Saturday, 29 June 2013 09:24

ወላጅ ለልጁ የሚያዘጋጃቸው 3 ትልልቅ ስጦታዎች

Written by 
Rate this item
(10 votes)

(1. የእንግሊዝኛ ቋንቋ 2. ኮምፒዩተር 3. ኢንተርኔት … ናቸው ስጦታዎቹ። መፃህፍት እንደልብ ለማንበብና ስኬትን ለመቀዳጀት) እውቀት የዶ/ር ቤን ካርሰን ታሪክ ምስክር ነው። በህፃንነቱ “ደደብ ነኝ” ይል ነበር - ትምህርት ጨርሶ የማይገባው። ከድህነት ጋር በምትታገል እናቱ ግፊት መፅሃፍ ማንበብ ጀመረ። በአንጎል ቀዶ ህክምና በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሃኪም ለመሆን በቃ። በ2016 ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ይወዳደራል ተብሎ ይጠበቃል። “ተአምር” መስራት የሚቻልበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ከሃያ አመታት በፊት በፍፁም የማይሞከሩ ነገሮች፣ ዛሬ በቀላሉ በመዳፋችን ውስጥ ልናስገባቸው እንችላለን። እስቲ አስቡት። በዚህ ሳምንት ብቻ፣ ከሁለት ሺ በላይ በእንግሊዝኛ የተፃፉ አዳዲስ የልብወለድ ድርሰቶች በኢንተርኔት አግኝቼ ኮምፒዩተሬ ውስጥ አስቀምጫለሁ - በ2012 እና በ2013 የታተሙ ተወዳጅ (bestseller) መፃህፍት ናቸው። በመቶ እና በሺ የሚቆጠሩ አዳዲስ መፃህፍት ማግኘት ይቅርና፣ ሦስት አራት አዳዲስ መፃህፍት ማግኘት ምን ያህል ብርቅ እንደነበር አታስታውሱም? ለነገሩ፣ ለብዙ ሰዎች ዛሬም ድረስ ብርቅ ነው።

የልብወለድ ድርሰቶችን ለጊዜው እንርሳቸው። ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ሃይስኩል፣ የሂሳብም ሆነ የተፈጥሮ ሳይንስ መማሪያ መፃህፍት፣ ከዩኒቨርስቲ የ‘ፍሬሽማን’ ትምህርት እስከ ማስተርስ ዲግሪ ድረስ፣ ከኤሌክትሪክ ምህንድስና እስከ ሕክምና፣ ከቢዝነስ ማኔጅመንት እስከ አለማቀፍ ዲፕሎማሲ… በመላው አለም እጅግ የሚፈለግ ውድ መፅሃፍ በየአይነቱ “በገፍ” ቢቀርብልን ብላችሁ አስቡ። ባለፉት ምዕተ አመታት የተፃፉ ዘመን የማይሽራቸው የሳይንስ መፃህፍትን ከፈለጋችሁ… ሞልቷል። አዳዲስ የዘመናችን ምርጥ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የመማሪያ መፃህፍትም እንደልብ ነው። እድሜ ለኢንተርኔት! በሺ ከሚቆጠሩት የትምህርት መፃህፍት መካከል፣ ለሙከራ ያህል ሁለት መቶ የሚሆኑትን ሰሞኑን ኮምፒዩተሬ ላይ ጭኛቸዋለሁ። አንዳንዶቹን ገለጥ ገለጥ አድርጌ አይቻቸዋለሁ። ባለፈው አመት ወይም ባለፉት ስድስት ወራት የታተሙ አዳዲስ የትምህርት መፃህፍትን እንዲህ እንደልብ ማግኘት “ተአምር” አይደለም? በቢዝነስ ጉዳዮች ዙሪያ እንደ ፎርብስ እና ዘ ኢኮኖሚስት የመሳሰሉ መፅሄቶች ሞልተዋል። የቴክኖሎጂና የሳይንስ ዘገባዎችን ወይም የጥናት ውጤቶችን ለመከታተልም፣ እንደ ፖፑላር ሜካኒክስ፣ ኔቸር፣ ዋየርድ፣ ናሽናል ጂኦግራፊ የመሳሰሉ መፅሄቶች አሉ። አዳዲስ የሰሞኑ እትሞቻቸውን በኢንተርኔት ወደ ኮምፒዩተሬ ገልብጬ አየት አየት እያደረግኳቸው ነው።

