Saturday, 22 June 2013 12:02

እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

Written by  አብደላ ዕዝራ abdiezra@yahoo.com
Rate this item
(4 votes)

“ሰዉ ባገሩ በወንዙ ማበድ መወፈፍ ካልቻለማ / ምን አገር ሆነ ያማ!” ጥበበኛ እንደልቡ ከገጠመኝ ለመሟገት፣ ዕዉነታዉን ቦርቡሮ የብርሃን ጭላንጭል ለመለጠጥ ያፈነግጣል፤ ርዕይ ይቋጥራል። “እንበድ” ሲል አረጋዊ እንደ መፈንከት ሳይሆን መገጣጠምን፣ የሃሳብ ወረርሺኝና - conformity - ከበባን እንደ መናድ ነዉ እንጂ።

ሂሳዊ ንባብ 
ክፍል ሶስት፥ የነቢይ ገሃድዘለል -
surrealistic - ግጥሞች
የነቢይን ግጥሞች ከማሰሴ በፊት ለመግባባት ሁለት እርከኖች መራመድ አለብኝ:: አንድ፥ surrealism ምን ማለት ነዉ? ሁለት፥ በአማርኛ ሥነፅሁፍ እነማን ወከሉት ? በደምሳሳዉም ቢሆን መልስ ይሻሉ። መንደርደርያዉ፥ በዚህ ስልት የተፃፉትን የነቢይ ግጥሞች ለማጣጣምና ለመገንዘብ እጅጉን ይበጃል።

ስያሜዉ
የ surrealism ገራገር ትርጉም ከዕዉነታ በላይ ማለት ነዉ። sur - ዲበ፣ በላይ ወይም ባሻገር፣ realism ዕዉነታነት። ለማቅለል ገሃድዘለል ማለትም ይቻላል። ዲበዕዉነታ በሃያኛ ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ የተከሰተ የጥበብና የስነፅሁፍ ስልት ነዉ፤ እንደ አንድ ንቅናቄም ይጤናል። ያልተለመደና የማይታመን ምስል በመቀሸር ህልምንና ኢንቁ - unconcious - ገጠመኝን ለመወከል ይጥራል። ከህልም፣ ከረቂቅ ራዕይ፣ ከእብደት፣ ከሰመመን፣ ከቅዠት ... ምስልና ሁነት ይጐነጉናል። ሆኖም ለመንፈሳዊ ህይወት መኖር ማረጋገጫ ሳይሆን፣ ግባቸዉ ንቃታችንን በማክረር ዓለምን መለወጥ ነዉ። ህልማዊ ምስልን ያባብላሉ፤ ከዕዉነታና ከህልም ቀላቅለዉ ይፅፋሉ። የሚጋፉ ቃላትና ቁሳቁስ በማጐራበት - juxstaposition - የሚያስጐመጅ ምስል እና ህብሩን የሚለዋዉጥ ቃላዊ ዉጤት ያስገኛሉ። አንድ ሀያሲ እንዳለዉ የድንጋይ ከሰል ማዕድንና ቦምብ ማጐራበት። አንድ ፍካሬዉ በማዕድን ጉድጓድ ፅልመት አቅጣጫ የሳተ ግለሰብ፣ የቦምብ ፍንዳታ ብልጭታ ለአፍታ ያጥበረብረዋል ሊሆን ይችላል።
ገሃድ-ዘለልነት በሥነፅሁፍ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃ፣ በስዕልና በሲኒማም ዐዉድ ይከሰታል። የልብስ ስፌት መኪና እና ዣንጥላ ከመክተፍያ ጠረጴዛ ላይ ማጋደም የመሰለ ትዕይንት፤ ገሃድ-ዘለሎች የማይጣጣም ቁሳቁስ በማጐራበት የፊልም ተመልካችን ማወክ ይሻሉ ትላለች Susan Sontag፥ Against Interpretation በሚለዉ መፅሃፏ። ፅንሰሃሳቡን በቀላሉ መጦቀም ይቻላል። “ትንኝም ለሆዱ፥ ዝሆንም ለሆዱ እወንዝ ወረዱ” ይህ ምሳሌያዊ ንግግር ደጋግመን ስለሰማነዉ ዶለደመ እንጂ ካጤኑት ይናደፋል:: የዝሆንና የትንኝ ጐን ለጐን መሄድ
