Print this page
Saturday, 29 June 2013 11:08

አዘኔታ!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ምሽቱ ገፍቷል፤ ለኮሌጁ ዘበኞች ደግሞ በጣም ገፍቷል፤ አንድ ተማሪ የግቢውን በር ማንኳኳት የሚፈቀድለት እስከ ምሽቱ 4፡30 ድረስ ነው፤ አሁን 4፡40 ሆኗል፤ በጣም መሽቷል፤ በዚህ ሰዓት ደፍሮም የሚያንኳኳ ተማሪ የለም፤ ዘበኞቹም አዝነው አይከፍቱም፡፡ አሁን ወደ ግቢው ለመግባት ሁለት አማራጮች ናቸው ያሉት፡፡ አንድ፣ በአጥር መዝለል ሌላም፣ዘበኞቹን በጥቂት ብሮች መደለል፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው አደጋ አላቸው፡፡ በአጥር ሲዘል የተገኘ ተማሪ ቢያንስ ለአንድ ሴሚስተር ከኮሌጁ ይታገዳል። ዘበኞቹ ደግሞ እንደ ጉስቁልናቸው አይደሉም፤ በብር አይታለሉም፤ በዚህ ላይ ሁለት እና ሶስት ስለሚሆኑ እርስ በርስ ይጠባበቃሉ፤ብቻ ደረቆች ናቸው፤ በሰላም ጊዜ እንኳ ተማሪዎችን የሻይ ግብዣ አይቀበሉም፡፡ ሌላኛው የተሻለ እና ብቸኛ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ቤርጎ ማደር ነው፡፡ ክፋቱ ግን እርሱ ሁሉንም መፈፀም አይችልም፡፡

“አምላኬ! ምን አይነት ጣጣ ውስጥ ነው የከተትከኝ!” አባቱ ደግሞ ደውለው ነበር፡፡ አደራቸውን ለማደስ፡፡ እሺ ታዲያ አሁን የት ሄዶ ነው? ይህን ያህል ከቶም አምሽቶ አያውቅም፡፡ 4፡53 እንደ አለመታደል ሆኖ ጊዜውም የፈተና ወቅት ነው፡፡ ደብተርና መፅሃፎቼን ለአመል ያህል ልግለጣቸው እንጂ አንዲት ዐረፍተ ነገር እንኳ መረዳት አልቻልኩም፡፡ የስሜት ህዋሳቶቼ በሙሉ ውጭ ነው ያሉት፡፡ ጆሮዎቼ የበሩን መንኳኳት ይጠብቃሉ፡፡ ሲራመድ ዱቄት ላይ ይሄድ ይመስል ኮቴው ባይሰማም መተላለፊያው ላይ ኮቴ ባዳመጥኩ ቁጥር አይኖቼን በር ላይ እሰካለሁ፡፡ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት፣ ከዚያ ድምጹ እየራቀ ይሄዳል፡፡ ጸጥታ፡፡ ነፋስ፡፡ ኃይለኛ ነፋስ፡፡ በመኝታ ክፍላችን ውስጥም ከባድ ጸጥታ ሆኗል። ቀና ብዬ ሌሎች ሶስት የመኝታ ክፍል ጓደኞቼን ቃኘኋቸው፡፡ ሁሉም አንገታቸውን ወረቀት ላይ ደፍተዋል፡፡ ጭንቅላታቸውን መጽሐፍት ውስጥ ደብቀዋል፡፡

እስቲፋኖስ በመሰላቸት ደጋግሞ ፀጉርን ያካል፤ ይፎክታል፤ የዘወትር ልምዱ ነው፡፡ አትክልቲ ጉንጮቹን እጆቹ መዳፎች ውስጥ ቀብሮ ደብተሩ ላይ አድፍጧል፡፡ መኩሪያ አንዳች ነገር ይጫጭራል፣ ሲያጠና እጁ አያርፍም፤ ካልጻፈ አይገባውም ወይም የገባው አይመስለውም፡፡ ክፍላችንንም ቃኘሁት፡፡ ያልተጠረገ ቤት፣ ያልተነጠፈ አልጋ፣ የተዘበራረቁ መጻህፍት፣ ያልተከደነ ደብተር፣ በአልጋው ስር የወደቁ ካልሲዎች፣ ያለቁ እስኪርቢቶዎች… ዐይኔን ወደ ጓደኞቼ መለስኩት። ያልተበጠረ ፀጉር፣ የደፈረሱ አይኖች፣ የጎበጠ ትከሻ፣ መረጋጋት የማይታይበት ፊት… ጥናቴን ትቼ አይኔን ሳንከራትት ጭንቀቴ ገብቷቸው ሶስቱም ካቀረቀሩበት ቀና ቀና እያሉ በቦዙ ዓይኖቻቸው ሲያፈጡብኝ የባሰ ጨነቀኝ፡፡ ሰዓቴን አየሁ፡፡ 5፡10፡፡ ማድረግ የምችለው ነገር ስላልነበር ወጥቼ ቀጥታ ወደ ግቢው በር አመራሁ፡፡ የእስጢፋኖስ የመሰላቸት እና የንጭንጭ ድምጽ ተከተለኝ፡፡ ነፋሻ ምሽት ነው፡፡

