Saturday, 06 July 2013 10:45

ተቃዋሚዎች በሂደቱ ላይ እንጂ በግድቡ ላይ ተቃውሞ የለንም አሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ አባይን የመገደብ ጥያቄ በኢህአዴግ ዘመን ብቻ ሳይሆን ከጥንትም የነበረ ስለሆነ መገደቡን እንደማይቃወሙ ገልፀው፣ የአገዳደቡ ሂደት ግን ችግር አለው ብለዋል፡፡ የግድቡን መገንባት ካልተቃወማችሁ ድጋፍ ለማድረግስ ፓርቲው ምን አስቧል በሚል ለሊቀመንበሩ ላነሳነውም ጥያቄ “እኛ እንደፓርቲ የምንናገረው አባይን የመገደብ መብት ተፈጥሯዊ እና አገራዊ መብት ነው፤ በዚህ ላይ ክርክር አናነሳም፣ ተቃውመንም አናውቅም” ካሉ በኋላ፣ ነገር ግን ኢህአዴግ “የአባይ ጉዳይ የኔ ብቻ ነው” በሚል ለፓለቲካ ፍጆታ ማዋሉን፣ ያለ ብሔራዊ መግባባትና ግልጽነት በጐደለው መንገድ ብቻውን በባለቤትነት መያዙን ግን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ የግድቡን ስራ በብቸኝነት ለመያዙ እንደ ማሳያ የጠቀሱት የወንዙን አቅጣጫ ያስቀረበት ቀን ከግንቦት 20 በዓል ጋር መገናኘቱን ሲሆን “ይህ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የታለመ እቅድ ነው” ብለዋል ዶ/ር ነጋሶ፡፡
የሆኖ ሆኖ አሁን ግድቡ እየተሰራ መሆኑንና ፓርቲያቸው የግድቡን ግንባታ ለማገዝና ለመደገፍ እቅድ እንዳለው ተጠይቀውም “እኛ አሁንም የግድቡን ስራ አንቃወምም፣ ነገር ግን የግድቡ ስራ ቀጣይነት እንዲኖረውና ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ህዝቡን በቀጥታ ተሳታፊ በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ላይ መደረስ አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ አስፈላጊ በሆነው ነገር ፓርቲያችን ድጋፍ ከመስጠት ወደ ኋላ አይልም” በማለት መልሰዋል፡፡ “አሁን ግን በውድም በግድም ገንዘብ አምጡ ከማለት በስተቀር ህዝቡ በግድቡ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነው ብዬ አላምንም” ብለዋል ዶ/ር ነጋሶ፡፡
“የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲበሰር እንቅስቃሴ የጀመርነው በድጋፍ ነው” ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ፤ ነገር ግን እንደዜጋም እንደፓርቲም የራሳቸው የሆኑ ስጋቶችና ጥርጣሬዎች እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ሙሼ ጥርጣሬና ሥጋቶች ካሏቸው ነጥቦች ውስጥም የ80 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ለማስተናገድ ምን ያህል ተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም አለን፣ የውሃ ሃይል አቅርቦቱ፣ ቴክኖሎጂውና ማይክሮ ኢኮኖሚው ይደግፈዋል ወይ የሚሉት እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ የግድቡን ጉዳይ የብሔራዊ ኮሚቴ አባል ሆነው በቅርበት እየከታተሉት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙሼ ፤ አሁን ግድቡ አመርቂ በሆነ ሁኔታ እየተገነባ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ትልልቅ ከተሞች እንጂ አብዛኛዎቹ የገጠር ከተሞችና የገጠር መንደሮች የመብራት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የገለፁት አቶ ሙሼ፤ እዚህች አገር ላይ ሰፋ ያለ የኢንቨስትመንት ስራ ለመስራት የሀይል አቅርቦት ትልቁ ግብአት በመሆኑ የህዳሴው ግድብ ግንባታ መከናወኛ ጊዜው እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
