Saturday, 06 July 2013 10:55

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

Written by  በኦሪዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(4 votes)

ተናጋሪዋ ምድር

ባለፈው ሳምንት ጉዞውንም ጽሑፉንም በይደር አቆይተነው ነበር፡፡ እነሆ ከዚያው ቀጥለናል፤ የቆምንበትን ቦታ ለማስታወስ ያህል አስደናቂ ለውጥ ወዳየሁበት ግራ ካ/ሀ ልመልሳችሁ፡፡ ግራ ካሱ መለመላውን የቆመ ሰው ይመስል ነበር፡፡ አሁን የተፈጥሮ ክብሩን ተጐናጽፏል፡፡ ሰው እና እንስሳት እንዳይደርሱበትም ሰባ የጥበቃ ሰራተኞች ተቀጥረውለታል፡፡ 
አቶ ከበደ አማረ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ኃላፊ እንደነገሩን፤ ቁጥራቸው የተጋነነ ባይሆንም በግራ ካሱ ደን ውስጥ ሰስ፣ ድኩላ፣ አነር፣ ጥንቸልና የመሳሰሉት በመራባት ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም እንስሳቱን የውሃ እጥረት ያጋጥማቸዋል፡፡ በግራ ካሱ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኘው “ጉምብርዳ” የተባለው ቦታም በደን ተሸፍኖ የተመልካችን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡ ጉምብርዳና ግራ ካሱ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው የመንግስት ጥብቅ ደኖች ናቸው፡፡
በግራ ካሱ ተራራ ላይ የተገነባውን መንገድ ሲያስተውሉት ተጣጥፎ የተኛ ዘንዶ ይመስላል፡፡ ዚግዛግ እየመቱ ከአንድ ቦታ ላይ መመላለስ የግራ ካሱን ተራራ ለመውጣት የሚያስፈልግ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ድሮ መንገዱ ጠባብ፣ ተራራውም ራቁት ስለነበረ ጉዞው አስፈሪም ዘግናኝም ነበር፡፡ አሁን ግን ተራራው በደን በመሸፈኑ፣ መንገዱም በመስፋቱ ያ ልብን እንደቄጠማ ያርድ የነበረ ጉዞ ተቀይሯል፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው መንፈስን በሐሴት ይሞላል፡፡
ግራ ካሱን በዚህ ዓይነት ሁኔታ ካለፍን በኋላ “ጨለማ ዱር” ከሚባለው ቦታ ደረስን፡፡ ግን ዱር የለም፤ ድሮ ጥቅጥቅ ያለ ደን እንደነበር ሰምተናል፡፡ አሁን የእርሻ ቦታ ነው፡፡