እንደምትሀት ይወረወራል ነፋሱ፡፡ ባሕር ዛፎቹን ገንድሶ ሊጥል የፈለገ ይመስላል፡፡ ያ ባይቻለውም ጎንበስ ቀና እያደረጋቸው ነው፡፡ ዛፎቹ መቅኔያቸው እንደተንጠፈጠፈ የሽማግሌ ጉልበቶች እየተንቋቁ አጎንብሰው ይመለሳሉ፡፡ ወደ ግቢው በር እየቀረብኩ በመጣሁ ቁጥር የሰዎች አጀብ ቢጤ ታየኝ፡፡ እርምጃዬን አፈጠንኩ፡፡ ረጃጅም ቅልጥሞቼን አወናጨፍኳቸው፡፡ የክርስቶስ ያለህ! ይህ ተዓምረኛ ልጅ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ሆኖ ዘበኞቹ መኻል ቆሟል፤ ቀጫጫ ሰውነቱ በብርድ ይንዘፈዘፋል፤ ረዥም ሉጫ ጸጉሩ ተንጨባሯል፤ ጥቋቁር አይኖቹ ወዲያ ወዲህ ይንከባለላሉ፤ ግትር አፍንጫውን ቅዝቃዜ አርጥቦታል፡፡ ተንደርድሬ መሀላቸው ገባሁ፡፡ አዟዙሬ አየሁት፡፡ ደህና ነው። ቆዳው ብቻ በብርዱ ሳቢያ ተጉረብርቦ ፎጣ መስሏል። የምለውን አጣሁ፡፡ ምላሴ እንኳን በእንዲህ አይነት ቀውጢ ሰዓት ይቅርና በደህናው ጊዜም አይታዘዝልኝም፡፡ በጥያቄ ዐይን አየሁት። ወተት ጥርሶቹ ስስ ከንፈሮቹን ሸርተት አድርጎ አሳየኝ። አሁን የሆነውን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀብኝም። ድሮውንም ሳየሁ ጠርጥሬያለሁ፤ እስከ አሁንም መሳቀቄ ራሱ ከንቱ ነበር፡፡ ቶማስን እንኳንስ የመቀሌ ኮሌጅ ማህበረሰብ፣ የመቀሌ ህዝብ ሳያውቀው አይቀርም፡፡

ዘበኞቹ በዚህ መኻል አዝነው ከህግ ውጭ እንዲገባ ፈቀዱለት፡፡ ይህን ጊዜ በእፎይታ ተነፈስኩ፡፡ እንዲያውም ትህትናቸዉ ለጉድ ነበር፤ ይግረምህ ብለው ነው መሰለኝ አንደኛው ዘብ እራሳቸውን ለብርድ አጋልጠው ጋቢያቸውን ከላያቸው ገፈው አለበሱት፡፡ ፊታቸው ላይ ያየሁት ርህራሄ ልቤን ዘልቆ ተሰማኝ፡፡ “የት ነበርክ?!” አልኩት፡፡ ፈገግታ - የእሱ ምላሽ፡፡ ቶማስ፣ “የት ነበርክ?!” ደግሜ ጠየቅሁት፡፡ ንጻታቸው የሚያስፈራ ጥርሶቹን በሰፊው ገለጻቸው፡፡ “የት ነ-በ-ር-ክ?!” አሁንም ፈገግታ፡፡ ትከሻውን ይዤ እንደ ጆንያ አራገፍኩት፡፡ “ለምጠይቅህ ጥያቄዎች መልስ እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ የት ነበርክ?! ደግሞስ ልብሶችህስ?! ትከሻውን አማታብኝ፡፡ ይዤው መንገድ ጀመርን፡፡ ትዕግስቴ ተሟጦ ቢያልቅም ምን እንደምለው ግራ ገብቶኛል፡፡ የመጨረሻ ልናገር የምችለው ክፉ ነገር ቢኖር፡- “ከእንግዲህ ስለ አንተ አያገባኝም፡፡ ገደል ግባ!” ይሆናል፡፡ በቃ፡፡ “ጃኬቱን ዛሬም አውልቀህ ሰጠህ አይደል?!” ከግድ-የለሽነት በተቀላቀለ አዎንታ ትከሻውን ነቀነቀ። በወዲያኛው ሳምንት የተገዛ ጃኬት ነበር፡፡

