Saturday, 29 June 2013 10:28

የበረከት “የመንፈስ ከፍታ”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት በሣሉ ብዕረኛ ተፈሪ መኮንን “ግጥም ሞቷል” ሲል በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ መርዶ በማርዳት ቁጣዬ የበረታ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከፀሐፊው ጋር የስልክ ሙግት መግጠሜም አልቀረም፡፡ ውሎ ሲያድር ግን የጥበቡን ሰማይ ሳይ ከዋክብት እየነጠፉ፣ ውበት እየጨለመ ሲመጣ ልቤ ደረቴን በስጋት መደብደብ ጀምራ ነበር፡፡ ያ ሥጋትም ስለግጥም ይበልጥ ማሰብ፣ ከዚያም አለፍ ሲል እያነበቡ ሃሳብ ወደማቅረብ የገፋኝ ይመስለኛል እንደተፈራው፡፡ የግጥሙ ሰፈር ልክ የሌላቸው ገለባዎች መፈንጫም መሆኑ አልቀረም፡፡ ነፍስ የሌላቸው ገለባዎች እንደፈርጥ የሚንቦገቦጉትን የብዕር ውበቶች እንዳያንቁ ብዙዎቻችን ሠግተናል። አዝነን አንገታችንንም ደፍተናል፡፡ ግና አሁን አሁን ሰማዩን ሳየው ተስፋ ያረገዘ፣ ውበት ያነገተ ይመስላል፤ ብዙ ገላባዎች ቢኖሩም ፍሬ ያላቸው ወጣት ገጣሚያን መጋረጃውን ገልጠው ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡

ወጣትነት ሙሉነት የሚጠበቅበት ዕድሜ አይደለም፡፡ ወደ ሙሉነት የመድረሻ ጉዞ ፍንጭ እንጂ፡፡ የቀደሙትና ብርቱ የሚባሉት ገጣሚያንም መንገድ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ አሁን የዘመናችን ወጣት ገጣሚያን መንገድ ጥሩ ተስፋ እየሰጠ ነው፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ለጥበቡ ውበት፣ መሥመር እያበጁ፣ ሕይወት እያፈሩ መምጣታቸው አይቀሬ ነውና ልብ የሚሞላ ጉጉት ፈጥሯል፡፡ እውነት ለመናገር የቀደመው ዘመን አፍርቷል ከምንላቸው ገጣሚያን የማያንሱ ገጣሚያን ቁጥርም እየፈጠርን ይመስለኛል፡፡ አሁን የሚያስፈልገን የንባብ ባህል ይበልጥ እንዲጨምር በማድረግ እምቡጦቹ አብበውና አፍርተው፣ ጐደሎዎቻችንን እንዲሞሉ ማስቻል ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ የታተሙ የግጥም መጻሕፍትን ሳይ የተሰማኝ ስሜት ያ ነው፡፡ ተስፋ ያንለጠለጠለ በሣቅ የታጀበ፡፡ ዛሬ ያየነው ተስፋ ነገ በውበት የደመቁ ዓመታት እንደሚወልዱልን አያጠራጥርም፡፡

ቀደም ሲል በዮሐንስ ሞላ መጽሐፍ ላይ የደመቀ ተስፋ እንዳየሁ ሁሉ የወሎው ገጣሚ መንግስቱ ዘገየም ደስ በሚል ልብና ኃይል ተገልጦ አይቼዋለሁ፡፡ ጋዜጠኛ በረከት በላይነህም “የመንፈስ ከፍታ” በሚለው ጥራዙ የፋርስ ግጥሞችን መርጦ በመተርጐምና የራሱን ግጥሞች በማቅረብ የጥበብ ሆዳችንን ረሃብ ለማስታገስ የሚችል አበርክቶት አኑረዋል፡፡ ደስ ይላል፡፡ የበረከት ግጥሞችን በጥልቀት የመገምገምና የመተንተኑን ሥራ ላቆየውና ለጊዜው ቀልቤን የኮረኮሩትን ግጥሞች ልዳስስ መርጫለሁ፡፡ “የፈሪዎቹ ጥግ” ስሜቴን ከዳሳሱት፣ ሃሳቤን ከነጠቁት ግጥሞቹ አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል:- በማያውቀው ስንዝር ዕድሜው እንዳይለካ፤ ባልቀመሰው እርሾ ነገው እንዳይቦካ፤ ይፈራል የሰው ልጅ፤ ይሰጋል የሰው ልጅ አይጨብጥ አይነካ፡፡ አይገርምም! መሸጥ አያሰጋው፣ መግዛት እየፈራ፣ “አለመወሰኑን” ትርፍ ብሎ ጠራ፡፡ እኔ የምለው! ቀኝ ግራ ኋላ፣ ፊት - እስካልተከለለ፤ በጥግ - የለሽ ነገር መሃል መስፈር አለ? ይህ ምስኪን ወገኔ! ላበጀው ጥያቄ እስካልተፈተሸ፤ ቅዠት አቅፎ ያድራል - ሕልሙን እየሸሸ፡፡ ገጣሚው በረከት ተናግሮታል ብዬ የማደምቀው ሃሳብ፣ ሰው ነገር የሚያይበት ተጨባጭ ራዕይ፣ የሚጓዝበትን መንገድ የሚያስተውልበት አይን አጥቶ፣ በሰከረ ዓይን የሚዋዥቅ ሆኗል የሚለውን ይመስላል፡፡ ሁሉ አማረሽ በመሆኑ ወደፊት ፈቅ የሚልበትን ምርጫ እንደ ጨርቅ አውልቆ ጥሏል።

