Print this page
Saturday, 22 June 2013 11:27

እርስ በእርስ አለመናበብ ዋጋ እያስከፈለ ነው!

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

“ከተማውን ሁሉ እንኩሮ አደረጉት!” - የመዲናዋ ነዋሪ ምሬት

              አዲስ አበባ ከተማ በ126 ዓመት ታሪኳ እንደአሁኑ በልማት ሥራ የተዋከበችበት ዘመን ያለ አይመስለኝም፡፡ ጅምር የልማት ሥራዎቹን ውጤት በተስፋ የሚጠብቁ፣ በአድናቆት የሚመለከቱ፣ ነቀፌታ የሚሰነዝሩ ፣ በቅሬታ የሚያዩ---ነዋሪዎች አሉ። የአመለካከት ልዩነት መኖሩ አልሚው አካል በአግባቡ ከተጠቀመበት ለልማት ሥራው መሻሻል የሚያበረክተው በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው አያጠራጥርም፡፡ በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ ግሬደር የማይፈነጭበት፣ አካፋና ዶማ ያላረፈበት መንደር ማግኘት ያስቸገራቸውና በተለይ በትራንስፖርቱ መጨናነቅ የተበሳጩ አንዲት ወይዘሮ ምሬታቸውን የገለፁት “ከተማውን ሁሉ እንኩሮ አደረጉት” በማለት ነው።

እንዲህ መሰሎቹ ቅሬታዎች በተለያዩ መድረኮችና የመገናኛ ብዙኃን ሲነገሩ በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ አዲስ አበባ “እንኩሮ” የመሆኗ ጉዳይ፤ አቶ አርከበ ዕቁባይ በከንቲባነት ዘመናቸው “ዘጠኝ ድስት ጥዶ…” በሚል በሥራ ጓደኞቻቸው ተተችተዋል የተባሉበትን ክስተት ያስታውሳል፡፡ አሁን የሚታየው እንኩሮስ በትክክል በስሎ ይወጣል ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ መሆኑ ፈፅሞ አያጠያይቅም፡፡ “ከተማውን ሁሉ እንኩሮ አደረጉት” የሚለው አባባል በአንድ በኩል አሉታዊ ቢመስልም በሌላ በኩል ግን ሥራና ጥረትን መኖሩንም አመላካች ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “አነኮረ” ከሚለው መነሻ ግስ ቀጥሎ “እንኩሮ” ለሚለው ቃል ካቀረባቸው ትርጉሞች አንደኛው “በውሃ ተበስብሶ በምጣድ ላይ እየተገለበጠ እንዲበስል የተደረገና ለጠላ የሚሆን ዱቄት” በሚል ይተረጉመዋል፡፡

ስለዚህ አዲስ አበባ ከተማ “እንኩሮ” የመሰለችው የበሰለና የተሻለ ነገር ለማስገኘት መሆኑ ቢያስደስትም ማንኮሪያው በማን እጅ ነው የተያዘው? የሚለው ግን ብዙ የሚያወያይ ነው፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በቅርቡ ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የበላይ ተቆጣጣሪ ቢሆንም ውሃና ፍሳሽ፣ መንገደኞች ባለስልጣን፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌኮሙኒኬሽን…መሥሪያ ቤቶች የየራሳቸውን ሥራ በየራሳቸው መንገድ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ ይህ ደግሞ የከተማው “እንኩሮ” በተለያዩ አካላት እየተነኮረ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የሥራ ክፍፍሉ ግድ መሆን ያለበትና ተገቢ ቢሆንም በሂደቱ የሚገኘው ውጤት ግን እርስ በእርሱ የማይናበብና የማይግባባ መሆኑ ትልቁ ችግር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ እውነታ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