- juxtapose - ልብ ካልነዉ የማይሆን ምስል ነዉ። በርሜል የሚሞላ ዉሃ ለመምጠጥ ኩምቢ ያለዉ ዝሆን ወንዝ ሊወርድ ይችላል፤ ትንኝ - ጭልፋ ዉሃ የሚያሰምጣት - ግን ጠብታ ፈሳሽ ከአካባቢዋ አታጣምና ወንዝ ደመኛዋ ነዉ። ይህ ገሃድዘለል ምስል ግን ሰዉ ለዕለት ኑሮዉ፣ ትንሹም ትልቁም እንደሚዳክር የጐላበት ነዉ። absolute reality ፍፁም ዕዉነታ ይሉታል። “ላም አለኝ በሰማይ፥ ወተቷን የማላይ” ይህ ከህልም፣ ከቅዠት የፈለቀ ምስል፣ ከዕዉነታ በላይ ነዉ፤ ጥልቀት አለዉ፤ የኛ እየመሰለን፣ ከመዳፋችን ያልገባ አልያም የህልም እንጀራ ሲደበዝዝ፣ እየተደናገርን ኑሮ ላይ ምላሳችንን አዉጥተን ለመዝለቅ እናፌዛለን። ትዝብትም ነዉ። “ድሃ በህልሙ ቂቤ ባይጠጣ፥ እከክ ይጨርሰዉ ነበር” ይህ መራር ዲበዕዉነታ ምስል ነዉ። ንቁ አዕምሮ የገደበዉን ድንበር በማፍረስ፣ ኢንቁ ህልም የመሰለ ምኞት ዉስጥ በመንሳፈፍ ሽንብራ ቆረጣጥሞ የሚያድረዉን፣ ቅቤ እንደ ካህን ትንቢት የራቀዉን ሰዉ፣ የቆዳዉ ልስላሴ በምን ይደረስበት? ህልም ከዕዉነታ በላይ ይጐተጉተናል። በዚህ ፈለግ ገድለ ሰማዕታት፣ የግዕዝ ቅኔና ተረቶቻችንን መቃኘት ብንጀምር፣ ለብዙ የፈረንጅ ... ism ማንፀርያ የሚሆን የሚፈለፈል ትዉፊት አናጣም። ለመቋጨት አንድ ዝነኛ ገሃድዘለል ስዕል እንመልከት። The Persistance of Memory [የትዉስታ እልህ] ዕዉቁ Salvador Dali የሳለዉ ነዉ።
ብዙ የተባለለት ገሃድዘለል ስዕል ነዉ። እንደታጠበ ፎጣ ርሶ የሚያንጠባጥብ የኪስ ሰዓት፣ ወይም እንደ አይብ ለስልሰዉ መቅለጥ የጀመሩ ሰዓቶች፤ አንደኛዉ እንድያዉም መሽተት የጀመረ ዳቦ ይመስል ጉንዳን ወረዉታል። ይህ ከኢንቁ አዕምሮ የተንሳፈፈ ህልማዊ ምስል ነዉ። አንዳንዶቹ ሲተረጉሙት እነዚህ እርጥብ ቀላጭ ሰዓቶች የጊዜን ግትርነትና አይበገሬነት አለመቀበልን፣ ለተሻለ ገሃድ መታከትን ያደምቃል ባይ ናቸዉ። ጥልቅ ትንታኔዉን ለሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህና ለሰዓሊ በቀለ መኰንን መተዉ ይመረጣል። እንድያዉም ሰዓሊ እሸቱ፥ የገብረክርስቶስ ደስታን ሥዕላዊ ዘይቤን ሲተነትን የጥበብ ገላጭነትን አራት ጠገግ ተጠቅሞ አምስተኛዉን ገሃድ-ዘለልነትን ግን አልሞከረም ይላል። እሸቱ surrealismን ሕልም-እዉነታነት ብሎታል፤ ለስዕል ይስማማል። [የኢትዮጵያ ጥናት መፅሔት፥ ቅፅ 37 ቁ2 ፥ ገፅ 62-63 ] መስፍን ሀብተማሪያም የደበበ ሠይፉን ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ የግጥም ስብስብ ሽፋን የሳለዉ ድንቅ በሆነ ዲበዕዉነታ እሳቦት ነዉ። የDaliን ለስላሳ ቀላጭ ስዕሎች ያስታዉሰናል። የተጓዥ ጥላ በሰዉየዉ ኩታ ጫፍ ታስሮ ብድግ ብሎ ሊከተለዉ፣ ከዝርግነት ለማቅናት የሚጣጣር የተማፅኖ እንቅስቃሴ ነዉ።