መላ ቅጡ በጠፋ ስካር ውስጥ ተዘፍቆ ትክክለኛ አድራሻውን የሚያሳየውን ሕልሙን ወደ ኋላ ዘንግቷል ነው የሚለው፡፡ ሕልም የሌለውና ሕልሙን የሸሸ ሰው መድረሻው የት እንደሚሆን ሊሰብከን አልሞከረም፡፡ የወደደ ሰው ወደ መጽሐፍ ቅዱሱ ዮሴፍ፣ ወዲህ ቀረብ ሲል ደግሞ ወደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ተጠግቶ “ሕልም አለኝ” የምትለውን ሃሳብ መፈልፈል አለበት፡፡ ለዚያም መሰለኝ “ይህ ምስኪን” ብሎ ለሕልም አልባው ሰው ከንፈር የመጠጠለት! “ሸማኔ ሲፎርሽ” ለኔ ከተመቹኝ ግጥሞች አንዱ ነው፡፡ “ታታሪው” ሸማኔ! ከመመሳሰል ውስጥ ውበትን ቀምሮ፤ “ጥበብ” ያለብስናል ካንድ ቀለም ነክሮ፡፡ ለባሾች አይደለን? እንተያያለን፤ እንተያያለን፤ ኤዲያ!! ጥለቱ ጋ ስንደርስ እንለያያለን፡፡ መቼም አይታክተን! እንወርዳለን ቆላ፤ እንወጣለን ደጋ፤ ጥለት አመሳሳይ ሸማኔ ፍለጋ እዚህ ግጥም ውስጥ ዋነኛው ተዋናይ ሸማኔ ነው፡፡ በእማሬያዊ ፍቺው ምናልባት ሸማኔው ብዙ ሲሆን፤ በብዙ ሊተነተን ይቻላል፡፡

በርግጥም ስለግጥም የፃፉ ምሁራን እንደሚሉት ግጥም ራቁቱን የተሰጣ ባይሆን ይመረጣል፡፡ ለአንባቢው አዲስ ቃና፣ ፍልፍል ውበት ቢያበቅል ደስ ይላል፡፡ እንደግጥሙ ሆኖልን ጥለት ውበት በመሆኑ ሸማኔ ፍለጋ ላይ ታች ካልን ይገርማል፡፡ ደስ የማይለው ግን ለማመሳሰል መሆኑ ነው፡፡ ከመመሳሰል መለያየት ሳይሻል አይቀርም፡፡ እንኳን ጥበብ ሰው ራሱ ቢመሳሰል ሕይወት ትሠለቻለች፤ ተስፋ ትርቃለች። ቀለምም አያምርም፡፡ ዜማም ይጠነዛል፡፡ በረከት ያለው የትኛው መመሳሰል እንደሆነ ስላላወቅን የየራሳችንን መጠርጠር እንጂ የየልባችንን መደምደሚያ ቀዳዳ የለንም፡፡ ቢሆንም እንዲህ ወዲያ ወዲህ መባዘንም ጥሩ ነው፡፡ መመርመር ክፋት የለውም፡፡ የበረከት “የመንፈስ ከፍታ” የፋርሶቹን ግጥሞችም ይዟል፡፡ ለዛሬ ላስቃኛችሁ የወደድኩት ግን የራሱን የበረከትን ስለሆነ አልነካውም እንጂ እጅግ ያደነቅሁለት ምርጥ ግጥሞችን አስሶ መተርጐሙ ነው፡፡ አሁን ግን ወደ በረከት “ልዩነት” ተመልሼ በመሄድ ጥቂት እላለሁ፡፡

