Saturday, 15 June 2013 11:12

ቀጠሮ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

እንደ ማሰላሰያ

አስታውሳለሁ፤ ድሮም እኔ ነበርኩ፡፡አሁንም እኔ ነኝ፡፡ እንደሌሎቹ “እኔ” ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ድሮም አልነበርኩም፡፡ አሁንም አይደለሁ፤ ስጨርስም አልሆንም፡፡ “እና ታዲያ ምንድነው ችግሩ?” ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ጠያቂው እራሴ፤ መልሱን ሳልመልስ ተመልሼ ዝም እላለሁ፡፡ ከድሮውም ፀሃፊ መሆንን እፈልጋለሁ ስል የሰማኝ ማንም የለም፡፡ ምን መሆን እንደምፈልግ ራሴም ለማወቅ ፈልጌ አላውቅም፡፡ እስር ቤት እንደሆነ ግን አውቃለሁ ህይወት፤ ምን መሆን እንደምትፈልግ ወይንም ምን እንደ ሆንክ ሳታውቅ የእስር ዘመንህን ጨርሰህ የምትለቀቅበት፣ ወደነፃነት መልቀቅ የለም፡፡ ሞትም ፤የተወለደ ሁሉ ደግሞ የሚወለድበት አማራጭ የሌለው እጣፈንታ ነው። የመጣውን መቀበል ነው፡፡ እስር ቤቱን ሰብሮ ነፃ የወጣ የለም፡፡ ፀሀፊነትም ነፃ መውጫ አይደለም። የራስን እጣ ፈንታ በድርሰት አለም ገፀ ባህሪዎች ላይ በክፋት መለማመድ ነው፡፡ ክፋቱ ነው ጥሩነቱ፡፡

ክፋትን በክፋት መመለስ ነው የትንሹ ፈጣሪ…የሰው ስራ፡፡ አንድ ወዳጄን ለማግኘት ቀጠሮ ያዝን። በአንድ የእስር ቤቱ ስፍራ፡፡ ብሔራዊ ትያትር ደጃፍ ተባብለን ተቃጠርን፡፡ በብሔራዊ እስር ቤት ውስጥ ጥበበኞች የሚገናኙበት ሁኔታ ራሱ ትያትር ነው። እስረኞች ስለ እስር ቤቱ ሲገልፁ… በትያትር ቤቱ ገለፃቸውን ያቀርባሉ፡፡ ገለፃቸው ሊገልፀው የማይችለው የእሳቱን ክፍል ግን ከቲያትር ቤቱ ውጭ ይኖሩታል፡፡ ኑሮአቸው ሊገለጽ፣ ሊገሰጽም አይችልም፡፡ ለማ? እንዴት ተደርጐ? የቀጠርኩት ወዳጄ ገጣሚ ነው፤ የሙዚቃ አዋቂ ነው፣ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢ ነው፤ የጥበብ መብት አስጠባቂ ነው…ሁሉንም መሆኑ እስረኛ ከመሆን አያድነውም፡፡ ግን የእሱ አይነቶች፤ በእስረኞች ነገድ መሃል ባይኖሩ ትርጉም አልባው እስር እና እስር ቤቱ የእለት ተእለት ተግባሩን አያከናውንም ነበር፡፡ ሽንት ቤቱን የሚያፀዳው ባልኖረ ነበር፡፡

አይጦቹ ወጥመድ ያስፈልጋቸዋል። ካልሆነ በአይጥ ወጥመድ ውስጥ እስረኛው ይወድቃል፡፡ የሞቱትን ካልቀበሩ የሞቱት እነሱን ይቀብሯቸዋል፡፡ የሞቱትን ለመቅበር የሞተውን በህይወት ካለው የሚለይ ዶክተርም ያስፈልጋል። ሁሉም እስረኛ ሆኖ ተወልዶ የሚሞት ቢሆንም በመሞቻው ሰአት የሚቀብረውን ጓዱን በእስር ህያው አድርጐ ማቆየት ይጠበቅበታል፡፡ የህያውነት ህልም የሚመነጨው ከሞት ውስጥ ነው፡፡ ሞት እና መቀበር መድረሻው ሲሆን… መነሻው ይመረጣል፡፡ ከመነሻው እስከ መድረሻ ያለው ጉዞ ደግሞ ህይወት ተብሎ ይጠራል፡፡ በእስር መቆየት መቻል ከነፃነት የበለጠ ይፈለጋል፡፡ የሚፈለገው የማይፈለገውን እንደ ተቃራኒ ያገባዋል፡፡ ከጋብቻው ውስጥ የእስረኛው ሰው ማንነት ይፈጠራል፡፡ በዚህ መሃል እኔና ወዳጄ አለን፡፡ ቀጠሮም አድርገናል፡፡ ቦታም መርጠናል፡፡ ብዙ ቀጠሮ እና ብዙ ምርጫ አለው የህይወት እስር ቤት ቆይታ።

