Saturday, 29 June 2013 10:27

ሰማይ ምድር ላይ ቢበቅልም አያድግም

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

(N.B The Issue “Art for Arts sake” arises when the Individual` is at odds with society) “በፈጣሪ የተሰራን፣ ነገር ግን ያልተሳካን፣ ብልሹ ንድፎቹ ነን” ይላል ፖስት ኢምፕሬሽኒስቱ ቫንጐ፡፡ ይቀጥልናም “አበላሽቶ ስለነደፈን ግን ልንፈርድበት አይገባም” ይህ አባባሉ፤ ለእኔ ፍለጋ መልስ መሆን ቢኖርበትም፤ ከመልስ ይልቅ ጥያቄ የሚያበጅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ጥያቄው ወይንም ጥያቄዎቹ ጥበብን ለምን እንፈጥራለን? የሚለውን የከረመ ጥያቄ በድጋሚ የሚያጠነክሩ ናቸው፡፡ ለምንድነው የምንፈጥረው? ከተባለ፤ ብልሹውን ንድፍ ለማደስ ነው፤ በአጭሩ፡፡ …በአጭሩ በተሰጠው መልስ ላይ ግን ረጃጅም ጥያቄዎች ይፈለፈላሉ፡፡ እስቲ ጥያቄዎቹን አብረን እንታቀፋቸው፡፡ ውበትን ለውበትነቱ ወይንም ለእውነትነቱ… አሊያም ለሚሰጠን የህይወት አገልግሎት ስንል እንፈጥረዋለን፡፡ አያከራክረንም፡፡

ከፈጠርነው በኋላስ?... የእግዜርን የተበላሸ ንድፍ ለማሻሻል ብለን የሰራነው የአርትኦት ንድፍ የተበላሸ አለመሆኑን ወይንም ቢሆን እንዴት ነው የምናውቀው? …ውበት ማለት ፍፁምነት ከሆነ፤ የፍፁምነት አቅጣጫ ወደ ሰማይ ነው? ወይንስ ወደ ምድር? ለእግራችን ጫማ የሰራልን እና ከጋሬጣ እና ከእንቅፋት የገላገለን ነው አርቲስታችን? ወይንስ ከህይወት እና ከሰው ተፈጥሮአዊ ማንነታችን በምናብ አንሳፎ ሰማይ የከተተንን ነው ፈጣሪ ብለን የምንጠራው? ሰው ወደ ሰው ነው የሚቀርበው ወይንስ ወደ የሰማዩ ፈጣሪ? …ወደ ፈጣሪ ካላችሁስ በየትኛው የተፈጥሮ ክፍሉ? …በስጋ እና አካሉ ወይንስ በሀሳብ እና በመንፈሱ? ለመንፈስ ጫማ ከሚሰራው ጠቢብ… እግር እና መሬቱን በጫማ ከሚያስማማው በምን እንደበለጠ እንዴት እናውቃለን? አርቲስቱ ቄስ ነው? ከሆነ ሰውን ወደ ሰው ነው ወይንስ ወደ ፈጣሪ የሚያቀርበው? Is he the ventriloquist of God; or the ventriloquist of his follow humans? ወይንስ ለማንም ቄስ አይሆንም… ለራሱም ጭምር? ጥበብ አሁን ካልኩት ወይንም እስካሁን ከምናውቀው የተለየ አላማ አለው? ሊኖረውስ ይገባል?... እነዚህ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሳንሞክር፣ የጥበብ የውበትን ሚዛን ልንለካ… የለካንበትንም ምክኒያት ልናውቀው አንችልም፡፡

