Saturday, 06 July 2013 10:53

“ከዚህ አይነት ህይወትስ እስከ ወዲያኛው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!
ይኸው ለ‘በጀት መዝጊያ’ ደረስን አይደል! ስሙኝማ…ይሄ የፈረንካው በጀት እንደሚዘጋ ሌሎች ዓመቱን ሁሉ አብረውን ያሉ ነገሮች አብረው ቢዘጉ እንዴት አሪፍ ይሆን ነበር! የመናናቅ፣ የመጣጣል፣ ከ“እኔ በላይ” የማለት፣ የጉልበተኝነት…ምናምን ነገሮች ጥርቅም ተደርገው የሚዘጉበት ዓመት ናፍቆናል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ የጉልበተኝነት ነገር በብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥ ነገር ሆነ እንዴ! ግራ ገባና! እኔ የምለው… ይሄ ደንብ ማስከበር ምናምን የሚሉትን ነገር ካነሳን አይቀር...በዛ ሰሞን በከተማው አንድ ክፍል ያየሁትን ስሙኝማ… እድሜያቸው ገፋ ያሉ ሁለት ‘ደንብ ማስከበሮች’ የሆነ ካልሲና ውስጥ ሱሪ አንጥፎ ይሸጥ የነበረን ልጅ ከነበረበት ያባርሩታል፡፡ እናማ… አንደኛው ምን ይል መሰላችሁ… “በዱላ ወገቡን መስበር ነበር…” ይሄኔ በዕድሜ በለጥ ያለ የሚመስለው ሰውዬ ምን ቢል ጥሩ ነው…“የምን ዱላ፣ በጫማ ጥፊ ማለት ነበር፡፡”እናላችሁ…የውቤ በረሀ ትዝታ ካልለቀቀውና “ቀን ባይጥለኝ ኖሮ…” የሚል አንጋፋ አይግጠማችሁ፡፡
ስሙኝማ…ስኖውደን የተባለው ሰውዬ ‘ታላቋን አገር’ ናጣት አይደል! (በነገራችን ላይ ስኖውደን የአማሪካንን ጉድ ከዘከዘከ በኋላ የጆርጅ ኦርዌል ‘1984’ መፅሐፍ ሽያጭ በአማዞን በ6000% አድጓል ተብሏል፡፡)
እናላችሁ…በዚህ ‘የሰለጠነ ዘመን’ ወዳጅ የሚባል ነገር እንደሌለ አያችሁልኝ አይደል! እናማ… ‘ወዳጃችን፣’ ‘የምናምን አጋራችን’ ብሎ ነገር የለም። አሀ… “በ‘አማሪካን’ ሳንባ ሊተነፍሱ ምንም አይቀራቸው…” የሚባሉት አገሮች… “አሜሪካንን ያመነ ጉም የዘገነ…” ብለው አረፉት አይደል!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የአገሮቹ ይሁን እዚህ እኛ ዘንድ ጠቅላላ እርስ በእርሳችን ስንሰላለል አይደል እንዴ የምንውለውና የምናመሸው!
ለምሳሌ…እሱ የሆነ እድገት ለማግኘት እናንተን በስጦታ ወረቀት ሳይጠቀልል በደረቁ ‘መታያ’ ሊያደርጋችሁ የሚፈልግ አይነት ሰው ገጥሟችሁ አያውቅም! እናማ…ደህና ከማንም ጋር የማያናክሰውን፣ ከማንም ጋር “የቡድንና የቡድን አባቶች…” የማያስብለውን የጆሴ ሞሪንሆን ወሬ እያወራችሁ በመሀል…“ስማ…” ይላችኋል፡፡ “እነዚህ ሰዎች አሁንስ አላበዙትም እንዴ!…” ምናምን ይላል። (“እነዚህ ሰዎች…” ስንባባል ትርጉሙ ‘የማያሻማ’ ወደ መሆኑ እንደተቃረበ ይታወቅልንማ!)
