Saturday, 06 July 2013 10:32

የግል ኢንቨስትመንት እየቀጨጨ፣ የመንግስት እየጎላ መጥቷል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)
  • ለኢኮኖሚው ግንባታ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል

 በተከታታይ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ነው በተባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው ከግል ባለሃብቱ ኢንቨስትመንት ይልቅ የመንግስት ኢንቨስትመንት መሆኑን አንድ ጥናት ሰሞኑን ጠቆመ፡፡ 

ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና በንግድ ሚኒስቴር የአለም ንግድ ድርጅት (WTO) ዋና አማካሪ የሆኑት አቶ ማሞ ምህረቱ ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል “The investment Climate in Ethiopia; some reflections” በሚል ርዕስ ለምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችና ለባለድርሻ አካላት ባቀረቡት ጥናት፤ እየተመዘገበ ባለው እድገት ውስጥ የግል ኢንቨስትመንቱ ሚና እየተዳከመ፣ በአንፃሩ የመንግስት ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ድርሻ እየያዘ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ እንደጥናት አቅራቢው፣ በ2011/12 ዓ.ም የአለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ8.5 በመቶ ማደጉን ያመለከተ ሲሆን በዚህ እድገት የመንግስት ኢንቨስትመንት 63 በመቶ ድርሻ ይዟል ተብሏል፡፡ የዓለም ባንክን ሪፖርት በመጥቀስ፣ ይህ አሃዝ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀርም አገሪቱን ከአለም አገራት በመንግስት ኢንቨስትመንት ድርሻ በ3ኛ ደረጃ ያስቀምጣታል ብለዋል - ጥናት አቅራቢው፡፡
ለማሳየነት በተጠቀሰው የእድገት ዘመን በቱርኬሚስታን የመንግስት ኢንቨስትመንት ለአመታዊ ምርት እድገት (GDP) ያለው ድርሻ 38.6 በመቶ የነበረ ሲሆን አገሪቱን ከአለም ሃገራት በ1ኛ ደረጃ ያስቀምጣታል፣ ቀጥሎ ያለችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ስትሆን መንግስት የ24.3 በመቶ ድርሻ አለው፤ በ3ኛ ደረጃ በምትከተለው ኢትዮጵያ ደግሞ የመንግስት ኢንቨስትመንት ለዓመታዊ ምርት እድገት ያለው ምጣኔ የ18.6 በመቶ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የግል ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ትንሽ መሆኑን የገለፁት ጥናት አቅራቢው፣እሱም ቢሆን ከአመት አመት እየቀነሰ በአንፃሩ የመንግስት ኢንቨስትመንት ሚና እየጎላ መጥቷል ብለዋል፡፡ ለመንግስት ኢንቨስትመንት መጨመር ማሳያ በማለት አጥኚው ሁለቱ አካላት ከባንክ የሚበደሩትን የብድር አቅም መጠን በማነፃፀር አቅርበዋል፡፡ በጥናት ውጤቱ ለማሳያነት በተጠቀሰው የ2011/12 አመት ከባንኮች በአጠቃላይ 224 ቢሊዮን ብር በብድር የተወሰደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 57 በመቶውን የመንግስት የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ሲወስዱ፣ 15 በመቶውን ብቻ የግል የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ወስደዋል፡፡ መንግስት ከወሰደው ብድር 90 በመቶውን ያዋለው ለኢንቨስትመንት መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
የግል ኢንቨስትመንቱ አሽቆልቁሎ የመንግስት እንዴት ሊጨምር ቻለ ለሚለው ጥናት አቅራቢው ምክንያት ያሏቸውን ነጥቦች የዘረዘሩ ሲሆን ከነዚህ መካከል የታክስ አስተዳደር ችግሮች፣ የመንግስት ኢንቨስትመንት መጠናከሩ፣የደንበኞች እጦት፣የሰው ሃይል አቅርቦት እጥረት፣ የሃይል እጥረት፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ የግል ባለሃብቶች አለመጉላት እንዲሁም በየጊዜው ተለዋዋጭ ፖሊሲዎች መኖራቸው የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የግል ኢንቨስትመንቱ መቀጨጭ ለኢኮኖሚ ግንባታው አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት አቶ ማሞ፤ መንግስት በቀጣይ የግል ባለሃብቱ ኢንቨስትመንት ድርሻ ጎልቶ እንዲወጣ ከፈለገ የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን መዘርጋት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በዚህ ረገድ አዋጭ አሰራር በሚል ካቀረቡት መካከል፣ የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎትን መጠቀም ይገኝበታል፡፡ ይህ አገልግሎት በአንድ የኮምፒውተር መስኮት ባለሃብቱ በተለያዩ የመንግስት መስሪያቤቶች ያሉትን ጉዳዮች ቢሮው ቁጭ ብሎ እንዲጨርስና ከተራዘመ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ እንዲድን ያደርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የታክስ ኮንፈረሶችን ማካሄድ፣ከግል ኢንቨስተሮች ጋር መወያየትና ችግሮችን አጥርቶ ማወቅ እንዲሁም የኤሌክትሪክና የመሳሰሉ የሃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታዎችን አጠናክሮ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

Read 14201 times