ብዙዎች አንደበቱ ባይጥም፤ ለጆሮ ባይመች ትምህርት አሰጣጡ “ኤዲያ” የጋን ውስጥ መብራት በማለት አድመው ካዳራሹ ወጡ፡፡ ጥቂቶች የመምህሩ ዕውቀት፤ “የጋን ውስጥ መብራት” መሆኑን ያመኑ፤ አምነው የተግባቡ አዳራሹን ትተው “ወደ ጋኑ” ገቡ፡፡ እዚህ ግጥም ውስጥ አንድ መምህር ጐልቶ ይታያል፤ ማስረዳት የማይችል፤ ለሌሎች ዕውቀቱን ማካፈል ያልታደለ፡፡ ቅላፄው ለጆሮ የማይጥም። በዚህ ምክንያት የክፍሉ ተማሪዎች ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ አንዱ ወገን እዚህ ሰውዬ ዘንድ ተቀምጦ ጊዜ ከማቃጠል አዳራሹን ለቅቆ መሄድ ይሻላል በሚል መምህሩን ንቆ ትቶት ወጥቷል፡፡ ሌላኛው ወገን ደግሞ መምህሩ ቀሽም በመሆኑ ተስማምቷል፤ ሃሳቡን ለሌሎች ማካፈል የማይችል የጋን ውስጥ መብራት በሚለው ተግባብቷል፤ ስለዚህም በተመሳሳይ አዳራሹን ትተው ወጥተዋል። ግን የውስጡን እሣትና ብርሃን ፍለጋ ጋኑን መፈልፈል ይዘዋል፡፡ የጋኑን መብራት ያነቀው ምንድነው የሚል ፍለጋ ይመስላል፡፡

ተስፋ የቆረጠና ተስፋውን ያልጣለ ወገን ለየቅል ቆመዋል፡፡ መምህሩ የተደበቀ ሕይወት፣ መንገድ ያጣ ውበት ቋጥሯል። ግን መንገድ የለውም፤ ጋን ውስጥ ገብቶ ከጋን ውስጥ እሣቱን ማውጣት ይቻል ይሆን…ቢሆንም የበረከት ከፊል ገፀ ባህርያት ወደ ጋኑ ገብተዋል። አዳራሹ ውስጥ መምህሩ ሻማ መሆን ካልቻለ መምህሩ ውስጥ ያለውን ሻማ ፍለጋ መዳከር ሊጀምሩ ይሆን? ማን ያውቃል? “ኑሮና ጣዕም” ሌላው የበረከት በረከት ነው፡፡ ሙያዬን ታውቃለህ፤ ማጀቴን ታያለህ፤ “እንጀራሽ እንክርዳድ፣ ገበታሽ ጣዕም - አልባ” ለምን ትለኛለህ በል ዝም ብለህ ብላ ቸርቻሪ መንግስታት፣ ሰነፍ ገበሬዎች፤ በዝባዥ ነጋዴዎች፣ በበዙባት ዓለም፤ ጠንካራ ጥርስ እንጂ ቀማሽ ምላስ የለም ሕይወትን አትመራመር፣ አታጣጥም…ዓለም በስግብግቦች ተሞልታለች፡፡

ቀልብ ያለው የለም፤ የሰው ጆሮ ሣንቲም ሲያቃጭል ከመደንበር ያለፈ ማጣጣም አቅቶታል ስለዚህ አቃቂር ለማውጣት አትሞክር! ይልቅ እዚህ ውበት ስትፈለፍል፤ ቃና ስታጣጥም ከሩጫው እንዳትቀር ዓለም ውበቷን ጥላለች፡፡ ሰውየው ብቻህን አትበድ…!ሁሉም ነገር ተናካሽ ጥርስ እንጂ አጣጣሚ ምላስ አጥፍቷል፡፡ ሰውየው አትጃጃል ባይ ትመስላለች፡፡ ጠቅለል ሲል በረከት፤ በቃላቱ ሃይል አያስደነግጥም፤ በዜማ ሽባነት ግራ አያገባም፡፡ ቀለል አድርጐ ስንኝ መቋጠር ይችላል፡፡ ግጥም ቀዳሚ ተግባሩ ደስታ መፈንጠቅ ነው - የሚለውን የበርካታ ምሁራን ሃሳብ ይዞ የሚቀጥል ይመስላል። ወደፊት ደግሞ የተሻለ ችቦ ከመንገዱ ሲንቦገቦግ ይታየኛል፡፡ ተስፋው ሩቅ፣ ዕድሜው ለጋ ነው….የወጣትነቱ እፍታ ጥሩ ነው፡፡ የፋርስ ግጥሞቹ ምርጫና ስልት ደግሞ ልዩ ነው፡፡

Read 2537 times