ከመስቀል አደባባይ ቦሌ የሚደርሰው አፍሪካ ጐዳና በአዲስ መልክ ከመሰራቱ ጥቂት ዓመታት በፊት የመንገድ አካፋይ (ፓርኩን) ለማስዋብ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ሥራ ተሰርቶ ነበር፡፡ ሁለቱ ፕሮጀክቶች እንዲናበቡ ያልተደረገው ለምን ይሆን? በመንገዱ ግራና ቀኝ ተነጥፎ የነበረው “ኮብል ስቶን” ከአፈር ጋር ተዝቆ ሲነሳ ስለባከነው ሀብትስ ቀደም ብሎ ማሰቡ ሳይቻል ለምን ቀረ? በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ሥራቸው ተጠናቆ ከተመረቁ መንገዶች መካከል ከልደታ ደሴ ሆቴል ወደ ካርል አደባባይ የሚያደርሰው መንገድ አንዱ ቢሆንም፤ መንገዱ ደሴ ቡና ቤት አካባቢ ለአዲስ ሥራ ግሬደሮች እየተርመሰመሰበት ነው፡፡ በልደታ አካባቢ፤ መስቀለኛ መንገድ ላይ እየታየ ያለው አዲስ ቁፋሮ ከባቡር መስመር ዝርጋታው ጋር ሊያያዝ እንደሚችል መገመት ቢቻልም በመንገዶች ባለስልጣን ስር ያሉት ሁለት ሥራዎችስ እርስ በእርስ መግባባት እንዴት አቃታቸው? የሚያስብል ነው፡፡ በ22 አካባቢ የሚኘው ትራፊክ ጽሕፈት ቤት አዲስ ሕንፃ ገንብቶ ካስመረቀ ሁለት ዓመት ያለፈው አይመስለኝም፡፡

ከሲ ኤም ሲ ወደ ጦር ኃይሎች የሚዘረጋው የባቡር መስመር በ22 በኩል ስለሚያልፍ የትራፊክ ጽሕፈት ቤት አዲሱን ሕንፃ የግንብ አጥርና ወደ ሕንፃው የሚያስገቡ ደረጃዎችን ከሰሞኑ እያፈረሰ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላንን ዳግመኛ የማሻሻል ሥራ ለማከናወን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ በ1995 ዓ.ም ነባሩ ማስተር ፕላን ተሻሽሎ ሲፀድቅ ከሲ ኤም ሲ እስከ ጦር ኃይሎች የባቡር መስመር ዝርጋታ እንደሚኖር ተጠቁሞ ነበር፡፡ ሕጉ፣ አዋጁ፣ መመሪያው…ቢኖርም አንዱ ከሌላው ጋር እርስ በእርስ የመናበብ ችግር ስለሚታይበት የትራፊክ ጽሕፈት ቤት ሕንፃ ሲሰራ ቦታው ከባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ እንደሚፈለግ የሚያመለክት ስላልተገኘ ለጉዳት መደረጉ እውን ሆኗል፡፡ ለዚህ ጥፋት ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው ማነው? በሙቀጫ የተገኘውን ሁሉ በአንድነት መውቀጥ እንዳይሆን ሕጐችን፣ ትዕዛዞችንና መመሪያዎችን ጠብቆ መሥራት ያስገኘውን ጥቅም ማመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በጊዮርጊስ በኩል ወደ መርካቶ የሚዘልቀው የባቡር መስመር ዝርጋታን መሠረት ያደረገ ነበር ይዞታዎችን የማፍረስ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

የመዘጋጃ ቤት አጥር፣ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት፣ “ቁጭራ ባንክ ቤት” የነበረበት የመርካቶው ጥንታዊ ሕንፃና የክፍለ ሀገር መናኸሪያ የመሳሰሉት ተቋማት የፈረሱም በመፍረስ ሒደት ላይ ያሉም አሉ፡፡ በዚህ መስመር ከመፍረስ የዳነው አዲስ ሕንፃ እንዴት ከመፍረስ ዳነ? በ1990ዎቹ አጋማሽ ግንባታው የተጀመረውና ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ የሚገኘው “ተፈራ ስዩም የገበያ ማዕከል” ሕንፃ ከሰሞኑ የማፍረስ ሂደት መትረፍ የቻለው የ1995 ዓ.ም መሪ ፕላንን ተከትሎ ከዋናው መስመር ገባ ብሎ መገንባት በመቻሉ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ ለዚህ መሰሉስ አርቆ አሳቢነት ምስጋናውን መቀበል ያለበት ማነው? ከአዲስ አበባ ልማት ጋር በተያያዘ አስተማሪ ተሞክሮ በመለገስ መርካቶ ያበረከተችውን ትልቅ አስተዋጽኦ በዚህ አጋጣሚ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የመርካቶ ነባር ይዞታዎች ፈርሰው በአዲስ የመተካት ሥራ የተጀመረው በ1996 ዓ.ም ቦንብ ተራ የሚገኘው አንድ ብሎክ በማፍረስ አዲስ ግንባታ ሲጀመር ነበር። አሁን አዲስ ፋና ኃ.የተ.የግ.ማ የሚገኝበት ባለ 8 ፎቅ ሕንፃ የተሰራበት ቦታ ላይ የሚገኝ አንድ ብሎክ የፈረሰ ዕለት ፍራሹን በመርካቶ ዙሪያ ባሉ መንደሮች ወስዶ የመድፋት ተግባር ተፈጽሞ ነበር፡፡