ስልጡን የፖለቲካ ባህል በቀጥታ ለማየት የሚፈልግ ካለም ምንም አይቸገርም። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ወይም ቃል አቀባያቸው ለጋዜጠኞች የሚሰጡትን መግለጫ በቀጥታ መከታተል ይችላል። በአሜሪካ፣ የኮንግረስና የሴኔት ምክር ቤት ውስጥ የሚካሄዱ ክርክሮችን፣ በዚያው ሴኮንድ በቀጥታ ሲሰራጩ መመልከትስ? ከአራቱ የሲ-ስፓን ቻናሎች መካከል እያማረጡ መመልከት ነው። የምክር ቤት አባላት፣ የአክብሮት ስነምግባርን ሳይጥሱ፣ የመንግስት ሚኒስትሮችንና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ወጥረው ሲያፋጥጡ ይታያሉ። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሰዎች እድሜ ይስጣቸውና፣ እንደየዝንባሌያችን እያማረጥን ያሻንን ያህል ማንበብና መከታተል የምንችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ሙሉ ትኩረታችንን የሚጠይቅ ትምህርታዊ መፅሃፍ ማንበብ፣… ምን ያህል እንደሚመስጥና እንደሚያስደስት ታውቁት ይሆናል። ግን በየመሃሉ አረፍ ብሎ መንፈስን ማደስ ያስፈልግ የለ? ለምሳሌ፣ ቀለል ያለ፣ ልብ አንጠልጣይ የልብወለድ ድርሰት ማንበብ፣ ጥሩ የመዝናኛ ዘዴ ነው። ምን ጠፍቶ! አምናና ዘንድሮ በአሜሪካ የታተሙ አዳዲስ የልብወለድ መፃህፍት ሰሞኑን “በገፍ” አግኝቻለሁ።

ግን፣ በ20ኛው ክፍለዘመን፣ በልብ አንጠልጣይ የልብወለድ ድርሰት ገንነው ከሚጠቀሱ ደራሲዎች መካከል አንዱ የሆነው ሚኪ ስፕሌን ትዝ አለኝ። የስፕሌን ድርሰት ባገኝ… ብዬ በኢንተርኔት ፈለግሁ። 13 ድርሰቶቹን አገኘሁና፣ በ5 ደቂቃ ውስጥ ሁሉንም ወደ ኮምፒዩተሬ ገለበጥኳቸው። አንዱን መርጬ አነበብኩታ። በእርግጥም ዘና አደረገኝ። በዚያው አጋጣሚ ግን፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ እና በፅሁፍ የተዘጋጁ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማሪያዎችን አይቻለሁ - ብዛታቸውና አይነታቸው እንዲህ ቀላል አይደለም። ከነባሮቹና ከአዳዲሶቹ የቋንቋ መማሪያዎች መካከል እየመረጥኩ ወደ ኮምፒዩተሬ መገልበጥ ነው የሚቀረኝ። በመላው አለም በጣም የሚፈለጉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሪያ መፃህፍትን ብቻ ሳይሆን፣ በድምፅና በቪዲዮ የተዘጋጁ አጋዥ መማሪያዎችን እንደ ልብ ማግኘት! “ምናለ፣ ይሄ ሁሉ እድል፣ ከአስር አመት ከሃያ አመት በፊትም በኖረ” ብዬ መቆጨቴ አልቀረም። ግን፣ አሁን መገኘቱም “ተአምር” ነው። ይልቅ፣ ይህን እድል ለመጠቀም መትጋት ነው የሚሻለው። ቀለል ባለ ልብወለድ መፅሃፍ ዘና ካልኩ በኋላ ወዲያውኑ ለሥራዬ በቀጥታ የሚጠቅመኝን መፅሃፍ ላነብ አልኩና… እንደአጋጣሚ ሃሳቤን ቀየርኩ። አልነገርኳችሁም እንጂ፤… በዚህ ሳምንት፣ ከልብወለድ ድርሰቶች በተጨማሪ፣ አንድ ሺ የሚሆኑ አዳዲስ “የሕይወት ታሪክ” መፃህፍትንም በኢንተርኔት ወደ ኮምፒዩተሬ ገልብጫለሁ።