እሱንም አውልቆ በሰጠው ጃኬት ምትክ ነበር የገዛነው። ምናልባት የዋጋው ውድነት አሸንፎት አይሰጥ እንደሁ ብዬ ለአንድ ጃኬት 500 ብር ስንከፍል ቅር አላለኝም ነበር፡፡ ይኸው ጉድ ሰራኝ፡፡ ያለ ወትሮዬ የማደርገውን መቆጣጠር ተሳነኝ፡፡ በድጋሚ ይዤ ወዘወዝኩት፡፡ “ለምስኪኑ አባትህ እንኳን አታዝንላቸውም?! እኔንስ ያለ ዕዳዬ ለምን ታሰቃየኛለህ?! ለምን ነብሴን ታስጨንቃለህ?! ለሰው ማዘን፣ የተቸገረን መርዳት፣ መጥፎ አይደለም፡፡ ግን እንዲህ ቅጥ ሲያጣ ደግሞ በምንም መልኩ ቢሆን ጥሩ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዴት ያን ያህል ብር አውጥተን የገዛነውን ጃኬት አውልቀህ ትሰጣለህ?! ለዚያውም በዚህ ብርድ …” አቋረጠኝ፡፡ “ምንተስኖት፣ ሰውየውን ብታያቸው እንዲህ አትልም ነበር፡፡ በዚህ ብርድ በብጣሽ ሸሚዝ ግንብ ስር ኩርምት ብለው ሳያቸው ልተባበራቸው ይገባኝ ነበር፤ ተባበርኳቸው፡፡ እስከ አሁን የቆየሁትም ሳጫውታቸው ነው፡፡ አየህ እናቴ “የተቸገሩ ሰዎች ከምንም በላይ ሰው ይናፍቃቸዋል” ትል ነበር፤ እና ከአንዱ የኔ-ቢጤ ጋር ማውራት ከጀመረች ቀኑ ይመሽ፣ ምሽቱ ይነጋ ነበር…” ጆሮዎቼ በሁለት እጆቼ ደፈንኳቸው፡፡ ሁሌም የሚነግረኝ ይህንኑ ነው፡- እናቴ፣ እናቴ፣ እናቴ … ኪሱ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በሙሉ አራግፎ “የኔ-ቢጤ” ለሚላቸው ያከፋፍላል፡፡

“ለምን?” ስል፡- “አየህ እናቴ ድሆችን መርዳት ያለብን ከተረፈን ላይ ቆንጥረን ሳይሆን ከሚያስፈልገን ጭምር ላይ መሆን አለበት፤ ትለኝ ነበር” ነው መልሱ፡፡ የራሱን ትቶ የሌሎች ተማሪዎችን አሳይመንት ይሰራል፡፡ “ተው” ስል እየፈገገ፡- “አየህ እናቴ ከራሷ በፊት ሌሎችን ታስቀድም ነበር” ይላል፡፡ እንዲህ እንደዛሬ ጃኬቱን አውልቆ የሰጠ ጊዜም፡- “ለምን?” ብዬ ስሞግተው፡- “እናቴ ሁለት ነጠላ ካላት አንዱን ለታረዘ ታለብስ ነበር’ ነው ያለኝ፡፡ ምን ዓይነት ልክፍት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ለተቸገሩ የሚቸረው ንብረቱን፣ ገንዘቡን እና ጊዜውን ብቻ አይደለም፤ እንባውንም ጭምር ነው፡፡ ሳንቲም አጥቶ ኪሱ ሲራቆት (ያው ሰጥቶ ሲጨርስ) እንባው ይጎርፋል፡፡ ደውሎ አባቱ ላይ ይጮህባቸዋል፤ እንደመታደል ሆኖ ደህና ኑሮ አላቸው አባቱ፤ እናም ገንዘብ ይልኩለታል፡፡ ለአራት ወራት መከርኩት፤ ተቆጣሁት፤ አብሬው ላይ ታች አልኩ፤ አሁን ግን ሰለቸኝ፤ መረረኝ፡፡ እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባሁበት ቀን ብላሽ ቀን ነው። አባቱ ናቸው እዚህ ጣጣ ውስጥ የነከሩኝ፡፡ እናም ደግሞ የኮሌጁ ዲን፡፡

