Saturday, 29 June 2013 09:27

ተቃዋሚዎች የመንግስት የቤት ፕሮግራም አይሳካም የሚል ጥርጣሬ አላቸው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውን የቤቶች ልማት ፕሮግራም ምዝገባ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የተጠየቁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ፕሮግራሙ የሚሳካ አይመስለንም ይላሉ፡፡ በርካታ የቤት ተመዝጋቢዎችም መንግስት ቃል የገባው የቤቶች ግንባታ ይሣካ ይሆን የሚል ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ይሄንን መነሻ በማድረግ የቤት ፕሮግራሙን በተመለከተ የተቃዋሚ አመራሮቹ አይሳካም የሚሉበትን ምክንያት በዝርዝር እንዲያስረዱን ጠይቀናቸው የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡


“እንደ ብሄራዊ ሎተሪ በእጣ ቤት ማደል የኢኮኖሚ ስራ ነው ብዬ አላምንም”
አቶ ሙሼ ሠሙ
የባንክ ባለሙያና የኢዴፓ ሊቀመንበር
መጀመሪያ ማንም ዜጋ ቤት ማግኘት ያለበት በጥረቱ ነው ብዬ ነው የማስበው እንጂ ልክ እንደብሄራዊ ሎተሪ በእጣ ቤት ማደል የኢኮኖሚ ስራ ነው ብዬ አላምንም፡፡ መጨረሻ ላይ ማጣፊያው ያጥራል፡፡ መጀመሪያውኑ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሲታደሉ መንግስት እያንዳንዱ ቤት ፈላጊ የተወሠነ ገንዘብ አጠራቅሞ ባጠራቀመው ገንዘብ ላይ ድጋፍ ተደርጐለት በረጅም ጊዜ ብድር ቤት የሚያገኝበት እድል ቢያመቻች ኖሮ ዛሬ የሚሠሩት ቤቶች አጣብቂኝ ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡ መንግስት ከዚህ አኳያ ሊገጥመው የሚችለው ችግር የገንዘብ አቅም ጉዳይ ነው፡፡ ገንዘቡ ከአሁን በኋላ ተጠራቅሞ ነው እንግዲህ ሠዎች የቤት ባለቤት የሚሆኑት። በዚህ መሀል መገንባት አለበት፡፡ ቤቱን ለመገንባት ደግሞ ወደ ብድር መግባት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትን አቅም እናውቀዋለን - 1.2 ሚሊዮን ቤት ለመገንባት የሚያስችል አቅም ሊፈጥር የሚችል ገንዘብ የተለየ ፈንድ ካላገኘ በቀር ከየትም ሊያመጣ አይችልም፡፡ ገንዘብ ማተም ውስጥ ካልገባ በቀር ወይም ደግሞ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ ከቻይናና ከህንድ የሚያገኝበትን ሁኔታ ካላመቻቸ በቀር እነዚህን ቤቶች በሰባት አመት ውስጥ ሊገነባ የሚያስችለውን አቅም ሊያገኝ አይችልም፡፡ ሁለተኛው ይሄንን ቤት ለመገንባት የሠው ሃይል ጥያቄ አለ፡፡ 1.2 ሚሊዮን ቤቶች ለመገንባት በቤት ግንባታ እውቀት ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሠዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሠዎች ከየት ነው የሚመጡት? ሶስተኛው ደግሞ የተፈጥሮ ሃብት ነው - መሬት፣ ድንጋይ፣ ብረት፣ ሲሚንቶ፣ ጠጠር የመሣሠሉት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከየት ነው ሊመጡ የሚችሉት? እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይሟላሉ ብዬ አላምንም፡፡ የተባለው ፕሮግራምም ይሣካል ብዬ አልገምትም፡፡
“መንግስት የዜጐች ቤት ሠሪ ሊሆን አይችልም”
የተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ
የፓርላማ አባል- የአንድነት ፓርቲ አመራር