ገሃድዘለል ስልት በአማርኛ ሥነፅሁፍ፥ እንደ መግቢያ
አንዳንድ የስብሀት ገ/እግዝአብሔር አጫጭር ልቦለድ ከህልም ከቅዠትም ተነስተዉ እንደ “አጋፋሪ እንደሻዉ” እንደ ”ስምንተኛዉ ጋጋታ” የገሃድ-ዘለልነት ጠባይ ታይቶባቸዋል። የአበራ ለማ “እቴሜቴ” አጭር ልቦለድ ገሃድና ቅዠት ተቀላቅሎባት፣ መገለል የጐዳት፣ ሥጋት የከበባት ገፀባህርይ ተቀርጾበታል። ላባቸዉ እላያቸዉ ላይ እንደ ጢስ በኖ ካለቀ ሁለት ዶሮዎች ትመካከራለች። ህፃኑ አኝኮ የጣለዉን ኮክ አንስታ “... ደጋግማ አገላብጣ አየችዉ። ቋንቋ ኖሮት ድምፅ አዉጥቶ ባያናግራትም፣ በፀጥታዉ አንድ ነገር እንደ ነገራት ሁሉ፣ ካካ!... ብላ ሳቀች” [የማለዳ ስንቅ፥ ገፅ 77] ከዕዉነታ በላይ፣ ኢንቁ አዕምሮዋ ዉስጠቱ የተበረበረበት ድንቅ ልቦለድ ነዉ።
አዉግቸዉ ተረፈ ታሞ ያዝ ለቀቅ ሲያደርገዉ እብደት ዉስጥ እያለ የፃፈዉን ስንዱ አበበ ከስር ከስሩ በመሰብሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ሥነፅሁፍ ገሃድዘለሎች እንደሚሉት ያለንቁ የአዕምሮ ቁጥጥር በ - automatism - ጥበብ የተፃፈ ልቦለድ አስነብባናለች። “ህልም ማየት ስጀምር ነብይ የሆንኩ መሰለኝ። ... አንድ ቤተክርስትያን አገኘሁ። ደረጃዉ ላይ ጠጅ ይሸጣል። ጠጅ ቀጂዉ ራሱን ተላጭቷል። እዉስጥ እየተቀደሰ እሱ ጠጅ ይቀዳል። እኔ ስገባ ብርጭቆ አቀረበልኝ እና ሊቀዳልኝ ሲል ጠጁ ብርጭቆ ዉስጥ አልገባ ይለዋል። ሌላ ብርሌ ያመጣል ...” [እብዱ፥ ገፅ 7+8] ገፀባህሪዉ ከንቁ አዕምሮዉ ተላቆ በየቀኑ የሚገጥመዉን ፣ ያዝ-ለቀቅ እያደረገዉ የፃፈዉ ያስደምመናል። ደምሴ ፅጌ በፍለጋ ልቦለድ ቅድስት በማኅበራዊና በወሲባዊ ጥሪ ተወርራ አዕምሮዋን መቆጣጠር ሲሳናት ይህን ዉስጣዊ ጭንቀት የተገለጠበት ትዕይንት ገሃድዘለላዊ ነዉ። የበዕዉቀቱ ልቦለዶችም ሲጤኑ - በተለይም ዕንቅልፍና ዕድሜ - በህልም፣ በምኞትና በዕዉነታ የፈሉ ምስሎች አሉት።
ዛሬ ዛሬ ማኅበራዊ ድረገፅ - እንደ facebook - ለአማርኛ ወጣት ፀሐፍት ግጥሞቻቸዉን የሚያስነብቡበት ዐዉድ ለገሳቸዉ፤ ይወያዩበታል። ሄለን ካሣ “ቅጥሩ ግንብ ነዉና እምነ በረድ ቤት / መቼ ይታየኛል ! የነዋሪዉ ሞት” ስትል ነፍሱ የፈረጠችበት የተፈረካከሰ ገላ እና የማይገጣጠም ደማቅ መቃብር ጐን ለጐን ስታነፃፅር - juxstapose - ሰዉ በትዕቢት ይሆን በብስለቱ መሻሸር ስንት እሚያስጨንቅ እያለ በተራነት መጠመዱ አስገርሟታል። እንደ መኖሪያ ቤትም ከተጤነ አርቆ አለማሰብን ያንፀባርቃል ምስሉ። ለአንድ አመት ያክል ወጣቶች በየድረገፁ እየተቀባበሉ የዘመሩት ግጥም የበረከት በላይነህ “የህልሜ ደራሲ”ን ነዉ።
ስ ስምሽ ስላደርኩ ትላንት በህልሜ
ዛሬ ቶሎ ተኛሁ ልስምሽ ደግሜ፤
ታድያ ምን ያደርጋል !
