Saturday, 15 June 2013 10:47

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዛሬ ሁለት ሳምንት 200 የሚደርሱ አባላት የተካተቱበት እውቅ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲከኞች ቡድን፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት አስተባባሪነት “የምስራቅ ኢትዮጵያን እንወቅ” በሚል መርህ የሶማሌ፣ የሃረሪ ክልል እና የድሬዳዋ መስተዳድርን ጐብኝተዋል፡፡ በዚህ ፅሁፌ በጉብኝቱ ወቅት ይፋ ስለተደረጉ አንኳር ፍሬ ጉዳዮች የማስቃኛችሁ ሲሆን ፅሁፌን የምጀምረውም የሱማሌ ህዝብ እንዴትና ለምን ኢትዮጵያዊ ሆነ ከሚለው ነው፡፡

አፍሪካን በቅኝ ግዛት በመቀራመት እንግሊዝ እና ፈረንሣይ ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ላይ አንዣብባ የነበረችው ጣሊያንም ተጠቃሽ ናት፡፡ እነዚህ ሶስት ሃገሮች የዛሬዋን ሶማሊያ በመቀራመት የኢጣሊያ ሶማሌ፣ የእንግሊዝ ሶማሌ እና የፈረንሣይ ሶማሌ (ጅቡቲ) እያሉ ያስተዳድሩ ነበር፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ይገኙ የነበሩ የሶማሌ ጐሣ አባላትንም በተለይ እንግሊዞች ድንበር ጥሠው እየገቡ አስተዳድረዋል፡፡ ለአካባቢው ማህበረሠብ ከማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግስት የተሠጠው ትኩረት እምብዛም በመሆኑም እንግሊዞች በአካባቢው የሶማሌ ተወላጆች ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ያደርጉ ነበር፡፡

የተለያዩ እርዳታዎችንና እጅ መንሻዎችን በማቅረብም በማህበረሠቡ ዘንድ ትልቅ ተሠሚነት ያላቸውን የጐሣ መሪዎች እየሠበሠቡ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ክህደት ፈፅመው አብረዋቸው እንዲያብሩ ይገፏፏቸው ነበር፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያን መንግስት ትተው በእነሡ አስተዳደር ስር እንዲጠቃለሉ ይወተውቷቸው ነበር፡፡ የሃገር ሽማግሌዎችና የጐሣ አባላትን እየሠበሠቡ፣ ከኢትዮጵያ መንግስት “ቅኝ አገዛዝ” ይልቅ የእንግሊዝ መንግስትን አስተዳደር በመምረጥ የአውሮፓዊ ስልጣኔ ተቋዳሽ ሲሆኑ በተደጋጋሚ መክረዋቸዋል፡፡ ይህን ተደጋጋሚ ውይይት የሚያደርጉት ደግሞ የክልሉ እምብርት በሆነው ለኦጋዴን አካባቢ በመገናኘት ነው፡፡ አሁን ያለው የክልሉ መንግስት ለጉብኝቱ አባላት ስለዚህ ታሪካዊ ሂደት ገለፃ አድርጓል፡፡

ለ“ኢትዮጵያ” ሶማሌዎች የእንግሊዝ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያቀርበው የእኔ ግዛት አካል ሁኑ ጥያቄ ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ያገኘው ዛሬ በሸበሌ ዞን በደናን ወረዳ ውስጥ በምትገኘው “ካሊ” በተባለች ስፍራ ነው፡፡ በወቅቱ ተልዕኮ የተሠጣቸው የእንግሊዝ መንግስት ተወካዮች ካሊ በመገኘት የሃገር ሽማግሌዎችን ሠበሠቡ፡፡ ሽማግሌዎቹንም ወይ እንግሊዝን ወይ ኢትዮጵያን እንዲመርጡና ቁርጠኛ ውሣኔያቸውን እንዲያሣውቋቸው ጠየቁ፡፡ የሃገር ሽማግሌዎቹ ግን ከእንግሊዝ ይልቅ የኢትዮጵያ መንግስት ይሻለናል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንጂ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አካል መሆን አንፈልግም ሲሉ በዚህች ታሪካዊ ቦታ ላይ አሣወቁ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላም ሱማሌዎች በኢትዮጵያዊነት ፀኑ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ይህን ታሪክ ለትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት የወሠዱት የሃገር ሽማግሌዎች ለጉብኝቱ አባላት እንደገለፁት፤ እንግሊዞች በዚህ ውሣኔ ተናደው ከአባባቢው ከመሄድ ባሻገር ይህ በሚስጥር ሲያደርጉት የነበረው ድርድር በማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግስት እንዳይሠማ ስጋት አድሮባቸው ነበረ፡፡