ብቻ መጀመሪያ አደራውን ስቀበል ይህን ያህል እቸገራለሁ ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር፡፡ … ከአምስት ወራት በፊት፣ እዚህ ኮሌጅ በገባሁ ማግስት አንድ አባት ልጃቸውን አስከትለው ወደ ዶርማችን መጡ፡፡ የኮሌጁ የተማሪዎች ዲን አብሮአቸው አለ፡፡ ካሉት አምስት አልጋዎች አራቱ በእኔ፣ በእስጢፋኖስ፣ በመኩሪያ እና በአትክልቲ ተይዘው አንድ አልጋ ብቻ ነው ያልተያዘው፡፡ እንግዳው ሰውዬ እና ዲኑ ጎርደድ እያሉ ክፍሉን ቃኙት፡፡ እንደ አጋጣሚ አራታችንም የዚያ መኝታ ክፍል ተጋሪዎች እዚያው ነበርን፡፡ ዲኑ ሲቀሩ አባትና ልጅ በየተራ ተዋወቁን፡፡ ልጅ ቶማስ፣ አባት ሙሉ ወርቅ ይባላሉ፡፡ ቶማስ በቅጽበት ተዋሀደን፡፡ አራታችን መኻል ሆኖ ሲያወራን ለረዥም ጊዜ የምንተዋወቅ እንመስል ነበር፡፡ ሁኔታው ገርሞኛል፡፡ የመጣንበትን ቦታ፣ የተማርንበትን ትምህርት ቤት፣ ሌላው ቀርቶ ውጤታችንን በየተራ አስለፈለፈን፡፡ እርሱም እንደ እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነው፤ መኩሪያ የሲዳሞ፣ እስጢፋኖስ የጅማ፣ አትክልቲ ደግሞ የዚሁ የመቀሌ ልጅ ነው፡፡ ቀልቤ ቶማስ የጫረው ጨዋታ ላይ እንደሆነ፣ ድንገት ቀና ስል የቶማስ አባት እና ዲኑ ባይናቸው መልዕክት ሲለዋወጡ አየኋቸው፡፡ አፈጠጡብኝ።

ዐይኔን ሰበርሁ፡፡ ተሰናብተውን ሊወጡ በር ጋ ከደረሱ በኋላ ከጓደኞቼ ነጥለው ጠሩኝ፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ሄድኩ፡፡ አቶ ሙሉ ወርቅ ባንድ እጃቸው እኔን፣ በሌላ እጃቸው ቶማስን ይዘው መንገድ ጀመሩ፡፡ ዲኑ ከጎኔ ሆኖ ተከተለን፡፡ ወደ እርሱ ቢሮ ነበር የሄድነው፡፡ ቶማስን የፊተኛው ክፍል ውስጥ አቁመው እኔን ይዘውኝ ወደ ዋናው ቢሮ ዘለቁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አንዳችም አልተናገርኩም። ቀጣዩ ነገር ምን እንደሚሆን በጉጉት ሳይሆን በአግራሞት እየጠበቅሁ ነበር፡፡ ሁለቱ ጎን ለጎን፣ እኔ ከፊት ለፊታቸው ተቀመጥን፡፡ አቶ ሙሉወርቅ “ልጄ…” አሉኝ ንግግራቸውን ሲጀምሩ፡፡ ልክ እንደ ልጃቸው ቶማስ ብስል ቀይ ይሁኑ እንጂ የሱን ያህል ዐይን አይስቡም፡፡ ቀጭን ናቸው፤ ጆሮአቸው ትልልቅ፣ ጥርሶቻቸውና ዐይኖቻቸው ትንንሽ፣ አፍንጫቸው ደግሞ አጠር አጠር ብሎ ወደ ግንባራቸው ሰቀል ያለ ነው፤ ጸጉራቸው ሉጫ ነው፤ ጥቁር ሉጫ፡፡

