Saturday, 29 June 2013 10:56

በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” የሚወዳደረው በአምላክ ለአገሩ ያለውን ፍቅር እየገለፀ ነው ተባለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

              በዘንድሮ የ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” አብሮ የመኖር ውድድር፣ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ወሲብ በመፈፀም አነጋጋሪ ሆና የሰነበተችው ኢትዮጵያዊቷ ቤቲ ከውድድሩ ተሰናበተች፡፡ ውድድሩ ከተጀመረ አራተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን እስካሁን ቤቲን ጨምሮ ስድስት ተባርረው 20 ተፎካካሪዎች ቀርተዋል፡፡ ከእነሱም መካከል ሌላው ኢትዮጵያዊ በአምላክ ተስፋዬ (ቢምፕ) ይገኝበታል፡፡ ቢምፕ ለውድድሩ የሄደው አገሩን ስለሚወድና በተገኘው አጋጣሚ ስለ ኢትዮጵያዊነቱ ለመግለፅ ነው ያሉት እናቱ ወይዘሮ ደብሪቱ ሰለሞን፤ ባለፈው አንድ ወር በነበረው ቆይታ ይህንኑ ፍላጎቱን ሲያንፀባርቅ መቆየቱን ተከታትያለሁ ብለዋል፡፡ ‹‹ልጄ የአገር ፍቅር ስላለው በቢግ ብራዘር አፍሪካ ውድድር ፍቅሩን ለመግለፅ እድል አግኝቷል፡፡ ባንዲራው አብሮት ነው፡፡ ሁልጊዜም በሚለብሰው ካኒተራ ወይ ኮፍያ አሊያም በእጁ ላይ የአገሩ ባንዲራን ትቶ አያውቅም፡፡

የሚኖርበት መኝታ ቤቱ እንኳን በባንዲራ ያጌጠ ነው›› በማለት እናቱ ወይዘሮ ደብሪቱ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ልጃቸው በአኗኗሩ እያሳየ ያለው ባህርይ ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገበት ስብእናው እንደሆነ የገለፁት እናቱ፤ ባለፉት አራት የውድድር ሳምንታት እንዲባረር አንድ ድምፅ ብቻ እንደተሰጠበት ገልፀው፤ የውድድሩን ውጣውረድ በመቋቋም ሳይሰላችና ለሌሎች ተወዳዳሪዎች እንክብካቤ ሳይነፍግ እስከመጨረሻው ምእራፍ ሊዘልቅና ሊያሸንፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ውድድር የኢትዮጵያውያን መሳተፍ ጠቀሜታ አለው የሚሉት ወይዘሮ ደብሪቱ፤ ውድድሩ የአገርን ባህል ለማስተዋወቅ እና ገፅታ ለመገንባት ሁነኛ መድረክ መሆኑን አስረድተው፤ ልጃቸው አብረውት ከሚኖሩት ተወዳዳሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡለት እሱም ስለ ባህሏ ፤ስለ ታሪኳ፤ የሰው ዘር መገኛ ስለመሆኗ፣ ስለ ቡና፤ ስለእንጀራውና ስለሽሮው ሳይሰለች ሲያስረዳ ተመልክተነዋል ብለዋል፡፡ ከውድድሩ በወጣች ማግስት አስተያየት የሰጠችው ቤቲ ስላሳለፈችው ጊዜ ስትናገር ቤቱን ለቅቆ መውጣት ከባድ ነው፡፡

ቦልት እና እኔ ጥሩ ወዳጆች ነበርን፡፡ ከውድድሩም በኋላ በወዳጅነት እንደምንቀጥል እርግጠኛ ነኝ” ብላለች፡፡ በውድድሩ ላይ እስከ መጨረሻው እዘልቃለሁ ብዬ አስብ ነበር ያለችው ቤቲ በውድድሩ፤ ምርጥ ተሳትፎ እንደነበራት፤ በዚህም መኩራቷን እንደተናገረች “ስዌታን” የተባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ቤቲ “ዘ ቼዝ” የሚል ልዩ ስም በተሰጠው የዘንድሮ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” አብሮ የመኖር ውድድር ገና በመጀመርያው ሳምንት ቦልት ከተባለው ሴራሊዮናዊ ተወዳዳሪ ጋር በፈፀመችው ወሲብ ትኩረት ስባ ስታወዛግብ ቆይታለች፡፡ በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” የስምንት አመት ታሪክ በቀጥታ ስርጭት የታየ ወሲብ ሲፈፀም የቤቲ እና የቦልት የመጀመርያው ነበር፡፡ ቤቲ ለአገሯ ባህልና ወግ ክብር አልሰጠችም በሚል በማህራዊ ድረገፆች እና በብሎግ መድረኮች ላይ ስትብጠለጠል መሰንበቷም ይታወቃል፡፡ ቤቲ በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ኢትዮጵያን አትወክልም በሚል ለተቃውሞ በተከፈተ የፌስ ቡክ ድረገፅ ላይም በአገር ውስጥ እና በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባታል፡፡

የቤቲ ከውድድሩ ድንገት መባረር ፍቅረኛዋ ሆኖ ለሰነበተው ሴራሊዮናዊ ቦልት መርዶ እንደሆነበት ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡ ስንብቷን ባረጋገጠችበት ምሽት ሁለቱም በሃዘኔታ ተውጠው ሲተቃቀፉ እና ሲሳሳሙ መታየታቸውንም እነዚሁ ዘገባዎች አውስተዋል፡፡ ቦልት ምስጢረኛው፤ የልብ ወዳጁ እና ፍቅረኛውን ቤቲ በማጣቱ ብቸኝነት እንደሚያስቸግረውና እሱም ቢሆን በውድድሩ የማሸነፍ እድሉ የጠበበ እንደሆነ “ዘ ስታንዳርድ ዲጂታል ኒውስ” ጽፏል፡፡ ለሴራሊዮናዊው ቦልት ከዚህ በኋላ የሚኖረው የ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ቆይታ ማራኪ እንደማይሆን እየተነገረ ሲሆን ፋቲማ ከተባለች ማሊያዊት ጋር የጀመረው ግንኙነት መፅናኛው ሊሆን እንደሚችልም ከወዲሁ ተተንብይዋል፡፡

Read 5949 times