Saturday, 29 June 2013 09:49

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

Written by  በኦሪዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(5 votes)

ተናጋሪዋ ምድር

ሰኔ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ጠዋት፡፡

ዕለቱ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ ነበርና ከቀጠሮው ቦታ የተገኘሁት ልክ ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ቡድኑ በጥዋት ተነስቶ ረጅም መንገድ መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡ ከአዲስ አበባ ለመነሳት ገስግሶ መሰባሰብ ያስፈልጋል ስለተባለ የቀጠሮው ጊዜ ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት ነበር፡፡ በርካታ ተጓዦች በተባለው ሰዓት ቢገኙም አንዳንድ ተጓዦች ግን በመንገድ መዘጋት (በዚያ ሰዓት መንገድ ተዘጋ ማለት አሳማኝ ባይሆንም) እና በተመሳሳይ ሰበቦች ጊዜ ባለማክበራቸው የመነሻ ሰዓት አልተጠበቀም፡፡ በዚህም ቀድመው የተገኙ አባላት መነጫነጭና መወቃቀስ ጀምረው የነበሩ ሲሆን በተለይ አስተባባሪዎቹ ተበሳጭተው እንደነበር አስተውያለሁ። የብስጭታቸው ሰበቡ “ለምን ሰዓት አይከበርም? ለምን የአበሻ ቀጠሮ እያልን ራሳችንን ስንዘልፍ እንኖራለን?” የሚል ነው፡፡ 11፡30 ላይ ከአዲስ አበባ ለመነሳት ተይዞ የነበረው ቀጠሮ በ1፡30 ተራዝሞ ልክ ከጥዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ጉዞው ተጀመረ፡፡ ጉዞው የጥበብ ጉዞ ነው፡፡

“የዓባይ ዘመን ሕያው የጥበብ ጉዞ ሶስት ወደ ቅዱስ ያሬድና ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ሀገር” በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ያዘጋጀው ታሪካዊ ጉዞ። ሙሉ ወጭውን የሸፈነው ደግሞ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው፡፡ የኪነጥበብ ሰዎች በሆነ ምክንያት ቢጋጩ እንኳ ቁጣቸው የሕፃን አይነት ቁጣ በመሆኑ ወዲያው ይረሱታል፡፡ የጥበብ ተጓዦችም በአርፋጆች ላይ እንዲያ ሲነጫነጩ እንዳልነበረ ሁሉ አዲስ አበባን እንደለቀቅን ዘፈኑና ትረባው ተጀመረና በሁሉም ተጓዦች ፊት ላይ የደስታ ስሜት ይነበብ ጀመር። ተጓዦች 43 ሲሆኑ በርካታውን ቁጥር የያዙት ደራስያን ናቸው፡፡ የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ሃያስያን፣ የስነ ጽሑፍ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ሰዓሊያንና ከማህበሩ ጋር በቅርበት የሚሰሩ ማተሚያ ቤቶች ተወካዮችም የጉዞው አካላት ናቸው፡፡ የዕድሜ፣ የሥራ፣ የዕውቀትም ሆነ የጾታ ልዩነት መኖሩ ባይካድም በተሳፈርንበት የዓለም 1ኛ ደረጃ አውቶብስ ውስጥ የነበሩት ተጓዦች ሁሉ ዕኩዮች ይመስሉ ነበር።