ብዙም ሳንርቅ የግራ ካሱን ተራራዎች ባየንበት ዓይናችን ለጥ ያለውን የኃያሎ ሜዳ ሐናይ “ተፈጥሮ ምን ዓይነት ድንቅ ናት” ማለታችን አልቀረም፡፡ ጥንታዊቷን የኃያሎ ማርያም ቤተክርስቲያን በቅርብ ርቀት እያየን ወደፊት ስንገሰግስ፣ የጥንታዊቷ ኮረም ከንቲባ አቶ ኃይሌ ምስጉን፤ ከከተማው ህዝብና ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ልክ አላማጣ ላይ በተደረገልን መንገድ በደማቅ ስነሥርዓት ተቀበሉን፡፡ ኮረም ድረስ የሸኙን የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ገብረ ትንሣኤ ፍስሃና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸውም ለኮረም ከተማ ባለሥልጣናትና ህዝብ አስረክበውን ወደ አላማጣ ተመለሱ፡፡
የኮረም ከተማ ህዝብና ባለሥልጣናት ከከተማዋ ወጥተው በሆታና በባህላዊ ጭፈራዎች ሲቀበሉን የጥበብ ተጓዦች አድናቆታቸውን የሚገልጹበት መንገድ የጠፋባቸው መስለው ነበር፡፡
ሆኖም አንዳንዶች ከህዝቡ ጋር እየጨፈሩ፣ ሌሎች በካሜራና በማስታወሻ ደብተራቸው ላይ ያዩትን ለመክተብ ሲጣደፉ ተመልክቻለሁ፡፡ የደቡባዊ ዞን ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ታረቀኝ እንዳስረዱን፤ ሮማን እንደ ገብስ ያመሳት ጀግናቸው ዘርዓይ ደረስ ኮረም ላይ በመምህርነት አገልግሏል፡፡ ኮረም የብዙ ዘግናኝ ድራማዎች መከወኛ መድረክም ነበረች፡፡ በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ከ100ሺህ በላይ ህዝብ በዳቦ ዕጦት እንደቅጠል ረግፎባታል፡፡ ክቡሩ የሰው ልጅ ከእንስሳት ባነሰ መንገድ ተጐሳቁሎባታል፤ የራበው ጅብ በሰው ልጆች አጥንት ተዘናንቶባታል፤ በአጠቃላይ መከራዎች ሁሉ ተጠራርተው የቅጣት ዳፋቸውን አውርደውባታል፡፡
ረሃቡንና ያስከተለውን ዘግናኝ እልቂት በፊልም የተመለከተው ዝነኛው አቀንቃኝ ቦብ ጊልዶፍ “ዊ አር ዘ ወርልድ” በሚል መሪ ቃል ታዋቂ አለምዓቀፍ የኪነት ሰዎችን ማስተባበር የጀመረውም ያኔ ነው፡፡ ባደረገው ሰብአዊ እንቅስቃሴም “ባንድ ኤይድ” የተባለ ዘመናዊ ሆስፒታል ለከተማዋ ህዝብ መገንባት አስችሏል፡፡
ኮረም ከረሃቡ ሌላ በህወሓትና በወቅቱ መንግሥት መካከል ከፍተኛ ጦርነት የተካሄደባት፤ በጦርነቱም ከግራ ቀኙ ወገኖች በርካታ ህዝብ የወደቀባት ቦታ መሆኗን አስጐብኚያችን ነግረውናል፡
ወደ መጥፎ ትዝታዎቿ ተሳብሁና አሁን ያለችበትን ሁኔታ ረሳሁ፡፡ ኮረም አሁን ሰላም ናት፡፡ እንደ ሌሎቹ የሃገራችን ከተሞች በእድገት ግስጋሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ያ ሁሉ ህዝብ የዕለት ዳቦ አርሮበት፣ በዓይኑ ላይ እህል እየተንከራተተበት፣ እንደ ቅጠል የረገፈባት ቦታ ዛሬ ተፈጥሮ ፊቱን አዙሮላት ፍጹም ለምለም ናት፡፡ ለነገሩ ያኔም ቢሆን ያለቀው ዕርዳታ ፍለጋ ከየወረዳውና ከየአካባቢው የመጣው ምስኪን ህዝብ ጭምር እንጂ የኮረም ከተማ ህዝብ ብቻ አልነበረም፡፡ ያም ሆነ ይህ የጥበብ ተጓዡ የኮረምን ዘግናኝ ታሪኮች ከባለስልጣናቱ ካደመጠ በኋላ በከንቲባው በአቶ ኃይሌ ምስጉን አማካይነት የምሳ ግብዣ ተደረገለት፡፡ ዝነኛው የኮረም ኮረፌም የምሳው አንድ አካል ነበር፡፡
