Saturday, 15 June 2013 11:36

ጄ ጄ አብርሃምስ በ“ስታር ትሬክ” ስኬቱ “ስታርዋርስ”ንም ይሰራል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ታዋቂው የፊልም ዲያሬክተር ጄ ጄ አብርሃምስ በ‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› ፊልም ባገኘው የገቢ ስኬት የጆርጅ ሉካስ ፊልም የነበረውን ስታርዋርስ 7ኛ ክፍል እንዲሰራ መዋዋሉን ዋሽንግተን ታይምስ ዘገበ፡፡ በጂን ሮደንበሪ በተደረሰው የስታር ትሬክ መፅሃፍ ላይ ተመስርቶ የተሰራውና የስታር ትሬክ የተሰኘ ፊልሞች ፍራንቻይዝ 12ኛ ክፍል የሆነው ‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› በመላው ዓለም ያስገባው ገቢ 376.54 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የስታር ትሬክ ፊልሞች ፍራንቻይዝ መሰራት ከጀመሩ 38ኛውን ዓመት ሲሆናቸው፣ ዘንድሮ ለእይታ የበቃውን 12ኛውን ክፍል ጨምሮ ያስገኙት ገቢ ከ1.628 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡

‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› በ190 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራና በፓርማውንት ፒክቸርስ የሚከፋፈል ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ በምድር አቅራቢያ ስለምትገኝና ጥንታዊ የዩኒቨርስ ስልጣኔ ያላት የኒብሩ ፕላኔት ፍጡራን በሰው ልጆች ላይ ስለሰነዘሩት የሽብር ጥቃት የሚተርክ ነው፡፡ ዲያሬክተር ጄጄ አብርሃምስ በ‹‹ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ›› ያገኘው ስኬት ነው የስታር ዋርስ ፊልሞች 7ኛ ክፍልን እንዲሰራና የገቢ ስኬቱን እንዲቀጥል ተመራጭ ያደረገው፡፡ የስታር ዋርስ 7ኛ ክፍል ቀረፃውንም በ2014 እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ የስታር ዋር ፊልሞች ፍራንቻይዝ በእውቁ ዲያሬክተር ጆርጅ ሉካስ የተሰሩ ሲሆን በመላው ዓለም ከ1.85 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስገኝተዋል፡፡

Read 1841 times