ምክንያቱም በወቅቱ ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ነበራትና ነው፡፡ በእንዲህ ያለ መልኩ ኢትዮጵያዊነትን የመረጡት ሱማሌዎች፤ ከተቀሩት ሱማሌዎች ንቀትና ጥላቻን አትርፈዋል፡፡ ይህ እውነታም ለዘመናት ደብዝዞ እንዲቀር የእነዚህ ሃይሎች ሚና ቀላል እንዳልነበረ መረዳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ ከእንግሊዝ የቀረበለትን የሪፈረንደም ምርጫ ኢትዮጵያዊነትን በመምረጥ ያጠናቀቀ መሆኑ በማዕከላዊው መንግስት የሚታወቅ ባለመሆኑ፣ ሁሌም በሃገር ክህደት ጥርጣሬ የሚታይ ነው፤ ይህም ሆኖ በአፄ ሃይለ ስላሴ ዘመን ሃገሪቱን ከቅኝ ግዛት ናፋቂዎች በምስራቅ በኩል በመከላከል በደጀንነት ሚናውን ተወጥቷል፡፡ “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን” የሚለው ውሣኔ በሃገር ሽማግሌዎች ከተላለፈ በኋላ፣ በክልሉ ህዝብ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ የተገለጠው የዚያድ ባሬ ጦር በ1968 መላዋን ኢትዮጵያ ለመውረር በተንቀሣቀሠበት ወቅትና ከዚያ በኋላ እስከዛሬ ድረስ ባለው ጊዜ ነው፡፡ ታላቋን ሱማሊያ የመመስረት አላማ አንግቦ የተነሣው ዚያድ ባሬ፤ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሱማሌዎችን፣ በጅቡቲ ያሉ ሶማሌዎችንና በእንግሊዝና በጣሊያን ስር የነበሩ ሶማሌዎችን አንድ በማድረግ ታላቋን ሶማሊያ እውን ማድረግ ቀዳሚው አላማ አድርጐ ተንቀሣቅሷል፡፡ የወረራው ቀዳሚ ሠለባ የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑም በርካቶቹ ጦርነቱን ሽሽት ወደ ዋናዋ ሱማሊያ እንዲሸሹ ተደረገ፡፡

የክልሉ የአሁኑ ርዕሠ መስተዳደር አብዲ መሃመድ ለጉብኝቱ አባላት ጅጅጋ ከተማ ላይ ባቀረቡት የክልሉ ታሪካዊ ዳራን የዳሠሠ ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ፤ በወቅቱ ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ሱማሊያ በመሄድ በካምፕ ያረፉ ስደተኞችን እየመለመለ፣ ዚያድ ባሬ በፕሮፓጋንዳ ያጠምቅ ነበር፡፡ ስደተኞቹን የታላቋ ሱማሊያ አካል ናችሁና ሃገራችሁን ከደርግና ከኢትዮጵያ አገዛዝ ነፃ ማውጣት አለባችሁ ይል ነበር፡፡ ሃሣቡን የተቀበሉትንም እያሠለጠነ ለሃይል ፍልሚያው ዝግጁ እንዲሆኑ አስታጠቃቸው፡፡ ድጋፋቸውን ማግኘቱን ሲያረጋግጥም በኬንያ፣ በሞቃዲሾ፣ በጅቡቲና በኢትዮጵያ ያሉ ሱማሌዎችን አንድ አድርጌ ታላቋን ሶማሊያ እውን አደርጋለሁ የሚለው ህልሙ የሚሳካ መስሎት የመጀመሪያ ኢላማውን ሠፊውን የሱማሌ ህዝብ አቅፋ በምትገኘው ኢትዮጵያ ላይ አነጣጠረ፡፡ ለጊዜው የተሣካ የመሠለ ድልም በመቀናጀት መሃል ሃገር ድረስ ዘልቆ በመግባት ብዙ ውድመቶችን አደረሠ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሱማሌዎችንም በአስተሣሠቡ አጠመቀ፡፡ ጥቂት የማይባሉትም ከዚያድ ባሬ ጦር ጋር በማበር መልሠው ሃገራቸውን ወጉ፡፡ አብዛኛው በተለይም ይህን ኢትዮጵያዊ የመሆን የሪፈረንደም ውሣኔ ያፀደቁና ሚስጥሩን የሚውቁት ግን አሁንም የዚያድ ባሬን ወረራ ተቃወሙ፡፡

እንዲያም ሆኖ ለማህበረሠቡ የተሠጠው የኢትዮጵያዊነት ማዕረግ አነስተኛ እንደነበር አቶ አብዲ በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ ደርግ የሱማሌ ማህበረሠብን እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ አይመለከትም፡፡ “አንተ ሽርጣም ሡማሌ” ከሚለው ዘለፋ ጀምሮ በጥርጣሬ ይመለከት ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ አብዛኛው ማህበረሠብ በኢትዮጵያዊነት አስተሣሠብ የተቀረፀ አልነበረም። ደርግ እንዲህ በጥርጣሬ ማህበረሠቡን ሲመለከት ዚያድ ባሬ በበኩሉ፤ ከእሡ ጐን ቆመው የማይዋጉትን ያሠቃይ ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ ህዝቡ ከሁለት ያጣ ሆኖ ለወራት በዘለቀው ጦርነት ብዙ ተጐድቷል፡፡ እንዲያውም ደርግ በዚያድ ባሬ ጦር ተሸንፎ ከቀብሪ ደሃር ለቆ በመውጣት ወደ ደጋሃ ቡር ሲገባ “አንተም ሱማሌ ያም ሱማሌ” እያለ በርካቶችን መጨፍጨፉን አቶ አብዲ በጥናታቸው ይገልፃሉ፡፡ ደርግም ዚያድ ባሬም የኢትዮጵያ ሱማሌን በእኩል ጨፍጭፈዋል፡፡ ደርግ በሃገር ክህደት እየወነጀለ ሲጨፈጭፍ፣ ዚያድ ባሬ ደግሞ አርፋችሁ ተገዙ በሚል ይጨፈጭፍ ነበር፡፡ ህዝቡም በአፀፋው ደርግን ከመውጋት ይልቅ ዚያድ ባሬን ነበር የሚፋለመው የሚሉት አቶ አብዲ፤ በትግሉ ሂደትም ዚያድ ባሬ የሾማቸው የወረዳ አመራሮች ላይ በድብቅ ጥቃት ይፈፅም ነበር፡፡ ለትዕዛዛቸውም ቀና ምላሽ አይሠጥም፡፡