የህልሜ ደራሲ አትታደል ቢለኝ
ህልሜን ገለባብጦ ሲስሙሽ አሳየኝ።
ይህ ለገሃድዘለል የአፃፃፍ ስልት ዐይነተኛ ምሳሌ ነዉ። አንድም፥ ኢንቁ የአዕምሮን ምኞት ህልም ዉስጥ በመዋኘት ማስገር ነዉ። አንድም፥ ክህደትን አልያም የታፈነ ፍትወታዊ ረሃብ ተናጋሪዉን ሲኮሰኩሰዉና ሲወረዉ እንደ ማምለጫ ህልምን ይማጠናል። አንድም፥ ኑሮ እኛ ባቀድነዉ ብቻ ሣይሆን የሆነ ኀይል ቱቦ እየቀደደ አቅጣጫ ማስለወጡን የመሰለ እሳቦት። ዋናዉ ግን በረከት ይፀዳ መስሎት ህልም ዉስጥ በዘፈዘፈዉ ግጥሙ የወጣቱን ስነልቦናና ፍላጐት፣ ይህን ፈጣን ንዝረት በመቀንበቡ፣ ምናብን አደፍርሶ ከዕዉነታ የላቀ የታመቀ ብዥታ መግራት መቻሉ ነዉ። ገሃድዘለሎች ከንቁ የአዕምሮ ቁጥጥር የማላቀቅ አርነት የሚሉትን አፈፍ ያደረገ ነዉ።
አዳም ረታ ለአማርኛ ልቦለድ የአፃፃፍ ክህሎት ሆነ የትረካ ስልት ፋና ወጊ - avant grade - እና ፈር ቀዳጅ ነዉ። ይህ ሂሳዊ ንባብ ለነቢይ ግጥሞች የተመደበ ነዉና ለገሃድዘለል በተለይም ዕዉነታን ለተሻገረ አንድ ድርጊት ከአዳም ልቦለድ ልጦቅም። መዝገቡ በልጅነቱ ወንዝ ዳር ያገኛት ድንጋይ “በጣቶቼ ስዳብሳት ነጭ ላባ እንደለበሰች ጫጩት የምትለሰልስ ነበረች። ያኔዉኑ ፍቅር ነገር ከእሷ ይዞኝ ...” የሚላትን ወደ ሰማይ ሲወረዉራት ሳትመለስ ቀረች። ከአመታት በኋላ ትዳር መስርቶ ቤተሰባዊ ፍቅር እየሞቀዉ ሳለ “ዐይኖቼን ወደ ቀኝ ስወረዉር መድረቅ የጀመሩ ሳሮች መሐል ያቺን ነጭ ድንጋይ አየሁዋት” ወደ ላይ ሊወረዉራት ሲል ምስትየዉ ከእጁ ላይ በፍጥነት አንስታት ተደመመች። “ ደስ አትልም? ሰዉ የሰራት ትመስላለች ... ከእጅዋ ተቀበልኩና ከእስዋ ፈቀቅ አልኩ። እዉስጤ የሆነ እምነት ነበር። ሕይወት ወፈረም ቀጠነም ዞር ብለን ስናየዉ የሆነ አስማትና ተአምር አለዉ። ሁሉ ክፉም ደጉም ከዉስጡ የተወሰወሰ ቶሎ ራሱን ከፍቶ የማያሳይ ተአምር አለዉ። ድንጋይዋን ... ወደ ላይ ወረወርኳት። ወደ ሰማይ በግምት አሥር ሜትሮች ያህል እንደተነሳች ... አንጋጠን እያየናት ጠፋች። ... ድንጋይዋ አልተመለሰችም:: [ግራጫ ቃጭሎች፥ ገፅ 50 + 440-442] እንዴት ሊሆን ቻለ? ይህ ዲበዕዉነታ ትዕይንት የልቦለዱን የተረክ ጥበብና የመዝገቡን ዉስጣዊ ህይወት እንዴት አበለፀገዉ? አስማትና ተአምርስ?
