Saturday, 06 July 2013 10:47

ዓለምን ዝም ያሰኘና ውግዘት ያልነካው መፈንቅለ መንግስት

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(15 votes)

ከግብፅ ዳግማዊ አብዮት የምንማረው ነገር አለ። በግለሰብ ነፃነት ላይ ያልተመሰረተ ህገመንግስት፣ ዲሞክራሲና ምርጫ ዋጋ እንደሌለው በግልፅ ያሳያል። በምርጫ ስልጣን ይዞ የዜጎችን ነፃነት የሚጥስ ሃይማኖታዊ አምባገነንነትም ሆነ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት መሰረታዊ ልዩነት የላቸውም።

የአፍሪካ “ዲሞክራሲ” እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል። አመፅና አብዮት ይለኮሳል። የቀድሞውን ባለስልጣን ወደ እስር ቤት ወርውሮ በሆታ ምርጫ ይካሄዳል። ከዚያ ውዝግብና ቀውስ ተባብሶ፣ እንደገና ወደ አመፅና አብዮት ይመለሳል። የአፍሪካ ፖለቲካ፣ ከዚህ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው አንዳች የጎደለና የተሳሳተ ነገር ቢኖር ነው። በዜጎች የተቃውሞ ድምፅና አመፅ አማካኝነት ስልጣን የያዘ ፓርቲና ፖለቲከኛ፣ በተራው በሌላ ዙር ተቃውሞና አመፅ ከስልጣን ይወርዳል። የፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ የስልጣን ዘመንም፣ የዚህ አዙሪት ውጤት ስለሆነ፣ በዚያው ልክ የአዙሪቱ ሰለባ ሆኗል - አጭር የቤተመንግስት ቆይታቸው በድንገት ተቋጭቶ፣ ወደ እስር ቤት! 
ሰሞኑን የተካሄደው የግብፅ አብዮት፣ በተደጋጋሚ ያየነው የለመድነው አፍሪካዊ አዙሪት ቢሆንም፣ እንደ አዲስ እንገረምበታለን። በጣም አስገራሚው ጉዳይ ግን ሌላ ነው - ለምሳሌ የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ሲንተባተቡ፣ ብዙዎቹ የአረብ መንግስታት ደግሞ ፈንድቀዋል። “ያለፈው አልፏል” የሚል ስሜት ያዘለ የተባበሩት መንግስታት ምላሽና የአፍሪካ ህብረት ዝምታም ያስገርማል። ህገመንግስት ሲፈርስና በምርጫ ስልጣን የያዘ ፕሬዚዳንት ሲታሰር… መንተባተብና መፈንደቅ ምን ይባላል? አይቶ ማለፍና ዝምታስ? “የግለሰብ ነፃነት” ጉዳይ ዋነኛው የፖለቲካ መመዘኛ መሆኑን ከልብ ለማመንና በግልፅ ለመናገር አለመፈለጋቸው ነው ችግሩ።
የግለሰብ ነፃነትን ለመጣስና ሃይማኖታዊ የፋሺስት ስርዓት ለመፍጠር የተነሳው muslim brotherhood የተሰኘውን የአክራሪዎች ቡድን በመወከል ስልጣን የያዙት መሀመድ ሙርሲ፤ ህገመንግስት ማፅደቃቸውና በምርጫ ማሸነፋቸው አይካድም። ነገር ግን ህገመንግስቱና ምርጫው ትርጉም የላቸውም። ቀድሞ ነገር፣ ህገመንግስት ማፅደቅና ምርጫ ማካሄድ ያስፈለገውኮ፣ የግለሰቦችን ነፃነት ለማስከበር ነዋ። የህጋዊነት ትክክለኛ መሰረት፣ የግለሰቦችን ነፃነት ማስከበር እንደሆነ አሜሪካዊያኑና አውሮፓውያኑ በግልፅ ለመናገር አለመድፈራቸውና መንተባተባቸው ነው አስገራሚው ነገር።
የሁለት ቀን እና የ48 ሰዓታት አማራጭ
