Saturday, 29 June 2013 09:38

ይመርና እኔ ህይወት ተቀያይረናል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የጀግና ሰው መልኩ ሁለት ብቻ ነው፤ አንድ ፊት መስዋዕት በአንድ ፊት ድሉ ነው፤ የሁሉም ማሰሪያ ማተቡ ብቻ ነው፡፡ (“የአሲምባ ፍቅር” ገፅ 140) ካህሳይ አብርሃ ወይም በበረሀ ስሙ አማኑኤል ተብሎ ይጠራል፡፡ መስከረም 27ቀን 1968 ዓም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ሰራዊትን ለመቀላቀል ወደ ትግል ወጣ፡፡ ሰኔ 27ቀን 1968 ዓም ወልዲያ ለተልዕኮ የወጣ የሠራዊቱ ቡድን ወደ አሲምባ በተመለሠበት ዕለት በተፈጠረ የጦርነት አጋጣሚ ከይመር ንጉሴ ጋር ተገናኘ፡፡

በ1970 በኤርትራ አድርጎ ሱዳን በመግባት ከሠራዊቱ ተለየ፡፡ ኑሮውም በአሜሪካ ሆነ፡፡ የደርግ አገዛዝ ሲገረሰስ ይመር ንጉሴን ለማግኘት እንዲሁም የመጀመሪያ የሴት ፍቅረኛው የተሠዋችበትን ቦታ ለማየት ወደ ኢትዮጵያ መጣ። በሰራዊቱ ውስጥ ስላሳለፈው የትግል ህይወት የሚተርክ “የአሲምባ ፍቅር” የተሰኘ መፅሀፍ ባለፈው ቅዳሜ የቀድሞ የኢህአፓ አባላትና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት አስመርቋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ በአሜሪካ ከሚኖረውና በፋርማሲ ባለሙያነት ከተሰማራው ካህሳይ አብርሃ ጋር ስለ መፅሀፉ እና የትግል ህይወቱ አነጋግራዋለች፡፡

                                                    ***

በየትኛው ስም ልጠቀም---- አማኑኤል በሚለው ወይስ በበረሀ ስምህ ካህሳይ? በፈለግሽው መጠቀም ትችያለሽ፡፡ ወደ አሲምባ የገባህበትን የመጀመሪያዎቹን ቀናት እንዴት ታስታውሳቸዋለህ? ስሜቱን ልገልፀው አልችልም፡፡ ለመብት ከሚታገል ድርጅት ጋር መቀላቀል ደስታ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ኑሮው ውጣ ውረድ ያለበት መሆኑ አልከበደህም? ረሀቡ፣ ጥማቱ እና ውጣ ውረዱ ያለ መሆኑን ገምቼ ስለገባሁበት እንቅፋት አልሆነብኝም፡፡ የታጠቁትን መሳሪያ ሳይ ደግሞ በጣም ደስ አለኝ። እዛ ያሉትን ጓዶች ሳያቸው የበለጠ ተደሰትኩ፡፡ በጣም አዋቂ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የመጡ፡፡ የኢህአፓ አባል የሆንከው ቆይተህ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ሠራዊት (ኢህአሠ) አባል ነበርክ፡፡ ስለፓርቲው ምን ያህል እውቀት ነበረህ? ፓርቲው የበላይ አካል እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ የፓርቲ አባል ባልሆንም የሚደረጉትን ነገሮች በሙሉ አውቅ ነበር፡፡