ጅምር ንግግራቸውን አቋርጠው ኪሳቸውን መዳበስ ጀመሩ፡፡ ከኪስ ቦርሳቸው ጉርድ ፎቶ አውጥተው አቀበሉኝ፤ ያለችበትን የዕድሜ ክልል መገመት የሚያስቸግር ሴት ምስል አለበት፤ በምንም በምንም ቶማስን የምትመስል ሴት ፎቶ፤ ጸጉር፣ ግንባር፣ ዓይን፣ አገጭ፣ አፍንጫ … ሁሉ ነገራቸው ይመሳሰላል ሳይሆን አንድ ነው፤ እህቱ ወይ እናቱ መሆን አለባት፡፡ “ልጄ” ቀጠሉ የቶማስ አባት፡፡ “ልጄ እርሷ የምታያት ሴት የቶማስ እናት ናት፤ አምና ነው በድንገተኛ ሕመም ያረፈችው፡፡ ቶማስ፣ የኔም የሷም ብቸኛ ልጃችን ነው፤ እና ለእርሱ የነበራት ፍቅር ፍፁም ልዩ ነበር፡፡ እኔን ከነመኖሬም አያስታውሱኝም፡፡ ሁለቱ አብረው ይበላሉ፤ አብረው ይጠጣሉ፤ በአንድነት ይጫወታሉ፤ አንድ ላይ ይተኛሉ … አሁን እንግዲህ አስራ ዘጠኝ ዓመቱ ነው፡፡ እስከ አስራ ስምንተኛው ዓመት ማብቂያው ድረስ … ማለትም በሞት እስክትለየው ድረስ ግን ጡቷን ይጠባ ነበር፤ ደረቅ ጡቷን ይመጠምጥ ነበር። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ለመኻላ እንኳን አንድም ቀን ተለያይተው ተኝተው አያውቁም፤ እና ይህን ሁሉ ያነሳሁት ለምንድነው? …እ… ዲኑ እንደነገሩኝ በኮሌጁ ውስጥ አንድ አልጋ ለሁለት መጋራት አይፈቀድም፡፡ የኔ ልጅ ደግሞ በዚህ በኩል ከፍተኛ ችግር አለበት። በምንም ዓይነት ብቻውን መተኛት አይችልም።

እና አብሮት የሚተኛ ሰው ከተገኘ ያን ማድረግ እንደሚችል ተነግሮኛል፡፡ ማለት፣ ፍቃደኛ ከሆነ ከአንድ ሌላ ሰው ጋር አልጋ እንዲጋራ ተፈቅዶለታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ እናንተ መኝታ ክፍል ውስጥ ተመድቧል …” ንግግራቸውን ገታ አድርገው አዩኝ፡፡ ስሜቴን ለማንበብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዲኑ ዓይኖችም እንዲሁ ላዬ ላይ ይተራመሳሉ፡፡ አንገቴን ደፋሁ፡፡ አካሄዳቸው ገብቶኛል፡፡ ቀጠሉ፡- “…እ…ምን ነበር ያልኩት? …እ…አዎ እናም ደግሞ ያች እናቱ፣ ፍጹም ደግ ነበረች፤ ካፏ ነጥቃ ታጎርሳለች፤ ተጠምታ ታጠጣለች፤ ተርባ ታበላለች፤ እሷ መሬት ወርዳ እንግዳን አልጋ ላይ ታስተኛለች፡፡ የብቻ ነበር የሷስ ደግነት፡፡ እንደኔ ልፋት ቢሆን ይሄኔ ስንት ጥሪት ባየቆየን ነበር፡፡ እርሷ ግን ያመጣሁትን ሁሉ አንዳንዴ ለቤት እንኳ እስኪቸግረን ድረስ ታከፋፍለው ነበር፡፡ ቶማስ ታዲያ ከርሷ ብሶ ቁጭ አለ፡፡ ምኑም አይቀረው፡፡ ልብሱ፣ ጫማው፣ ለኪሱ የሚሰጠው ገንዘብ፣ ሁሉንም እናቱ ታደርግ እንደነበረው ተቸግሮ ላያቸው ያከፋፍላል … ታዲያ አሁን እኔ ብዙ ነገር ያስፈልጋልና ከአዲስ አበባ ገንዘብ ብልክለት አንዳችም አይጠቀምበትም፡፡ ይረጨዋል፡፡ ለዚህም ከጎኑ ሆኖ የሚረዳው ሰው ያስፈልገዋል፡፡

