Saturday, 15 June 2013 11:18

ሕልምና ቅዠት

Written by  ከዮሐንስ ገ/መድኅን
Rate this item
(0 votes)

እሷ

ይኸ ሕይወትን በጅምላ የሚያስሮጠኝ ዕድሜ፣ ቀኔን እንደ ጉልት ሽንኩርት ሲቸርችረኝ ይውልና መኖሬን ሲያዝለው፣ የድካሜን ጣመን ልወጣ እተኛለሁ፡፡ እናም የተስፋዬን ምንጣፍ ነገዬን ዘርግቼ ተኛሁ፡፡ እንደተኛሁ ሰመመን ይመስል አንዴ ሲያሸልበኝ ወዲያው እየባነንኩ ጥቂት ከቆየሁ በኋላ ድካሜ በርትቶ ዕንቅልፌ ጭልጥ አድርጐ ወሰደኝ፡፡ እንደወሰደኝ በዕንቅልፌ መሀል እንዲህ ሆነ፡፡ ይመስለኛል ጭ...ል...ጥ ያለ ምድረ-በዳ ነው፡፡ ውኃ ሰው ጠምቶኛል፡፡ ነገር ግን ጥሜን የሚከላ ምንም ጠብታ የለም፡፡ በዚያ ንዳድ ብቻዬን እንደ ቆምኩ “የሰው ያለህ!” እያልኩ ሰው እፈልግ ጀመር። ዙሪያዬን እየቃኘሁ በጩኸት ብጣራም የራሴን ድምፅ ከመስማት በቀር አቤት የሚለኝ ጠፋ፡፡

“የሰው ያለህ!” እያልኩኝ በጩኸቴ ብደክምም ሰው ናፍቄ እንደተኛሁ ሰው ናፍቄ ባነንኩ። ከዕንቅልፌ እንደነቃሁ እሷን ከአጠገቤ አየኋት፡፡ እንዳየኋትም በህልሜ ያየሁትን ሁሉ እንድትፈታልኝ ነገርኳት፡፡ ከጐኗ እንደተቀመጥኩ የሕልሜን … ሕመሜን ሰምታኝ … ሰምታኝ ስታበቃ “ይህ ቅዠት ነው!” አለችኝ! … እኮ እንዴት? ውሎዬን ደክሜ ስንዝር ጋደም ባልኩኝ ቁጥር ሌቱን ሳታት እየቆምኩ የውኔን ልደገፈው ሰው መሆን ዳዊቴን ሳነበንብ ዝርው በተበተንኩ! … እውነትና ሰውን ስፈልግ እንደ ጀምበር ሽርትት ሳሽቆለቁል እያየች? በውን የናኘሁት ውሎ በሕልሜ እያጐነቆለ ነብሴን ሲያባክነው “ለእሷ ቅዠት የሆነባት ምኔ ብታየው ይሆን? ከመኖሬ ጉድጓድ ሸማ ተዘርግቼ ኩታ ዕድሜ ልሸምን በቀንና ለሊት መወርወሪያ መሀል ቀሰም ተጋድሜ እያየች … ቅዠት ነው? ሕልሜ እንደ ጥፍጥሬ ተፈልቅቆ፣ ይኸ ደጋን ኑሮዬ በቀን እየተነደፈ፣ ጥሜ እየተባዘተ ቀጭን ብፈተላት፣ ኑሮ ቅዠት ባልሆነባት ነበር! ውኃ ሰው ጥማቴን ሳትጠማ፣ ሀሩሬን ተቃጥላ ጩኸቴን ሳታዳምጥ፣ ሰው ተርባ የናፍቆትን ክሳት ሳትረዳ፣ የባይተዋርነትን ፍርሃት፤ የብቸኝነት መራራ ጣዕም ሳትቀምሰው እንዴት ህልሜን ታረክስዋለች … እብሰለስላለሁ፡፡ እየተብሰለሰልኩ እባክሽ ሆድዬ … ሕልሜን አታርክሺው እላታለሁ፡፡ በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ የዕርዳታ ድርጅት ውስጥ ሠራተኛ ነኝ፡፡