ለምሳሌ የፓርቲው አባሎች ስብሰባ ሲያደርጉ ለፀጥታ ጉዳይና ለደህንነት በሚል መሪዎች ይነግሩናል፡፡ ስለዚህ ኮሚሳሩ “እገሌ እገሌን ይዘን እንሄዳለን” ካለኝ የፓርቲ ስብሰባ እንዳለ እናውቃለን ማለት ነው፡፡ የሆነ መመሪያ በሚወጣበት ጊዜ በመጀመሪያ የፓርቲ አባሎች ይወያዩበታል፤ ከዛ ወደ ሠራዊቱ ይመጣል፡፡ የፓርቲ አባል ስሆን በህይወት እቆያለሁ የሚል ሀሳብ አልነበረኝም፡፡ በማንኛውም ወቅት ግዳጄን ስወጣ ህይወቴ ሊያልፍ እንደሚችል ነበር የማምነው፡፡ እስቲ ይመር ንጉሴ ከተባለው የገበሬ ሚሊሻ ጋር የተገናኛችሁበትን አስገራሚ ገጠመኝና ከዛ በኋላ የሆነውን ነገር ንገረኝ … ወሎ ግዳጅ ወጥተን ጉራወርቄ በምትባል ቦታ እየሄድን የሁካታ ድምፅ ሰማን፡፡ የገበሬ ታጣቂ ሚሊሽያዎች ከኋላችን እየተከተሉን ነበር፡፡ አጠገባችን ሲደርሱ ተኩስ ከፈቱ፡፡ አንዳንድ ጓዶች ጥይት ጨርሰዋል፡፡ አንዱ በመጥረቢያ ተመትቶ ወድቋል፤ ሌላው በጩቤ ተወግቷል፡፡

ሁኔታዎች ከቁጥጥራችን ውጪ ሆነዋል፡፡ በዚህ መሀል ያነጣጠርኩበትን ገበሬ ያለምንም ጥቅም እንደምገድለው እርግጠኛ ነበርኩ። በዚያ ሁኔታ ውስጥ ነፍስ ማጥፋት ዋጋ እንደሌለው ተሰማኝ፡፡ በመተኮስና ባለመተኮስ መሀል ሳመነታ ገበሬው ሰፈረብኝ፣ ተያያዝን ወደቅን፡፡ “ጥይት አልጨረስክም፤ ለምን ተኩሰህ አልገደልከኝም” ሲለኝ “እንኳን አልገደልኩህ” አልኩት፡፡ ምን መለሰልህ? በጣም ገርሞት “ምን ማለትህ ነው” አለኝ፡፡ “አንተ ምናልባት የምታስተዳድራቸው ብዙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ እኔ የለኝም፡፡ ብትገድለኝ አንድ ብቻዬን ነኝ” ስለው በተኛሁበት በያዘው ገመድ እጆቼን ማሰሩን ተወው፡፡ የሞቱትን ጓዶቻችንን ከቀበርን በኋላ፣ ጠመንጃውን አውርዶ ወደ ሰማይ እየተኮሰ ወደእኔ መጣ፡፡ “ይህን ሰው አላስይዝም፤ መሄድ ወደሚፈልግበት እሸኘዋለሁ” ብሎ ወደቤቱ ወሰደኝ፡፡ ከዛስ? የመጀመሪያው ሌሊት እንቅልፍ የሚባል በአይኔ አልዞረም፡፡

ምክንያቱም ጠዋት ምን ሊፈጠር እንደሚችል እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ይገድለኛል? ያስረኛል? አሳልፎ ይሰጠኛል የማውቀው ነገር የለም። ስለዚህ ጠዋት ማምለጥ የምችልበትን ሁኔታ እያሰላሰልኩ ነበር፡፡ ነገር ግን ወዲያው እሱ እኔን ይዞ ሲመጣ ፈጥኖ ደራሽ መጥቶ “ይመር ንጉሴ” እየተባለ ሲጠራ ሰምቻለሁ፡፡ እሱ ግን “ምንም አትሆንም አሳልፌ አልሰጥህም፤ ወደዚህ የሚመጡና የምንታኮስ ከሆነ ወደ ደኑ ማምለጥ ትችላለህ፡፡ እኔ በህይወት ካለሁ መጥቼ እፈልግሀለሁ” ሲለኝ እሱን ከማመን ውጪ ምንም ምርጫ እንደሌለኝ አወቅሁኝ፡፡ በዚህ ወቅት ምን ተሰማህ? እኔና ይመር በህይወት ተቀያይረናል፡፡ እሱን እኔ አልገደልኩትም፤ እሱም በተራው የእኔን ህይወት አትርፏል፡፡ ከዛ ወደ ሚስቱ ዘመዶች አገር ወስዶኝ ተመልሼ አሲምባ ገባሁ፡፡ አሲምባን ስናስብ የሚመጣብን የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ መፅሀፍህ “የአሲምባ ፍቅር” ይላል፡፡