ደበበ ሠይፉ፥ ወጣቱ በሰመመን መለከፉንና ልቡ ዉስጥ ጨለማን ማጠራቀም መጀመሩን ተገንዝቦ የተቀኘዉ አንድ አሳሳቢ ገሃድዘለል ግጥም አለዉ። ዕፀ ፋርሱን በማሽተት ወደ ኢንቁ አዕምሮዉ የዘቀጠዉን የሳለበት።
እንደ ባዕድ አካል
ተገንጥሎ ሲሄድ ራሱ ከራሱ
እጆቹ እያጠሩ
አቅቶት ሲቸገር መዳበስ ማበሱ
እያደገ ሒዶ
የገዛ አፍንጫዉ ይላጋል ከአድማሱ! [የብርሃን ፍቅር፥ ገፅ 93]
በአማርኛ ስነፅሁፍ በ surrealism ስልት አስቦበት የፃፈዉ ሰለሞን ደሬሳ ነዉ። በወቅቱ የረጋዉን ሥነግጥም የበጠበጠዉ አርባ አራት ተኩል ግጥሞች በማለት ልጅነትን ያሳተመ ጊዜ ነበር። ለመፅሃፉ የመረጠዉ ጥቅስ ከዝነኛ ፈረንሳዊ ገሃድዘለል ገጣሚ Paul Eluard የተቀዳ ነዉ። “እረፍት በጠጠርና በእሾህ መድቦች / ላይ መገቻዉን አገኘ”። የመጋቢት 23/ 1992 አዲስ አድማስ፣ ሰለሞን በ1959 መነን መፅሄት ላይ የፃፈዉን አስነብቦናል። “ወረድ ብዬ ሁለት የራሴን ግጥሞች አቀርባለሁ። “ዘላለምሽ” የሚለዉ ከተለመደዉ የአማርኛ የወል ግጥም እምብዛም አይርቅም ... ረዘም የሚለዉ “ኤዉሮፓ” ግን ኬላ ሰባሬ ብጤ ሳይሆን አይቀርም። የሞከርኩት ኤዉሮፓዉያን ሱሪያሊዝም (ባማርኛ ከዕዉን በላይ ልንለዉ ይፈቀድ ይሆናል) የሚሉት አይነት ግጥም ነዉ። “በባህላችን ያሉት የግጥም ዓይነቶች መች አነሱንና!” ለሚሉት አንባቢዎች “አይበቁንም” ብዬ ያላንድች ጥርጣሬ እመልሳለሁ። ኤዉሮፓዉያንም የኛን የቅኔ ሥርዓት ቢያዉቁት ምነኛ በጠቀማቸዉ። በዚህ ዓለም ላይ ራሱን ችሎ ከጐረቤቱ ብድር የማያስፈልገዉ ህዝብና ሥልጣኔ አለ ብዬ አላምንምና።
ሸክላ ተሰብሮ ፍልጥ ጥርሱ ሲዳም
ዉሽማዬ ቁጭ ብላ በጐን ታለቅሳለች።
እንዳለቀ ሻማ ፍቅር ሲያቅማማ
አይኗ ተቀዶ ጥቁር ዉሃ ሲያፈስ [... እያለ ይቀጥላል ልጅነት፥ ገፅ 17]
ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል። የነቢይ ዲበዕዉነታ ግጥሞች ግን ማራኪና ላቅ ያሉ ናቸዉ።

የነቢይ ገሃድዘለል ግጥሞች
“ነፃነት ለጠማቸዉና ተባብረዉ ማበድ ለተሳናቸዉ ያገር ልጆች” በማለት ነቢይ የዛሬ ሃያ አመት “ኧረ እንበድ ጐበዝ” በሚል ግጥሙ ልክ እንደ ገሃድዘለሎች ከንቁ አዕምሮ ተፅዕኖ ለማፈትለክ ጥሪዉን ዘምሯል። “ሰዉ ባገሩ በወንዙ ማበድ መወፈፍ ካልቻለማ / ምን አገር ሆነ ያማ!” ጥበበኛ እንደልቡ ከገጠመኝ ለመሟገት፣ ዕዉነታዉን ቦርቡሮ የብርሃን ጭላንጭል ለመለጠጥ ያፈነግጣል፤ ርዕይ ይቋጥራል። “እንበድ” ሲል አረጋዊ እንደ መፈንከት ሳይሆን መገጣጠምን፣ የሃሳብ ወረርሺኝና - conformity - ከበባን እንደ መናድ ነዉ እንጂ።
ዜጋ አብዶ ገዱ ተንጋዳ
ነካ ነካ ካላረገዉ፣ በገዛ አገሩማ ጓዳ
ቢሻዉ ካልተሸማቀቀ፣ እገዛ ቤቱ እንደእንግዳ