በዚህም በኩል ዲኑ ሊተባበሩኝ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ገንዘቡን በሳቸው ስም እልካለሁ …እ… ለትምህርት የሚያስፈልጉ መገልገያ መሳሪያዎች ሆኑ ሌሎች አላቂ የየዕለት መገልገያ ቁሳቁሶች የሚያጋዛው ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ እንደ አንተ ተማሪ የሆነ፣ ለተማሪ የሚያስፈልጉትን እቃዎች የሚያውቅ ሰው መሆን አለበት፤ እና በእነዚሀ ሁለት ጉዳዮች ላይ ብትተባበረኝ …እ” ብለው ድንገት ሳግ አፈናቸው፡፡ እንባቸውም ተከተለ፡፡ ነገሮች ግራ አጋቡኝ፡፡ መናገር አልቻልኩም፡፡ ፀጥታ፡፡ የለቅሶ ድምጽ፡፡ ፀጥታ፡፡ የመናገር ተራ ዲኑ ወሰዱ፡፡ የችግሩን ሁኔታ በገባቸው አቅጣጫ ነገሩኝ፡፡ ብተባበራቸው በትምህርቴም ሆነ በሌላ ልጎዳ እንደማልችል ሊያሳምኑኝ ሞከሩ፡፡ ካልፈለግሁ እና የማልችል ከመሰለኝ ግን አለመተባበር ሙሉ መብቴ እንደሆነ አስረዱኝ፡፡ ዝምታ ሰፈነ፡፡ በዚህ ቅጽበት አስቤ ፍቃደኛ ብሆን የሚከተለውን መዘዝ ወይም ፈቃደኛ ባልሆን የሚሰማኝን ፀፀት ማመዛዘን አልቻልኩም።

ፊት ካለው ክፍል የዲኑ ፀሐፊ ታይፕ ስትቀጠቅጥ ይሰማል፡፡ “ላግዝሽ? ታይፕ መምታት እችላለሁ፡፡” የቶማስ ድምጽ፡፡ ማሰብ አላስፈለገኝም፡፡ “እሺ፤ ልተባበራችሁ ዝግጁ ነኝ፡፡” አልኩ፡፡ አቶ ሙሉወርቅ ተንደርድረው በመምጣት አቀፉኝ፡፡ “እንግዲህ እኔም አንተን ቶማስን በማይበት ዐይኔ ነው የማይህ፤ ቃል ኪዳን ፈፀምን ማለት ነው፡፡” አሉኝ፡፡ እኚህ መከረኛ አባት ታዲያ ዛሬም ደውለው ነበር፡፡ ከአሳቤ ስመለስ ጐንበስ ብዬ አየሁት ቶማስን፡፡ አሻቅቦ ያየኛል፡፡ “እሺ አባትህም በሰቀቀን እንዲሞቱ ትሻለህ?!” የሞት ነገር ሲነሳ ስሜቱ በጣም እንደሚነካ አውቃለሁ፡፡ ያለሁበት ሁኔታ ግን ስሜቱን እንድጠብቅለት የሚያደርግ አልነበረም፡፡ የተደበላለቀ ስሜት ሰፍኖብኛል፡፡ ሐዘን፡፡ መታከት፡፡ ንዴት፡፡ ተስፋ መቁረጥ፡፡ ወደ ዶርም ስናመራ መንገድ ላይ እነ እስጢፋኖስን አገኘናቸው፡፡ እኛን ፍለጋ መውጣታቸው ነበር። ቶማስ በወፍራም አዲስ ጃኬት ፈንታ አዳፋ ጋቢ ለብሶ ሲያዩት ምን እንደተከሰተ ለመገመት ጊዜ አልወሰደባቸውም። ሁላቸውም ቃል እንኳን ሳይናገሩ ተያይዘን ወደ ዶርም ገባን፡፡ ብርድ ልብሳችንን ከአልጋችን ላይ አንስቼ አለበስኩት። መቼስ የኔ የምለው ነገር የለኝም፤ ሁሉ ነገር የኛ ሆኗል፤ ጊዜዬ እንኳን የኔ አይደለም፡፡

