Saturday, 06 July 2013 11:04

ታላቋ የአፍሪካ መዲና ከትንሿ ሸበዲኖ ምን ትማር?

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የበርካታ ታላላቅ አለም አቀፋዊ ድርጅቶች መናኸሪያ ነች፡፡ ከተማችን አዲስ አበባ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች መሄዷ ቢነገርላትም በፅዳትና በንፅህናዋ ረገድ ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ዋና ዋና የከተማይቱ ጎዳናዎችና ትላልቅ አደባባዮች ሳይቀሩ የቆሻሻ ማጠራቀሚያና ዋጋ የማይከፈልባቸው መፀዳጃ ቦታዎች በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እዚህም እዚያም እየተንጠባጠቡ የሚታዩትን እዳሪዎችን ላለመርገጥ እየዘለሉ መራመድ በብዙ የከተማዋ አካባቢዎች የተለመደ ተግባራት ናቸው፡፡ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደሚኖርባት በሚነገርላት በዚህችው ከተማ ውስጥ የሚገኙ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች አንድና ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በማህበር ተደራጁ ለተባሉ ቡድኖች ተሰጥተው ለተጠቃሚው አገልግሎት የሚሰጡት ገንዘብ እየተከፈለባቸው ሆኗል፡፡ ለመፀዳጃ ቤት አገልግሎቱ ገንዘብ የመክፈል አቅም የሌላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች፤የኔ ቢጤዎችና ከተማዋን በአግባቡ የማያውቁ እንግዳ መንገደኞች የተፈጥሮ ጥሪን የመመለስ ግዴታ አለባቸውና እዳሪያቸውን በመንገዱና በየአደባባዩ ለመውጣት ይገደዳሉ፡፡

ይህ ሁኔታ በከተማዋ እጅግ የተለመደና እንደ ባህል ሆኖ የኖረው ጉዳይ ነው፡፡ “ሐበሻ መንገድ ላይ ሲበላ እንጂ ሲፀዳዳ አያፍርም” እየተባለ ሲተረትበትም ኖሯል፡፡ በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት፣ ንጉሱ ህዝቡ ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት እንዲቆጠብ የሚያሳስብ አዋጅ አስነግረው የመፀዳጃ ቤትን ጠቀሜታ ለህዝባቸው ለማስተማር ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በአፄ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመነ መንግስታት ሲከናወን የቆየ ተግባር ነው፡፡ የህዝብ የመፀዳጃ ቤቶች በከተማው ዋና ዋና ስፍራዎች ላይ እንዲገነቡ ተደርገው ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ህብረተሰቡ ከመፀዳጃ ቤት ውጪ መጠቀምን እንዲፀየፍ ለማድረግ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱና የህዝቡም የአኗኗር ሁኔታ የተጨናነቀና የተፋፈገ እየሆነ ከመምጣቱ ጎን ለጎን፣ የመፀዳጃ ቤት እጥረቱ እየተስፋፋ በመሄዱ ጎዳናዎችና አደባባዮች ሁሉ አገልግሎቱን ለመስጠት ተገደዱ፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ጎዳናዎቿ፣አደባባዮቿ የገበያና የመዝናኛ ስፍራዎቿና የእምነት ተቋሞቿ ሳይቀሩ ለአይን የሚያስፀይፍ እና መጥፎ ሽታ ያላቸው እዳሪዎች መጠራቀሚያ ሆነዋል፡፡

