Saturday, 29 June 2013 09:19

የስምንት ሚኒስትሮች ሹመት ሰሞኑን ይፀድቃል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(27 votes)

        የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ዛሬ ግምገማ ያካሂዳል

የኢህአዴግ 36 ከፍተኛ መሪዎችን ያካተተው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመታዊ ግምገማ ለማካሄድ ዛሬ የሚሰበሰብ ሲሆን የስምንት ሚኒስትሮች ሹም ሽርና ሽግሽግ በሚቀጥለው ሳምንት ለፓርላማ ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡ ለሹመት የሚቀርቡት ባለስልጣናት፤ የፍትህ ሚኒስትር፣ የከተማና ኮንስትራክሽን ልማት ሚኒስትር፣ የግብርና ሚኒስትር፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ የገቢዎች ሚኒስትር የደህንነትና መረጃ ሚኒስትር፣ የደንና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሁም በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ናቸው ተብሏል፡፡ አንዳንዶቹ ሹምሽር እርምጃዎች ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር እንዲዛወሩ በተደረጉ ባለስልጣናት ምትክ የሚካሄድ ሽግሽግ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የእጩ ተሿሚዎችን ማንነት ለማወቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ዛሬ የሚካሄደው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ከሹምሽሩ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢታሰብም፣ የሰብስባው ዋና ርዕሰ ጉዳይ አመታዊ ግምገማና አመታዊ እቅድ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት አስፈፃሚ አካል የመቆጣጠር ስልጣን ያለው የአገሪቱ ፓርላማ ጠንካራ የቁጥጥር ሃላፊነቱን በተግባር ማሳየት እንደጀመረ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭምር ቢናገሩም፤ በሚኒስትሮች ሹመት ዙሪያ ግን የቀድሞው አሰራር አልተሻሻለም፡፡ በተለያዩ ዲሞክራሲያዊ አገራት ውስጥ የእጩ ሚኒስትሮች ማንነት በይፋ ታውቆ ለበርካታ ሳምንታት በፓርላማና በዜጐች ዘንድ ውይይት የሚካሄድበት ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን የተሿሚዎች ማንነት የሚገለፀው ሹመታቸው በሚፀድቅበት እለት ነው፡፡

የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ዛሬ ስብሰባ እንደሚያካሂድ የገለፁት የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ የስብሰባው ዓላማ የዓመቱን የስራ አፈፃፀም በመገምገም ድርጅቱ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የሚያካሂደውን ትግል አጠናክሮ ለመቀጠል በእቅዶች ላይ መወያየት ነው ብለዋል፡፡ የህዝቡን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ በማጐልበት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን፤ የህዝብ፣ የመንግስትና የድርጅት አቋሞች እንዲጠናከሩ፣ ችግሮች ያሉባቸውን ደግሞ አንጥሮ ለማውጣት ያለመ ስብሰባ ነው ብለዋል፡፡ በነባር ፖሊሲዎችና አሰራሮች ላይ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መክሮባቸው አቋም ከወሰደባቸው በኋላ፤ የማስፋት፣ የማጠናከርና የማጐልበት እንዲሁም ተጨማሪና አዳዲስ ዝርዝር የአሰራር አቅጣጫዎችን በመተለም በመጪው አመት እቅድ ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ብለዋል - አቶ ሬድዋን፡፡

Read 30947 times