ብዙም ሳይቆይ ግን መገንባት ብቻ ሳይሆን ማፍረስም ሥራና ካፒታል ሊፈጠርበት እንደሚችል ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ተግባር ያሳየችው መርካቶ ነበረች፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ለዳግም ልማት የሚፈርሱ ቤቶች ለሥራ ፈላጊዎች አንዱ ሥራ ማስገኛ መፍትሔ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ማፍረሱም፣ ፍርስራሹን መሸጡም፣ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ሆኗል። ከልማት ሥራ ጋር በተያያዘ እንዲፈርሱ በመደረግ ላይ ያሉት አሮጌ ቤቶችና የደከሙ መንደሮች ብቻ ሳይሆኑ ነባር ትላልቅ ሕንፃዎችንም በመንካት ላይ ስለሆነ አፈራረሱን አንድ ደረጃ ማሳደግ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ከሲ ኤም ሲ ወደ ጦር ኃይሎች ለሚዘረጋው የባቡር መስመር ሥራ እንዲፈርሱ ተወስኖባቸው ተግባራዊ በመሆን ካሉ ነባር ሕንፃዎች ሁለቱ ለገሀር መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሕንፃዎቹን የማፍረሱ ሥራ በሰው ኃይል እየተከናወነ ይገኛል። አገሪቱ እርካሽ የሰው ኃይል ስላላትና ያንንም መጠቀም ስለሚኖርባት ሕንፃዎችን ለማፍረስ ይህንን ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ነው ካልተባለ በስተቀር ሕንፃዎችን በሳይንሳዊ ጥበብ ወደ ብናኝነት መለወጫ ዕውቀቱ ያለው ባለሙያ አይጠፋም፡፡ በከተሞች ከሚታየው የልማት ሥራ ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ስለሚቻልበት ሁኔታ በያዝነው ሳምንት አንድ ስብሰባ በሒልተን ሆቴል አካሂዷል፡፡ የሚወጣው ሕግና ፖሊሲ በልማት ሥራ “እየተነኮረች” ባለችው አዲስ አበባ፤ ማንኮሪያውን ለመያዝ ዕድል የሚያገኙትን አካላት በጥብቅ የሚቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ መንገዶች ሲሰሩ ሕንፃዎች እንዲፈርሱ ከማድረግ ይልቅ ሕንፃዎች ሲሰሩ ማን ተከትሎ እንደሚመጣ ቀድሞ መታሰብ አለበት፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አሁን በጀመረችው ፍጥነት እድገቷ የሚቀጥል ከሆነ መብራት ኃይል ባለስልጣን የኤሌክትሪክ ሽቦ ተሸካሚ ምሰሶዎችን ነቃቅሎ ጥሎ የመብራት መስመሩን በሙሉ መሬት ውስጥ መቅበር አለብኝ የሚልበት ዘመን መምጣቱ አይቀርም፡፡ እዚያ ዘመን ላይ ደርሰን ሕንፃና መንገድ በማፍረስ ሀብት፣ ጉልበትና እውቀታችንን ከማባከናችን በፊት ዛሬ ላይ አርቆ ተመልካች ያስፈልገናል፡፡ ማን ኮሪያው በማን እጅ ነው የተያዘው? ብዬ እንድጠይቅ ያነሳሳኝ ይህ ስጋት ነው፡፡

Read 2284 times