የፈለገ ይዘፍናል፤ ያሻው ያቅራራል፤ ሌላውም ወይ ገጠመኙን ያወራል፤ ወይም ግጥም ያነብና ተጓዡን ያዝናናል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ጉዞው ቀጠለና በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተመሠረተችው ጥንታዊቷ የደብረ ብርሃን ከተማ ቁርስና ምሳ አንድ ላይ ተበሉ፡፡ አንዳንድ ተረበኞች “ቁምሳ” ብለው በአህጽሮተ ቃል እንደሚናገሩት መሆኑ ነው፡፡ ከቁርስ በኋላ ሁካታውና ጨዋታው በእጅጉ ደርቶ ሰሜናዊው ጉዞአችን ቀጠለ፡፡ የጣርማ በርን ዋሻዎች፣ አናቷ ላይ ጉም የማይለያትና የጠመጠመ ቄስ የምትመስለዋን ደብረ ሲናን፣ ኤፍራታን፣ ሸዋሮቢትን፣ ማጄቴን፣ ካራቆሬን፣ ከሚሴን፣ ሐርቡንና ኮምቦልቻን አቆራርጠን በ19ኛው ክፍለዘመን የንጉሥ ሚካኤል ከተማ ከነበረችው ደሴ ላይ ሻይ ቡና አልን፡፡ በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን የዞን ከተሞችም በእጅጉ መነቃቃታቸውን ማስተዋል ችያለሁ፡፡ ከተመሰረተች ከ573 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረችው ደብረ ብርሃን እንደ ኦሪታዊው አቤሜሌክ አንቀላፍታ እንዳልኖረች ሁሉ፣ ዛሬ የዘመናዊ ህንፃዎችና ጐዳናዎች ባለቤት ሆና ማየት “ይበል” የሚያሰኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

በ15ኛው ክፍለ ዘመን በጉንዳጉንዶ መነኮሳትና በአፄ ዘርዓያዕቆብ መካከል በነበረው የሃይማኖት እሰጥአገባ ምክንያት የሀገራችን ሥነጽሑፍ ጣራ ደርሶ የነበረው በዚች ታሪካዊት ከተማ ነበር፡፡ ልጅ በዕደ ማርያም ዙፋን ከወረሰ በኋላ ግን ደብረ ብርሃን ክብሯም ስሟም በአያሌው ተጐሳቁለው ነበር። የሀገሪቱ ዋና ከተማነቷ ሲቀር በስልጣኔ መራመድ አቅቷት መፍገምገሟ ግድ ሆነ፡፡ አሁን ግን የሚታይ ለውጥ እያስመዘገበች ነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ከሚሴም በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን ዋና ከተማ ከሆነች በኋላ እየተነቃቃች መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። በነገራችን ላይ የጠቀስኋቸውንም ሆነ ወደፊት የማነሳሳቸውን ከተሞችና አካባቢዎች ቀደም ብዬ ስለማውቃቸው ነው ለውጥ አለ ብዬ መመስከር የፈለግሁት፡፡ ኮምቦልቻ መልክዓምድራዊ አቀማመጧ ስለሚያግዛት ዘመናዊ ከተማ የመሆን ዕድሏ ሰፊ ነው። “የአሰብ መንገድ መስተጓጐል በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የተወሰነ ተጽእኖ ይፈጥራል” የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም ከተማዋ እንዲያውም ከታስበው በላይ ፈጥና የተጓዘች ትመስላለች፡፡ ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ እየተገነባላት ሲሆን ከጐጃም ጋር በየብስ የሚያገናኛት መንገድ ግንባታም እየተጠናቀቀ በመሆኑ ለዕድገቷ ተጨማሪ ጉልበት ይሆናታል፡፡ የጦሳ ተራራ መፈናፈኛ ያሳጣት ደሴም አሮጌ ልብሷን አውልቃ እየጣለች በተሃድሶ ላይ ትመስላለች፡፡ የቦታ ጥበት እያለም ደሴ በለውጥ ላይ ናት፡፡ አሮጌና ደሳሳ ቤቶች በዘመናዊ ህንጻዎች እየተተኩ ናቸው፡፡ ግን አሁንም የጦሳ ተራራ አናቷ ላይ ሆኖ ቁልቁል ይኮረኩማታል፡፡ ጦሳን በደን መሸፈን ካልተቻለ እና ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ትኩረት ካልተሰጠው የደሴ ተስፋ ረጅም ጉዞ ላይዘልቅ ይችላል፡፡