ታዋቂው ሥራ ፈጣሪና ቢሊዮነር ሪቻርድ ብሮንሰን በ2011 ያሳተመው የግል የህይወት ታሪክ፣ የአሜሪካዊቷ ፖለቲከኛ ሳራ ፓይሊን፣ የበርማዊቷ የፖለቲካ መሪ አንሷን ሱኪ የህይወት ታሪኮች … በኢራቅ ጦርነት ብዙ አሸባሪዎችን በመግደል ሪከርድ የሰበረው ክሪስ ካይል ያሳተመው መፅሃፍ ሳይቀር… ብቻ ምን አለፋችሁ? በያዝነው የሰኔ ወር “ቤስትሴለር” ሰንጠረዥ ውስጥ ቁንጮውን ቦታ የተቆጣጠሩ መፃህፍት ሁሉ ቁጭ ብለው ለመነበብ ይጠብቃሉ። አንድ በአንድ አየኋቸው… የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ያዘጋጁት መፅሐፍ፣ የጆርጅ ቡሽ መፅሃፍ… እነዚህ ቆየት ያሉ ናቸው። ሌላ ጊዜ አነባቸዋለሁ። አዳዲሶቹንም አየሁ - ታዋቂው የአንጎል ቀዶ ህክምና ባለሙያ ዶ/ር ቤን ካርሰን ያሳተሙት መፅሃፍ ላይ ደረስኩ። በቅርቡ ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር በትልቅ አመታዊ ጉባኤ ላይ ንግግር እንዲያቀርቡ ተጋብዘው የነበሩት ጥቁሩ አሜሪካዊ ቤን ካርሰን፣ ኦባማን በመተቸት ባቀረቡት የግማሽ ሰዓት ንግግር “አጃኢብ” ሲባልላቸው እንደሰነበቱ አውቃለሁ። ከኦባማ ጋር የሚያለያያቸውን ሃሳብ ዶ/ር ካርሰን ሲገልፁ፣ ድሆችን እንደግፋቸው በሚል ሰበብ የአገሪቱ ዜጎች የመንግስት ጥገኛ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው በማለት ተናግረዋል።

አሜሪካ የተመሰረተችው ግን፣ ዜጎች ምንም ድሃ ቢሆኑ እንደየጥረታቸው ራሳቸውን ችለው የሚበለፅጉባት የነፃነት አገር እንድትሆን ነው ይላሉ - ዶ/ር ካርሰን። ይህን ሃሳባቸው ለማስረዳትም ነው አዲስ መፅሐፍ ያሳተሙት። ሃብታሞችንና ድሆችን የሚለያቸው ምንድነው? ዶ/ር ካርሰን ስለ ድህነትም ሆነ ስለ ሃብታምነት ቢናገሩ ያምርባቸዋል። ያለፉበት ሕይወት ነው። ከችጋር ወደ ብልፅግና እንዴት እንደተሸጋገሩ መነሻና መድረሻውን ያውቁታል። መፅሃፋቸውን አግኝቼ ላነበው ከተዘጋጀሁ በኋላ ነው፣ ካሁን በፊት ያሳተሟቸውን የመፃህፍት ዝርዝር ያየሁት። የመጀመሪያው መፅሃፍ “ጊፍትድ ሃንድስ” በሚል ርዕስ የታተመ ነው። ርዕሱን አስታወስኩት። መፅሃፉን ባላነበውም፣ ፊልሙን አይቼዋለሁ። ለካ፣ ኩባ ጉዲን የተወነበት ያ ምርጥ ፊልም፣ በዶ/ር ቤን ካርሰን የህይወት ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት፣ የሕይወት ታሪካቸውን ባሰፈሩበት መፅሃፍ ውስጥም፣ ወደ ኋላ መለስ ብለው በድህነትና በ“ደደብነት” ያሳለፉትን የልጅነት ጊዜ ይተርካሉ። ስኬታማ ሰው ለምልክት ያህል በማይታይበት የድሆች ሰፈር ውስጥ ነው፣ ሕፃኑ ቤን ካርሰን ያለ አባት ያደገው። “እንደ እገሌ ስኬታማ እሆናለሁ” የሚያስብልና በአርአያነት የሚጠቀስ ሰው አልነበረውም - በቤተሰቡም ሆነ በሰፈሩ ውስጥ። ያልተማረችና ማንበብ የማትችል የካርሰን እናት፣ ሁለት ልጆቿን ለማሳደግ ያላየችው መከራ የለም። የሃብታሞችን ሰፈር ስታካልል ነው የምትውለው።