ታዲያላችሁ…እናንተ ደግሞ “ሂድና ምስር ወጥ፣ ካቲካላና ‘እንትን ሰፈርን’ የለመደ የቻይና ባቡር ሀዲድ ሠራተኛ ብላ…” ትሉና ጭጭ፡፡ ይቀጥልና ምን ይላል መሰላችሁ… “እንደው የያዘ ይዞኝ ነው እንጂ እነሱን የማላይበት ቦታ፣ ለምን ቱራ ቦራ አይሆንም እሄድ ነበር…” እናንተ ደግሞ…ጭጭ! እናላችሁ…እንዲህ አይነት…አለ አይደል… ኳሷን ሆነ ብሎ ወደ እናንተ ክንድ ወርውሮ “ዳኛ… ማኖ ሲነካ ዝም ትላለህ እንዴ! ቀይ ስጠው እንጂ!” የምንል አይነት ሞልተንላችኋል፡፡
ስሙኝማ…እንደው እዚች ከተማችን እንኳን ያለ የእንትናና የእንትናዬ የመሰላለል ታሪክ አይደለም የስኖውደን የሲ.አይ.ኤ. ኮምፒዩተሮች አይችሉትም። “የፍላጎት እንጂ የአቅርቦት ችግር የለም…” በተባለበትና የሶዶምና ገሞራን ታሪክ ቀሺም የፊልም ጽሁፍ በሚያስመስል ዘመን…የእሷና እሱ መሰላለል በሽ ነው፡፡
ልክ ነዋ…“ትናንት አሥር ሰዓት ላይ አብረሽው ፒያሳ ስትሄጂ የነበርሽው ሰውዬ ማነው?” “ቅድም ሃያ ሁለት አብረሀት ሻይ ስትጠጣ የነበረችው ማናት?” አይነት ጥያቄዎች እኮ ያው የስለላ ውጤቶች ናቸው። “የት፣ የት እንደምትውል የማላውቅ መሰለህ…” “ተሰብስባችሁ ምን እንደምታወሩ የማልሰማ መሰለሽ!” ምናምን በሙሉ ከስለላ የሚገኙ መረጃዎች ናቸው፡፡
ስሙኝማ…“ትናንትና ቺቺንያ ቢራውን ላይ በላይ ትጨልጥ ነበር አሉ…” የሚል ነገርም የስለላ ውጤት ነው፡፡ አሀ…የምትጠጡትን ቢራ ቁጥር የሚያሰላ…አለ አይደል… ለስለላ ካልሆነ ለምንድነው?
ደግሞላችሁ…የሆነች የምታውቋት እንትናዬ አለች፡፡ እና የሆነ እንትና ልቡ ይፈቅዳታል፡፡ እናላችሁ… ግንኙነታችሁ ምን እንደሆነ እርግጠኛ ስላልሆነ… ‘ይሰልላል’፡፡
“ከእንትና ጋር ትቀራረባላችሁ?” ይላል፡፡ እናንተም… “አዎ፣ በጣም…” ትላላችሁ፡ እሱዬውም “ስሰማ እኮ በጣም ቅርብ ናችሁ አሉ…” ይላል፡፡ ‘በጣም’ ላይ ጫን ይላል፡፡ እናንተም “አዎ፣ በጣም…” ትላላችሁ፡፡ ከዛ ወዴት ይመጣል መሰላችሁ… “እንዴት ነው… ማለቴ እንትን ነገር…” ምናምን ብሎ ባላለቀ ቀለበት መንገድ ላይ አቅጣጫ ይጠፋዋል። ይሄኔ… “አቦ፣ ስለላውን ተውና ሄደህ ለራሷ ማመልከቻህን አስገባ…” ማለት ነው፡፡ እናላችሁ…በየቀኑ ስንሰላለል ነው የምንውለው፡፡
ደግሞላችሁ ...ሳይታወቃችሁ ለስለላ የምትመለመሉበት ጊዜ አለ፡፡ “ስማ… መሥሪያ ቤታችሁ ለአካውንታት ሠራተኛ ማስታወቂያ ሊያወጣ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ…” ይላል፡፡ ከዛ አከታትሎ… ምን ይላል መሰላችሁ…“እስቲ ለቦታው ያጩት ሌላ ሰው ካለ ሰልልኝ!” እናላችሁ መልማዮች ሲ.አይ.ኤና ኬ.ጂ.ቢ. ብቻ አይደሉም፡፡
“አንቺ… ያቺ ጓደኛሽን ሥራ አስኪያጁ ሙድ ያዘባት አሉ፡፡ እስቲ በእናትሽ ሳይታወቅብሽ ሰልያት…” የሚል አይነት ምልመላ አለ፡፡
በነገራችን ላይ… “ሙድ መያዝ” የሚሉት በንግግር ውስጥ የካርታውን ‘ጆከር’ ቦታ ይዞላችኋል፡፡ “ሙድ ይዛብሀለች…” ማለት ወይ “ተመችተሀታል” ወይም “ለዓይኗም አስጠልተሀታል” ማለት ሊሆን ይችላል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ከዚህ በፊት ያወራትን እንድገማትማ…ሰውየው የሆነ አልቤርጎ ተከራይቶ ለሽ ብሏል፡፡ እናማ… ድንገትም ጎኑ ካለውና የሆኑ ‘እሷና እሱ’ ከተከራዩበት ክፍል ድምጾች መስማት ይጀምራል፡፡ “እነሆ በረከት ተጀመረ ማለት ነው…” ይልና ጆሮውን አቁሞ ያዳምጣል፡፡ ሰውየው “አንቺ ከላይ ሁኚ…” ይልና አተነፋፈሶች ላይ የኦክሲጅን እጥረት ይከሰታል። ቀጥሎ ደግሞ ሴትዮዋ “አንተ ከላይ ሁን…” ትልና አሁንም አተነፋፈስ ላይ የኦክሲጅን እጥረቱ ይባባሳል፡፡ ታዲያላችሁ…ትንሽ ቆይቶ ሰውየው ምን ሲል ሰማ መሰላችሁ… “ሁለታችንም ከላይ እንሁን…” “ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል…” ማለት ይሄኔ ነው! እናላችሁ… ክፍሉ ከወደጣሪያው ክፍተት ስለነበረው “ይህንን የዘመናችንን ፈጠራማ ማየት አለብኝ…” ብሎ ወንበር ላይ ይቆምና ተንጠራርቶ ያያል፡፡ እናላችሁ… ምን ቢያይ ጥሩ ነው…ለካ ሁለቱ ሰዎች ሻንጣ አልዘጋ ብሏቸው ለመቆለፍ መከራቸውን እያዩ ነበር፡፡
እናማ…“ሁለታችንም ከላይ እንሁን…” ስንል ብትሰሙን ለ‘ሌላ ጉዳይ’ ብቻ ሳይሆን… ሻንጣ አልዘጋ ብሎን ሊሆን እንደሚችል ይታወቅልንማ! ቂ…ቂ…ቂ…
የስለላ ነገር ካነሳን አይቀር…ስታሊን ሠራተኞቹ እንዴት እንደሚኖሩ ለማየትና ስለ እሱ ምን እንደሚሉ ለማወቅ ራሱን ለውጦ ከክሬምሊን ሹልክ ብሎ ይወጣል፡፡ ትንሽ ዘወር፣ ዘወር ብሎ ይቆይና ሲኒማ ቤት ይገባል፡፡ እናላችሁ…ፊልሙ ሲያልቅ ስክሪኑ ላይ የስታሊን ፎቶ በትልቁ ይታያል፡፡ ይሄኔ ሁሉም ሰው ተነስቶ ይቆምና መዝሙር መዘመር ይጀምራል፡፡ ያልተነሳው ራሱ ስታሊን ብቻ ነበር፡፡ እናማ…ጎኑ የነበረው ሰውዬ ጎንበስ ብሎ ምን አንሾካሾከለት መሰላችሁ…“ስማ ጓድ፣ እንዳንተ እኛም ይሄንን ሰይጣን ሰውዬ አንወደውም፡፡ ግን ሰላዮቹ እንዳይበሉህ፤ ተነስተህ ብትዘምር ይሻለሀል፡፡” አሪፍ አይደል!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ‘ኮሚ’ ዘመን ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ… ኢቫኖቭ የተባለ ሩስያዊ ሰው የኮሚኒስት ፓርቲው አባል ለመሆን አመልክቶ የፓርቲው ኮሚቴ ቃለ መጠይቅ እያደረገለት ነው።
“ጓድ ኢቫኖቭ፣ ታጫሳለህ?”
“አዎ፣ ባይበዛም አጨሳለሁ፡፡”
“ጓድ ሌኒን እንደማያጨስና ኮሚኒስቶች እንዳያጨሱ እንደሚመክር አታውቅም?”
“ጓድ ሌኒን እንዲሀ ካለማ ማጨስ አቆማለሁ።”
“ትጠጣለህ?”
“አዎ፣ አልፎ፣ አልፎ፡፡”
“ጓድ ሌኒን መጠጥን እንደሚያወግዝ አታውቅም?”
“እንግዲያው ሁለተኛ አልጠጣም፡፡”
“ጓደ ኢቫኖቭ፣ ሴቶች ታበዛለህ?”
“ይሄን ያህል ባይሆንም…”
“ጓደ ሌኒን እንዲህ አይነት ከሞራል ውጪ የሆኑ ጉዳዮችን እንደሚያወግዝ አታውቅም?”
“ጓድ ሌኒን እንዲህ ካለ ከእንግዲህ ሴት አጠገብ አልደርስም፡፡”
“ጓድ ኢቫኖቭ፣ ህይወትህን ለፓርቲው ለመሰዋት ፈቃደኛ ነህ?”
“በደንብ አድርጌ፣ ከዚህ አይነት ህይወትስ እስከወዲያኛው ፍግም ብል ይሻለኛል፡፡”
የምር ግን…“ምን በላ…” “ምን ጠጣ…” “የት ገባ…” “የት ወጣ…” “ከማን ዋለ…” “ከማን አመሸ…” አይነት ጆፌ መጣል አሪፍ አይደለም፡፡ ከሀያ አራት ሰዓት ሀያ ሦስት ሰዓት ከሀምሳ አምስት ደቂቃውን…የራሳችንን ህይወት የምናይበትን ዘመን ያምጣልንማ! በደጉም፣ በክፉም “ያገባኛል ባይ…” የበዛበት ህይወት “ከዚህ አይነት ህይወትስ እስከወዲያኛው…” ማለት ያመጣል፡፡
እናላችሁ…እኛ ዘንድ እርስ፣ በእርስ መሰላለል በሽ ነው…ላይ ‘ዋናዎቹ’ ቦሶች፣ የቅርብ አለቆች፣ እንትናና እንትናዬዎች፣ ጎረቤቶች፣ የልብ ጓደኞች፣ የሥራ ጓደኞች…ልጄ፣ ዘመኑ አንዳችን አንዳችንን የመሰላለል ዘመን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4359 times