አስገራሚው ነገር የአሜሪካዊያኑና የአውሮፓውያኑ መንተባተብ ነው ብልም፤ በሶስት ቀናት የተቃውሞ ሰልፍ መንግስት ሲፈርስና ፕሬዚዳንት ሲታሰር ማየት፣ … በየአገሩ በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ተራ ነገር ነው ማለቴ አይደለም። በሁለት አመት ውስጥ፣ አለምን ጉድ የሚያሰኙ ሁለት አመፆችንና አብዮቶችን የምታስተናግድ አገር አስገራሚነቷ አያጠራጥርም። እንደዘበት በ48 ሰዓታት ወታደራዊ ማስጠንቀቂያ፣ ያ ሁሉ የመሀመድ ሙርሲ ስልጣን ድንገት ማክተሙ ሳያንስ እስረኛ ሆነዋል። ለካ፣ የጄነራሎቹ ማስጠንቀቂያ የቀልድ አልነበረም፤ የመፈንቅለ መንግስት ዝግጅት መጠናቀቁን የሚጠቁም እንጂ። የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ፣ ብረት ለበስ መኪኖችና ታንኮች በካይሮ ጎዳናዎች የተሰማሩትም ለማስፈራራት ብቻ አልነበረም፤ የመፈንቅለ መንግስት ሂደት መጀመሩን የሚያሳይ እንጂ።
ለነገሩ፤ እሁድ ምሽት በቴሌቪዥን የተሰራጨው የጄነራሎቹ ማስጠንቀቂያ፣ በደንብ ላደመጠው አሻሚ ትርጉም የሚያስተላልፍ አይደለም። ማስጠንቀቂያው፣ ቃል በቃል ዛቻን ያዘለ ባይሆንም፣ መሀመድ ሙርሲን ከስልጣን ለማስወገድ ያነጣጠረ እንደሆነ፣ የግብፅን ፖለቲካ በቅርበት ለሚከታተሉ ታዛቢዎች ግልፅ ነበር። ለምን ቢባል፤ የጄነራሎቹ ማስጠንቀቂያ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሳሰቢያ ጋር ይመሳሰላል። በጊዜ አቆጣጠርና በአገላለፅ ብቻ ነው የሚለያዩት። ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሁለት ቀን የጊዜ ገደብ ሲሰጡ፣ ጄነራሎቹ ደግሞ የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ! ይሄው ነው ልዩነቱ።
እሁድ እለት የተቃውሞ ሰልፍ ዘመቻቸውን የጀመሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ፕሬዚዳንቱ እስከ ማክሰኞ እለት ከስልጣን እንዲወርዱ የሁለት ቀናት የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል። የተቃውሞ ሰልፈኛው፣ እሁድ እለት የካይሮ ጎዳናዎችንና የታህሪር አደባባይን ሲያጥለቀልቅ ከሄሊኮፕተር ላይ ሆነው የተመለከቱ የጦር ጄኔራሎች በፊናቸው፣ በዚያው እለት ያንን ዝነኛ ማስጠንቀቂያ በአዋጅ ለማስነገር ወሰኑ። ፕሬዚዳንቱ ማስጠንቀቂያውን የሰሙት ከሌላው ህዝብ ጋር በቴሌቪዥን ነው።
ለተቃውሞ የወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር ሰልፈኛ፣ የግብፅን ህዝብ እውነተኛ ፍላጎት ያንፀባርቃል ያሉት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጄነራል አብደልፋታህ አልሲሲ፤ የአገሪቱ ጦር ሃይል ከህዝቡ ጎን እንደሚቆምና የህዝቡ ፍላጎት ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ተናገሩ። ምን ማለታቸው እንደሆነ ግልፅ ነው። ሰልፈኛው በተደጋጋሚ የሚያስተጋባው ጩኸት አንድ ጥያቄ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደሆነ ይታወቃላ - ሙርሲ ይውረዱ የሚል ጥያቄ ብቻ። ከሰልፈኛውና ከህዝቡ ጥያቄ ጎን ቆመናል ብሎ መናገር፤ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ እንፈልጋለን ብሎ ከመናገር አይለይም። በዚያ እለትም ነው፤ አምስት የጦር ሃይል ሄሊኮፕተሮች የአገሬውን ባንዴራ እያውለበለቡ በታህሪር አደባባይ ዙሪያ በማንዣበብ ለተቃውሞ ሰልፈኛው ድጋፋቸውን የገለፁት።