የሃብታሞችን ቤት በማፅዳት በምታገኛት አነስተኛ ገቢ ካርሰንና ወንድሙ ፆም እንዳያድሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከትምህርት እንዳይርቁም ከንጋት እስከ ምሽት ትሰራለች። የእለት ተእለት ልፋቷ ትዕግስትን የሚፈታተን ቢሆንም፣ እጅግ የሚከነክናትና የሚያንገበግባት ግን፣ የድካሟን ያህል ውጤት አለማየቷ ነው። ልጆቿ፣ በየእለቱ ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸው ባይቀርም፣ ጠብ የሚል እውቀት አልቀሰሙም። ካርሰን እንደ ወንድሙ ክፍል ውስጥ “ሲማር” ይውላል፤ አስተማሪ አንዳች ጥያቄ ሲሰነዝር፣ ሌሎቹ ተማሪዎች መልስ ለመስጠት ይሻማሉ - እውቀታቸውን ለማሳየት። ግን፣ ካርሰን ሲጠየቅ ማየትም ያጓጓቸዋል - መመለስ ሲያቅተው ወይም ከጥያቄው ጋር የማይገናኝ ነገር ሲዘባርቅ መሳቅ ለምደዋል። ፈተና ሲመጣ፣ ካርሰን ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር አብሮ ይፈተናል። ተማሪዎች የፈተና ውጤታቸውን በኩራት ይናገራሉ፤ 25 ከ25 የሚደፍን ይኖራል፣ አነሰ ቢባል 20 የሚያመጣም ይኖራል። ካርሰን ድምፁን ዝቅ አድርጎ የራሱን ውጤት ይናገራል። አስተማሪዋ በደንብ አልሰማቸውም… “Nine?” በጣም ጥሩ ነው፤ 9 ከ 25? በጣም ተሻሽለሃልሳ! አለችው... ደስ ብሏታል። ካርሰን አስተማሪዋን ሊያርማት ይሞክራል - “Nine” ሳይሆን፣ “None” በማለት። ከፈተናው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱንም በትክክል አልመለሰም፤ ዜሮ ነው ያመጣው። እንደተለመደው ተማሪዎቹ ይስቁበታል። ሲስቁበት አይከፋውም።