ጉዞው ቀጥሏል፤ የኮረምን ህዝብና ባለሥልጣናት አቀባበል እያደነቅን፣ ጉዟችንን ቀጥለን ሳለ በክልሉ ብቸኛ የሆነው የአሸንጌ ሃይቅ ድንገት ከፊትለፊታችን ድቅን አለ፡፡ አካባቢው የኦፍላ ወረዳ ነው፡፡
በዚያ አካባቢ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አህመድ በሚመራው እና በክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ንጉሥ ልብነ ድንገል መሃል መራራ ጦርነት ተካሂዷል፡፡
አፄ ልብነ ድንግልን ሊረዳ ከፖርቱጋል መጥቶ የነበረው የባስኮ ደጋማ ወንድም ዝነኛው ክርስቶፎር ደጋማ የተገደለው እዚያ አካባቢ ነው፡፡
በ1928 ዓ.ም የጣሊያን ፋሽስቶች ሀገራችንን ሲወርሩ አሸንጌ አካባቢ በርካታ ህዝብ አልቋል፡፡ ቸኮዝሎባኪያዊው ወዶ ዘማች አዶልፍ ፓርለስክ እንደሚለው፤ የኢትዮጵያ የጦር ሚኒስትር የነበሩት ራስ ሙሉጌታ ይገዙ ከእነ ልጃቸው የተገደሉት አሸንጌን ሲያቋርጡ ነው፡፡ ኪውባዊው ኮሎኔል ዴል ባዬ ግን “ሚኒስትሩ የሞቱት መቀሌ አካባቢ በተካሄደ ጦርነት ነው” ብሎ ጽፏል፡፡
በአካባቢው ንጉሥ ኃይለሥላሴ ከጣሊያን አውሮፕላኖች ድብደባ ተደብቀውበት የነበረ “የንጉሥ ዋሻ” የሚባል ቦታ መኖሩንም አስጐብኚያችን አስረድተውናል፡፡ “ወርጭጋ” ከሚባል በአካባቢው ከሚገኝ ሌላ ዋሻም ተደብቀው ከጣሊያን መቅሰፍት ድነዋል፡፡ እንዲህ እያሰብን፣ እንዲህ እየቃኘን ታሪካዊቷ ማይጨው ከተማ ስንደርስ ከንቲባውና የከተማው ህዝብ ልክ እንደ አላማጣና ኮረም ተሰልፈው በሆታና በዕልልታ ተቀበሉን፡፡ በነገራችን ላይ በየደረስንበት ከተማ ሁሉ ባህላዊ ዳቦ የግድ የተባለ እስኪመስል ድረስ በገፍ ይቀርብልን ነበር፡፡ ማይጨውም ቄጠማ ጐዝጉዛ፣ ደግሳና ተዘጋጅታ በክብር ተቀበለችን፡፡
የማይጨው ስም ሲነሳ የ1928ቱ አሳፋሪ ውድቀት መነሳቱ የግድ ነው፡፡ በረጅሙ ታሪካችን ድል የሆንባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጐላ ብለው የሚጠቀሱት የማህዲስቶች ድል (መተማ ላይ) እና የጣሊያኖች ድል (ማይጨው ላይ) ናቸው፡፡
ለመሆኑ ለምን ተሸነፍን? አምባራዶም ላይ የጣሊያንን መንጋ አፈር ያስጋጠ ጀግና ሠራዊት እንዴት ማይጨው ሲደርስ ተሸነፈ? ንጉሠ ነገሥቱ በውጊያው ወቅት ምን ሚና ነበራቸው? ከውጊያው በፊትስ የኢትዮጵያ ህዝብ ከእርሳቸው ጋር የሚሰለፍበትን ሁኔታ አመቻችተው ነበር? በአጠቃላይ የአድዋ ድል ለምን ማይጨው ላይ አልተደገመም? እጅግ በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ግን ያኔም ሆነ አሁን መልስ ያላገኙና የማገያኙ ጉዳዮች በርካታ ናቸውና የጥያቄ ሰልፈኛ መደርደሩ ብዙም ርባና ያለው አይመስልም፡፡