እስቲ ስለ አሲምባ እና ፍቅር ግንኙነት ንገረኝ? አሲምባ የኢህአሰ የመጀመሪያው ቤዝ ነው። አሲምባ ላይ ብዙ ነገሮች ተካሂደዋል፡፡ ሰዎች ተገድለውበታል፡፡ ግን እኔ የማየው ከዛ በላይ ነው። ምክንያቱም የጓዶች ፍቅርና መተሳሰብ … ከብዙ የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ግን የአንድ ቤተሰብ ያህል የሚተሳሰቡና የሚዋደዱ ነበሩ። ሠራዊቱ ከህዝቡ ጋር ህዝቡም ከሠራዊቱ ጋር ያለውን ፍቅር ያሳያል፡፡ ህዝቡ ባይፈቅድ ኖሮ እዛ መኖር አንችልም ነበር፡፡ ሌላው የአገሩ ፍቅር ነው። ጋራው፣ ሸንተረሩ፣ ወንዙ ይናፍቃል፡፡ ትግራይ፣ ወሎ፣ በጌምድር ሁሉም የሚናፈቅ ፍቅር አላቸው፡፡ የመጀመሪያ የሴት ፍቅረኛዬ እና ጓዴ የድላይ ፍቅር አለ፡፡ አንተ የፍቅር ጓደኝነት በጀመርክበት ጊዜ ፓርቲው ያንን ይፈቅድ ነበር? አይፈቅድም እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት ተፈጽሞ ቢገኝ እርምጃው ምንድነው? በህገ ደንቡ መሠረት መባረር ነው፡፡ ግን ፍቅረኞች ነበርን እንጂ ወሲብ አልፈፀምንም፡፡ ስለ ኃይማኖት አቋምህ ስትጠየቅ የተሰማህ ስሜት ምን ነበር? ኃይማኖት ከሌለኝ ኮምኒስት አይደለህም የምባል ወይም የሚመልሱኝ መስሎኝ ስጋት ገብቶኝ ነበር ግን እውነቱን ነግሬያቸዋለሁ፡፡ እስቲ ስለ በረሀ ምግቦች ንገረኝ? ምን ነበር የምትበሉት? ቁርስ የሚባል ነገር የለም፡፡ ለምሳ ለእራትም የሚባል ራሸን የለም፡፡ ያገኘነውን ነው የምንበላው።

ዳቦም ይሁን ቂጣ ወይም እንጀራ ህዝብ የሰጠሽን ትበያለሽ፤ ህዝብ ካልሰጠሽ ደግሞ የተገኘውን ነው የምትበይው፡፡ በለስም ቢሆን … ካልተገኘ ደግሞ ውሀ ጠጥተሽ ታድሪያለሽ፡፡ ውሀም የማይገኝበት ጊዜ አለ። ያንንም መቻል ነው፡፡ አንድ ጊዜ ወደ አርባያ በለሳ ስንሄድ ውሀ በጣም ጠማን፡፡ አንድ ወንዝ አገኘን፤ ውሀው በጣም ቆሻሻ ነበር፤ ግን ትንሽ መጐንጨት ነበረብን፡፡ በነጠላ ትሎቹን እያጠለልን ትንሽ ተንሽ ቀምሰን ሄደናል፡፡ ሽንት የሚጠጡም ነበሩ፡፡ በመፅሃፍህ ውስጥ ፀጋዬ ገብረመድህን (ደብተራው) “ቅማል መቅመል ይወዳል” ብለሀል፡፡ እስቲ ስለሱ ንገረኝ…. በየጊዜው ገላ መታጠብ እና ልብስ ማጠብ አይቻልም፡፡ አኗኗራችን የትግል ነው፤ ከቦታ ቦታ ነው የምንሄደው፡፡ ጊዜ ስናገኝ እንቀማመል ነበር። በተለይ ደብተራው መቅመል ይወዳል፡፡ ልጆች ስለነበርን በቅማል ስንሰቃይ በጣም ይጨንቀው ነበር፡፡ ቅማላችንን አራግፎ ሲሰደን በጣም ነበር የሚደሰተው። እኛ ደግሞ እሱን እንቀምለው ነበር። አንድ ጊዜ በኤርትራ በኩል የመጣ መድሃኒት ነበር፤ ዱቄት ነው፡፡ በውሀ በጥብጠን ልብሳችንን እንነክረዋለን፤ ከዛ እናሰጣዋለን፤ ቅማሎች ይራገፋሉ። አንዳንዴ ለፀጉራችንም እንጠቀምበት ነበር፡፡