ራሱም ቢሆን፣ “ትምህርት አይገባኝም፣ ደደብ ነኝ” ብሎ በግልፅ ይናገራል። እናቱ ግን በዝምታ አታልፈውም። “ደደብ አይደለህም፤ አንጎል አለህ አይደለም?” ትለዋለች። “አዎ” ይላል እያመነታ። “ስለዚህ፤ አንጎልህን ተጠቀምበት። አለም ሁሉ በእጅህ ናት” ትለዋለች። ባትማርም፣ በጣም አስተዋይና ብልህ እናት ናት። የካርሰን እናት፣ ልጆቿ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ከምር ታምናለች። እንዴት ስኬታማ እንደሚሆኑ ነው ያላወቀችው። ማሰብ ማሰላሰሏን ግን አላቋረጠችም። የሰፈሯን የድህነት አኗኗር በደንብ ታውቀዋለች። የሃብታሞች ሰፈር ሄዳ ቤት ስታፀዳም አኗኗራቸውን ትመለከታለች። ድሆቹንና ሃብታሞቹን የሚያለያቸው ምንድነው? አስተዋይ መሆኗ ጠቀማት። አንድ ቀን፣ በሃብታም ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሰፊውን ክፍል እያፀዳችና ቴሌቪዥን የተቀመጠበትን አካባቢ እየጠራረገች ሳለ… ተገለጠላት። ተደራርበው የተቀመጡት መፃህፍት ቴሌቪዥኑን በከፊል ከልለውታል። አንዳንዶቹ መፃህፍት ገለጥ ገለጥ ተደርገው ተቀምጠዋል። ቀና ስትል… ያን የሚያክል ሰፊ ክፍል፣ ከወለል እስከ ጣራ ድረስ… መደርደሪያው ሁሉ በመፃህፍት ተጠቅጥቋል። በቃ! ገባት። ያን እለት በየቦታው ለሥራ ስትደክም ውላ ማታ ወደ ቤት ስትመለስ፣ ካርሰንና ወንድሙ አሮጌ ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጠው አገኘቻቸው። ቴሌቪዥኑን አጠፋችው። “ከዛሬ ጀምሮ፣ ቴሌቪዥን የምታዩት በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ነው” አለቻቸው።

ለምሳሌ፤ የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር ማየት ይችላሉ። “ሁለት ቀን ብቻ? ሌላውንስ ጊዜ ምን እንሰራበታለን?” ብለው ጠየቁ። “ይህንን ጥያቄ ነበር ከናንተ የምጠብቀው። ምን እንደምታደርጉ እነግራችኋለሁ። ቤተመፃህፍት ትሄዳላችሁ። በሳምንት ሁለት መፅሃፍ ታነባላችሁ” ስትላቸው፣ የምሯን አልመሰላቸውም። መፅሃፍ ማንበብ የሚባል ነገር በእውናቸውም በህልማቸውም መጥቶላቸው አያውቅም። እንግዲህ ምን ይደረጋል? ከቤተመፃህፍት በውሰት መፅሃፍ ማምጣት የግድ ቢሆንም፣ የውሸት “አንብቤዋለሁ” ብሎ መመለስ እንደሚቻል ማሰባቸው አልቀረም። ሃሳባቸውን ያወቀች ይመስል፣ ሌላ ትዕዛዝ ጨመረችላቸው። “ያነበባችሁትን ቁምነገር፣ በየራሳችሁ አገላለፅ አሳጥራችሁ ትፅፉና ለኔ ትሰጡኛላችሁ” አለቻቸው። መፅሃፍ ማንበብ፣ ለካርሰንና ለወንድሙ ቀላል አልሆነላቸውም። ትግል ነው። ግን ደግሞ፣ መፃህፍቱ ውስጥ በሚያገኟቸው አስደናቂ ታሪኮችና እውቀቶች… ተገርመዋል። እስካሁን የማያውቁትና ጨርሶ ያልጠበቁት አይነት ልዩ ደስታ አግኝተውበታል። ብዙም ሳይቆይ፣ መፅሃፍ ማንበብ፣ “ግዴታ” መሆኑ ቀረ።

በንባብ ፍቅር፣ መፅሃፍ እንደያዙ ሌሊቱ ይጋመሳል። መፅሃፍ አንብቡ እያለች ስትወተውታቸው የነበረችው እናት፣ ቶሎ አንብበው በጊዜ እንዲተኙ መምከር ጀመረች። ካርሰን፣ “ደደብ” እንዳልሆነ ገባው። የሳይንስም ሆነ የሂሳብ፣ የቋንቋም ሆነ የታሪክ ትምህርቶችን ሁሉ በቀላሉ መረዳት እንደሚችል ሲያይ፣ ለማመን ከብዶት ነበር። ግን፣ የፈተና ውጤቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሻሽሏል። በሁለተኛው አመት ደግሞ፣ ከክፍሉ አንደኛ ወጣ። ከዚያም ከትምህርት ቤቱ አንደኛ በመሆን ተሸለመ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በመላ አሜሪካ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን አወዳድሮ ወደሚቀበለው ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ገባ - በከፍተኛ ውጤት ነፃ የትምህርት እድል ተሰጥቶት። በቃ፤ የሚያቆመው አልተገኘም። ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ገብቶ፣ የአንጎል ቀዶ ህክምናን በማጥናት ተመረቀ። በሳይንሳዊ ጥናቶች ዙሪያ፣ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲን የሚስተካከል የትምህርት ተቋም በአለማችን የለም። 33 የዩኒቨርስቲው ተመራቂዎችና አስተማሪዎች የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። በዚህ ዩኒቨርስቲ ተምሮ መመረቅ ራሱ፣ ለካርሰን ትልቅ ስኬት ነው።