“ለምሳሌ የብረታ ብረት ማቅለጫ ኢንዱስትሪ ልገንባ ቢባል ያለው የሃይል አቅርቦት የትም አያደርስም፤ እነዚህ የተደራረቡ ችግሮች ስላሉ የሃይል አቅርቦቱን ከፍ ማድረግ እንደሚገባ በማኒፌስቶአችን ላይ ገልፀናል” ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት፤ “እኛ እንደውም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የሀይል አቅርቦቱ እስከ 10ሺህ ሜጋ ዋት ከፍ ማለት አለበት ብለን ነበር” ይላሉ፡፡ አሁንም ግን የሚሠራው ግድብ ከሌሎቹ ጋር ተደምሮ የሃይል አቅርቦቱን ወደ 10ሺህ ሜጋ ዋት ማድረስ ይችላል ብለዋል - አቶ ሙሼ፡፡
ግድቡ በተያዘለት ጊዜ ይጠናቀቅ እንደሆነ ተጠይቀውም ሲመልሱ፤ጥያቄው በጣም አስቸጋሪና ቴክኒካል እንደሆነ ገልፀው፤ በሁለት ዓመቱ ግድቡ 21 በመቶ መሠራቱንና በቀሪዎቹ ሶስት ዓመታት ይጠናቀቃል ወይ የሚለውን መመለስ አዳጋች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“ባለሙያዎቹ እንደገለፁት ዋና ዋና የግድቡ ስራዎች መሬቱን መጥረግና ማመቻቸት እንዲሁም የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየስ ነው” ያሉት አቶ ሙሼ፤ እነዚህ ስራዎች መገባደዳቸውን ጠቁመው ግንባታው ከታቀደለት ጊዜ ሁለትና ሶስት ዓመታት ቢጨምር ብዙም እንደማይገርም ገልፀዋል፡፡ “አስዋን ግድብ በአምስት ይጠናቀቃል ተብሎ ከአስር ዓመት በላይ ወስዷል” ያሉት የኢዴፓ ሊቀመንበር፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በቁሳቁስ አቅርቦትና በመሰል ጉዳዮች ሁለት እና ሶስት ዓመት ቢራዘም ሊያስደንቅ አይችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መንግስት የግድብ ሥራው በስኬት እንዲጠናቀቅ የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ አገራትን በዲፕሎማሲ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዳመጣ ሁሉ፣ በግድቡ ተጠቃሚ ከሚሆኑት እንደ ግብጽና ሱዳን ያሉ ሀገራት ተጨማሪ ገንዘብ ለማሰባሰብ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግም አቶ ሙሼ ገልፀዋል፡፡ “ህዝቡ ከአንድ ጊዜ በላይ ለማዋጣት አቅሙ ያለው አይመስለኝም” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ አስቸጋሪ በሆነበት በአሁኑ ወቅት የ80 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት በህዝብ መዋጮ እንደማይጠናቀቅና መንግስት ሶስት ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ በረጅም ጊዜ የሚከፈልና ወለዳቸው አነስተኛ የሆነ ብድር የሚያገኝበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ግሽበቱን ለመቀነስ የሚረዱ መንገዶችን ማመቻቸትም ሌላው መንገድ ነው ያሉት አቶ ሙሼ፤ ነጋዴውና የመንግስት ሠራተኛውን በየጊዜው ገንዘብ አምጣ ብሎ ማሰላቸት ህዝቡን ሊያማርርና አስተሳሰቡን ወደሌላ ሊቀይር ስለሚችል መንግስት አሁንም በርካታ የገንዘብ ማስገኛ መላዎችን መዘየድ አለበት ብለው እንደሚያምኑ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ ስጋታቸው ከነዚህ የሃብት አቅርቦቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ የግድቡን የማጠናቀቂያ ጊዜም ሊያራዝመው ይችላል የምንለው ይሄ ነው ይላሉ፡፡
መንግስት ይህን በርካታ ገንዘብ ማሰባሰብ ከማይችልባቸው ምክንያቶች ዋነኛው በርካታ ፕሮጀክቶችን በአንድ ጊዜ መዘርጋቱ ነው የሚሉት የኢዴፓ ሊቀመንበር፤ የስኳር፣ የባቡር እና የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ በጀት የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው የግድ ሌሎች የሀብት ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን መቀየስ ይኖርበታል ባይ ናቸው፡፡