ሁሉም ቀጠሮ ተደማምሮ የሚያመራው ወደ እማይፈለገው ነው፡፡ ሁሉም ቦታ የመጨረሻው ቀጠሮ ተቀጣሪውን የሚያገናኘው መሬት መቀበሪያውን ሊሆን ይችላል፡፡ ከአንዱ ቀጠሮ በኋላ ሌላ ይከተላል፡፡ ይከታተላል፡፡ የቀጠሮ ብዛት እና ከአንዱ ቀጠሮ በማምለጥ በሌላው መጠመድ እድሜን ይጨምራል፡፡ ይደምራል፡፡ ድምሩ ባዶ ነው። ወደማይፈለገው ነው፡፡ ወደማይፈለገው ለማምራት እስረኛ እየተፈላለገ ይገናኛል፡፡ ይገናኛል፣ ይለያያል። ይወያያል፡፡ ወንዴና ሴቴው በቀጠሮ ይተኛኛል፡፡ ከቀጠሮ ሌላ ቀጠሮ ይረገዛል። የተረገዘው ከሆድ ሲወጣ የእስረኛነት ቀጠሮ ተይዞለት ነው፡፡ ሁሉም ቀጠሮ ወደ ማይፈለገው ነው የሚያመራው፡፡ ነፃነት የማይፈለግ ነገር ነው፡፡ ሞት ለህይወት እረፍት ነው፡፡ ህይወት ለሞት ቀጠሮው ነው። በህይወት ቀጠሮ ሞት እየተረገዘ ጽንሱ ይገፋል። እድሜ እንደ ሆድ ይነፋል፡፡ ከዛ ከህይወት እስሩ ወጥቶ ወደ ጐርጓድ ይደፋል፡፡ እየተነፋ ያለው የህይወት ቅጥረኛ የሚደፋውን መቅበር አለበት፡፡ ሞቱን በውስጡ ይዞ በውጭ ሟቹን ይቀብራል፡፡ ያለቅስለታል፡፡ የሚያለቅሰው ለራሱ ነው፡፡

ከራሱ በላይ ለሆነው የራሱ እጣ ፈንታ ያለቅሳል፡፡ ቢቀብረውም ባይቀብረውም ቀባሪ እና ሟች ሊለወጥ በማይችል ውስን የእጣ ፈንታ ጉርጓድ አንድ ላይ ተቀብረዋል፡፡ ለእስር ቤቱ ካቦ የእስር ቤቱ ህግ አይራራለትም። ለሰንሰለት ጐንጓኙ… ሰንሰለቱ ድር አይሆንለትም። የእስር ቤቱን አስተዳዳሪ እስር ቤቱ አያስተዳድረውም…ነፃ በህይወቱ አይለቀውም፡፡ ፍርዱን አያቀልለትም፡፡ ታዲያ ምንድነው ችግሩ? ስል እጠይቃለሁ፤ ወደ ላይ አያለሁ፡፡ መሬታቸው ላይ ያሉ ክዋክብትም በተበየዱበት ሆነው ወደኔ ያያሉ፡፡ እንደኔው ያዝናሉ፡፡ እነሱም እስረኛ ናቸው፡፡ በቀዝቃዛ ጠፈር ላይ በብርሐን ጥፍር የጨለማን ድንቁርና ያደማሉ። ዘላለማዊ ጨለማ በብርሃን ጥፍር ተቧጥጦ ምን መፍትሔ ሊገኝ?! እስረኛ እስር ቤቱን ለመስበር ያደረገው አመጽ ሁሌ የራሱን አእምሮ ሰብሮ በማምለጥ ነው መፍትሔ ሲያገኝ ያየነው፡፡ ከእስር ነፃ የወጣ እብድ ነው ይላሉ፡፡ እብድ በእስሩ ላይ ያኮረፈ…”በእስሩ” የእላይ የሆነ ምስኪን ነው፡፡ ሁሉም ምስኪን ነው፡፡ ሁሉም ማንም ነው፡፡ ጨክኖ የሚመሰክን ወዮለት…በራሱ ደስታን የፈረደ ነው፡፡ ሌሎችን ማስደሰቻ ይሆናል አመፁ፡፡