የጥበብ ተጓዦች ታሪካዊቷ ማይጨው ከተማ ላይ ስለሚገኙ ነው ይህን ያህል የጥያቄ ጋጋታ ያስነሳው፡፡ ማይጨው ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን በከተማው ደቡባዊ ጫፍ ላይ በተሰራ አነስተኛ ሙዚዬም ውስጥ የተቆለለ የምስኪን ኢትዮጵያውያን ጭንቅላትና አጽም ነው ብዙ እንድንናገር ሰበብ የሆነን፡፡ የእኒያ ጀግኖች አጽም፣ የእኒያ ወኔ ሙሉ አርበኞች የራስ ቅል በመደርደሪያ ሆኖ ዘግናኝ ትዝታውን ይመሰክራል፡፡
ያ ሁሉ አጥንት የተለቀመውና ቢያንስ ለዚያ ደረጃ የበቃው የአምስት ዓመቱ ወረራ ካበቃ በኋላ፣ አገር ሰላም ከሆነች በኋላ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ከተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች ስንቁንና መሳሪያውን ተሸክሞ ለስድስትና ሰባት ወራት በእግሩ ኳትኖ አገርን ከነጭ አራዊት ሊታደጋት በሙሉ ወኔ ገስግሶ በአካባቢው የደረሰው ያ ሁሉ ኩሩ አርበኛ፣ ለሀገሩና ወገኑ ሲል በሀገሩ አፈር ላይ እንደ ገብስ ታጭዶና ተወቅቶ ማይጨው ላይ ቀርቷል፡፡
አካሉ ከዚያች ለትንግርት የተፈጠረች ከምትመስል አካባቢ ወድቆ ቢቀርም ታሪኩ ግን ዓለም እና ትውልድ እስከቀጠሉ ድረስ በክብር ሲዘከር ይኖራልና እኛም ከአንገታችን ሳይሆን ከልባችን ሸብረክ ብለን በክብር አሰብነው፡፡
ጉዞው ቀጥሏል፤ ሁለመናዋ የታሪክና የዕውቀት ምድር የሆነችው ትግራይም ምስጢሯን ማውጋትዋን ቀጥላለች፡፡ ወደ አላጄ እየተጠጋን ነው፡፡ አምባ አላጄም ሌላ ታሪክ አላት፡፡ ደጃዝማች ገበየሁ በ1888 ዓ.ም የጣሊያንን መንጋ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ የወደቀው እዚሁ ቦታ ነው፡፡ የአድዋ ድል ዋዜማ የተበሰረውና ጣሊያኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ድባቅ የተመቱትም እዚሁ አምባአላጄ ነው፡፡
በትግራይ ክልል ተራራ ሞልቷል፤ ግን ዝም ብሎ የቆመ አይደለም፤ የሚመሰክረው፣ የሚናገረው እጅግ ብዙ ምስጢር አለው፡፡ አላጄም እንደዚያ ነው፡፡
የአላጄ ከተማ ነዋሪዎችና ባለስልጣናትም ደግሰው በሆታ፣ በጭፈራ ነው የጥበብ ተጓዦችን የተቀበሉን፡፡ አላጄን ከሌሎች ልዩ የሚያደርገው ሁኔታም ተከስቷል፡፡ አላማጣ፣ ኮረምም ሆነ ማይጨው ስንደርስ ጠንከር ያለ ፀሐይ ነበር፡፡ ህዝቡም ያን ጠንካራ ሙቀት ተቋቁሞ ነው የተቀበለን፡፡ አላጄ ግን ከባድ ዝናብ ነበር፡፡ በዚያ ከባድ ዝናብም ቢሆን ህዝቡ ፍቅሩን አልነፈገንም፡፡ በሆታና በእልልታ ተቀብሎ ደግሶ አስተናግዶናል፡፡