እንግሊዛዊቷ ክርስቲና፣ አሜሪካዊቷ ሊዛና ታይላንዳዊቷ ዚሃ የሥራ ባልደረቦቼ ናቸው፡፡ ከመስክ ሥራ ስንመለስ አክስቴ ያፈላችውን ቡና ሳይጠጡ ወደ ቤታቸው አይሄዱም፡፡ ዛሬም እንደተለመደው ቡናቸውን አጣጥመው ሸኝቻቸው መመለሴ ነው፡፡ የጠጣሁት ቡና ስላነቃቃኝ ከመተኛቴ በፊት ዜና ለመከታትል ቴሌቪዥኔን ከፈትኩ፡፡ እሱ እሱን ሳውቀው ሃያ ዓመታት አለፈ፡፡ ተስፋ ላጣች ወንበሩ ሽቅብ ቁልቁል እያለ ሲባዝን፣ ሥልጣን የሚሏት ጣር ፈተናዋ በዝቶ በእግሬ ቆምኩኝ ሲል ዘርጥጣ እየጣለች መነሻው ሲጠፋበት አየዋለሁ። ሽበቱ ገብስማው እስከሚታይ ድረስ ተስፋው እየሸሸበት፣ ግብሩ ዘመኑን በዜሮ እያባዛው ቀኑ ሲመሽበት አየዋለሁ፡፡

የቀናቶቹን ቀን ከተስፋ ባህር ላይ በተስፋ እየጨለፈ፣ የተስፋ አክርማውን በተስፋ እየቀጨ ምኞቱ ያደመቀውን ሙዳይ ሲሰፋ … ሲሰፋ … የሰፋው ሙዳይ ተስፋ ሳይቋጥር አንድ ጊዜ ከዚህ አንድ ጊዜ ከዚያ ተስፋ እየቆነጠረ … በግብረ አልቦ ሰማይ ላይ ምኞቱ የዘራውን ኮከብ ሲቆጥር … ሲቆጥር … ሃያ ዓመታት ሙሉ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያለ አየዋለሁ፡፡ ያየሁት ለታ የልቡን ሳይሆን ያፉን ይነግረኛል፡፡ ከረባትና ሱፍ ቢቀያይርም ንግግሩ አርማ ስላለው አውቀዋለሁ፡፡ በማያልቀው ነገ … ነገ ይሳካል ይለናል … ለሞተበት ተስፋ ትንሣዔ እንድንሆነው ገንዞ ሳይቀብረን፣ በተባ አንደበቱ የለመድነውን ሞት ደጋግሞ ይገለናል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንት የሰላ አንደበቱ ቢጐለድፍም ጭብጧችንን በተስፋ እየቀማ “እኔ ዛሬ ልብላው ለእናንተ ደግሞ ነገ” ይለናል፡፡ በተስፋው እየገደለን … በምላስ እያባባለን … ሲደልለን … ሲደልለን … ኡፍፍ … ደከመኝ፡፡

ቴሌቪዥኑን አጠፋሁትና ተኛሁ፡፡ እንደተኛሁ… በልማደኛው ህልሜ ውስጥ ያ ሃያ ዓመት ሙሉ በቴሌቪዥን መስኮት የማየውና አንድም ቀን አግኝቼው የማላውቀው ሰውዬ፤ ገብስማ ፀጉሩን እያከከ ከአጠገቤ ቆመና አንድ ወረቀት አቀበለኝ፡፡ “ምንድን ነው?” አልኩት “እ… እንደምታውቀው በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ሙስና ላይ ዘመቻ እያካሄድን ነው …እ… እንደምታውቀው “የዓሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” እንደሚባለው ከጭንቅላቱ ጀምረናል፡፡ ወደታች ማጥራቱም ቀጥሏል … ስለዚህ በቦታው ክፍተት እንዳይፈጠር ምክትል ዳይሬክተር ሆነህ በጊዜያዊነት እንድትሰራ አንተን መርጠንሃል እ … በቦታው ክፍተት እንዳይፈጠር … ስለዚህ አሁን ሄደህ ሥራህን ጀምር አለኝ” እኔ ግን “የዓሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” የሚለውን አባባል እያስተነተንኩ ነበር፡፡ ቆይ … የዚች ሀገር ጭንቅላት ያለው ጉምሩክ ውስጥ ነው እንዴ?” አልኩኝ በልቤ፡፡ አፍ አውጥቼ ለመናገር አልደፈርኩም፡፡ አንድ ሰው ሲሾም ምን እንደሚሰማው ለማወቅ ፈልጌያለሁ፡፡ እናም ወደ ጉምሩክ ዋና መሥሪያ ቤት አመራሁና የምክትል ዳይሬክተሩን ቢሮ ከፍቼ ገባሁ፡፡