ግን በጣም አደገኛ ነው፤ አንዳንዶች ራሳቸውን ይስቱ ነበር፡፡ ምክንያቱም መጠኑን አናውቀውም ነበር፡፡ ሰራዊቱ የሴቶች አያያዝ ላይ እንዴት ነበር? በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ የሴቶች ጭቆና ድርብርብ መሆኑን ያምን ነበር፡፡ የመደብ እና የፆታ ችግር እንዳለ ያምናል፡፡ ከመጀመሪያ ፍቅረኛህ ከድላይ ጋር እቃ እንድታመጣ አብራችሁ ሄዳችሁ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ደግሞ … ጓዶች ሱሪህን አውልቀህ ስጣት አሉኝ፡፡ ያኔ የሚቀልዱ ነበር የመሰለኝ፡፡ “ቶሎ በል ጊዜ ስለሌለ ቶሎ አውልቀህ ስጣት” ስባል ነው ያመንኩት፡፡ ትንሽ ዞር ብዬ ነጠላዬን አገለደምኩና ሱሪዬን አውልቄ ሰጠኋት፡፡ ያኔ ሱሪዋ ቆሽሾ ይሆናል ብዬ ነበር ያሰብኩት፡፡ ወደ ማታ ደግሞ “ይዘሀት ወደ ነበለት ትገባለህ፤ የምትፈልገውን እቃ ይዛ ትመለሳለች” ሲሉኝ ለድርጅቱ ስራ አብሪያት እንደምሄድ ነበር የጠረጠርኩት፡፡ እሷን ስጠይቃት ግን ሞዴስ ላመጣ ነው አለችኝ፡፡ ምን እንደሆነ ስጠይቃት ብትነግረኝም አልገባኝም፡፡

በመንገድ ላይ ስኮረኩራት ስኮረኩራት ነው ምን እንደሆነ የነገረችኝ፡፡ ፍቅረኛህ ድላይ በተደጋጋሚ ውሳኔህን እንድታሳውቃት ታስጠነቅቅህ ነበር፡፡ ሰራዊቱን ትተህ ወደ ሱዳን ለመውጣት ስታስብ ለመንገር ባትችል እንኳን ለምን መልዕክት አልላክባትም? ሱዳን ሆኜ ተስፋይ ኢዲዩ ደብዳቤ ላድርስልህ ቢለኝም የምልከው በነሱ ከሆነ ያነቡታል፤ ስለዚህ የግል ሚስጥር የሚባል ነገር የለም፤ ለዚህ ነው ደብዳቤውን ያልላኩት፡፡ አሲምባ የሠራዊቱ ፍርድ ቤት ነበር፡፡ አንተም ተከሰህ ለፍርድ ቀርበህ እንደነበር በመፅሃፉ ገልፀሃል። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ፍትሀዊ ነው የሚል አዝማሚያ በፅሁፍህ ላይ ይንፀባረቃል፡፡ እውነት ፍትሀዊ ነበር ትላለህ? ለኔ በጣም ፍትሃዊ ነው፡፡ እኔ ከስሼም ተከስሼም ስለማላውቅ አማካሪ ያስፈልገዋል ተባልኩ፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሰላማዊት ጠበቃዬ የሆነችው፡፡ መከሰሴን ተገቢ ነው ባልልም ውሳኔው ግን ጥሩ ነበር። ፀሎተ ህዝቅያስ በፍርድ ቤት ውሳኔ ነው የተገደለው? መፅሐፍህ ላይ “ፀሎተን ደጀኔ ገደለው፣ ደጀኔን ዳዊት ገደለው፣ ደብተራው ወደ ላይ እየተኮሰ መጣ” ብለህ ነው የገለፅከው፡፡ ምንድን ነበር የሆነው? ያየሁትን ብቻ ነው የምናገረው፡፡ ፀሎተ ገና ሳይሞት ነው የደረስኩት፤ ደጀኔ ሞቶ ነበር፡፡ ይሄ የፍርድ ቤት ውሳኔ አይደለም፡፡