ወይ ከት ከት ብሎ ካልሳቀ፣ አሊያም ድንገት ካልተቆጣ
ወፈፍ ወፈፍ ካላረገዉ፣ የእብደት አብሾ እንደጠጣ፤
እንዲህ እንዲያ ካልሆነማ
ምን አገር አለዉ እሱማ። [ጥቁር ነጭ ግራጫ - ገፅ 8]
ጥልቅ እሳቦት ሲመዘምዘዉ፣ ተለምዶ አልመጥነዉ ሲል ነቢይ ያፈተልክና ከዕዉነታ የላቀ ግጥም ይቀኛል።
ዕድሜዬን በሙሉ
በአፌ ፈረስ ልጓም
እጄ ላይ ሰንሰለት
ሲያኖሩ ስላየች፤
ፀሐይ ሰማይ በቅቷት
ዉሃ ሰጥማ ሞተች።
ዉሃ ዉስጥ ተኝታ
ከኔ ትዋሳለች፣ ይኸዉ ብርሃን አጥታ። [ስዉር-ስፌት፥ ገፅ 137]
ነቢይ የህዝባዊ ታጋይን ፅናት ለመፈልቀቅ ከህልም መዋስ አለበት፤ ከኢንቁ አዕምሮ ጠልቆ ምስል ያጠነፍፋል። ግለሰብ ሲታሰርና ሲታፈን ለአመታት አስተዉላ፣ እሱ ተስፋ ሳይቆርጥ ፀሐይ ብሶባት ከዉሃ ትሰጥማለች። ብርሃን አጥታ ትዋሰዋለች። ለወገናዊ ዓላማ በየዕለቱ ሲገጣጠብ ያልተሸነፈ ታጋይ፣ ገጣሚዉ እስከ ታህተንቃቱ ለመቆፈር ደፈረ - የብርታቱን ምስጢር ሥራስሩን ለመማስ። ፀሐይ ቢደርስባት የማታዝለዉ እንግልት፣ እሱን ከጨለማ አልዘፈቀዉም። ገላዉ ብርሃን ተርፎት ለሌላዉ ያበድራል::
በንቁ አዕምሮ ቢጤን የማይመስል ብቻ ሳይሆን፣ አለመምሰሉንና ቅዠት-አከል እንቅስቃሴዉ ወኔ የሚቦካበት ቡሃቃን ጠፈጠፈ። እንዲህ ነዉና ዲበዕዉነታዊ አፃፃፍ። “ዋሽ ቢሉኝ እዋሻለሁ፣ ነፋስ በወንፊት እይዛለሁ” ሳይሆን የግለሰብን ዉስጠት የመቧጠጥ ልክፍት እንጂ። የዕለት በዕለት የኑሮ ደለል የሸፈነዉን ግለሰባዊ፣ ህይወታዊ እንግልትና ወኔ፣ ህልማዊ ምስልን በማቀጣጠል ቦግታን መጫር ይቻላል። ይህ ዕድሜ እኮ፣ ከዉስጡ የታጐረ የአመታት ጠጠሮች ይርመሰመሱበታል። ገጣሚዉ ኅቱም ገጠመኝን መቀኘት አለበት - “ሙሴ የህዝበ እስራኤልን ዉሀ ጥም ለማብረድ ዉሀ ከፈለቀበት ኅቱም ድንጋይ” ድንግል ትዕይንት እንደማለት። የሚሸሽጉት ሳይሆን እንደማቅ የሚደርቡት ገመና። ይህ ከኢንቁ አእምሮ ለመግባት መፈርፈር፣ ህልምን መሸርሸር፣ ዕዉነታዉ ሽፋኑ ብቻ እንደማይታመን ክርስቶስም አስተምሯል።
“የበግ ለምድ ለብሰዉ ይመጣሉ፤ ዉስጣቸዉ ግን ተኩላ ነዉ” ነቢይ ግን በዚህ ግጥም ዉስጡ በተስፋና በወኔ የራሰዉን ነዉ ቅዠት ለዉሶ የተቀኘለት። “አዲስ ነገር ለመፍጠር፣ ... አሮጌ አብራክ የማስፈለጉን ያህል፣ አዲስ አተያይ ይዞ አዲስ ጥበብ መዉለድም ያሻል” ብሏል ነቢይ በመፅሐፉ መግቢያ። ከዕዉነታ በላይ በህልም ድንኳን፣ ገሃድዘለል ምስሎች እንደ ችግኝ የፈሉት ነቢይ ለሎሬት ፀጋዬ ህልፈት ሲቀኝ ነዉ። “ክረምት አለወሩ ገብቶ፥ ... ፀሐይ አለሰዓት ጠልቃ፥ ... ጨረቃም ጥቁር ሻሽ አስራ፥ ... ” ለፀጋዬ ቀብር ከመሬት ይወርዳሉ።
ከዋክብት አሸርጠዋል፣ የብርሃን ደረት ጥለዉ
በእድር አዉቶቡስ፣ ምድር ወርደዉ