ፕሬዚዳንቱ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተስማምተው ለህዝቡ ምላሽ ካልሰጡና አዲስ አቅጣጫ ካልቀየሱ፣ የራሴን እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ማስጠንቀቅስ ትርጉሙ ግልፅ አይደለም? ፕሬዚዳንቱ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መስማማት ከፈለጉ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባስቀመጡት ቀነ ገደብ መሠረት እስከ ማክሰኞ ድረስ ከስልጣን መልቀቅ ይኖርባቸዋል። በጄነራሎቹ አባባል ደግሞ፣ በ48 ሰዓት ማለት ነው።
መሀመድ ሙርሲ፣ የጄነራሎቹን ማስጠንቀቂያ ሲሰሙ፣ የስልጣን ቆይታቸው እንዳበቃለትና በሰዓታት ወይም በቀናት ብቻ የሚቆጠር ጊዜ ብቻ እንደቀራቸው የገባቸው ይመስላል። ማብቂያው እንደተቃረበ ካልገባቸውና ተጨማሪ ምልክት ካስፈለጋቸው፣ ዞር ዞር ብለው ማየት አያቅታቸውም። ማስጠንቀቂያው በተሰጠ ምሽት፣ ወደ ገዢው ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የዘመቱ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ቢሮዎቹን ገለባብጠው ህንፃው ላይ እሳት ለቀውበታል - የፀጥታ ሃይሎችም ተሳትፈውበታል። አገሬውን በሃይማኖታዊ መንግስት ስር አፍኖ ለመግዛት የሚገለገሉበትና በእጅጉ የሚጓጉለት የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸው ከእጃቸው ማፈትለክ መጀመሩን ካልተገነዘቡት ሞኝነት ይሆናል።
መዘዙ ግን ከዚህም ያልፋል። አገሬውን አፍኖ ለመግዛት የሚፈልግ ገዢ፣ ከስልጣን ሲወርድ የአፈና ሰለባ መሆኑ አይቀርም። ለነገሩ፣ ገና ከስልጣን ሳይወርዱ ነው፣ ፕሬዚዳንቱና የፓርቲያቸው መሪዎች ከአገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳ እንደተጣለባቸው የተነገረው። ብዙም ሳይቆይ፣ የፕሬዚዳንቱ መጨረሻ እስር ቤት ሆነ። ፕሬዚዳንቱ ለምንድነው የታሰሩት ተብሎ ለቀረበ ጥያቄ፣ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤትን ተዳፍረዋል የሚል ምላሽ ተሰጥቷል። ይሄ ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው። እውነታውኮ፣ ብዙም ሚስጥር አይደለም። አምባገነን ለመሆንና ዜጎችን አፍኖ ለመግዛት የሚፈልግ ፓርቲና ፖለቲከኛ፣ ከስልጣን ሲወርድ በተራው የአምባገነንነት ሰለባ መሆኑ አይቀርለትም - የአዙሪቱ አካል ነውና። እናም፣ ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ ወደ 40 የሚጠጉ የአክራሪው ገዢ ፓርቲ መሪዎችና ባለስልጣናት ታስረዋል። ሌሎች 300 የሚሆኑ መሪዎችና አባላት ላይም የእስር ትዕዛዝ ተቆርጦባቸው እየታደኑ ነው።
በሙርሲ ደጋፊዎችና በተቃዋሚዎች መሃል በተፈጠሩት ግጭቶች ሳቢያ የበርካቶች ህይወት ባይጠፋ ኖሮ፣ ሰሞነኛው የግብፅ አብዮት ማራኪ የ“ሪያሊቲ ሾው” ትዕይንት ይወጣው ነበር። ጉዳዩ በሃይማኖታዊ የፋሺዝም መንግስት ስር የመሰቃየት ወይም በወታደራዊ ትዕዛዝ ስር የመገዛት ዘግናኝ አጣብቂኝ ባይሆን ኖሮ፤ የአገሬው ፖለቲካ አዝናኝ ድራማ ተብሎ ለመጠቀስ ምንም አይጎድለውም።