መኩሪያ እና አታክልቲ ቀኑን ሙሉ ከመጽሐፍ ጋር ሲታገሉ ስለዋሉ በተቀመጡት ማንቀላፋት ጀመሩ፡፡ እስጢፋኖስም ወፍራም ጉንጮቹ ተንጠልጥለዋል። ዐይኖቹ ደክመዋል፡፡ እየተነጫነጨ ራሱን ያካል፡፡ መኩሪያና አታክሊቲ ገፍቶ የመጣ እንቅልፋቸውን መቋቋም ስላልቻሉ ተኙ፡፡ ቶማስ፣ እስጢፋኖስ እና እኔ ብቻ ቀረን፡፡ ብዙም ሳይቆይ እስጢፋኖስ ማላዘን ጀመረ። እስካሁን ባለው ህይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ ሰዎች ከቶማስ እኩል የሚገርመኝ ሰው ቢኖር እስጢፋኖስ ነው፤ ምንም ነገር አያስደስተውም፤ ሁሌ ይነጫነጫል፡፡ በትምህርቱ ከማንም አያንስም፤ በኑሮውም ብዙ አይጐድለውም፤ ቤተሰቦቹ ከጅማ በየወሩ በቂ ብር ይልኩለታል፤ ግን ሁሌ እንዳላዘነ፣ እንደተነጫነጨ ነው የሚኖረው፡፡ ሲለው የኮሌጁ ምግብ አልተስማማኝም፤ የአገሩ አየር ፀባይ ጥሩ አይደለም፣ እከሌ የሚባል መምህራችን ደካማ ነው፣ ሴቶች አፍጠው ያዩኛል፣ የቤተሰብ ደብዳቤ ዘገየብኝ፣ እያለ እዬዬ ይላል፡፡ ሁሉም ነገር ሞትን ያስመኘዋል፡፡ “ሕይወት ዋጋ ቢስ ናት፣ ከመኖር አስር ጊዜ መሞት ይሻላል፡፡” የሚለው የዘወትር መነባንቡ ነው፡፡

በእርሱ የተነሳ ዶርማችን ውስጥ ሰላም ጠፍቷል። እርሱ መነጫነጭ ሲጀምር ቶማስ እያባበለው ያለቅሳል፡፡ እስጢፋኖስ ግን አይጽናናም፡፡ ቶማስ ሊረዳቸው ያልቻለ ሰዎች ቢኖሩ እስጢፋኖስ ዋነኛው ይሆናል፡፡ አሁንም መነጫነጭ ሲጀምር ቶማስ ማባበሉን ያዘ፡፡ “እስጢፍ ለምን አትረጋጋም? ሁሌ ለምን እንዲህ ትሆናለህ?!” “በዚህች ዓለም ውስጥ ምን መረጋጋት አለ? ይታይህ ቀን ከሌት ማጥናት ነው፤ ለአስራ ስንት ዓመት ፍዳ ማየት፤ መሰቃየት፤ ከዚህ ሁሉ ታድያ ሞቶ መገላገል አይሻልም?!” ጠረጴዛውን በቡጢ ደለቀው፤ እና የሚወደውን የመጽሐፈ መክበብ ጥቅሶች አዥጐደጐዳቸው፤ መጽሐፈ መክበብን በቀን ቢያንስ አንዴ ሳያነብ አይውልም፤ ሙሉ መጽሐፉን በቃሉ ሸምድዷል፡፡ “….ከፀሐይም በታች የተሰራው ሥራ ሁሉ ከብዶኛልና ህይወትን ጠላሁ፤ ሁሉም ከንቱ ንፋስንም እንደመከተል ነው…ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ ሃሳብ የሰው ጥቅም ምንድነው? ዘመኑ ሁሉ ሀዘንና ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው…አሁንም ቢሆን ከኛ ይልቅ የሞቱት ከነሱም ደግሞ ገና ያልተፈጠሩት ይሻላሉ…ፈተና፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መባዘን፣…ከንቱ ነው፤ ሁሉ ነገር…” ቀባጠረ የራሱንም እያከለ፡፡ በቃ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ነገር ነው የሚያስመርረው፤ ሞት የሚያስመኘው፡፡ ቶማስ ብዙም አልገፋም፡፡ የእስጢፋኖስ ጭንቀት አስጨነቀው፡፡ ሊያለቃቅስ ጀመረ፡፡ እስጢፋኖስ ደግሞ ካለ ነገሩ ለሰው ግድ የለውም፡፡ ቶማስ ሰውን መርዳት ሲያቅተው ምን ያህል እንደሚጨነቅ፣ ምን ያህል መንፈሱ እንደሚረበሽ አውቃለሁ፡፡ ደግነቱ እስጢፋኖስ ወዲያውኑ ተነስቶ ተኛ፡፡ እኔም አካሌ ዝሎ ስለነበር ጋደም አልኩ፡፡