ኢዴፓ የግድቡን መገንባት በሃሳብ ከመደገፍ ባለፈ እንደ ፓርቲ የገንዘብና የሙያ ድጋፍ ላይ ይሳተፍ እንደሆነ ተጠይቀው “እዚህ ውስጥ ሶስት ነገሮች ይካተታሉ፤ አንደኛ እንደዜጋ የምንወጣው አለ”ያሉት አቶ ሙሼ፤ በሁለተኛ ደረጃ ፓርቲው እንደ ፓርቲ አገራዊ ግዴታውን የሚወጣበት አካሄድ መኖሩንና የብሔራዊ ኮሚቴ አባል እንደመሆናቸው የሚወጣቸው ሚናዎች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡ በብሔራዊ ኮሚቴው ውስጥ ገንቢ ሃሳቦችን በማፍለቅ፣ መረጃዎችን በመለዋወጥና ማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የፓርቲ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ከአለምአቀፍ ማህበረሰብና ከዲፕሎማሲ ቡድኖች ጋር በመገናኘት እና በመወያየት በየትኛውም አቅጣጫ ስለግድቡ በጐ ገጽታና ምልከታ እንዲኖር ኢዴፓ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ እንደ ግለሰብና እንደዜጋ ከየመስሪያ ቤታችን ከደሞዛችን እየተቆረጠ ቦንድ ገዝተናል፤ በግልም ቦንድ የገዛን አለን፤ ከዚህ የበለጠ ሚና ሊኖረን አይችልም” ብለዋል፡፡
ኢዴፓ ቦንድ ገዝቶ እንደሆነ ተጠይቀውም ፤ ፓርቲው ለፖለቲካ ስራው የሚያውለው እንጂ ለግድቡ ቦንድ ለመግዛት የሚያስችል የተለየ ገንዘብ እንደሌለው ገልፀው፤ የኢዴፓ አባላት ግን እንደማንኛውም ዜጋ በየመስሪያ ቤታቸው ከደሞዛ\ቸው ቦንድ መግዛታቸውንና በግልም ቦንድ የገዙ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ አስመልክቶ በግብጽ በኩል ተንኳሽና የኢትዮጵያን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ መግለጫዎች ሲለቀቁ አቋማቸውን በግልጽ ማስቀመጣቸውን የተናገሩት የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ ኢትዮጵያ በወንዟ ስትለማ ማየት ላይ ችግር እንደሌላቸው ጠቁመው “ተቃውሟችን የግድቡ የግንባታ ሂደት ግልጽነት የጐደለው መሆኑ ላይ ነው” ብለዋል፡፡ ግልጽነት የጐደለው ሲባል ምንን ያካትታል በሚል ለተጠየቁትም፤ ግድቡ የ80 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት እንደመሆኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አለመጽደቁን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያልተወያየበትና በአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ አለመካተቱ ሂደቱን ግልጽነት የጐደለው ለማለት ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡ “ለምሳሌ ጨረታውን ማን እንደወሰደ አይታወቅም፤ እንዲህ ዓይነት ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ሁሉም ሳይመክርበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላዘዙ ብቻ የሚደረግ ከሆነ በቀጣይነቱም በጥራቱም ላይ እምነት ለመጣል ይከብዳል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ፓርላማ ሳያፀድቀው፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳይወያይበት እና ሰፊ ውይይት ሳይደረግበት እንዲህ በችኮላ የሚሰራና የፖለቲካ ሞቲቭ ያለበት ሥራ ውሎ አድሮ ችግር ማስከተሉ እንደማይቀር ጠቁመው፤ በተፋሰሱ አገሮች በኩል ገና ያላለቁ ሥራዎችን፣ ብድርና እርዳታ ለማግኘት በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች እንዲሰሩ፣ ጉዳዩ በግልጽና ክፍት በሆነ መልኩ ለውይይት መቅረብና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ መመስረት እንዳለበት በጽኑ እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ “በተረፈ ግን በገዛ አገራችን ላይ በሚመነጭ ወንዝ ለመልማትና መብታችንን ለመጠቀም በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ እንዴት ተቃውሞ እናነሳለን?” ሲሉም ጠይቀዋል - ኢንጂነር ይልቃል፡፡