እኔ በግሌ ትርጉም የሚሠጥ ነው ብዬ አስቤውም አላውቅም፡፡ የህዝቡን ስሜት ለመግዛት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲያስቡ የመጣላቸው እና የታያቸው አንዱ መንገድ ነው፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ነገር በዋናነት የሃገር ውስጥ ቁጠባ አነስተኛ ነው ከሚለው በመነሣት የመጣ ነው፡፡ እርግጥ ነው የሃገር ውስጥ ቁጠባ አነስተኛ ነው ነገር ግን ህዝቡ ዝም ብሎ አይቆጥብም። ስለዚህ መንግስት ህዝቡ እንዲቆጥብ አንድ ነገር ራቅ አድርጐ ሠቅሎ ማሣየት ነበረበት፡፡ የቤቶች ፕሮግራሙ ዋና አላማው በሃገር ውስጥ ያለውን የቁጠባ ባህል ከፍ ማድረግ ነው፡፡
ስለዚህ ቤት በማግኘትና ባለማግኘት ቁም ነገር ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ሣይሆን የሃገር ውስጥ ቁጠባን ለማሣደግ ተብሎ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን በመርህ ደረጃ መንግስት የዜጐች ቤት ሠሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሣሌ ባለፈው ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ መቶ ሺህ ቤቶች ሠርተናል ብለው በኩራት ተናግረዋል፡፡ እነሱ ጉልበትና ስልጣን ስላላቸው የሠው ስራ ቀምተው በመስራታቸው ሊኩራሩ አይገባም፡፡ በ1998 ለተመዘገቡ 450 ሺህ ቤት ፈላጊዎች በስምንት አመት ጊዜ ውስጥ ቤቶች ሰርተን እናጠናቅቃለን ብለው ይኸው ስምንት አመት አልፎ እንኳ 100ሺህ ቤቶች መስራት አልቻሉም፡፡ ጅምሮቹን ጭምር ነው 100 ሺህ ቤቶች ሠርተናል ያሉት። ለእነዚህ ቤቶች አንድ ጊዜ መሠረት በመጣል፣ አንድ ጊዜ በማስመረቅ ሌላ ጊዜ ቁልፍ በመስጠት አምስት ጊዜ ይወራና 500ሺህ ያስመስሉታል። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተሠሩት ቤቶች 100ሺህ ናቸው - እስክስታው ዘፈኑ ግን ሚሊዮን ነው። በተቃራኒው ግን በማህበር በመሣሠሉት ከዚህ ከላይ ቤቶች ተሠርተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር መታየት ያለበት ፕሮግራሙ አንደኛ አላማው ለዜጐች ቤት መስጠት ሣይሆን የቁጠባ ባህሉን ማበረታታት ነው፡፡ ግን በየአመቱ ትንሽ ትንሽ ነገር እየሠጡ በማሣየት ሠዎች በተስፋ እንዲቆጥቡ ይደረጋል፡፡ በዚህ ማሣያው ቁጠባውን ያቋረጠ ይሠረዛል ይላል፡፡ ቤቱን ይሠሩታል አይሠሩትም ለሚለው በእርግጠኝነት አይሠሩትም፡፡ የሆነ አስማት እንኳ ተፈጥሮ ቢሠሩት ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ሌሎች በሪል ስቴት ውስጥ ተሣትፈው ይሄን ሊያደርጉ የሚችሉ ሠዎችን ስራ እየቀሙ ነው እንሰራለን የሚሉት፡፡ መንግስት ዜጐች በተመጣጣኝ ዋጋ ቤት ማግኘት አለባቸው የሚል አቋም ሊይዝ ይችላል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ቤትን ውድ የሚያደርገው አንደኛው መሬት ነው - ራሱ ሲሠራ በነፃ መሬት ይወስዳል፡፡ የግንባታ ግብአትም ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በርካሽ ዋጋ የመስራት አቅምን ለራሱ ያመቻቻል፡፡ ይህን አቅም ወደ ግል ሴክተሩ አዘዋውሮ እነዚህን ማበረታቻዎች ሠጥቶ ሜዳውን ለነሡ ቢለቅ ነበር የሚሻለው፡፡ አሁን ግን ፕሮግራሙን ወደ ገጠር አካባቢዎችም ለማስፋት እቅድ ያለው ይመስላል። በየቦታው የተከፈቱ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችም ለዚህ የተመቻቹ ናቸው፡፡ ሠው አሁን ቆጥቦ በኋላ ባይደርሠው ገንዘቡን መውሠድ እንደሚችልም አማራጭ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ቆጣቢው ኋላ ላይ የሚያገኘው ገንዘብ በዋጋ ንረት የተጐዳና የመግዛት አቅም የሌለው ነው የሚሆነው፡፡