መቀሌ ገብተን ማደር ስላለብን መፍጠን ያስፈልጋል፡፡ ግን ትግራይ ገብቶ መፍጠን ተገቢ አይሆንም፤ የሚታየው ማራኪ መልክዓምድር፣ የሚደመጠው ታሪክ፣ የህዝቡ መስተንግዶ በቀላሉ መንቀሳቀስ አያስችሉም፡፡ አምባ አላጀንና ጦርነቱ የተካሄደባቸውን አካባቢዎች በተደሞ ስንጐበኝ ቆይተን፣ ወደፊት ስንገሰግስ የሜርሲ ውሃ ፋብሪካ “የጥበብ ጉዞና ውሃ አይነጣጠሉም” ብሎ እጅግ በርካታ እሽግ ውሃ አውቶቡሳችን መያዝ እስኪያቅተው ድረስ ለገሰን፡፡ እውነትም ጉዞ ከንፁህ ውሃ ጋር ይሰምራልና የጥበብ ተጓዦች ሜርሲ ውሃን እየተጐነጩ፣ የፋብሪካውን የሥራ ሃላፊዎችና ሠራተኞች በማመስገን ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ በነገራችን ላይ በየደረስንበት ቦታ የሚደረገው አቀባበልና ግብዣ በቀጣዩ ከተማ ህዝብ ላይ መጉላላትን ከማስከተሉም በላይ በጊዜ ወደታሰበው ቦታ የመድረስ ችግርም በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ አሁን ደግሞ የመቀሌ ከተማ ከንቲባ፣ የክልሉ የካቢኔ አባላትና ህዝቡ ኲሃ ላይ ተሰልፈው እየጠበቁን ናቸውና መፍጠን ያስፈልጋል፡፡ ግን ጊዜው እንዴት ባከነና መሰላችሁ እየመሸ ነው፡፡
ስለዚህ ከአላማጣ ተቀብለውን አብረውን የሚጓዙት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ከበደ አማረና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሃየ አለማየሁ የሚጠብቀን ህዝብ መጉላላት የለበትምና በስልክ እንዲነግሩ ማድረግ ግድ ሆነ፡፡
ሆኖም ከምሽቱ 1፡30 አካባቢ ኲሃ ስንደርስ ህዝቡም ባለሥልጣናቱም ቆመው ሲጠብቁን አገኘናቸው፡፡ በእውነቱ ያን ያህል ጊዜ ማስጠበቅ ከባድ ነበር፡፡ እርግጥ ነው የትግራይ ህዝብ እንግዶቹን በፍቅርና በክብር እንደሚቀበል ባለፍንባቸው ከተሞች ሁሉ ያየነው ስለሆነ የመቀሌው ልዩ ላይሆን ይችላል፡፡
ለማንኛውም መቀሌ በሰላም ገባን፡፡ መቀሌ ታምራለች፤ በተለይ ማታ ላይ እንዳ ኢየሱስ ላይ ሆኖ ቁልቁል ሲመለከቷት ከዋክብት ህዋቸውን ትተው የረገፉባት መስክ ትመስላለች፡፡ ልዩ ልዩ ቀለማት ያሏቸው የመንገድና የቤት መብራቶች ልዩ ውበት፣ ልዩ ድምቀት ለግሰዋታል፡፡ መቀሌ መንገዶችዋ ጽዱ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ላይ አናት የሚበጠብጠው አስቀያሚ ሽታ መቀሌ የለም፡፡
ከዚህ ሌላ የጫት ገረባ በየፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦው አይታይም፡፡ በጥርብ ድንጋይ የተሰሩት መንገዶች ያምራሉ፡፡ የሁለተኛው ቀን ውሏችን የተጠናቀቀው በርዕሰ መስተዳድሩ የራት ግብዣ ነው፡፡ ሚላኖ ሆቴልም ከፍተኛ ቅናሽ በማድረግ እንግዶቹን አስተናግዷል፡፡ ለነገሩ የትግራይን ምድር በሰላም የረገጠ ሁሉ እንግድነቱ ለህዝቡም ለመንግሥትም ነውና አይደንቅም፡፡ ጉዞውም ጽሑፉም አልተጠናቀቀም፡፡

 

Read 3575 times