አሁንስ ጉዳዩ ወደ ፓርላማና ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ትጠብቃላችሁ ወይ በሚል ለተጠየቁት “አንጠብቅም ግን አሁንም መንግስት የግንባታውን ሂደት ለሁሉም አካል ግልጽ ለማድረግ ጊዜው አልረፈደም” በማለት መልሰዋል፡፡ “እኛ አሁንም ግልጽነቱ ላይ ነው ጥያቄያችን፤ባለፈው መግለጫቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲዛይንና ግንባታው የሚሰራው ደረጃ በደረጃ ነው” ሲሉ ሰምቻለሁ ያሉት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፤ በየደረጃውና በሂደት የዲዛይን ክለሳ ካለ፣ የግድቡ አቅምና ሃይል የማመንጨት ጉልበቱም እንደየሁኔታው ከፍም ዝቅም ሊል እንደሚችል አብራርተው፣ እንደገና የአካባቢያዊ ተጽእኖ ጥናቱ የሱዳንና የግብጽን መረጃ አላከታተም መባሉ ሁሉ የተዘበራረቀ ስሜትን ስለሚያመጣ መንግስት አጠቃላይ ሂደቱን ለህዝቡ በግልጽ ማስረዳትና ህዝቡም እምነት እንዲጥልበት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ “የተፋሰስ አገሮቹ የአካባቢያዊ ተጽእኖ ሁኔታ እስካልተሰራ ድረስ ትክክል ይሁን አይሁን አይታወቅም” ያሉት ኢንጂነር ይልቃል፤ እንዲህ አይነት ብዥታ ባለበት ሁኔታ አቋም መውሰድ እንደሚያስቸግርም ጨምረው አብራርተዋል፡፡
መድረክ ግድቡ አይሰራ የሚል አቋም የለውም ያሉት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ በአካሄዱ ላይ ያሉትን ችግሮች ግን እንደማይቀበል ተናግረዋል፡፡ “በ2003 ዓ.ም የግድቡ ስራ መሠራት ሲበሰር ጀምሮ አካሄዱ ግልጽ ይሁን የሚል ጥያቄ አቅርበናል” ያሉት ፕ/ር በየነ፤ ከዚያ ውጭ አባይን ጨምሮ ሌሎቹም የአገሪቱ ወንዞች መጐልበት እንዳለባቸው በመድረክ የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡ “ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ለመያዝ ስርዓቱ አልፈቀደልንም፤ የራሱን አካሄድ አስቀምጦ በዚያ እንድንጓዝ ነው የሚያደርገን ያሉት” ፕ/ር በየነ፤ እኛ በመሠረተ ሃሳቡና በግድቡ ግንባታ ላይ ተቃውሞ ባይኖረንም በአካሄዱና ውሳኔ ላይ በተደረሰበት መንገድ ላይ ቅሬታ እንዳለን ገና ሲበሰርም ገልፀናል ብለዋል፡፡ “ይህ ግድብ ሊሠራ ሲታሰብ መድረክም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ማወቅ ነበረባቸው” ያሉት ፕ/ሩ፤ መድረክ እንደፓርቲ መንግስትና ህዝብ የሚያውቀው ከመሆኑም በላይ በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ ሆኖ ስለ ጉዳዩ ምክክር ሳይደረግ ስራውን መጀመሩ አግባብ ነው ወይ? የሚለውን በተደጋጋሚ ፓርቲው ማንሳቱን ተናግረዋል፡፡
“የ80 ቢሊዮን ብር ትልቅ ፕሮጀክት በደሀው ህዝብ ጫንቃ ላይ መጣሉም አንዱ የማንቀበለው ነገር ነው” የሚሉት የመድረክ አመራር፤ እነዚህን ሂሶች በወቅቱ አቅርበው እንደነበርና አሁንም 21 በመቶ ተገንብቷል የሚባለው ግድብ፤ በድሀው አቅም ፍፃሜ ላይ ይደርሳል ወይ የሚለው የመድረክ ሃሳብ እንዳለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህን ሁሉ አልፎ ግድቡ ከተጠናቀቀ ግን ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው የሚከፋውና ጠብ ያለሽ በዳቦ የሚልበት ምክንያት እንደሌለም አክለው ገልፀዋል፡፡ “እኛ በምን አቅም ነው የሚጠናቀቀው የሚል ጥርጣሬ አለን? ለምን ጥርጣሬ አስቀመጣችሁ የሚል የለም” ያሉት ፕ/ር በየነ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት የህዝቡ ደሞዝ ተጠራቅሞ 10 ቢሊዮን መድረሱን እንኳን እንደሚጠራጠሩ ገልፀው፤ አሁን ከቦንድ ሽያጭና ከደሞዝ የተገኘው ብር ከፕሮጀክቱ ፍላጐት ጋር ሲታይ አባይን በጭልፋ ነው በማለት መድረክ የግድቡ ፍፃሜ ላይ ያለውን ጥርጣሬ አብራርተዋል፡፡ “ግልጽ ለመናገር መድረክ በግድቡ አሠራር ላይ ሂስ አለው፤ ግን ይቁም አይሰራ የሚል አቋም የለውም” ብለዋል፡፡