ከዚህ ቀደም በተግባር የታየ ነገር ስላለ ከእሱ መማር ብልህነት ይመስለኛል፡፡ ከደሴ ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋና በሃገራችን ታሪክ ቀዳሚው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የነበረባት ታሪካዊቷ የሃይቅ ከተማም እየተስፋፋች መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ ጉዞው ቀጥሏል፤ ቀኑ እየተገባደደ ስለሆነ መፍጠን አለብን፡፡ ጭፈራውም፣ መዝናናቱም ቀጥሏል፡፡ የአምባሰልን ሰንሰለታማ ተራሮች እየቃኘን ስንጓዝ አስተባባሪው ድንገት ተነሳና ዝም እንድንል ጋበዘን “በግራ በኩል ከምታይዋት ደልዳላ ቦታ ላይ ነው ያ መዘዘኛ ውል የተፈረመው፡፡ አፄ ምኒሊክ ከጣሊያኑ ወኪል ጋር የውጫሌን ውል የፈረሙት ከዚያ ቦታ ላይ ነው፤ ስሙም ይስማ ንጉሥ ይባላል” ሲለን ቦታዋን የማያውቋት ደራስያንና ጋዜጠኞች የሰሙትና የሚያዩትን ማስታወሻቸው ላይ በፍጥነት ያሰፍሩ ጀመር፡፡ አሁን ጨዋታው ሁሉ ቆመና ውጫሌ የውይይት ርዕስ ሆነች፡፡ የአምባሰል ተራራ እንደ ጆፌ አሞራ በላይዋ ያንዣበበባት ውጫሌ የዕድሜዋን ያህል አላደገችም፡፡ አምባሰልም ራቁቱን ነው፡፡

የኪነጥበብ ሰዎች “አምባሰል ለገደል ምን ያሽሟጥጡታል ፈረስ ባያስጋልብ ማር ይቆርጡበታል” እንዳላሉት ሁሉ ዛሬ ገጽታው አስፈሪ ነው፡፡ እንኳን ለንብ የሚሆን አበባ ያለው ዛፍ ለምልክት ቢፈለግም የሚገኝበት አይመስልም፡፡ ስለዚህ የዞኑ ህዝብና መንግስት ልዩ ትኩረት ቢሰጡትና በደን ቢሸፈን የአምባሰል ውበት፣ የአምባሰል ወዘና የማይመለስበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሆኖም አምባሳል የተጓዦችን ስሜት ሰቅዞ መያዙ አልቀረም፡፡ ውርጌሳ ያው ናት፤ መርሳ መጠነኛም ቢሆን ለውጥ አላት፡፡ ሲሪንቃ የእርሻ ምርምር ጣቢያ ለአካባቢው ውበት ቢሆንም የታሰበውን ያህል እየሰራ መሆኑን መናገር አልቻልሁም፡፡ በጉዞ ላይ ሆኜ ነዋ ያየሁት፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ በኋላም ስለሚጠሩት ከተሞችና አካባቢዎች የምሰጠው አስተያየት ሳልፍ ባስተዋልሁት መረጃ ላይ ተመስርቼ መሆኑ ልብ ይባልልኝ፡፡ መኪናችን ክንፍ ባይኖረውም ይከንፋል፡፡

