Saturday, 29 June 2013 09:07

የህዳሴው ግድብ በቀን 2 ሚ. ዩሮ ገቢ ያስገኛል ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

       ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ለመቶ አመታት በየቀኑ 2 ሚሊዮን ዩሮ ከኤሌክትሪክ ሽያጭ እንደሚያስገባ ተገለፀ፡፡ ገቢው የኢትዮጵያዊያንን ህይወትና ኢኮኖሚ መልክ ይቀይራልም ተብሏል፡፡ ትላንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ላይ ማንዴላ የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ በቀረበው ጥናት፤ ግድቡ በየቀኑ የተጠቀሰውን ያህል ገቢ ከማስገኘቱም በላይ በጎርፍ አደጋ የሚጠቁትን እነ ሱዳንን ከጎርፍ አደጋና ከድርቅ ይታደጋል ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውሃ ሃብት ኢንስቲትዩት ምሁር ዶ/ር ይልማ ስለሺ፤ “Nile Hydrology and Ethiopian Dams, Great Ethiopian Renaissance Dam - a case study” በሚል ርዕስ ለሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች ባቀረቡት ጥናት፤ የግድቡ መገንባት ከኢትዮጵያ ሌላ ለሱዳንና ለግብፅ እንዲሁም ለአለም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀው፤ በተለይ ሱዳን ስትቸገር ለኖረችበት የጎርፍ አደጋ ፍቱን መፍትሄ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ ጎርፍንና ፍሰቱን በመቆጣጠር ከአደጋ ከመከላከሉም በላይ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በማጠራቀም፣ ሱዳንና ግብፅ በድርቅ ወራት ሊመጣባቸው ከሚችለው የውሃ ችግር ራሳቸውን ለማዳን ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ግድቡ ካሉት ጠቀሜታዎች መካከል በየአመቱ በትነት የሚባክነውን ውሃ መቆጠብ አንዱ ሲሆን ድርቅን ለመቋቋም፣ አዲስ የሀይል እድሎችን ለመጠቀም፣ ደለልን ለመቆጣጠርና መሰል ጥቅሞች እንዳሉት ተጠቁሟል፡፡ ግድቡ ከድንጋይ ከሰልና ከነዳጅ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ በመቀነስ የአለምን የሙቀት መጠን (global warming) ለማስተካከል ትልቅ ሚና እንዳለውም ተገልጿል፡፡ በሲምፖዚየሙ ወደ አምስት የሚጠጉ አባይን እና ታላቁን የህዳሴ ግድብ የተመለከቱ ጥናቶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን አንድ ምሁር ሲምፖዚየሙን አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የዛሬው ሲምፖዚየም የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ መንግስታት በቅርበት በመወያየትና ለችግሮቻቸው እልባት በመስጠት ወደፊት የሚራመዱበትን አቅጣጫ ለመወሠን ይረዳቸዋል” ብለዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩን አቶ አለማየሁ ተገኑን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣አምባሳደሮች፣ባለድርሻ አካላትና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡ በሲምፖዚየሙ የተሳተፉት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ “ጥናቱ ቴክኒካል ቢሆንም ብዙ እንድናውቅ እና አንድ አቋም ስንወስድ በእውቀትና በመረጃ የተደገፈ እንዲሆን ይረዳናል” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላምና የልማት ኢኒስትትዩት ዋና ዳሬክተር አቶ ስብሃት ነጋም፤ ጥናቱ እጅግ አስተማሪ መሆኑን ጠቁመው፤ በአማርኛም ተተርጉሞ ቢሰራጭና ሁሉም ቢያውቀው ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Read 14120 times