“አስታዋሻችን ሞቶ፣ ሰማይ ምናችን ነዉ” ብለዉ
ቀብር አለብን ይላሉ፣ መቃብር ያለህ መስሏቸዉ
ያንተኮ ልዩ ማዕረግህ
ያለመቃብር ማረግህ። [ገፅ 29]
መንደሩና አካባቢዉ አልበቃ ብሎ ነቢይ ከአንጀቱ ሲያዝን ምናቡ ወደ ህልምና ቅዠት ተሰደደ። ደብዝዞ፣ ቀዝዞ ለመስለምለም ሳይሆን አንድ ትልቅ ሰዉ ሲገረሰስ እንዴት ሰምና ወርቁን ይለየዉ ? እነዚህ ገሃድዘለል ምስሎች ዕዉነታዉ እንዲፈጀን፣ እንዲለበልበን አግዘዉታል። ነቢይ ዲበዕዉነታ ስልትን የተገለገለዉ ኮስተር፣ ኮምጠጥ ለሚል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ሠርክ ለሚያጋጥመን ለምንርበተበትለት የስሜትና የእሳቦት ለጋ ህይወትም ጭምር ነዉ። ነቢይ በመቅድሙ እንደፃፈዉ ከሆነ ለጭብጥ ቅርፅን በማማረጥ አይደለም የሚገጥመዉ። ግን የአገጣጠምን ዘዬ ለመስበር፣ ህልም ዉስጥ ለመወራጨትም ሆነ ብሎ እንደተቀኘ ይመስክራል::
“... ቀልቤ እንደወደደ፣ ልቤ እንደፈቀደ እንጂ ለዚህ ይዘት፣ ለዚህ ሀሳብ ይሄን ቅርፅ ብዬ ምዳቤ ለመስጠት ጭንቅላቴን ይዤ ለማሰብ አልዳዳሁም። ... በዚህ የግጥም መድብሌ አልፎ አልፎ የባለቅኔ-ነፃነትን በመጠቀም ... ቃላቱን እንደፈተተኝ የተጠቀምኩበት ቦታ ይኖራል።
... እንደ “ዉሃ ዳር የቆመ ክራር” እና “ያላለቀ ቀሽም ግጥም የመሰለች ልጅ” የማሳሰሉት ግጥሞቼ፣ እንደዚሁ የእብደትና የጥጋብ ሊቼንሳዬን በመጠቀም የፃፍኳቸዉ ለየት ያሉ ፍሬዎቼ ናቸዉ። እብደቴን ለሚወዱና ለሚጋሩኝ ይሆኑ ዘንድ አክያቸዋለሁ። [ስዉር-ስፌት፥ መግቢያ]
ስዕል የወለደዉን ክራር፣ በግጥም አንቀልባ አሳድጐ
በጥልቅ የመለኮት ትንፋሽ፣ እፍ ሲል፣ ሙዚቃ አድርጐ
ጥበብ ነዉ ብሎ ሰጠና!
ይሄ የእብደት ነዉ የጤና? [ገፅ 150]
“ለካ ሰዓሊ ሲያብድ ገጣሚ ይሆናል” በሚለዉ ሶስትዮሽ ግጥሙ በአማርኛ ቅኔና ዝርዉ ያልተሞከረ ልዩ ገሃድዘለል እሳቦትና ምስሎች የተቀኘበት ነዉ። ሶስትዮሹ ዋናዉ ግጥም “ለካ ሰዓሊ...”፥ “አሪፍ እብደት” እና “ዉሃ ዳር የቆመ ክራር” ናቸዉ። የሚደንቀዉ ሶስተኛዉ ርዕስ፣ ለብቻው ንኡስ ግጥም ሳይሆን ከህልም እምብርት እንደሚገጥመን ዝብርቅርቅ ነገር፣ ግማሽ ስንኝ ሆኖ ሳለ ከመካከል ዋናዉን ርዕስ ለመቀናቀን እንጣጥ ብሎ ይወጣል። [ገፅ 148] ለስዕል ርዕስ ሆኖ ቃል ብቻ የነበረ ድንገት “ክራሩ እባህር ወደቀ/ መዋኘት አቃተዉና ያገር-አረፋ ደፈቀ።” እዚህ ከህልም፣ ከምናብ የፈለቁ ቅንጭብጫቢ ኢተጨባጭ ግዘፍ ነስተዉ የግላቸዉን ህይወት ፈጥረዉ ዕዉነታን ተሻሙት። ልክ የምናነበዉ የልቦለድ ገፀባህሪያት ከወረቀት ፈልሰዉ ክፍላችንን ሲያተራምሱ የማስተዋል ያክል ሆነ። ግጥም-ስዕል-ሙዚቃ፣ አንዱ ሌላዉን ወለደ። ከባህር የወደቀዉ ክራር ...