በጊዜ ወልድያ ለመግባት ከፍተኛ ፍላጐት የነበረን ቢሆንም ሲሪንቃ ላይ ጐማ ተነፈሰና እኛም ተናፈስን፡፡ አመሻሽ ላይ 521 ኪሎ ሜትሮችን አጠናቀን ወልድያ ገባንና አዳር እዚያው ሆነ፡፡ ዙሪያዋን የከበቧት ተራሮች ባይገድቧት ወልድያም በዕድገት ለመመንጠቅ እየተንደረደረች መሆኗን ተገንዝቤያለሁ፡፡ የሁለተኛው ቀን ጉዞአችን ቀጥሏል፡፡ ጉዞው ደግሞ ወደ ሰሜን ነው፤ ወደ ቅዱስ ያሬድና ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ ሀገር፡፡ በጥዋቱ ከወልድያ ተነስተን ጐብየን “እንዴት ነሽ?” ብለናት ቆቦ ላይ እረፍት አደረገን፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ከመቀሌ የሚመጡ እንግዶች ስለነበሩ ትንሽ ጊዜ መጠየቁ የግድ ስለሆነ ነው፡፡ ራያዎች፣ አማራዎች፣ ትግሬዎችና አፋሮች በፍቅር የሚኖሩባት ቆቦ፤ በጥዋቱም ሞቅ ደመቅ እንዳለች ነው ያገኘናት፡፡

አዳዲስ ህንፃዎች ለቆቦም እንግዳዎች አይደሉም፤ እዚያም እዚህም ተስፋ ሰጭ ጅምሮች ይታያሉ፡፡ የቆቦ ቆይታችን በሻይ ቡና ከተጠናቀቀ በኋላ ዞብልን በርቀት እያየን ጉዞ ወደ ትግራይ ክልል ሆነ፡፡ ትረባው፣ ዘፈኑ፣ ግጥሙ፣ ተረቱ….አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ልክ የአማራን ክልል እንደጨረስን አንድ ፒክአፕ መኪና በፍጥነት ቀደመንና ቪዲዮ ካሜራ የያዙ ወጣቶች አውቶብሳችንን ይቀርጽ ጀመር። ለጊዜው ማንነታቸውን ባንለያቸውም የኋላ ኋላ የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መሆናቸውን ተረድተናል፡፡ ከአላማጣ ከተማ ወጣ ብሎ በርካታ መኪኖችን ስናይ መንገድ የተዘጋ መስሎን ጉዟችንን ሊያጓትትብን ነው የሚል ስሜት ተፈጠረብን፡፡ እየተጠጋን ስንሄድ ደግሞ መንገዱ በመኪና ብቻ ሳይሆን በርካታ ባጃጆች ጭምር ተዘጋግቷል፡፡

መዘጋጋት ብቻ ሳይሆን የከበሮ፣ የዕንቢልታ፣ የዕልልታና የጥሩንባ ድምጽ በአያሌው እያስተጋባ ጠበቀን፡፡ ማለፍ ስለማንችል መኪናችንን አስጠግተን መቆም ግድ ሆነ፡፡ እኛ ስንቆም ዕልልታውና ጭፈራው ይበልጥ ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ መኪኖችና ባጃጆችም በጥሩንባዎቻቸው አካባቢውን አደመቁት፡፡ ግራ ተጋብተን ሳለ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሃየ አለማየሁና የክልሉ ባህል ቱሪዝም ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ከበደ አማረ ከመኪና እንድንወርድ ነገሩን፡፡ ከመኪና መውረድ ስንጀምር ዕልልታውና ዘፈኑ እጅግ ደመቀ፡፡ ለካ ያ ሁሉ የመኪናና የባጃጅ ሰልፍ፣ ያ ሁሉ ዕልልታና ደስታ፣ ያ ሁሉ ደማቅ ሰልፍ ለጥበብ ተጓዦች የተዘጋጀ አቀባበል ኖሯል፡፡ ከመኪናችን እንደወረድን በባህላዊ አልባሳት የተዋበ ህዝብ ከቦን ጭፈራውን ያቀልጠው ጀመር፡፡ አቀባበሉ ለአንድ የሀገር መሪ እንጂ ለኪነጥበብ ሰዎች የተደረገ አይመስልም፤ አላማጣ ቄጠማ ጐዝጉዛ፣ ፈንዲሻ እየበተነች በልጆቿ ውብ ዜማና ጭፈራ ከሰርግ በደመቀ ሁኔታ ተቀበለችን፡፡ እውነት ለመናገር የህዝቡን ሁኔታ ሳስተውል እንባዬን መቆጣጠር አቅቶኛል፡፡ አቀባበሉ ከአንገት በላይ አይደለም፤ ከንፁህ ልብ ስር በመነጨ ፍቅር የታጀበ መሆኑን እንደ እኛ በቦታው የተገኘ ብቻ ሊያየውና ሊመሰክር ይችላል፡፡