“ቅድመ ሥነ-ውበት” ብለን ልንጠራቸው የምንገደድ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹን ሳንመልስ የውበትን ደረጃ ማውጣት ባንችልም፤ በየዕለቱ ግን… የተለያዩ ፈጠራዎችን መዝነን አፋዊ ወይንም ፅሁፋዊ ሂስ እንሰጣለን፡፡ የእንትና ግጥም ምርጥ ነው፣ የእንቶኔ ሙዚቃ ትንፋሽ ያሳጥራል… ወዘተ እንባባላለን፡፡ እንዴት ለካነው?፤ እንዴት ነካን… የቱ ጋ? …የበለጠ እንዲነካን ምን መጨመር ነበረበት? መንካት መቻሉ ውበት መሆኑን አረጋጋጭ ነው? ማነው መቶ ፐርሰንት ውበትን የጨበጠ አርቲስት? ወይንም ስንት ናቸው? ለምን መቶ ፐርሰንት ብቻ ጣራው ሆነ… አንድ ሺ ፐርሰንት እንዳይሆን ማን ያዘው? እድሜአችን?… ሰውኛ መጠን? በተመጠነ መጠናችን ውስጥ መጠን የለሹን እንዴት አወቅነው? እግዜር ጥበበኛ ሆኖ እኛን ከሆነ የፈጠረን፤ እኛ መበላሸታችንን ያወቅነው ከምን አንፃር ነው? እኛ የፈጠርናቸው ድርሰቶች ከእኛ ከፈጣሪዎቻቸው አንፃር ራሳቸውን ተመልክተው ተበላሽተናል ይሉ ይሆን?... ከነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች አንፃር ውበት የቱ ጋ ነው የሚገኘው?

                                                      * * *

እንደ ጀርመናዊው ሃሳባዊ ሄግል እይታ (Preromonology) ማህበረሰብ ሲስማማ፤ ወይንም ባልተቃረነ ማህበረሰብ ውስጥ ጥበብ አይፈጠርም ይላል፡፡ “Beauty will be lived no longer imagined” ተፈጥሮ እና እውነታ በማህበረሰቡ አእምሮ ውስጥ እና ጋር ግጭት ስለሌላቸው እንቆቅልሽን አይፈጥሩም፡፡ የተፈታ እንቆቅልሽ አዲስ ፍቺ አይፈልግም፡፡ የማህበረሰቡ ትዝታ፣ ህመም፣ አላማ፣ እና ራዕይ አንድ ስለሚሆን ቅራኔ አይኖርም፡፡ ውበቱም፣ እውነቱም አንድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ፈጠራ እና ጥበብ አይኖርም፡፡ የፈጠራ እና የጥበብ አለመኖር አመልካች የሆነው አንድን ነገር ነው፡፡ ግለሰብ የሚባል የተነጠለ ህዋስ መጥፋቱን። ግለሰብ ሲኖር፤ ከማህበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል፣ አሊያም ማህበረሰቡን ወደ እሱ ማንነት ለመቀየር ቅራኔ ይፈጥራል፡፡ ጥበብ የቅራኔው መገለጫ ነው። ቅራኔው እንቆቅልሽ ተብሎ ይጠራል፡፡ በግለሰብ እና በማህበረሰብ መሀል የሰማይ እና የምድር ያህል ልዩነት አለ፡፡ በእኔ እይታ፣ መሬት እና ሰማይ ማህበረሰብን እና ግለሰብን ለመግለፅ የምንጠቀምባቸው ልኮች ናቸው፡፡ ብዛትን ገላጭ ናቸው፡፡ ውበትን ወይንም እውነትን ሳይሆን የቁጥር ብዛትን ይወክላሉ። በብዛት ያነሰው ሰማይ ነው፡፡ ከሼክስፒር እና ከጫማ ጠጋኙ ማነው በቁጥር ብዛት የሚበልጥ ካላችሁኝ መልሱ፤ ጫማ ጠጋኙ ነው፡፡ ጫማ ጠጋኙ መሬት ነው፡፡

ሼክስፒር ሰማይ ነው፡፡ (ሰማይ ስል ከፍታ፣ እግዜር፣ ምርጥ፣ ብርሃን፣ መንግስተ ሰማይ … ወዘተ የሚሉትን ባህሪ ገላጭ እይታዎችን ወደ ጐን እንድታደርጉ በትህትና እጠይቃለሁ) ሼክስፒር ጥቂት (አሊያም አንድ) ጫማ ጠጋኙ ብዙ ነው፡፡ ፒሳሬቭ የሚባል የሩሲያ አልቦአዊ (nihilist) “I would rather be a Russian shoemaker than a Russian Raphel” ይላል። ጫማ የሚሰራልኝን እንጂ የማልገለገልበትን ውበት የሚጠበብብኝ አርቲስት (እንደ ራፋኤል) አያስፈልገኝም ማለቱ ነው፡፡ ወደ ምድር ነው። ወደ ሰው ልጅ፡፡ የሰው ልጅን አካል ከብርድ ከከለልን እና የማህበረሰቡን እግር በጫማ ከሸፈንን ለመንፈስ ብርድ አንጨነቅ፤ ሰው መሆናችንን አንድ ላይ ካመንን ውበቱ ይኸው ነው፤ እንደማለት ነው፡፡ ለምድር፤ የሰማይ ጥበብ አያስፈልግም፡፡ ምድርን በመሰለ ቁጥር ውበትና እውነት ነው፡፡ በቂው ነው። ከዚህ በተቃራኒ፤ ግለሰብነት በበዛበት አለም ደግሞ ሼክስፒር ይፈለጋል፤ ውበት ነው፡፡