እንቅልፍ ሊወስደኝ አካባቢ ቶማስ ነቅነቅ አድርጐ ቀሰቀሰኝና ጠጋ ብሎ በጆሮዬ “እስጢፎን የምረዳበትን ዘዴ ሳስብ ነበር፤ አሁን አገኘሁ፡፡” አለኝ፡፡ አየት አድርጌው ፊቴን አዙሬ ተኛሁ፡፡ ጠጋ ብሎ አቀፈኝ፡፡ ጠዋት አንድ ሰዓት ግድም ዶርማችን ውስጥ ትርምስ ሰምቼ ነቃሁ። ቶማስ አጠገቤ የለም፡፡ አትክልቲና መኩሪያ ዶርማችንን ያምሱታል፡፡ ዘልዬ ተነሳሁ፡፡ ምን እንደሆኑ ብጠይቅ የሚመልስልኝ ጠፋ፡፡ ኋላ መኩሪያ በጣቱ ወደ እስጢፋኖስ አልጋ ጠቆመኝ፡፡ ተንደርድሬ ሄድኩ፡፡ እስጢፋኖስ ዓይኖቹ ተገለባብጠው አልጋው ላይ ተዘርሯል፡፡ “ምን?!” ብዬ ጮህኩ፡፡ ለጥንቃቄው ደንታ አልነበረኝም፡፡ አቅፌ ነቀነቅሁት፡፡ ዝም፡፡ ሰውነቱን ዳበስኩት፤ ይቀዘቅዛል፡፡ ደረቱ ላይ እጄን ጫንኩ፤ ምንም፡፡ ሰውነቴ መንዘፍዘፍ ያዘ፡፡ ቀድሞ የነቃ ሌላውን የመቀስቀስ ልማድ ስለአለ ከእንቅልፉ ሊቀሰቅሱት ሲሉ ነበር እንዲያ ሆኖ ያገኙት፤ ሞቶ። አትክልቲ ፊቱ ገርጥቶ ባለበት ሐውልት መስሎ ተገትሯል፡፡ ከንፈሮቹ ደርቀዋል፡፡ መኩሪያም ምንም አይናገርም፡፡ ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ይዞ፣ አፉን በሰፊው ከፍቶ ቆሟል፡፡

“ሰዎች እርዳታ እንጥራ እንጂ፡፡ ተንቀሳቀሱ።” እያልኩ በባዶ እግሬ ወጥቼ ሮጥኩ፡፡ ወዴት እንደምሄድ ግን አላውቅም፤ኋላ ነው መንገድ ቀይሬ ወደ ዲኑ ቢሮ ያመራሁት፡፡ እዚያ ስደርስ ቶማስ በር ላይ ቆሞ አገኘሁት፡፡ እርሱም እንደኔው ሁኔታውን ሊነግር እንደመጣ ገባኝ፡፡ “ዲኑ አልገቡም?” አልኩት፡፡ ጥያቄዬን ችላ ብሎ “አየህ ምንተስኖት እስጢፋኖስ በጣም ነበር የሚያሳዝነኝ፤ ልረዳው ባለመቻሌ ዘወትር እንደተጨነቅሁ ነበር፡፡ የተቸገረ ጓደኛን መርዳት አለመቻል በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ አስቤ እንደደረስኩበት ደግሞ ከዚህ የተሻለ እስጢፋኖስን የምንረዳበት መንገድ የለም፤ እና…” አላስጨረስኩትም፡፡ እጄ ቡጢ ሆኖ ሲወናጨፍ ይታወቀኛል፡፡ አጓርቶ ወደ ኋላ ተዘረረ፡፡ ደነዘዝኩኝ፡፡ ባለሁበት ቆሜ ቀረሁኝ፡፡ እንደምንም ከወደቀበት ተነሳ፡፡ “አንተምኮ ታሳዝነኝ ነበር፡፡” አለኝ ፈገግ እንደማለት ብሎ፡፡ ሲናገር ጥርሶቹ በምላሱ እየተገፉ ወደቁ፤ ባዶ ድድ፡፡ ጭንቅላቴን ይዤ መጮህ ጀመርኩ፡፡ እንባዬ ጅረት ሆኖ ፈሰሰ፡፡ በዚህ መሃል አእምሮዬ ውስጥ አንድ ነገር ፈነዳ፡፡ “ለእናቱም ያዝንላቸው ነበር ማለት ነው?” ከዚህ በኋላ ማሰብ አልቻልኩም፡፡ ጨለማ ሆነ፡፡ ፀጥታ ሆነ፡፡ (ውድ አንባቢያን- ከዚህ በላይ የቀረበው ታሪክ በድጋሚ የወጣ ነው)

Read 4117 times
Administrator

Latest from Administrator