“አዝናኝ ነው” ባንለውም እንኳ፣ ድራማነቱን ግን መካድ አይቻልም - ለዚያውም እየተጧጧፈ የሚጦዝ ልብ አንጠልጣይ ድራማ። የሆስኒ ሙባረክ ደጋፊ የነበረው የጦር ሃይል፣ የህዝብ ተቃውሞ ሲበረታ ሙባረክን በማውረድ ተወዳጅነትን ለማትረፍ የበቃው የዛሬ ሁለት አመት ነው። ግን ተወዳጅነቱ ከአንድ አመት በላይ አልዘለቀም። ስልጣን ላለማስረከብ ሲያንገራግር የህዝብ ተቃውሞ ስለተነሳበት፣ በምርጫ ላሸነፉት መሀመድ ሙርሲ ስልጣኑን አስረከበ። የድራማው ውጥረት ለጊዜው ቢረግብም፣ እንደገና አቅጣጫውን ቀይሮ ለመጦዝ ጊዜ አልፈጀበትም። ጦሩ የዛሬ አመት ለሙርሲ ያስረከበውን ስልጣን ሰሞኑን መልሶ ሲወስድ፣ እንደገና በእልልታና በሆታ አቀባበል ተደረገለት። አንድና ሁለት የለውም… በታህሪር አደባባይ በርችት ትዕይንት የተጠናቀቀው የተቃውሞ ሰልፍና የጄነራሎቹ መፈንቅለ መንግስት (በጥቅሉ የግብፅ አብዮት)… አጃኢብ የሚያሰኝ ድራማ ነው። ይበልጥ የሚያስገርም ድራማ የታየው ግን ከግብፅ ውጭ ነው - በአለማቀፍ መድረክ።
አሜሪካና አውሮፓ አላወገዙም፤ የ“መፈንቅለ መንግስት” ትርጉም ተቀየረ እንዴ?
በተቃውሞው ማዕበል ያልተደሰቱና መፈንቅለ መንግስቱን የተቹ መንግስታት 3 ብቻ ናቸው - ደግሞም ባይደሰቱ አይገርምም። የኢራኑ ሃይማኖታዊ መንግስት አንዱ ነው። ሃይማኖታዊ መንግስት በቱኒዚያ ላይ ለመጫን የሚታገለው የቱኒዚያ ገዢ ፓርቲም እንዲሁ የመሀመድ ሙርሲ አይነት እጣ እንዲደርሰው ስለማይፈልግ የግብፅ ጄነራሎችን ተቃውሟል። ወደ ሃይማኖት የሚያዘነብለው የቱርክ ገዢ ፓርቲም በተመሳሳይ ምክንያት መፈንቅለ መንግስቱን ተችቷል።
አብዛኞቹ የአረብ መንግስታት ግን ተደስተዋል። የሳውዲ አረቢያ፣ የሶሪያ፣ የተባበሩት የአረብ ኢሜሬት፣ የኢራቅ … በአጠቃላይ ብዙዎቹ የአረብ መንግስታት የግብፅ ጄነራሎችን ውሳኔ በማድነቅ የደስታ መግለጫቸውን አስተላልፈዋል። ምክንያታቸው ግልፅ ነው - እንደ መሀመድ ሙርሲ የመሳሰሉ የለየላቸው የሃይማኖት አክራሪዎች ስልጣን ላይ ከወጡ፣ የአረብ መንግስታት መናወጣቸው አይቀርም። በሙርሲ ውድቀት ቢደሰቱ ምን ይገርማል?
አቋማቸውን በግልፅ መናገር ያልቻሉት፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ናቸው። የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም እንዲሁ። ለምን? ከህገመንግስት ውጭ ስልጣን መያዝ፣ በዲሞክራሲያዊ አሰራር የተዋቀረውን መንግስት ማፍረስ፣ በምርጫ ያሸነፈውን ፕሬዚዳንት ማውረድ ተገቢ ነው እንዴ?
ተደጋግሞ እንደምንሰማው ቢሆን ኖሮ፣ በፖለቲካ ስርዓት ውስጥ እንደ ትልቅ ቁም ነገር የሚቆጠረው፣ “በህገመንግስትና በምርጫ የሚመራ” የዲሞክራሲ ስርዓት ብቻ ነው። የመሀመድ ሙርሲ መንግስት ደግሞ እነዚህን ነገሮች ያሟላል። ህገመንግስት አለው፤ በምርጫ አሸንፏል። እንግዲህ፤ ይህን “መመዘኛ” የሚያሟላ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው በህዝብ ተቃውሞና በጄነራሎች ውሳኔ የፈረሰው። ታዲያ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታት ለምን አላወገዙትም? የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ለምን ተቃውሟቸውን አልገለፁም?