በዛን ጊዜ ማንኛውም የአመራር አባል ለደህንነቱ ሲባል የሚሄድበትን ይነግረናል፡፡ ጠዋት ደብተራው መጣና “ደጀኔና ፀሎተ ወደ ወንዝ ለመታጠብ ሄደዋል፤ ጥበቃ እንዲደረግላቸው” ሲለኝ የተባለው ተደረገ፡፡ በተለይ ፀሎተ የአመራር አባል ስለሆነ ጥበቃው ጠንከር ይላል፡፡ ከዛ ደብተራው ትንሽ ቆይቶ ተመለሰና “እኔና ዳዊት ይህ ቦታ ስለጠበበን ፊትለፊት ካለው ጋራ ቤት እናያለን፤ ስለዚህ ጥበቃ ይደረግ” አለ፤ ያንን አደረግን። ወድያው የሁለት አውቶማቲክ መሳሪያ ተኩስ ሰማን፡፡ መጀመሪያ እኔ ወደ ወንዙ ስደርስ ደብተራው ወጥቶ ሽጉጥ ወደሰማይ ይተኩሳል፡፡ እርዳታ ፈልጐ ይመስለኛል፡፡ እኔ ከደብተራው በስተቀር ሁሉም የተገደሉ ነበር የመሰለኝ ፡፡ ደብተራውን ምን ተፈጠረ ብዬ ስጠይቀው “ደጀኔ ፀሎተን ገደለው፤ እኛ ደግሞ ደጀኔን ገደልነው” አለኝ፡፡ ደጀኔ ሞቷል፤ ፀሎተ አልሞተም ነበር፡፡ ዳዊት ጭንቅላቱን ይዞ ሲያለቅስ ነበር፡፡ ፀሎተን ወደ ጥላ ወሰድነው፤ ከዛም ብዙ ሳይቆይ ሞተ፡፡ የዕበዮ፤ የኢህአሰ ሰራዊት ውቅሮ ላይ ባደረገው ውጊያ ነው የተገደለው፡፡ ከሱ ጋር ያለውን ተያያዥ ታሪክ ንገረኝ… የዕበዮ የውቅሮ ልጅ ነው፡፡

ስለዚህ ውቅሮ በሚደረገው ውጊያ እንዳይገባ ተወስኖ አይሆንም ብሎ ተከራክሮ ነበር ወደ ውጊያው የገባው፡፡ በውጊያው ከተሰዋ በኋላ በህይወት የተረፍነው እሱን ስንቀብር ሌሎቹ ጓዶች “አንገቱ ይቆረጥና ይቀበር፤ ምክንያቱም ደርግ የእሱ አስከሬን መሆኑን ከለየ መንገድ ላይ ያወጣዋል” ሲሉኝ “አይኔ እያየ አንገቱን አይቆረጥም” ብዬ ሳይቆረጥ ተቀበረ፡፡ እኔ ሠራዊቱን ትቼ ሱዳን ከገባሁ በኋላ ደርግ በማግስቱ አስከሬኑን ስለለየው ውቅሮ ከተማ መንገድ ላይ አስከሬኑን በመዘርጋቱ፣ እናቱም ያንን አይታ የአዕምሮ ህመምተኛ እንደሆነች ሰማሁ፡፡ ዛሬ ላይ ሳስበው ተቆርጦ ቢሆን ኖሮ እናቱ ትድን ነበር እላለሁ፡፡ ያን ጊዜ ግን የምወደውን ሰው አንገት ቆርጦ ለመውሰድ ህሊናዬ አልፈቀደልኝም፡፡ በበጌ ምድር፣ በባሕር ዳር በየከተማው የነበረውን የኢህአፓ እንቅስቃሴ በቅርበት ታውቁ ነበር? በረሃ በወጡት የፓርቲው ተወካዮች በኩል የምንሰማው መረጃ እንጂ ሌላ እውቀት የለም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ስትገናኙ እንዴት ነበር? የተገናኘው በ1968 ዓ.ም ነው፡፡ ከራዛ ጦርነት በኋላ የተገኘውን መሳሪያ ለመውሰድ ኤርትራ ውስጥ መነኩሲቶ የምትባል ቦታ ሄድን፡፡ አቶ መለስን አይተነው፤ ስለሱ ሰምተንም አናውቅም ነበር፡፡ እሱ የሆነ መልዕክት ይዞ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ለሊቱን በመደዳ ተኝተን አሳለፍን፡፡ በቆይታችን ስለነበረን ልዩነቶች ተነጋግረናል፡፡ የሀሳብ ልዩነት ላይ መስማማት ስላልቻልን “ብሬይን ወሽድ ስለሆናችሁ እናንተን ማሳመን አይቻልም” አለን፡፡

ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሰማሁት ፃፍኩትና ወደ ቦታችን ስንመለስ፣ መለስ ያለንን ነገርኳቸውና ምን ማለት እንደሆነ አስረዱኝ፡፡ ከህወሓት እና ከኢህአፓ ህዝቡ የቱን እንደሚመርጥ ሪፈረንደም አድርጋችሁ ነበር፡፡ እስቲ ምንድነው የሆነው? በወቅቱ የአንድ መንደር ህዝብ አስተዳዳሪው የቱ እንደሚሆን ይመርጥ ነበር፡፡ ከሁለቱ ድርጅቶች በየቱ መተዳደር ትፈልጋላችሁ ይባልና ውሳኔው ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ወያኔ ካለ እኛ እንለቃለን፤ ኢህአፓ ካሉ እነሱ ይለቃሉ፡፡ ህዝቡ ተወካዩን እንዲመርጥ እናደርጋለን፡፡ ታድያ ሁኔታዎች ለምን ተበላሹ? በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው ነገር በኔ ደረጃ የሚገለፅ አይደለም፤ እኔ ተራ ታጋይ ነበርኩ፡፡ ከበለሳው ቡድን በኋላ ኢህዴን/ብአዴን ከሆኑት ማንን ታውቃለህ? ያኔ አብረውን ከነበሩ ሰዎች እንደሰማሁት አርባፀጓር ላይ አቶ በረከት ስምኦን አጠገቤ እንደነበሩ ነግረውኛል፡፡ ግን አንተዋወቅም፡፡ አቶ በረከትም ከቤጌምድር ጋንታ መጥቶ ነበር፡፡ ከደብተራው ጋር ከነበራችሁ ፍቅር የተነሳ ስትለያዩ ማስታወሻ ስጠኝ ብለኸው ለማስታወሻነት መሳሪያችሁን ተለዋውጣችኋል፡፡ የደብተራው ማስታወሻ መሳሪያ የት ገባች? ከደብተራው ጋር ለየት ያለ ፍቅር ነበረን፡፡ በኔ ላይ ጥሩ እምነት ነበረው፡፡

ስለ አማኑኤል ጥሩ እንጂ መጥፎ ነገር አትንገሩኝ ይል እንደነበር አሁን በህይወት ያሉ አመራሮች ይነግሩኛል፡፡ ስንለያይ ብረት ተለዋወጥን፡፡ ወደ ሱዳን ስሄድ በኤርትራ በኩል ስለሆነ ለኤርትራ ድርጅት አስረከብኳት፡፡ ሳስረክባት እውነቴን ነው እሱንም ያስረከብኩት ነው የመሰለኝ፡፡ ኢህአፓ እና ኢህአሠ የተቆራኙ ወይም የሚናበቡ አይመስሉም፡፡ ወታደራዊ ግዳጆቹ የተበጣጠሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ? እኔ በማውቀው ደረጃ ያንቺን ጥያቄ መመለስ ይከብደኛል፡፡ እኛ ዛሬ እዚህ ትሄዳላችሁ ስንባል እንሄዳለን፤ ውጊያ ታካሂዳላችሁ ሲባል እንፈፅማለን። ፓርቲው ሠራዊቱን ያዛል፤ ሠራዊቱ ይፈፅማል፤ በየክፍሉ የፓርቲ ወኪሎች አሉ፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ የነበረው የተማሩና ያልተማሩ አባላትን ልዩነት ንገረኝ? እኛ የታዘዝነውን እንፈፅማለን፡፡