ግን አልበቃውም። በየአመቱ ከሶስት መቶ በላይ ከባድ የቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት የብዙ ሰዎችን ህይወት አድኗል። ይህም ብቻ አይደለም። በህፃናት የአንጎል ህክምና ላይ፣ መፍትሄ ላልነበራቸው በሽታዎች አዳዲስ የህክምና ዘዴዎችን በመፍጠር በመላው አለም በቀዳሚነት የሚጠቀስ ታላቅ ሰው ለመሆን በቅቷል - ዶ/ር ቤን ካርሰን። ሰዎች በራሳቸው ጥረት፣ ከ“ደደብነት” ወደ እውቀት ማማ መምጠቅ፣ በእውቀታቸውም ከድህነት ወደ ብልፅግና መሸጋገር እንደሚችሉ ይጠረጠራል? በቤን ካርሰን የጀግንነት ታሪክ ውስጥኮ ቁልጭ ብሎ ይታያል። አርአያነቱ፣ ለሁላችንም ነው። እውቀትን እየጨበጡ ወደ ስኬት መጓዝ ይቻላል። እስካሁን በጥበበኛ ሰዎች ጥረት የተገኙ አስደናቂ እውቀቶችን በስፋት መቅሰም የምንችለው ከመፃህፍት ነው። አዳዲስ እውቀቶችን ለመጨበጥ የሚያስችሉ ሳይንሳዊ ዘዴዎችንም ከመፃህፍት ውስጥ እናገኛለን። ያኔ፣ እንደ እውቀታችን መጠን እየሰራን ስኬትን እናጣጥማለን - በቃ… የጥረት ጉዳይ ነው፤ የንባብን ፍቅር የማዳበር ጉዳይ ነው። በእርግጥ፣ ሁሉም ሰው እንደ ልብ ጥሩ ጥሩ መፃህፍት ያገኛል ማለት አይደለም። የምንፈልገው አይነት መፅሃፍ ማግኘት… ለብዙዎች ብርቅ ነበር - እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ቤተመፃህፍት ያላቸው ከተሞች ስንት ቢሆኑ ነው? እነሱም ቢሆኑ፣ የያዙት የመፃህፍት አይነትና ብዛት ቢቆጠር ኢምንት ነው። ዛሬ ግን፣ ያ ሁሉ “የመፅሃፍ ችጋር” ተረት እየሆነ ነው። የ“ኮፒ ራይት” ጥያቄ አነጋጋሪ ቢሆንም፣ በየትኛውም የእውቀት መስክ፣ በየትኛውም የእውቀት ደረጃ… ማማረጥ እስኪቸግረን ድረስ እልፍ መፃህፍት ማግኘት እንችላለን - በኢንተርኔት። ዛሬ፣ በመፃህፍት እጥረት ማሳበብ አይቻልም። የእውቀትና የስኬት በር፣ እዚሁ አጠገባችን መጥቷል። አንኳኩቶ መክፈትና መግባት ነው የኛ ድርሻ። በሩ ኮምፒዩተር ነው። ኢንተርኔትን በመጠቀም እናንኳኳ። መክፈቻው፣ የ“እንግሊዝኛ” ቋንቋ ነው። አብዛኞቹ መፃህፍት በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ ናቸውና።

Read 3541 times