ጫማ ሰሪው ከሚገንንበት አለም የግለሰቡ ሃሳብ ከሚቆለጳጰስበት አለም የራቀ ነው፡፡ የሼክስፒር “ሰማይ የሚወደስበት እና የጫማ ሰሪው ምድር የምትወደስበት ዘመኖችም የተለያዩ ናቸው፡፡ ኒቼ (In “the birth of tragedy…”) ምድር እና ሰማይን ለማቀላቀል ሞክሮ ነበር፡፡ ምድር እና ሰማይን ለማቀላቀል በሁለት አፍ ማውራት አስፈልጐት ነበር፡፡ አንደኛው አፍ ወደ “Dionysian ሌላኛው ወደ Apollonian” አፖሎናዊ:- ወደ ግለሰብ የሚያደላ፣ በግለሰብነቱ ምክኒያት ወደ ሰው ልጅ ከሚቀርበው ይልቅ ወደ እውቀት፣ መንፈስ ከፍታ የራቀ…. ፍፁምነት ወደ ሰው በመቅረብ ሳይሆን ወደ እውቀት፣ እና የሀሳብ መራቀቅ አስጠግቶ፣ አካልን ረስቶ ለመንፈስ እና የጭንቅላት አቅም የሚያደላ አድርጐ ይገልፀዋል፡፡ “አይዲያሊዝም” ልንለው እንችላለን፡፡ ዳይኖኤዥያን:- ምድራዊ፣ ለእንስሳ አለም የወሲብ እና ጭካኔ ተፈጥሮው የቀረበ፣ እውነታ በግለሰብ አእምሮ ሳይሆን በማህበረሰብ የሚፈታ በተፈጥሮ ትስስር እና አንድነት (Primordial Unity) የሚገለፅ መሆኑን የሚያምኑ ናቸው፡፡

በእግር ኳስ ሜዳ ወይንም በዘፈን ጭፈራ አንድ ሆነው የሚሰባሰቡ “In which everyone feels himself not only united, reconciled, and fused with his neighbor, but as one with him” (እዚህ ጋር ራሴ እምነት እንድደፍር ይፈቀድልኝ፡- የእግር ኳስ ውጤታችን ጥሩ እንዲሆን፤ የግጥም ውጤታችን አፈር ድሜ መብላት አለበት) በእዚህ ሁለትዮሽ ድብልቅ (እንደ ኒቼ አገላለፅ) የሰው ልጅ በአካሉ (ማህበረሰብ) እና በግለሰቡ (ሀሳቡ) መሀል ሳይበጠስ አንድ ላይ ተሳስሮ ማስቀመጥ ይቻላል፤ ባይ ነው፡፡ በኒቼ እምነት ዳይኖስየስን (ማህበረሰብን) የገደለው አፖሎ (አይዲያሊዝም) መሆኑ ነው፡፡ ምድርን የገደለው ሰማይ ነው በአጭሩ፡፡ ይሄንን ነጥብ ይዘን የቅድሞቹን ጥያቄዎች ተመልሰን እንያቸው፡፡ ቫንጐ የፈጣሪ ብልሹ ንድፎች ነን ማለቱ፤ ፈጣሪን ፍፁም አድርጐ መቀበሉን አመልካች ነው፡፡ ወደ ሰማይ፣ ወደ ሀሳቡ… ወደ ግለሰብ ምልከታው የሚያደላ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር ቅራኔ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ሀሳቡ በአካሉ ውስጥ እስረኛ ሆኖ ምድር እንዲርቀው ሆኗል፡፡ በቀደመ (የተነጠለ) ሀሳቡ የሰራቸው በቁጥር ወደ ሁለት ሺ ገደማ ብዛት ያላቸው ስዕሎቹ በህይወት በነበረበት ወቅት ተሸጠውለት አያውቁም፡፡