“መንግስት የሚመረጠው ነጋዴ እንዲሆን አይደለም”
አቶ ቡልቻ ደመቅሣ
የፋይናንስ ባለሙያና የመድረክ አመራር አባል
የቤቶች ፕሮግራሙ የተዘረጋው የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ነው፡፡ የእነዚህ ፕሮግራም ተሣታፊዎች የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ ነው የሚደረጉት፡፡ ለምሣሌ አንድ ሠው ቤት ልስራ ብሎ 40/60 የሚባለው ውስጥ ቢገባ መጀመሪያ ማረጋገጥ የሚፈልጉት የኢህአዴግ አባል መሆኑን ነው፣ ስለዚህ ይሄ ጠቃሚ ሳይሆን ጐጂ ነው። መንግስት የሚመረጠው ነጋዴ እንዲሆን አይደለም። ፍርድ እንዲሠጥ፣ የፖሊስ ስራ እንዲሠራ፣ ጉምሩክ እቃ ሲገባ ቀረጥ እንዲያስከፍል፣ መሬት በደንብ እንዲለማ፣ የኢኮኖሚ ልማት እንዲመጣ ነው እንጂ ንግድ ውስጥ ገብቶ እንደ ተራ ነጋዴ ለመቸብቸብ አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ደግሞ ይሄ ሃገራችንን ይጐዳል፡፡ የአለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ያልቻልነው እኮ መንግስት ከንግድ ውስጥ መውጣት ባለመቻሉ ነው፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ አለመግባት ደግሞ ለዘለቄታው ጉዳት አለው፡፡ ለኢህአዴግ ንግድ ፖለቲካ ነው። በንግዱ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት ይችላሉ፡፡ አሁን ለህዝቡ ቃል እንደገባው ተሣክቶለት ቤቱን ቢሠራም ትክክል አይደለም፡፡ ገንዘብ ከዚህ ሁሉ ሠው መሠብሠቡ በራሱ ቀላል አይደለም። የመንግስት ዋነኛ ስራው መሆን የለበትም፡፡ የመንግስት ሠራተኛ የሚቀጠረው የመንግስት ስራ ተብለው የተለዩትን ለመስራት ብቻ ነው፡፡ ግብር መሠብሠብ እንጂ ከህዝቡ ጋር እየተጋፉ ገንዘብ ለማስገባት አይደለም፡፡ አሁንም አጥብቄ የምናገረው ይህ የመንግስት ተግባር አለመሆኑን ነው፡፡ የመንግስት ሥራ ዳር ድንበር መጠበቅ፣ ፍትህ ማስፈን፣ መንገድ መገንባት እንጂ ብር እያበደሩ ቤት መስራት አይደለም፡፡

“የቤት ፕሮግራሙ ለቀጣዩ ምርጫ የታለመ ይመስላል”
ዶ/ር መረራ ጉዲና
የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር እና የመድረክ አመራር አባል
መንግስት ብዙ ድስቶችን ጥዶ ነው የሚንቀሣቀሰው፡፡ አንደኛው ድስት ይሄ መሆኑ ነው፡፡ ዋናው ግን ይሄ የቤት ፕሮግራም ለ2007 ምርጫ የታለመ ይመስላል፡፡ የዚያን ጊዜ እኛን ካልመረጣችሁ ቤት አታገኙም ሊሉ ይመስላል ዳር ዳር የሚሉት፡፡ አሁን እንግዲህ ወደ 2 ሚሊዮን ቤት ነው እንሰራለን ያሉት፡፡ ይሄ ደግሞ በኛ አቅም አጠያያቂ ነው፡፡ ደግሞ ሁሉን አይነት ሠው ነው የሚመዘግቡት፡፡ ውጤቱን እንግዲህ ውሎ አድሮ ማየቱ ይሻላል፡፡ የኔ ጥርጣሬ ግን የ2007 ምርጫን ታሣቢ አድርገው ነው የሚል ነው፡፡ ጨዋታው ቀላል አይደለም፡፡
ቤት መስራት ብቻ ሣይሆን ከዚያ ጋር ብዙ የተያያዙ ነገሮች አሉ፡፡ መሠረተ ልማቱ መጨመር አለበት- ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ ስልክ አለ። እኒህን ሁሉ ማሳካት ከቻሉ ጥሩ ነው፣ ግን አይመስለኝም፡፡

Read 3604 times