አረፋዉ በወጀቡ-ምት ተነድፎ ባዘቶ ሆኖ
ዉሃ በሙዚቃ አብሾ፣ ይኸዉ ጨርቁን ጥሎ አበደ
አገር ምድሩ አብሮ ራደ፣ ተራራም ቁልቁል ተናደ
ነቢይ የገጣሚን፣ የሰዓሊንና ሙዚቀኛን የጥበብ ነፃነትን፣ አለመገደብን ከዕዉነታ ብቻ ሳይሆን ከኢንቁ አእምሮ ስንቅ የሚሻ አባዜን ነዉ ህይወት የተነፈሰበት። “ያላለቀ ቀሽም ግጥም የመሰለች ልጅ” ግጥሙ የአራት ገፀባህርያት ተረክ ነዉ። አራተኛዉ “ሸዉራራ ድንክ ዉሻ” ናት። ተራኪዉ ከአንድ ቡና ቤት “መልኳ ጉራማይሌ” ከሆነች ሴት ፊት ለፊት ቁጭ ብሏል። በአእምሮዉ ዉስጥ ከራሱ ጋር ብቻ የሚያወራዉን ግለወግ - interior monologue - አስተናጋጁም ልጅቷም ቃል በቃል ይደግሙታል። በእርግጥም ያበደና የቀወሰ መሰል። እኩል ከገሃድና ከቅዠት ወጣ ገባ የሚሉ ግለሰቦች ናቸዉ። አነጋገሯ የሚያስጠላዉ ይመስላል፤ ግን ከእሷ አንደበት የፈለቀ ወይስ እየከጀላት የእሱ ባለመሆኗ እያስቃዠዉ ይሆን? ይህን የተበጠበጠ አእምሮ የግጥሙ ቅርፅና የስንኞች መዘበራረቅ የተናጋሪዉን ልቦና - psyche - አጉልተዉታል። ነባራዊዉ ከህዋሳቱ ላይ የሳለዉ ሳይሆን ከኢንቁ ህልማዊ ጓዳ ተከታትለዉ የሚሸሹ ምስሎች እንጂ። ግጥም በብጅት ላይ ሳለ ከቢጋሩ የፈረጠጡ ስንኞች፣ በየአቅጣጫዉ እየተንጫጩ ይደናገራሉ።
እኔም፥ ያልተጨረሰችዉን ቀሽም ግጥም ልጅ
ልታልቅ አንድ-አሙስ የቀራት
እራፊ ጠቀሳ ጠቀስኳት።
ከዚያም ያልተገረዘ ፈገግታ እያሳየኋት
እንዳላለቀ የገጠር መንገድ እየተንገዳገድኩ
አስፋልቱ ጋ ስደርስ፣ ቡችላዬን አገኘሁዋት
የዚያችን፣ ያልተጨረሰ ቀሽም ግጥም ልጅ ነገር
ለሸዉራራዋ ድንክ ዉሻዬ ነገርኳት!
እሷም “ O my God!
ምነዉ መጀመሪያዉኑ ሳትፃፍ ብትቀር !
እፀሃፊዉ አንጐል ዉስጥ፣
አርፎ መቀመጥ ማንን ገደለ ?!”
አለች:: [ገፅ 159]
ነቢይ ከሌላ የአማርኛ ገጣሚይን በበለጠ ገሃድዘለል ግጥሞችን የደፈረና ያስተዋወቀ ነዉ። እንድያዉም አንድ ግጥሙን “የማበጃ ሰዓት” [ገፅ 124+160] በእንግሊዘኛና በአማርኛ እያፈራረቀ “ጨረቅ ድምቡልቦቃ / አፄ ቤት ገባች አዉቃ”ን ያልተዳሰሰ ለጋ እሳቦት ዉስጥ ዘፍቆ የቀን ሱፍ አበባን ከሌሊት ጨረቃ ጋር አስተኝቶ “የኮከብ ቅርፅ ያላት / ትንሽ ቢራቢሮ፣ የፍቅር ተምሣሌት ትወልዳለች” ምናቡን ከዕዉነታ በላይ እንዲከንፍ ፈቅዶ ከ surrealism ዉስጥም ዉጭም ተዘረጋጋ:: ከዉስጡ፥ ግራ በሚያጋቡ ምስሎች፣ በህልም ድባብ እና በቋንቋ ዝብርቅርቅነት ሲሆን፤ ከዉጩ፥ ለረቂቅ እሳቦት፣ ነባራዊ ገጠመኝን ለማይመጥነዉ መብሰክሰክ ልባዊነት ማበጀቱ ነዉ።
ሆኖም ሰብአዊ መናወዝን፣ የሚቆረፍድና ዉብ ተመክሮን፣ ኢንቁ ህሊናዊ ትዉስብን ለመግራትና ለመጐልጐል ነብይ ቢሳካለትም በስዉር-ስፌት በቻ ሳይገታ መቀኘትና መድፈር አለበት። በሩህ ምናብን እሚያተጉና እሚያደፈርሱ፣ የገጣሚዉን ልቦና እሚጭሩት የትካዜና የግርምት ንቁና ኢንቁ ክስተቶች እንደ የማገዶ ዝምታ አድፍጠዉ ይጠብቁታል::

Read 5374 times