ማህበረሰቡ በቁጥር ብዙ ነው፡፡ እንደ ጫማ ሰፊው ለወቅታዊ አገልግሎቱ የሚሆን መፍትሄ የሚሰጠው አርቲስት ይሻል፡፡ ቫንጐ ማህበረሰቡን መራቅ የቻለው፤ ከሰው በላይ በጋለ ስሜታዊነቱ፣ በጥበቡ፣ በእብደት እና በሞት ብቻ ነበር፡፡ ለሰማይ ዘልሎ ጣራ ነክቶ ተመለሰ፡፡ መሬት ላይ የሚኖሩ ስዕሉን ከሞተ በኋላ ተረዱለት፡፡ በሞተበት ገዙት፡፡ ግለሰቡ አርቲስት “ሰው የፈጣሪ የተበላሸ ንድፍ ነው” እንዳለው፡፡ ማህበራዊ አርቲስቱ “ለማህበረሰቡ አስተዋፅኦ የማያደርግ ሀሳብ ፀረ-ህዝብ” ነው የሚል ይመስለኛል፡፡ ከቫንጐ ይበልጥ ዳቦ ጋጋሪው ለማህበረሰቡ ይጠቅማል፡፡ ዳቦ ጋጋሪው ሼክስፒር ይሆንለታል፡፡ እንግዲህ፤ መሬት እና ሰማይ ይህንን ያህል ቢለያዩም፣ ሁለቱም በሰው አማካኝነት እየተፈራረቁ እስከምናውቀው የአሁኑ ዘመን ዘልቀዋል፡፡

ውበትን ለመመዘን መሬቱም - አየሩም - ሰማዩም ያስፈልጉናል thesis, antitheisis and synthesis ሺፑትሊን (A.P. SHEPTULIN) የተባለ የማርክሲስት ሌኒኒስት ፈላስፋ ማቆራኘት እና መነጣጠል የተለያዩ ሳይሆኑ አንድ ነገር እንደሆኑ ይገልፅልናል Although connection and isolation are different types of relations, they exist together, in union, rather than separately. The existence of connection involves the existence of isolation and vice versa መሬት የሚሰጠው ምርት ከመልከአ ምድራዊ አቀማመጡ ጋር ቁርኝት አለው፡፡ ሁለቱ የተነጣጠሉ ቢመስሉም ግንኙነት አላቸው፡፡

መሬቱ እና የአየር ፀባዩም ግንኙነት አላቸው፡፡ …በዚሁ አተያይ ለዘመናችን ጥበብ ማበብ ወይንም መድረቅ የአየሩ ሁኔታ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የፖለቲካው የአየር ሁኔታ፡፡ መሬት እና ሰማይም በመነጣጠላቸው ውስጥ አንድነት ሁሌም ይኖራቸዋል፡፡ የመሬት ሰብል ለመሬት እንጂ ለሰማይ አይጠቅምም፡፡ የሰማዩም ለመሬት እንደዚሁ፡፡ በመግቢያ ላይ የጠየቅኋዋቸው የጥበብ/ውበት መለኪያ ጥያቄዎችም እንደ አየሩ ሁኔታ እና እንደ መልከአ ምድሩ አቀማመጥ መልሶቻቸው የሚለያዩ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን በልዩነቱ ውስጥም አንድነት አላቸው፡፡ ሰው በግለሰብነቱ ዘመን የፃፋቸው የምናብ ነክ ሀሰሳዎች፣ ሰው በማህበረሰብነቱ ዘመን ከሚፅፋቸው፣ ከሚዘፍናቸው፣ ከሚቀኛቸው በእጅጉ የተለዩ ናቸው፡፡ የማህበረሰብነት ዘመን ሲመጣ እንደ ምስኪኑ ቫንጐ ከመሆን ያድነን፡፡ ባይሆን እንደ ኒቼ መሬት እና ሰማዩን ቀላቅሎ… መሐል ቤት (አየር) ላይ መንሳፈፍ ሳይሻል አይቀርም፡፡

Read 1861 times Last modified on Saturday, 29 June 2013 10:56