Saturday, 15 June 2013 11:07

“ሕይወት ከአንድ ቀን ደስታና ጭፈራ በላይ ነው”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(7 votes)

ቦታው ጉርድ ሾላ አካባቢ በሚገኘው ሳህሊተ ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ ነው፡፡ ዕለቱ ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ በ10 ሰዓት ላይ፤ ያለ ምንም ግርግርና ሁካታ ቤተክርስቲያኑ ደጅ መጥቶ የቆመው ዲኤክስ የቤት መኪና በውስጡ ሙሽሮችን ይዞ ነበር፡፡ ሙሽሪት ቬሎ ለብሳለች። ባልም በሙሉ ልብስ ደምቋል። በሌላ መኪና የመጡ ሁለት የሴት ሚዜዎች አጀቧቸው። የወንድ ሚዜ የለም፡፡ ሙሽሮቹ ደጀ ሰላሙ ላይ ተንበርክከው ፀሎት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ሥነ ስርዓቱን ለታሪክ የሚያስቀሩ አንድ የካሜራና አንድ የቪዲዮ ባለሙያዎች አሉ። ሙሽሮቹ ፀሎታቸውን ሲጨርሱ በመጡበት ፍጥነት ተመልሰው ሄዱ። በሳህሊተ ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ ከ10 ደቂቃ በላይ ያልወሰደው ሥነ ስርዓት ትኩረት ሳቢ ስለነበር ከሙሽራው ስልክ ቁጥር እንድቀበል ገፋፋኝ፡፡ እሱም ፈቃደኛ ሆነልኝ፡፡

በተለያዩ አገራት፣ ሕብረተሰብና ባህሎች በተለያየ መልኩ ተግባራዊ እየሆኑ ለዛሬ ከደረሱ ልማዶች አንዱ ጋብቻ ነው፡፡ ከግራ ጎኑ በተወለደች አጥንት ተሰርታ፤ ሚስቱ ከሆነችው ሔዋንና ከባሏ ከአዳም ጀምሮ የጋብቻ ሥነ ስርዓት ብዙ አስገራሚ ታሪኮችን እያስመዘገበ ለዛሬ ደርሷል፡፡ 33 ዓመት በምድር የቆየው ኢየሱስ ክርስቶስ በተለይ በመጨረሻው ሦስት ዓመታት አስገራሚ ተአምራትን መሥራት የጀመረው በቃና ዘገሊላ በተገኘበት ሠርግ ቤት ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየር ነው፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በሠርግ ወቅት የተከሰቱ አስደማሚ ገጠመኞች ተሰብስበው ቢፃፉ (በዚህ ዙሪያ የተሰራ ነገር መኖሩን አላውቅም) ዳጎስ ያሉ በርካታ መፃሕፍት ሊዘጋጁበት የሚችል ነው ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ “አዝናኝ ትዝታ” በሚል ርዕስ በመድኃኔ ዘካርያስ የቀረበው የሠርግ ገጠመኞች ለዛሬው ጽሑፍ መነሻ ሆኖኛል፡፡ ለሕብረተሰብ መሠረት የሆነው ጋብቻ ሲፈፀም፤ በየሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ አስገራሚ፣ አስተማሪ፣ አዝናኝ፣ አናዳጅ … ሁነቶች ይከሰታሉ፡፡

ባለ ሀብቶች፣ ምሁራን፣ መንፈሳዊ ሰዎች … ሲያገቡ በየሠርግ አዳራሹ ብዙ ታሪክ ታይቷል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንኳን አንዳንድ የአገራችን ታዋቂ አትሌቶች በታሪክ ሊጠቀሱ የሚችሉ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችን ፈጽመዋል፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ በአትላንታ ኦሎምፒክ አሸንፎ ሲመጣ አየር መንገድ ግቢ ውስጥ የቀለበት ሥነ ሥርዓት በመፈፀም ነበር ባለትዳር የሆነው፡፡ የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሠርግ ደግሞ በ35 ሚሊዮን ብር በተሰራ የመናፈሻ ቦታ ላይ ነበር የተካሄደው፡፡ በሒልተን ሆቴል መስመር የሚገኘውና አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ የሚል ሦስት የተለያዩ ክፍሎች ያሉት የመናፈሻ ሥፍራ፤ በሼህ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን ልግስና በአዲስ መልክ ከተሰራ በኋላ፣ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ የመሞሸሪያ ዕለት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ ሠርጉን በአዲስ አበባ ስታዲየም በማሰናዳት ብቻ ሳይሆን ባለቤቱ የምትለብሰው ቬሎ 600 ሜትር ርዝመት እንዲኖረው በማድረግ በዓለም ሪከርድ ለመመዝገብ ሞክሯል፡፡ በጊነስ ቡክ መመዝገብን ዓላማ ያደረገ የሠርግ ሥነ ስርዓት ደግሞ በቅርቡ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ተከናውኗል።

በዚህ ሠርግ ላይ ሙሽራውና ሙሽሪት እያንዳንዳቸው 100 ሚዜዎችን፣ በድምሩ 200 ሚዜዎች በማሰለፍ የልዩ ታሪክ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። እነዚህ ጥንዶች እግረ መንገዳቸውን ለሠርጋቸው የጠሯቸው ሰዎች የአመለካከትና የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንዲያገኙ ባለሙያዎችን በመጋበዝ እንዲያስተምሩላቸው አድርገዋል፡፡ በተለያዩ ሠርጎች ላይ ጋብቻ ፈፃሚዎች በሚለብሱት ልብስ፣ በሚያዘጋጁት አዳራሽና የምግብ ዓይነት፤ በሚጓዙበት የትራንስፖርት ዓይነት፤ በሚያጅቧቸው መዘምራን፣ ፈረሰኞች፣ ሞተር ባይስክሎች፣ ጋሪዎች … የተለዩ ለመሆን ሲጥሩ ይታያል፡፡ ውድ በሆኑ ሊሞዚንና ሠረገላ ከመሞሸር ባሻገር ለሠርጋቸው ሒሊኮፕተር የሚከራዩ ተጋቢዎች እየታዩ ነው፡፡ ተጋቢዎች ልዩ ታሪክ ለማስመዝገብ ወይም አስተማሪ መልዕክት ለማስተላለፍ የሚጠቀሙበት ዘዴ አንዳንዱ ከፍ ያለ ወጭን ሲጠይቅ፣ከፊሉ የገንዘብ ብክነትን ሲያስቀር ይታያል፡፡