የነፃነት ህልሙ ግን ሌሎቹን የሚያስፈራ ለእሱ ግን ስቃዩ ነው፡፡ ታዲያ ምንድነው ችግሩ? ስል እጠይቃለሁ …ምንስ ብሆን ማነው የሚጠይቀኝ? ሁሉንም ነገር ማድረግ አልፈልግም…ሁሉንም ማድረግ ግን እችላለሁ፡፡ ሁሉንም ማድረግ ዋጋ የለውም፡፡ ዋጋ የሌለውን ሁሉ ግን አደርጋለሁ፡፡ ነፃ ስለመሆን እሰብካለሁ፡፡ ስብከቴ፤ ክዋክብቶቹ የጠፈርን በጨለማ መደንቆር በብርሃን መርፌአቸው ጠልፈው አንድ ቀን ሙሉ ብርሃን በሰማይ ላይ እንደሚያነጥፉ በጥቅሻቸው እንደሚሰብኩት ነው፡፡ ከዚህ ወዳጄ ጋር ብርሐኖች ሆነን እንዴት ሰማዩን በብርሃን መቅደድ እንደምንችል ልናወራ ነው ቀጠሮ የያዝነው፡፡ የያዝነው ነገር እኛን አይይዘንም። በሰፊው የምናወራው በቀጭኑ አያግባባንም፡፡ ቀጠሮዎች ጥበቃ ናቸው፡፡ ሞትን የምንጠብቅባቸው ፊርማታዎች፡፡ የምንጠብቀው መጓጓዣ አሳፍሮን እየሄደ እንደሆነ ብናውቅም እምንጠብቀው በመምሰል ወደ ቀጠሮአችን እንሄዳለን፡፡ በብዙ ቀጠሮ አንድ ፌርማታ ላይ ሆነን እንጠብቃለን። የምንጠብቀው የምንፈልገውን እንደሆነ እንወያያለን። የሚሆነው ግን የማንፈልገው ነው።

ቀጠሮን “አልፈልግህም” ብትለው እንኳን እርሱ ይፈልግሃል፡፡ ሳትፈልገው ቆይተህ ትሸሻለህ። እሱ ሲፈልግህ ወደ መቃብርህ ፌርማታ ላይ ይጥልሃል፡፡ በተለያየ መቀመጫ ላይ ሆነን የምናወራው በፌርማታው ላይ ቆመን ነው፡፡ ፌርማታው ድሮውኑ መጓጓዣ ነው፡፡ የመቀመጫ ልዩነት ነው ያለን፡፡ ሁላችንም እስረኞች፡፡ ቀድሞ የታሰረ እና ቆይቶ የሚፈታ፣ ቀድሞ የታሰረ ቀድሞ የሚገታ፣ ቀድሞ የታሰረ እና ቆይቶ የሚፈታን ልጅ ብሎ የወለደ አባት …እራሱ እስረኛ ሆኖ ሌሎችን የሚፈታ ጉልበተኛ…መፈታት ወደ ሞት ነው፡፡ ሞት ነፃነት አይደለም፡፡ ሌላ እጣ ፈንታ ነው፡፡ ሌላ ያለመፍጨርጨር እስር፡፡ “እላይ” ሳይሆን “እስር”፡፡ያለ “ከመስበር ወዲያ ሌላ ህላዌ የለም” አልኩት ወዳጄን፤ የአንዱን እስረኛ ግጥም አስታውሼ፡፡ ቀጠሮአችን አገናኝቶናል፡፡ በህይወት አገናኝቶናል በሞትም አይለያየንም፡፡ የነፋን ህይወት በመቃብር ይደፋናል አንገናኝም አንለያይም፡፡ ህላዌ በሙሉ እስር ከሆነ… ህልውና ለህያው ምኑ ነው? ሁሉም ችግር በሆነበት “ምንድነው ችግሩ?” ብሎ የሚጠይቅ…ቢስቅ ማቆም የማይችል ልጅን፣ በሳቁ የሚደማ የካንሰር በሽተኛን እንደመኮርኮር ይቆጠራል፡፡

Read 3271 times