“ከህገመንግስት ውጭ ስልጣን መያዝ ክልክል ነው” የሚል ግልፅ መመሪያ በመያዝ የመፈንቅለ መንግስት ድርጊቶችን እያወገዘ ከአባልነት ሲያግድ የቆየው የአፍሪካ ህብረት፣ እስካሁን ዝምታን መርጧል። በእርግጥ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ቅሬታቸውን ገልፀዋል። “የጄነራሎቹ ውሳኔ ያሳስበናል” ብለዋል። በቃ። “ያሳስበናል” ከማለት ውጭ፣ መፈንቅለ መንግስቱን አላወገዙትም። ከነጭራሹም፣ “መፈንቅለ መንግስት” ብለው አልጠሩትም። “ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያሳስበናል” በሚል አለዝበውታል።
“የዓለም መንግስታት መፈንቅለ መንግስቱን አለማውገዛቸውና “መፈንቅለ መንግስት” ብለው ከመጥራት መታቀባቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው” ያሉት የመሀመድ ሙርሲ ፓርቲ ቃል አቀባይ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲህ አይነቱ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱና በዝምታ መታለፉ አስገራሚ ነው ብለዋል። ዞር ብለው የራሳቸውን ፓርቲ ሲያዩም ተመሳሳይ ሃሳብ መናገር ነበረባቸው። መገረም ነበረባቸው። በ21ኛው ክፍለዘመን ሃይማኖታዊ የፋሺስት አገዛዝ ለመመስረት የሚፈልግ ፓርቲያቸው ስልጣን መያዙና ዓለም ሁሉ መሀመድ ሙርሲን በዝምታ ተቀብሎ ሲያስተናግድ መቆየቱ ይገርማል። ሂትለርምኮ በምርጫ ነው ስልጣን የያዘው።
ይሄ ሁሉ መምታታት የተፈጠረው፣ በአንድ ጉድለት ምክንያት ነው - በአንድ መሰረታዊ ጉድለት ምክንያት። ዋነኛ የፖለቲካ ስርዓት መመዘኛ የነበረው፣ “የግለሰቦች ነፃነት” ወደ ጎን ገሸሽ መደረጉ ነው ዋናው ጉድለት። ምርጫና ህገመንግስት በቁንፅል ዋነኛ የፖለቲካ መመዘኛ እንዲሆኑ በመደረጉ፤ በዝምታ የሚስተናገድ ሃይማኖታዊ የፋሺስት ስርዓትና በዝምታ የሚታለፍ መፈንቅለ መንግስት ለማየት በቅተናል። ሃሙስ እለት 237ኛ አመቱ የተከበረው የአሜሪካ የነፃነት መግለጫ ላይ በግልፅ የሰፈረው የፖለቲካ መሰረታዊ መመዘኛ፣ ቀስ በቀስ ገሸሽ ባይደረግ ኖሮ እንዲህ አይነት አሳፋሪ አለማቀፍ ድራማ ባልተፈጠረ ነበር።
እያንዳንዱ ሰው ከተፈጥሮው የማይነጠሉ መብቶችን የተጎናፀፈ መሆኑን በመግለፅ የሚጀምረው የአሜሪካ የነፃነት መግለጫ፣ ከእነዚህ መብቶች መካከልም፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ህይወት የመጠበቅ፣ የራሱን ህይወት የመምራትና በራሱ ጥረት ደስታን የመሻት መብቶችን ይጠቅሳል። የእያንዳንዱን ሰው መብቶች ለመጠበቅም ነው፣ መንግስት በሰዎች መልካም ፈቃድ የሚቋቋመው በማለትም ዋነኛ የፖለቲካ መመዘኛውን ቁልጭ ባለ ቋንቋ አስፍሯል - መግለጫው። ያለ ሰዎች መልካም ፈቃድ (ያለ ምርጫ) ስልጣን መያዝ ህገወጥ ነው። ለምሳሌ በመፈንቅለ መንግስት አማካኝነት ስልጣንን የሙጢኝ ይዞ መቀጠል አይቻልም። ዋናው ቁም ነገር ግን ይሄ አይደለም። ዋናው የፖለቲካ መመዘኛ፤ “መንግስት የግለሰቦችን ነፃነት ለማስከበር የሚቋቋም መሆን አለበት” የሚለው ነው። አለበለዚያ ህጋዊነት አይኖረውም።