በከተማዋ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ጥጋጥጎች፣የሆቴልና የቡና ቤት ደጃፎችና መካነ መቃብሮች የመፀዳጃ ስፍራዎች ሆነዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ የሚቃረን ተግባር ከሚከናወንባቸው የደቡብ ክልል ወረዳዎች በአንደኛው ተገኝቼ፣ ህብረተሰቡን ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ነፃ የወጣበትን ቀን ሲያከብር አብሬ ታድሜ ነበር፡፡ ስፍራው በደቡብ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ በወረዳው ውስጥ ከሚገኙ ቀበሌዎች መካከል ፋራ የተባለው ቀበሌ ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ነፃ የወጣው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ወረዳ ሆኗል፡፡ በ1999 ዓ.ም በዚህ ቀበሌ የተጀመረውን ሜዳ ላይ መፀዳዳትን የሚያስቀር ዘመቻ ብዙዎቹ የአካባቢው ቀበሌዎችና ወረዳዎች ተከትለውታል፡፡ ዘመቻውን በድል ያጠናቀቁ በርካታ በወረዳው ውስጥ የሚገኙ ቀበሌዎች፣ ራሳቸውን ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ነፃ አውጥተው የነፃነታቸው ምልክት የሆነውን ነጭ ባንዲራ በግዛታቸው እንዲውለበለብ አድርገዋል፡፡ የሸበዲኖ ወረዳ ጤና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ቡረሳ ብላሾ እንደገለፁልን፤ በአካባቢው ሜዳ ላይ መፀዳዳት እንደ ትልቅ ነውር የሚታይና በህብረተሰብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት የሚያሳጣ ተግባር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አካባቢው ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ነፃ መሆኑ እንደየደረጃው በሚሰጠው ቢጫ፣ አረንጓዴና ነጭ ባንዲራዎች ስለሚገልፅ ህብረተሰቡ ራሱ ደረጃው ከጎረቤት ቀበሌዎች ያነሰ እንዳይሆንና ውርደት እንዳያገኘው በማሰብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ዘመቻ ውስጥ ለማይሳተፍ ቀበሌ የሚሰጠውን ቀይ ባንዲራ ላለማግኘት ሁሉም በዘመቻው ውስጥ ይሳተፋል፡፡ በወረዳው ባለፈው ሰኔ 18 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው “ከመፀዳጃ ቤት ውጪ ከመፀዳዳት ነፃ የመውጣት ቀን” (open deification free day) (ODF) በዓል አከባበር ስነስርዓት ላይ የወረዳው የጤና ቢሮ ኃላፊዎችና በዘመቻው ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወገኖች የነፃነት አረንጓዴ ባንዲራቸውን ተቀብለዋል፡፡ በቀጣይነት ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ነገሮች በማስተካከልም ነጩን ባንዲራ (ሙሉ በሙሉ ነፃ የመውጣት ምልክት) የሆነውን ባንዲራ ለመቀበል እንደሚሰሩም በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል። ለዚህ ዘመቻ መሳካት “ፕላን ኢንተርናሽናል” የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑንም በዚህ ወቅት ተነግሯል፡፡ በአዲስ አበባ በ348 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ ክልል ውስጥ በምትገኘው በዚህች ወረዳ ውስጥ ተገኝቼ ይህንን እንደ አዲስ አበባ ላሉ ታላላቅ ከተሞች እንኳን አርዓያ ሊሆን የሚችል ተግባር ለመመልከት እና የበዓሉ ታዳሚ ለመሆን የቻልኩት “Because I am a girl” (ሴት በመሆኔ እንደማለት) በሚል ዘመቻ ሴቶችን በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች የማብቃት ተግባር ላይ ተሰማርቶ በሚገኘውና “ፕላን ኢንተርናሽናል” በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካኝነት ነው፡፡

ድርጅቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በተለይም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ አመቺ የትራንስፖርት አቅርቦት በሌለባቸው ቦታዎች እየሄደ የሚያከናውናቸውን የልማት ተግባራትና እነዚህ ሥራዎች ለህብረተሰቡ እየሰጡ ያለውን ጠቀሜታ መመልከቱ የጉዞዬ ዋንኛ አላማ ነበር፡፡ ድርጅቱ በሸበዲኖ ወረዳ ለኩ ከተማ ውስጥ ያስገነባው የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ ወጣቶች በትምህርት፣ በስፖርትና በጤና ራሳቸውን እያነፁ ለማሳደግ የሚረዳቸው እንዲሆን ታስቦ መገንባቱን የማዕከሉ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ዳባሶ ገልፀውልናል፡፡ ማዕከሉ ወጣቶች የኮምፒዩተር፣ የምግብና የፀጉር ሥራ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ራሳቸውን ለማስቻልም ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጣቸው እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪ ወጣቶች ይናገራሉ፡፡ ቀደም ባሉት አመታት አካባቢው በድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ተፈጥሮአዊ ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት፣ ህብረተሰቡ በምግብ እጥረት እንዳይጐዳ ለማድረግ እንዲያስችልም የእህል መጋዘን በመሥራት ለወረዳው አስተዳደር አስረክቧል፡፡ መጋዘኑ በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ማከማቻ በመሆን ወረዳውን እያገለገለ ይገኛል፡፡ የምንጭ ውሃን በሶላር ኢነርጂ በሚሰራ የውሃ መሳቢያ በመሳብ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለህብረተሰቡ ማዳረስ ከድርጅቱ ሥራዎች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሶላር ኢነርጂውን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመቀየር ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ኬላዎችና ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረጉ ተግባር በድርጅቱ ከተከናወኑ ሥራዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ለትራንስፖርት እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በድርጅቱ የገነቡት ሁለት ትምህርት ቤቶች በጋዜጠኞች ቡድኑ ከተጐበኙት ሥፍራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የሀርቤሻሾ እና የጐናዎ ጐዳ ት/ቤቶች በፕላን ኢንተርናሽናል ተገንብተው የተለያዩ የመሳሪያና የቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው የሸበዲኖ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ት/ቤቶች ናቸው፡፡ ድርጅቱ በክልሉ ወረዳዎች ላይ እየተንቀሳቀሰ የሚያከናውናቸውን የተለያዩ የልማት ተግባራት በመደገፍና እንደመንገድ ያሉ አጋዥ የልማት ተግባራትን በማከናወን ረገድ የክልሉ መንግስት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እምብዛም አጥጋቢ አለመሆኑን ታዝበናል፡፡ ስለጉዳዪ የጠየቅናቸው የሽበዲኖ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ጋቤራ፤ ድርጅቱ በአካባቢው እያከናወነ የሚገኘውን የልማት ስራ ለማገዝና ለመደገፍ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ለስራው እንቅፋት ከሚሆኑ ጉዳዩች መካከል ዋነኛው የሆነውን የመንገድ ስራ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀምሩ ገልፀውልናል፡፡ ምንም መሰረተ ልማቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ በወረዳው ገጠራማ አካባቢዎች በድርጅቱ የተገነቡት ተቋማት የአካባቢውን ነዋሪ ህዝቡ ኑሮ ለማሻሻልና በተለይም ሴት ህፃናትን ለማስተማር እንዲሁም ያለዕድሜ ከመዳር ለመታደግ እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ድርጅቱ በወረዳው ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት አድርጎ ከሚያከናውንባቸው የልማት ስራዎች መካከል በጤናው ዘርፍ የተከናወኑትን ተግባራት በስፋት የማየት አጋጣሚውን አግኝተን ነበር። በወረዳው የተለያዩ አካባቢዎች ከተገነቡት ስምንት ጤና ጣቢያዎች አብዛኛዎቹ የመድኃኒትና የመሳሪያዎች አቅርቦትም ተደርጎላቸዋል፡፡ የኤሌትሪክ ሃይል በማይደርስባቸው የወረዳው ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ለተገነቡት ለነዚህ የጤና ጣቢያዎች የክትባት አገልግሎት እንዲዳረስ ለማድረግ እንዲቻል ተቋማቱ በፀሃይ ኃይል የሚሰራ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ጋቤራ ነግረውናል፡፡ በድርጅቱ የተከናወኑት የልማት ተግባራት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደልብ በማይገኝባቸውና እራቅ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች መሆኑ ድርጅቱን የሚያስመሰግነው ተግባር እንደሆነም አስተዳዳሪው ገልፀዋል፡፡

Read 3256 times