በቅርቡ ሥራና ታሪካቸው በዚሁ ጋዜጣ ላይ የቀረበላቸው ዶክተር ማይክል ዳንኤል አምባቸው (ዐፈሩ ይቅለላቸው) “የትዳር አጋሬን ከወላጆቿ ቤት ወደ እኔ ቤት የማመጣት መኪና ተከራይቼ ሳይሆን በግል ቮልስ ዋገን መኪናዬ ነው” ብለው በተግባር አሳይተዋል፡፡ በሠርጋቸው ዕለት አስተማሪ ተግባራትን ካከናወኑ ኢትዮጵያዊያን መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህሩ “የኔታ” አለማየሁ ሞገስ ምሳሌነትን መጥቀስ የግድ ይላል፡፡ በ1954 ዓ.ም “ሠርግና ልማድ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው፤ የማይጠቅሙንና ጎጂ ባህሎቻችን ናቸው የሚሏቸውን ለማስወገድ፤ የራሳቸውን የጋብቻ ሥነ ስርዓት ባልተለመደ መልኩ ስለመፈፀማቸው ዝርዝር ታሪኩን በመጽሐፉ አቅርበዋል፡፡ ባልተጠበቁ መንፈሳዊ ጉባኤዎች ላይ፤ በዩኒቨርስቲ የተማሪዎች መመረቂያ መድረክ፤ ለሠርግ ሥነ ስርዓት በማይታሰቡ ዕለትና ሰዓታት … የተለያዩ ጋብቻዎች ሲፈፀሙ ይታያል፡፡ ግንቦት 29 ቀን በሳህሊተ ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ በአጋጣሚ ያገኘኋቸው ሙሽሮችም በዚህ ክፍል ሊመደቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ በዕለተ ሐሙስ፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሙሽሮች ብቻቸውን በቤተክርስቲያን ግቢ ይገኛሉ ብሎ ማሰቡም ሆነ መገመቱ ያልተለመደ ይመስላል፡፡ አቶ ብዙአየሁ በላይ የቴሌኮሚኒኬሽን ሠራተኛ ሲሆን ወ/ሮ የዓለምዘውድ ተስፋዬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ናት፡፡

የዛሬ 8 ዓመት የግል ኮሌጅ ተማሪ ሳሉ የጀመረው ትውውቃቸው እያደገ መጥቶ በጋብቻ ተሳስረው አብረው ለመኖር ከወሰኑ አንድ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ሠርጋቸውን ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ ብዙ አስበውበታል፡፡ ሙሽሪት ለሚዜነት የመረጠቻቸው ሁለት እህቶቿን ነው፡፡ አቶ ብዙአየሁ ሚዜ አያስፈልገኝም ብሏል፡፡ ለትራንስፖርት መኪና ቢከራዩም በአበባ አሳምረው ትኩረት መሳብ አልፈለጉም፡፡ ቀድመው ወደ ሙሽሪት ቤት ሽማግሌዎች ከመላካቸው ውጭ ሁሉም የሠርግ ሥነ ሥርዓት በአንድ ቀን ነው ያለቀው፡፡ ሐሙስ ጠዋት እሷም ከቤቷ፣ እሱም ከመኖሪያው ወጥቶ ቦሌ ክፍለ ከተማ ጋብቻ ማፈራረሚያ ቢሮ ተገኙ፡፡ በዕለቱ ብዙ ሙሽሮች ስለነበሩ በመቀመጥ ጊዜያችንን ከምንጨርስ ብለው ወደ ፎቶ ስቱዲዮ ሄዱ፡፡

ቀለል ያሉ ፎቶግራፎችን ከተነሱ በኋላ ለምሳ የጠሯቸው 40 እንግዶች ወደሚጠብቋቸው ሬስቶራንት አቀኑ፡፡ ከምሳ በኋላ እንግዶቻቸውን አሰናብተው በክብር መዝገብ ላይ ለመፈራረም ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሄዱ፡፡ ያንን ሲጨርሱ በሲኤምሲ አካባቢ ወደሚገኘው የአትሌቶች መንደር መኖሪያ ቤታቸው ሲሄዱ እግረ መንገዳቸውን በሳህሊተ ማርያም ቤተክርስቲያን የፀሎት ሥነ ስርዓት አከናወኑ፡፡ “ብዙ ተጋቢዎች ያልተገባ ወጭ በማውጣት ለጭቅጭቅና ለትዳር መፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ተግባራት ሲፈጽሙ ማየታችን የእኛን ሠርግ ቀላል ለማድረግ አነሳስቶናል” ያሉኝ ሙሽሮቹ ፣ “ሕይወት ከአንድ ቀን ደስታና ጭፈራ በላይ ትርጉም ያለው ነገር ነው፡፡ ሕይወት ስለ ነገ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ይህን ሃቅ መረዳታችን ነው ሠርጋችንን ቀላል ያደረገው” ብለዋል፡፡

Read 7674 times