“ማንኛውም አይነት መንግስት”፣ የግለሰብ መብቶችን የሚፃረር ከሆነ፣ ሰዎች ይህንን መንግስት የመለወጥ ወይንም የማስወገድ እንዲሁም አዲስ መንግስት የማቋቋም መብት አላቸው ይላል መግለጫው። … to secure these rights, Governments are instituted among Men, deriving their just powers from the consent of the governed. That whenever any Form of Government becomes destructive of these ends, it is the Right of the People to alter or to abolish it, and to institute new Government…
የአሜሪካ መስራቾች፣ “ማንኛውም አይነት መንግስት” በሚል አገላለፅ በመግለጫው ላይ ያሰፈሩት አለምክንያት አይደለም። የአፍጋኒስታኑ ታሊባንና የሶማሊያው አልሸባብ በተፈጥሯቸው ልክየለሽ አምባገነኖች አይደሉ? በምርጫም ሆነ ያለ ምርጫ ስልጣን ቢይዙ ለውጥ የለውም። ሂትለር ስልጣን የያዘው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስለሆነ፣ ፋሺስትነቱንና አምባገነንነቱን አያስቀርለትም። ከውጭ የመጣ ቅኝ ገዢም ሆነ የአገር ውስጥ ገዢ፣ የትውልድ ሃረግ ቆጥሮ አልያም የሃይማኖት እምነቶችን ታቅፎ ዘውድ የደፋ መንግስት፤ በመፈንቅለ መንግስትም ሆነ በምርጫ ስልጣን የያዘ ፓርቲ፣ የትኛውም አይነት ቢሆን፣ የግለሰብ መብቶችን የሚፃረር ከሆነ፤ ሰዎች ይህንን መንግስት የመጣልና የማስወገድ መብት አላቸው። የግለሰብ ነፃነት ላይ ያልተመሰረተ መንግስትና ህገመንግስት ዋጋ የላቸውም።
በዚህ የፖለቲካ መመዘኛ ስናየው፣ የመሀመድ ሙርሲ መንግስትን ማስወገድ ተገቢ ነው - ሃይማኖታዊ እምነታቸውን በሁሉም ሰዎች ላይ ለመጫን (በጅምላ የግለሰቦችን ነፃነት ለመጣስ) ዘመቻ የጀመረ መንግስት ነውና። የሃይማኖት አክራሪዎች አላማ፣ ሁሌም የግለሰቦችን ነፃነት ለማጥፋት ያነጣጠረ ነው። በተግባርም፣ ስልጣን ሲጨብጡ ምን እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ አይተናል … መዝፈንና መደነስ አይቻልም፤ ቴሌቪዥን መመልከትና ኳስ መጫወት አይቻልም…። መበደርና ማበደር፣ ፂም ማሳደግና አለማሳደግ፣ ፊትንና ፀጉርን መሸፈን ወይም አለመሸፈን፣ መፆምና መስገድ፣ ማተብ ማሰርና አለማሰር፣ መጠመቅና አለመጠመቅ የእያንዳንዱ ሰው የግል ነፃነት ሆኖ ሳለ፤ ይህን ነፃነት ለመጣስና ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳን ፓርቲና ፕሬዚዳንት ከስልጣን አሽቀንጥሮ መጣል ጥሩ ነው። ለምን? ዋነኛው የፖለቲካ መመዘኛ፣ የግለሰብ ነፃነት ነውና። ይህ፣ ለአሜሪካ ታላቅነት መነሻ የሆነ ትክክለኛ የፖለቲካ መመዘኛ ወደ ጎን ገሸሸ ባይደረግ ኖሮ፣ እነ አሜሪካና አውሮፓ ሰሞኑን እንዳየናቸው በግብፅ መፈንቅለ መንግስት ሳቢያ ባልተንተባተቡ ነበር። የሙርሲ ከስልጣን መወገድ መልካም ነው። በዚያው መጠን፤ በትክክለኛው የፖለቲካ መመዘኛ መሰረት፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከአገሬው ሰዎች መልካም ፈቃድ ማግኘት ስለሚያስፈልግ፣ ጄነራሎቹ ስልጣንን የሙጢኝ ይዘው መቀጠል የለባቸውም።

 

Read 4464 times