ያለው፡፡ አልጋውን አራገፈ፡፡ ወደ በሩ ተመለከተ፡፡ በሩ ጐን ባለው በርጩማ ላይ ተቀምጧል፡፡ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”… የሱም የጭንቀት፣ የፍለጋ ታሪክ መጽሐፉን በማግኘት ከሸፈ፡፡ ቅድም በሩን ከፍቶ ሲወጣ በርጩማው ላይ ጣል ማድረጉ ትዝ አለው፡፡ ራዲዮኑ መጫወት ጀምሯል፡፡ በቀስታ። አሁን አልደነገጠም፡፡ ትዝ ይለዋል ሲያበራው።

ቤቱን ከውጭ የሚጭረውም ውሻ ነው…ከውጭ የሚስቀው ድምጽም የዛፎቹ ነው፡፡… “ለምን አረቄ ጠጪ ሆንኩ? የኑሮ፣ የብቸኝነት፣ የደስታ ማጣት፣ ባይተዋርነቴ ጣጣ እንዳያሳስበኝ፤ እንዳያሳብደኝ፡፡ ለምን አረቄ አቆምኩ? አረቄው በዝቶ፤ ስራ አላሰራ፣ ምግብ አላስበላ፣ ከሰው ጋር አላስማማ ስላለኝ፡፡ ለምን አረቄ መጀመር እንደገና ፈለግሁ…ፍርሐት፣ ፀጥታ፣ የራሴ አእምሮ አንድ ላይ አብረው እንዳያሳብዱኝ፡፡” እያለ ለራሱ ያሰላስላል። “ማበድ ከሆነ በሁሉም ጐኑ የተጠመደብኝ…እኔ ደግሞ አላብዳትም” ብሎ እጁን ጨብጦ ፎከረ፡፡ በዚህ መሀል ሽንቱ ወጥሮታል፤ “እንደ ትንሽ ልጅ ቤት ውስጥ በማስታጠቢያ አልሸናም? ቆሜ ነው የምሸናት፡፡ እደጅ፡፡ ከራሴ ቤት ራቅ ብዬ…ጅብ የለ፣ ውሻ የለ…ቢኖርም…እኔ ክቡር የሆንኩ የሰው ልጅ ነኝ…በቤቴ ሸንቼ አልቀርም” በሩን በኃይል ከፍቶ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ለብቻው እየፎከረ፡፡ “አያቶቼ ከጣሊያን ጋር ነው ብዙ ሆነው…መድፍን በጐራዴ የወጉት፡፡ እኔ ከማይታዩ ሀይሎች ጋር ነው የምዋጋው፡፡ ብቻዬን፡፡ እነሱ የሀገርን ድንበር ነው አላስደፍርም ያሉት፡፡

እኔ የጤነኝነት ድንበሬን ለእብደት አላስደፍርም?”… እያለ ሸንቶ ጨረሰ፡፡ …ከቤቱ ውስጥ በበራው መብራት ውጋጋን ጅብ አየ፡፡ ጅቡ ስሪያ ላይ ነው፡፡ ስሪያ ላይ ያለው ጅብ በፊት እግሩ የወጣባት እና የሚደቀድቃት ሴት ጅብ መሆን አለባት፡፡ ነበረባት፡፡ ለእሱ ግን የታየችው ሌላ እንስሳ ናት፡፡ ከጅብ ጋር በጭራሽ የማትመጣጠን እንስሳ፡፡ ነፍሳት ናት፡፡ “ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ ቁንጫና ጅብ ስሪያ ሲፈጽሙ አሳየነው ልትሉ ነው፡፡ አላምንም፡፡ አላብድም፡፡ አልፈራም፡፡…እንዴት ይሆናል ብዬ እንድቀውስ ነው?...አልቀውስም፡፡ አልከሽፍም። …ሬዲዮውን ሳላበራው ለምን በራ…አላውቅም የሰራውን ሰው ጠይቁት፡፡ ጥፋቱ ግን ከእኔ አይደለም እመ ብርሐንን! ሳልጠጣ ለምንድነው የምጮኸው? አላውቅም! እንዳላብድ ነው፡፡ ስፈራ አይደለም የማብደው? … አልፈራም … መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ በኔ አይሰራም፡፡ እኔ ታሪክ አይደለሁም፡፡ እኔ እኔ ነኝ፡፡ ታሪክ አልሆንም፡፡ በሩን ክፍት ትቶ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ አንድ ያለችው ጫማ በር ላይ እንደወለቀች ናት፡፡ ጫማ አድርጎ ለሽንት እንደወጣ እርግጠኛ ነው። አሁን ሲመለስ ጫማው በእግሩ ላይ እያለም ወልቆ ቁጭ ብሏል፡፡ … እንባው መጣበት። እያበደ እንደሆነ ግልፅ ሆነለት፡፡ ጥርሱን ነከሰ። የጨበጠውን እጁን ፈታ፡፡ “መክሸፍ” የሚለው መፅሐፍ ከበርጩማው ላይ ቅድም አንስቶት ነበር፤ አሁንም በርጩማው ላይ ተቀምጧል፡፡ አልጋው ላይም ቢፈልገው ምናልባት ያገኘው ይሆናል፡፡ እንባው ወረደ፡፡ “እንቢየው! አላብድም፡፡ እኖራለሁ፡፡ መብቴ ነው ጤነኛ መሆን” አለ በሹክሹክታ፡፡ “ኧረ ባክህ?! አብደሀል፤ ጤነኛ የመሆን መብት የለህም” አለው አንድ ሌላ ድምፅ፡፡ አሁን ግን ድምፁ … በክፍሉ ውስጥ በአካል ያለ ሰው ይመስል ለሱ ጆሮ የቀረበ ነው፡፡ ድምፁ ቀጠለ፡- “መኖር ብትቀጥልም ታብዳለሀ፣ በአረቄ ውስጥ መደበቅ ብትቀጥልም ታብዳለህ፡፡

መፍራት ብትቀጥልም ታብዳለህ፡፡ … አሁን እየጮህክ እንዳለኸው … መድፈር ብታበዛም … እሱም የእብደት አይነት ነው፡፡ ስለዚህ ከሽፈኻል፡፡ “አላበድኩም፤ አላብድም … ስለ መክሸፍ የሚያወራ መፅሐፍም ሁለተኛ አይለምደኝም … አላነብም፡፡ ሁለት እግር ነው ያለኝ፤ አንድ ህይወቴ ላይ እራመድበታለሁ” “ተመልከት አልጋህ ስር ጫማዎቹ ስንት እንደሆነ ትመለከታለህ? … አለው ድምፁ፡፡ ቅድም የአማኑኤል ነው አልክ፡፡ አሁንስ? … ስድስት ጥንድ ሆነውልሀል። የጭንቅላትህ ሀሳብስ ስንት ጥንድ እንደሆነብህ ትመለከታለህ፡፡ ከሽፈሀል፡፡ “አላብድም” የሚል የእብደት ንግግር በእርግጥ ለመናገር አንተ የመጀመሪያው ነህ፡፡ ይጨበጨብልሀል፤ ግን እውነታውን ይሄ አይለውጠውም፡፡ አብደሀል” ከራሱ ጋራ እየጮኸ ማውራቱን ገፋበት እስከ ንጋት፡፡ አልፈራም! እያለ ሲጮህ … ሌሎች ፈርተው ሸሹት፡፡ እሱ ፍርሀቱን ያሸነፈበት መንገድ ለእነሱ እብደት ተብሎ ተተረጎመ፡፡

Read 3803 times