ጠረጴዛው ላይ ሻንጣዎች አሉ፡፡ ማን አስቀመጣቸው? … ለም አስቀመጣቸው? አንድ አዲስ ሰው ሲሾምና ቢሮውን ከፍቶ ሲገባ … ጠረጴዛው ላይ የሚጠብቀው ሻንጣዎች ነው? ተራ በተራ ከፈትኳቸው” አንዱ በዶላር ተሞልቷል! … በሚቀጥለው ዩሮ! … በሚቀጥለው … ፓውንድ! … ጥቂት የታይላንድ ገንዘቦች ጠረጴዛው ላይ ተበታትነዋል፡፡ ይኸ ሁሉ የኔ ቢሆንስ? … ልክ ይኸን እንደተመኘሁ አስራ አንድ በመቶ አይደለም! (በለው!) … አርባ አራት በመቶ ያደግን መሰለኝ! በሕልሜ መሀከል “እርጉዝ ላም ያለው ድርቅን አያውቅም” የሚለው ብሂል ቢመጣም ከልቤ አልጣፍኩትም፡፡ ብሮቹን ተራ በተራ በእጆቼ መዳሰስ ጀመርኩ፡፡ መዳሰስ ብቻ! ወይ አንስቼ አልጨበጥኳቸው ወይ ወደ ኪሴ አልከተትኳቸው እንዲሁ እየዳሰስኳቸው ሳለ ከዕንቅልፌ ነቃሁ፡፡ እንደ ነቃሁ ዙሪያዬን ተመለከትኩ፡፡ ማንም ካጠገቤ አልነበረም፡፡

“ድኃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ንጣት በገደለው ነበር!” ሳቄን ለቀቅሁት! እየሳቅሁ ልብሴን ለባብሼ ወጣሁ፡፡ ይኸ ቅዠት እንጂ ህልም አይደለም እያልኩ፡፡ ቆይ ያ ሃያ ዓመት ሙሉ በቴሌቪዥን የማየው ሰውዬ በህልሜ ሳልጐበኘው በቅዠቴ መሀል ብቅ ማለቱ ደግ ሰራሁ ብሎ ነው? አክስቴ ቡና አፍልታ ቁርስ አቅርባ እየጠበቀችኝ ነበር፡፡ ተኝቼ ያየሁትን ሁሉ ነገርኳት፡፡ ካዳመጠችኝ በኋላ “አብረውህ ተሚሰሩት ፈረንጆች ተወይትኛዋ ጋር ነው የጀመርኸው?” “ምን የጀመርኩት?” “እንዲያው … ፍቅር ቢጤ” አለችኝ፤ ፈገግታዋን አክላ “እንዴት ማለት?” “አሀ! የነገርከኝ ህልም ነዋ! ዶላር፣ ፓውንድ፣ ዩሮ ማይደል ያልኸኝ? … ዙሮ ዙሮ ገንዘብ መሆኑ ማይደል?” “እና?... ቢሆንስ?” “ገንዘብ በህልም ከታዬ ልጅ ነው … ተማንኛዋም ይሁን ልጅ ልትወልድ ነው” አለችኝ “ዳሰስኩት እንጂ … በእጄ አልያዝኩትምኮ!” “ሁሉም በዳሰሳ ነው የሚጀምረው! … ሌላውን አንተ ታውቃለህ፡፡” ብላኝ እየሳቀች ወደ ጓዳ አመራች፡፡ በህልሜና በቅዠቴ መሀከል ተሰንቅሬ ሳለሁ የበረከት በላይነህ “የፈሪዎች ጥግ” የሚለው ግጥም የመጨረሻ ስንኝ ታወሰኝ፡፡ “ይህ ምስኪን ወገኔ! ላጀበው ጥያቄ እስካልተፈተሸ ቅዠት አቅፎ ያድራል - ህልሙን እየሸሸ”

Read 4765 times
More in this category: « ቀጠሮ እምቢኝ! »