አንዳንድ የተማሩት እኛን “የአመራር ቡችሎች” እና “ክሊኮች” ይሉናል፡፡ እኛ ስለፓርቲው ጠልቀን አናውቅም፤ እነሱ ስለፓርቲው ድክመትና መፈረካከስ ያውቃሉ፤ በዚህ መሀል መናበብ የለም፡፡ ያኔ እነሱ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ናቸው፤ እኛ ደግሞ ለምን የታዘዙትን አይፈፅሙም እንላለን፡፡ እኛ ስላልተማርን ንቀውን ሳይሆን ውስጣችን የተለያየ ነገር ስለነበር ነው፤ በአቅምም እንድናድግ ጥረት ይደረግ ነበር፡፡ ለምሳሌ ጓድ ሽፈራው “The military Tactic of the Vietnamese Revolution” የሚል መፅሐፍ አስነብቦናል፡፡ ኢህአፓ/ኢህአሠ ለምን ፈረሰ? ብዙ ብቃት ያላቸው ለመስዋእትነት ዝግጁ የሆነ ሠራዊት ነበረው፡፡ ድርጅቱ ለምን ፈረሰ በኔ አቅም አይመለስም፡፡ ልዩነቶች እንደነበሩ እንሰማ ነበር፡፡ እኛ በይፋ የተነገረን በ1970 ቢሆንም ችግሩ ከ1968 ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ብርሃነመስቀል ከድርጅቱ ወጥቷል ይባል ነበር፡፡ ያንን የፓርቲ አባሎች ያውቃሉ፡፡

እኛ ግን በሀሜት ደረጃ እንጂ በይፋ አልተነገረንም፡፡ ድርጅቱ እየተከፋፈለ አንጃ ተብለው ታስረው የተገደሉ አሉ። በጣም የምንወዳቸውና የምናከብራቸው መዝሙር፣ በሽር፣ ታሪኩ የተባሉ እና ሌሎችም ተገደሉ፡፡ ብዙ ጓዶች በዚህ ላይ ቅሬታ ነበራቸው፡፡ ከኤርትራና ከወያኔ ጋር የነበረን ግንኙነት መሻከር ተደማምረው ይመስለኛል ለመፍረስ የበቃው፡፡ “የአሲምባ ፍቅር” … ይቅርታ ጠይቀን አስቆምናቸውና “እዚህ አካባቢ የሚኖር ሰው ብጠይቃችሁ ታውቃላችሁ?” አልናቸው፡፡ አንደኛው ሰውዬ “መሃመድ እባላለሁ፤ እዚሁ አካባቢ ነው ሀገሬ ፣እዚህ ወጣ ብሎ ይሄንን ጋራ ተሻግራችሁ ነው፡፡ ማንን ፈልጋችሁ ነው? ስሙን ታውቃላችሁ?” አሉን፡፡ “ይመር ንጉሴ የሚባል ሰው” አልኳቸው “ይመር ንጉሴ? ወይ ወንድሜን!” ብለው ጭንቅላታቸውን ይዘው ማልቀስ ጀመሩ፡፡ ልቤ ስንጥቅ አለ፡፡

የሆነውን መጠየቅ አስፈላጊ አልነበረም፤ አውቄዋለሁ፡፡ እውነቱን መቀበል ግን አልፈለግኩም፡፡ ለመናገር መዘጋጀቴን ሳላውቀው ከአፌ ምነው? የሚል ቃል ሲወጣ በጆሮዎቼ ተሰማኝ። “ይመር ንጉሴ እኮ ሞቷል!” አሉ፡፡ “እንዴት ሆኖ?” “በቃ እንዴት እንደሆነ አላወቅንም፤” የወያኔ ታጋዳዮችና በርካታ መሪዎች አውቅ ነበር፤ ብዙዎቹን በአካል ሌሎቹን ደግሞ በዝናና በወሬ ደረጃ ስማቸውን ሰምቻለሁ፣መለስን ግን ያየሁትም ሆነ ስሙን የሰማሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ መለስ የለበሰው የዘማቾች ካኪ ዩኒፎርም ሲሆን አንድ ቦርሳ ሙሉ መፅሃፍ ይዟል፡፡ ሰውነቱ ጠንካራ፣ ከመካከለኛ ሰው ትንሽ አጠር ያለ ቁመት ያለው፣ ክብ ፊትና ንቁ ዓይኖች ያለው ሰው ነው፡፡ መለስ ጨዋታና ቀልድ የሚያውቅ፣ ሃለኛ ተከራካሪ፣ በውይይት ጊዜ ፊቱን ቅጭም የሚያደርግና የሚመሰጥ እንደሆነ በዛን ቀን ቆይታችን አስተውያለሁ፡፡…የምንከራከረው እኔና አስመሮም ከአንድ ወገን፣ መለስ ደግሞ ብቻውን ስለነበር ውይታችን አድካሚ ሳይሆንበት አልቀረም። እርሱ ግን እንዲህ በቀላሉ ደክሞት የሚተው ሰው አልነበረምና እኛን ለማሳመን ብዙ ደከመ።