መድረክ ይሰራ የሚል አቋም ካለው በሙያ፣ በሃሳብና በገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አስቧል ወይ በሚል ለተነሳው ጥያቄ፤ መድረክ የህብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ የመድረክ አባላት መሃንዲሶች፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችና ሌሎች አባላትም እንደሚሳተፉ የገለፁት ፕ/ር በየነ፤ መድረክ ፓርቲ እንጂ መንግስት ባለመሆኑ በአባላቱ በኩል የተለያዩ ተሳትፎዎችን እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ “መድረክ አባላቱ በተለያየ መልኩ እንደሚሳተፉ ነው የሚያውቀው፤ እኛስ የመድረኩ አመራሮች ቦንድ ገዝተን የለም እንዴ?” ያሉት አመራሩ፤ የአባላት ተሳትፎ መድረክ በህዳሴው ግድብ ላይ ይሳተፋል በሚል እንደሚመነዘር ገልፀዋል፡፡ መድረክ ግን እንደፓርቲ ልማት ላይ ኢንቨስት የሚያደርግበት አግባብም አቅምም እንደሌለው ተናግረዋል - ፕሮፌሰሩ፡፡ ህዝቡ ቦንድ በደሞዙ መግዛቱን በተመለከተ መድረክ “ህዝቡ ቦንድ እየገዛ ያለው በግዳጅና በጭንቀት ነው እንጂ በፍላጐት አይደለም” ማለቱን በማስታወስ አሁን ቦንድ መግዛታቸውን ያምኑበት እንደሆነ ጠይቀናቸው ሲመልሱ“ይህ በሁሉም የአገሪቱ ዜጐች ላይ የመጣ በመሆኑ እኛንም ለይቶ እንደማይተው ሃቁ ያሳያል” ያሉት የመድረክ ከፍተኛ አመራር፤ “ኢህአዴግ በፕሮፖጋንዳው ደሞዝ ያለው ሁሉ ይክፈል ሲል እኛም ለአገራዊ ቁምነገር አምጡ ስንባል ዝም ብሎ ማለፉ ተገቢ አልመሰለንም” ብለዋል፡፡ አናምንበትም በሚል ፍ/ቤት ተከራክረው ብራቸውን ያስመለሱ አንዳንድ አባላት መኖራቸውንም ገልፀዋል - ፕሮፌሰሩ፡፡
አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የብሔራዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እየተሳተፉ መሆናቸውን በማንሳት ለምን ፓርቲያቸው በኮሚቴ አባልነቱ አልተጋበዘም ወይም ለምን አባልነቱን አልጠየቀም? ቢጋበዝስ አባልነቱን ይቀበል ነበር ወይ በሚል ለጠየቅናቸው “መድረክ ግብዣ አልቀረበለትም፤ አባል የሆኑትም ብቃት አለን ብሔራዊ ኮሚቴ እንሁን ብለው አይደለም” ያሉት ፕ/ሩ፤ ገዢው ፓርቲ መርጦ ነው ያስገባቸው ብለዋል፡፡ መንግስት አቋቁሜያለሁ ብሎ ማወጁን፣ ነገር ግን አባል መሆን የምትፈልጉ ተሳተፉ አለማለቱን የጠቆሙት ፕሮፌሰር በየነ፤ አንዳንድ አባል ሆኑ የተባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የኢህአዴግ ልዩ ባለሟሎች እንደሆኑና ገንዘብም ተሠፍሮ የሚሰጣቸው በመሆኑ የብሔራዊ ኮሚቴው አባልነታቸው የሚያስገርም አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ ግብዣ ቢቀርብ ትቀበሉት ነበር ወይ ለተባለው “አሁን ብቻዬን የምመልሰው ሳይሆን እንደመድረክ የሁሉም ሃሳብ ተካቶ የሚመለስ በመሆኑ በግሌ እንቀበላለን አንቀበልም ለማለት እቸገራለሁ” ብለዋል፡፡
“ኢህአዴግ እኛን አግልሎናል፤ መድረክ ከዚያ ሁሉ ችግር ጋር ባለፈው አገር አቀፍ ምርጫ 38 በመቶ የህዝብ ድምጽ ያገኘ ፓርቲ እንደመሆኑ በሀገሪቱ በሚደረጉ ጉዳዮች ላይ ሊያሳትፈን ሲገባ በተለያዩ መንገዶች አድልኦና መገለሉን እያሳየ ነው፤ የብሔራዊ ኮሚቴ አሰባሰቡም ከዚህ አካሄድ የተለየ አይደለም” ብለዋል፤ ፕ/ር በየነ፡፡

Read 4092 times