አላማጣ አቀባበል ያደረገችልን በሆታና በእልልታ ብቻ አይደለም፤ በከንቲባዋ በአቶ ገብረ ትንሣኤ ፍሥሐ አማካይነት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ከሞቀ ቁርስና የቡና ስርዓት ጋር ቀርቦልን ተዝናንተናል፡፡ ከዚህ ሌላ ያለ ዕድሜው በድንገት በተለየን በኢያሱ በርሄ ስም የመሰናዶ ትምህርት ቤት መሰየሙን ተረዳንና አላማጣ ለኪነጥበብ ሰዎች ተገቢውን ክብር እንደምትሰጥ አረጋገጥን፡፡ አብረው የተጓዙ የቅኔ ሊቃውንትም የአላማጣ ህዝብ ስላሳየን ጥልቅ ፍቅር ቅኔ ዘረፉ፤ ተጓዡንም አዝናኑ፡፡ መቀሌ ገብተን ማደር ይጠበቅብናልና መፍጠን አለብን፡፡ ስለሆነም ራያዎች የሚዙበትን አላማጣን መሰናበት ግድ ሆነ፡፡ ጐልጐል ራያን (የራያ ሜዳ) አልፈን ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ወደሰሜን እንደተጓዝን፣ የግራ ካሱ ተራራ እናት ዶሮ ጫጩቶቿን ከጭልፊት ለመታደግ በአክናፍዋ እንደምትሸፍናቸው እኛንም ከሆነ አደጋ ይጠብቀን ይመስል በጉያው ወሸቀን።

ግራ ካሱ “ገራህት ካሱ/የካሱ እርሻ” የሚል መነሻ እንዳለው አቶ ከበደ አማረ ነግረውናል፡፡ ግን ግራ ካሱ ቀጥ ያለ ግን ደግሞ ሰንሰለታማ ተራራ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ግራ ካሱ ጥርሱን ያገጠጠ፣ አለቱ የፈጠጠ ተራራ ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ በቀድሞው መንግሥትና በህወሓት መሃል ዘግናኝ ጦርነቶች እንደተካሄዱበት ተረድተናል፡፡ ዛሬ ግን ግራ ካሱ በእርስ በርስ ጦርነት የሚያፏጭ አረር አይሰማበትም፤ ዛሬ የሁለት ወንድማማቾች በድን እንደአልባሌ ዕቃ የትም ወድቆ አሞራ አይጫወትበትም፤ ይልቁንም ህይወትን በሚታደግ ውብ ነገር ተሸፍኗል - በተፈጥሮ ደን፡፡ ከግራ ካሱ ተራራ ልጆች ሊማሩት የሚገባ ዐቢይ ቁምነገር አለ፤ እሱም ተፈጥሮ ልክ እንደሰው ልጆች ነፃነትዋን የምትሻ መሆንዋን ነው፡፡ የክልሉ ባለስልጣናትና ነዋሪዎች ያደረጉት ነገር የለም። ያደረጉት ቢኖር አካባቢውን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ያ ጣረሞት ይመስል የነበረ ተራራ በተፈጥሮ ደን ተሸፍኖ የዱር እንስሳት መፈንጫና ቀልብን የሚስብ መሆን ችሏል፡፡ ይህ ለብዙ የአገራችን አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገሮችም አብነት የሚሆን ይመስሉኛል፡፡ ጉዞውም ጽሑፉም ይቀጥላል፡፡

Read 3723 times