Print this page
Saturday, 15 June 2013 10:51

‘መኝታ’ እና ‘ቀለብ’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…አዲስ አበባ ውስጥ በብዙ አቅጣጫ መንቀሳቀስ እንዲህ አስቸጋሪ ይሁን! የምር ግን…በተለይ የመኪናውን ትርምስ ያባባሰው ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ሁላችንም መንገዱን በሊዝ የተኮናተርነው ይመስል ‘ቀድመን ማለፍ’ ስለምንፈልግ ይመስለኛል፡፡ ልክ እኮ…አለ አይደል… ቀድሞ ያለፈው ሰው የሆነ ቦታ “ማሰሮ ወርቅ ይጠብቀዋል…” የሚል መመሪያ ነገር የወጣ ነው የሚመስለው፡፡ ከተማዋ በአብዛኛው የእሽቅድድም ሜዳ ሆናለች! ግለኝነታችን በዛ!… በጣም በዛ!… እጅግ በጣም በዛ! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ትራፊክ ፖሊሶች እያስተናበሩ እንኳን ለመሽቀዳደም መሞከር ምን ይባላል! በዚች እንኳን “አንተ ትብስ/ አንቺ ትብሽ” መባባል ሲያቅተን…ያሳዝናል፡፡ አለ አይደል…በአንዲት ስኩዌር ሜትር አስፋልት ላይ አምስት ሆነን ‘እኔ እቀድም፣ እኔ’ እየተባባልን እንዴት ነው የእውነት ከልባችን ለአገር የጋራ ህልም የሚኖረን! ደጉን ያምጣልንማ! እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የህልም ነገር ካነሳን አይቀር… ይቺን አንድ ወዳጄ ሰብሰብ ብለን ሳለ ያጫወተንን ስሙኝማ…ሰውየው ህልም በጣም አስቸግሮት ሲገላበጥ ነው የሚያድረው፡፡ እናላችሁ…መፍትሄ ባገኝ ብሎ አንድ የሚያውቃቸው ቄስ ዘንድ ይሄዳል፡፡

ለእሳቸውም “አባ ህልም አስቸገረኝ፣ ሰላማዊ እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም፣” ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም “ለመሆኑ ምን አይነት ህልም ነው የምታየው?” ይሉታል፡፡ እሱም… “በቃ፣ የሆነ በሬ እንዲሁ አገር ለአገር ሲያሳድደኝ ነው የሚያድረው” ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም “ያው ሁላችንስ ህልም እናይ የለ፣ ግዴለም ይተውሀል፡፡ ደግሞ ሌላ ቀን ሌላ አይነት ህልም ታያለህ” ይሉታል። እሱም “ኧረ አባ… ይኸው በሬ በየዕለቱ አልለቀኝ ብሎ ሲያሳድደኝ ስንት ሳምንቴ!” ይላል፡፡ ይሄኔ ቄሱ “ለመሆኑ ምን ላይ ነው የምትተኛው?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ እሱም “ሳር ፍራሽ ላይ…” ሲል መለሰላቸው፡፡

ይሄኔ ቄሱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…“ታዲያ በሬውስ ቢሆን ምን ያድርግ… ቀለቡ ላይ ነው እኮ የተኛህበት…” አሉት አሉ፡፡ (ወዳጄ ስለ ‘ኮፒራይቱ’ በኋላ እንነጋገራለን፡፡) እና ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ቀለባችን ላይ ተኝተውብን…ወይ ማንቀሳቀስ አንችል፣ ወይ ራሳቸው አይንቀሳቀሱ! መሥራት የምትችሉትን ነገር ሁሉ በተለያየ ምክንያት መሥራት እንዳትችሉ ስትሆኑ… ቀለባችሁ ላይ ተተኝቶበታል ማለት ነው! ሙሉ አቅማችሁን ተጠቅማችሁ እንዳትሠሩ የቃልና የጽሁፍ መመሪያዎች፣ ሰርኩላሮች ‘የኮሚቴ ውሳኔዎች’ ምናምን እንቅፋት ሲሆኑባችሁ…ቀለባችሁ ላይ ተተኝቶበታል ማለት ነው! በአለቃነት ሰፊ ወንበር ላይ ተቀምጠው (‘ተኝተው’ የሚለውም አማራጭ ሊሆን ይችላል) እንደ ፈረስ ልጓም ካላገባሁልህ፣ እንደ በቅሎ ካልተቀመጥሁህ... ምናምን ሲሏችሁ ቀለባችሁ ላይ ተተኝቶበታል ማለት ነው! ዕውቀቱና ችሎታው ሳያንሳችሁ የሚገባችሁን ቦታ በ‘ቦተሊካ’ ወገንተኝነት ወይም በ‘አገር ልጅነት’ እንድታጡት ሲደረግ… ቀለባችሁ ላይ ተተኝቶበታል ማለት ነው! ቀን ተሌት እየፈጋችሁ በኦፊሴላዊ ወረቀቶችና ኦፊሴላዊ ባልሆኑ የመጋረጃ ጀርባ ሹልክልኮች የሚገባችሁን ዕድገትና የተሻለ ቦታ እንዳታገኙ ስትደረጉ…ቀለባችሁ ላይ ተተኝቶበታል ማለት ነው! እናላችሁ…እንዲህ፣ እንዲህ ቀለቦቻችን ላይ የተኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡

(በሬውስ ቢያንስ፣ ቢያንስ ቀለቡን ነጻ ለማውጣት በ‘ህልም’ እንኳን መጥቶ ያሳድዳል፡፡ እኛ አለን እንጂ…አለ አይደል…ሥጋዊና መንፈሳዊ ‘ቀለቦቻችን’ ላይ ተተኝቶባቸው እኛም ለሽ ብለን አብረን የተኛን!) ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ጥያቄ አለን… ይሄ ሰውየውን በህልሙ እያሳደደ ያስቸገረው በሬ…አንድ ጊዜ መንገድ ላይ እየተነዳ ሲሄድ ሳለ አልሄድም ብሎ ለግሞ በጆሮው “እንትን መጣልህ!” ሲሉት በአራት ሳይሆን በአሥራ አራት እግሩ ‘ያቀጠነው’ በሬ ይሆን እንዴ! ልክ ነዋ…ዘንድሮ እኮ በአንደኛው በር ወጥቶ “ላይመለስ ዓለም ዳርቻ ሄዷል” ያላችሁት በሌላ በር ተመልሶ ከች ይልላችኋል፡፡ የህልም ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝ…ሚስት ሆዬ ጧት ከእንቅልፏ ስትነቃ ለባሏ… “ዛሬ እንዴት አይነት ቆንጆ ህልም አየሁ መሰለህ…” አለችው፡፡ ባል ምን አየሽ አላት፡ ሚስትም ምን የመሰለ ሀያ አራት ካራት፣ ሠላሳ አምስት ግራም የወርቅ ሀብል በስጦታ ስትሰጠኝ አየሁ፡፡

ትርጉሙ ምን ይመስልሀል?” ስትል ጠየቀችው፡፡ ባልም “ማታ መልሱን ታገኚዋለሽ…” አላት፡፡ ማታ ሲመጣም የሆነ ነገር በአሪፍ የስጦታ ወረቀት የተጠቀለለ ነገር ይዟል፡፡ ሚስትም በደስታ ተጠመጠመችበት። እየተፍነከነከች የተጠቀለለበትን ወረቀት ስትከፍተው ምን አገኘች መሰላችሁ…‘የህልም አተረጓጎም’ የሚል መጽሐፍ! እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ሳልረሳው… ጥያቄ አለን፤ በቃ የፈርኦን ሰዎች “ካልሆነማ…” ምናምን አይነት የተዘዋዋሪ “ነብር አየኝ በሉ!” ምናምን ሲሉ…አለ አይደል…ነገርዬው “ቀጥኜ ቢያየኝ ጅማት ለመነኝ!” ምናምን አይነት መሰለ እኮ! አሀ…ቢሆንም ባይሆንም “አይ አልበዛም! በአባቱ ባድማ የተኛውን በሬ ባትነካኩት ይሻላችኋል…” አይነት ነገር ማለት ያስፈልጋላ! የጣይቱ “ከፈለግህ ዛሬውኑ አድርገው…” ይሄኔ ነበር! ነው… ወይስ ወዳጃችን “እመሃል ገብታ በለው…” የምትለውም፣ ወዳጃችን አፋፍ ቆማ “ተው ሽሽ…” የምትለውም ተቀላቅለን ያረፍን መሰላቸው! ነገርዬው…አለ አይደል…‘ቁርበት ምን ያጓጓሀል ቢሉት ባያድለኝ ነው እንጂ የነጋሪት ወንድም ነበርኩ አለ’ አይነት እንዳይሆን፡፡