በመጨረሻም ከሀሳቡ መደጋገም በቀር አዲስ ነገር እያለቀብን ሲመጣ፣ “ብሬይን ወሸድ(brain washed) ስለሆናችሁ፣ እናንተን ማሳመን አይቻልም” አለ፡፡ ጸጋዬ ደብተራውን በጣም ስለምወደው “አሁን ጎንደር ከሄድኩ ላንገናኝ እንችላለንና አንተን ማስታወሻ የሚሆነኝ አንድ ነገር ስጠኝ” አልኩት፡፡ እሱም ሳቅ አለና ትንሽ ካሰበ በኋላ “እንካ ጠመንጃዬን ልቀይርህና ማስታወሻ ይሆንልሃል” ብሎ ሰጠኝ፡፡ የእርሱን ወስጄ የእኔን ሰጠሁትና ተቃቅፈን ተሳሳምን፡፡ ሁለቱም የክላሽን ኮቭ ጠመንጃዎች ነበሩ፤ምንም ልዩነት የላቸውም፡፡ ቢያንስ አንዳንዴ ጠመንጃዬን ሳይ ግን እሱን ያስታውሰኛል ብዬ በጣም ደስ አለኝ፡፡

… በጣም ግራ ገባኝ “ከሴት አስተማሪዎች የምትቀበይው ወይም ደግሞ የምታመጪው ምን እቃ ነው?” ብዬ እንደገና ስጠይቃት ሳቀች፡፡ “አንተ አታውቀውም፣ የሴት እቃ ነው፣ አማኑኤል” አለችና እንደገና አከታትላ “አማኑኤል እኔ እኮ አሞኛል፡፡ ቀኑን በሙሉ ያንተን ልብስ ለብሼ እንደዋልኩ ታውቅ የለ፡፡ የእኔ ሱሪ ተበላሽቶ ስለነበር ለማጠብ ነበር የአንተን ለብሼ ወደ ወንዝ የወረድኩት” ብትለኝም ችግሯን በትክክል አልተረዳሁትም፡፡ “ታዲያ ምንድን ነው የምናመጣው?” “እቃው ሞዴስ ይባላል” አለችኝ፡፡ “ሞዴስ ምንድነው?” “ሞዴስ ሴቶች ብቻ የሚጠቀሙበት የሴት እቃ ነው፡፡ ወንዶች ብዙም አታውቁትም” አለችና ለአፍታ ያህል ስታስብ ቆየች፡፡ “ወንዶች እኮ እንደዚህ ዓይነት ነገር ስለማታውቁ ታድላችኋል” በድምጿ ውስጥ ሐዘን ተሰማኝ፤ ችግሩ ወይም ሕመሟ ቀላል እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ ግን ምን እንዳመማት በትክክል አልተረዳሁም፡፡ “ሞዴስ” የሚለውን ቃል ስሰማ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ አሁን ግን የሴት እቃ ከመሆኑ ሌላ ያሽልሻል ማለት ነው?” አልኳት፡፡ (በካህሳይ አብርሃ ብስራት ተፅፎ ባለፈው ቅዳሜ ከተመረቀው “የአሲምባ ፍቅር” መፅሃፍ የተቀነጨበ)

Read 3420 times