(ደግሞም…አንዳንድ ‘ቦሶቻችን’ መፎከር ‘እኛ’ ላይ ብቻ አይደለም! “ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት ሚስቴን አለ…” የሚለው አባባል ለምን ትዝ እንዳለኝ ለማወቅ እየሞከርኩ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…) ልጄ ሰዎቹ ካሜራ እያለ እንደዛ ከተለፋለፉ፣ ብቻቸውን ሲሆኑማ የማይሉን አይኖርም ማለት ነው፡፡ ስሙኝማ…ምን ያሳዝንሀል አትሉኝም፣ ምናልባት ሊሆን የማይችል ቢሆንም ወይም የመከሰቱ ነገር በጣም የጠበበ መሆኑም ጦርነት የሚለው ቃለ ዕለታዊ መዝገበ ቃላታችን ውስጥ እንደገና ‘ሾልኮ መግባቱ’ አያሳዝናችሁም? የእኛ የማዳመጫ ህዋሳት በጎ፣ በጎ ነገር ሳይጠግቡ ሌላ ሚሌኒየም ሊደርስ ነው! አንድዬ ብቻ ሁሉንም ያስተካክለው! እኔ የምለው…የተለያዩ ሚዲያዎችን ስትሰሙ ደግሞ አንዳንዴ የሚሰጡት ማብራሪያዎች ‘የተሳሳተ’ ከመባል ይልቅ ‘ውሸት’ ወደ መሆን ይጠጋሉ፡፡ እናማ… ግጥምና መዝሙር ብቻ ሳይሆን “እንዲህ በአደባባይማ እንደልባችሁ ስትዋሹ ዝም አንልም…” ማለት ያስፈልጋል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንድ ሰውዬ ማንም ሰው ውሸት በሚናገርበት ጊዜ በጥፊ የሚያጮል መሣሪያ ይፈለስፋል፡፡

ማታ ሰውየው፡— ሚስቱና ወንድ ልጃቸው ለእራት ይቀመጣሉ፡፡ አባት፡— ጎረምሳው፣ ዛሬ በትምህርት ሰዓት የት ነበርክ? ልጅ፡— ትምህርት ቤት (መሣሪያው በጥፊ አጮለው) አይ፣ ሲኒማ ገብቼ ነበር፡፡ ምን ፊልም አየህ? ልጅ፡— ሃሪ ፖተርን (መሣሪያው በጥፊ አጮለው) አይ፣ የወሲብ ፊልም ነው ያያሁት፡፡ አባት፡— ምን! እኔ በአንተ ዕድሜ በነበርኩበት ጊዜ የወሲብ ፊልም አይቼ አላውቅም (መሣሪያው በጥፊ አጮለው) ሚስት፡— ምንም ቢሆን የአንተ ልጅ ነው፡፡ (መሣሪያው ደህና አድርጎ በጥፊ አጮላታ!) ስሙኝማ…የህልም ነገር አንስተን የለ…ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሰውየው አሉ ብዙ ጊዜ በህልሙ የሚያየው ጓደኞቹን ብቻ ነው፡፡ እንደውም በእውኑ ከሚያገኛቸው ጓደኞቹ በህልሙ የሚያገኛቸው ይበዛሉ! ታዲያላችሁ… ማንኛውንም ጓደኛውን በህልሙ ባየ ቁጥር ድምጹን ከፍ አድርጎ “ሄሎ!” ይላል፡፡ ሚስት ደግሞ እሱ በጮኸ ቁጥር እየባነነች ተቸግራለች፡፡

እናማ…ነገርየው ስልችት ያላት ሚስት አንድ ቀን ማታ ምን አለችው መሰላችሁ… “ዛሬ ድንገት በህልምህ የሆነ ጓደኛህን ካገኘህ እባክህ እጅህን አወዛውዘህ ብቻ ሰላም በለው፡፡” አሪፍ አይደል! እናላችሁ…በሬው ቀለብ ላይ እንደተኛው ሰው ቀለባችን ላይ ‘የተኙብን’ መአት ነገሮች አሉ፡፡ ከአስተሳብና አመለካከት ጀምሮ እስከ ግለኝነትና ፍጥጥ ያለ ክፋት ድረስ… ቀለባችን ላይ የተኙ ነገሮች ተቆጥረው አያልቁም፡፡ አንድ በአንድም፣ በጅምላም ቀለባችን ላይ ያለ ቀስቃሽ ‘ለሽ ያሉትን’ ነገሮች የሚያነሳልንን ተአምር አንድዬ ይላክልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4613 times