በዚህም ብዙ የዚያድ ባሬ የሡማሊያ አመራሮች ተገድለዋል፡፡ በድርጊቱ የተናደደው ዚያድ ባሬም ጦሩ ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ሲወጣ በመውጫ መንገዱ ያገኛቸውን ኢትዮጵያውያን ሱማሌዎችን ጨፍጭፏል፡፡ የታላቋ ሶማሊያ ጦር ሃገሪቱን ለቆ ቢወጣም በተለይ ኦጋዴን አካባቢ የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሡ ነበር፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ በኋላ ሃገሪቱን ከደርግ ተረክቦ ማስተዳደር በጀመረው የኢህአዴግ ስርአትም ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የክልሉ ህዝብ ሶስተኛው የታሪክ ምዕራፍ የሚጀምረው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ከ1983 ዓ.ም በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለው ሃሣብ ሲመጣ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ የተማሩ የሚባሉ የማህበረሠቡ ተወላጆች ፓርቲ ማቋቋም ጀመሩ። 14 ድርጅቶችም ወዲያው ተመሠረቱ፡፡

እነዚህ ድርጅቶች መመስረታቸው ባልከፋ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉም የተመሠረቱት በዚያድ ባሬ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስትን ሲወጉ በነበሩ ጀነራሎችና የጦር መኮንኖች ነበር፡፡ እነዚህ መኮንኖች ፓርቲዎቹን ሲመሠርቱም በጐሣቸው ተከፋፍለው ስለነበር የኋላ ኋላ ብዙ መዘዞችን አስከትሏል፡፡ በወቅቱ ፓርቲዎቹ የተለያየ ፍላጐት ይዘው ቢመሠረቱም ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው አጀንዳ ግን ነበራቸው፡፡ ይኸውም የሶማሌ ክልልን ከኢትዮጵያ መገንጠል የሚለው ነው፡፡ አስራ ሶስቱ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለውን የሶማሌ ማህበረሠብ ግዛት ይዘን ወደ ታላቋ ሶማሊያ እንቀላቀል ሲሉ፣ የኦጋዴ ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በበኩሉ፤ ከሶማሊያ ጋር ሣንቀላቀል የኦጋዴን ነፃ ግዛት (ሃገርን) መመሥረት አለብን አለ፡፡ ይህ ሁሉ የሃሣብ ፍጭት ሲካሄድ ምንም እንኳ ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረ ቢሆንም የደርግ አመራሮች በሱማሌ ክልል መደበኛ ስራቸው ላይ ነበሩ፡፡ አቶ አብዲ እንደሚሉት፤ በወቅቱ የነበሩት የደርግ አመራሮች ቦታውን ለሱማሌ ተወላጆች ሣያስረክቡ ትንሽ ስልጠና ተሠጥቷቸው ቢቆዩ ኖሮ፣ የኋላ ኋላ በክልሉ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ባልተከሠተ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ደርጐችን ከቦታው ሲያስለቅቅ ወዲያው የዚያድ ባሬ ጀነራሎች እና የደህንነት ሠዎች ነበሩ ቦታውን የተቆጣጠሩት። የመጀመሪያውን የክልሉን መንግስት ስልጣንም ኦብነግ ተቆጣጠረ፡፡

የተቀሩት 13 ድርጅቶችም በጐሣ ተሰባጥረው “ሊግ” የሚባል የጋራ ህብረት የፈጠሩ ቢሆንም ብዙም ሣይቆይ ሊፈርስ ችሏል፡፡ ኦብነግ ነፃይቱን ኦጋዴን ለመመስረት ይንቀሣቀስ እንጂ ዋነኛ የአስተሣሠብ ቅኝቱ የዚያድ ባሬ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ ጀምሮ የኢትዮጵያን ባንዲራ፣ የህዝብ መዝሙር፣ መከላከያ የመሣሠሉትን ብሄራዊ መገለጫዎችን አይቀበልም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታም ክልሉ እስከተረጋጋበት እስከ 2000 ዓ.ም ቀጥሎ መስተዋሉን አቶ አብዲ ይገልፃሉ፡፡ የክልሉ ብሄራዊ መዝሙር ቀደም ሲል ለታላቋ ሶማሊያ ሠንደቅ አላማ የተዘመረ ነበር፡፡ በፍሬ ሃሣቡም የኢትዮጵያ መንግስትን አጥብቆ የሚቃወም ነው፡፡ ይህ መዝሙር ሲዘመር በነበረበት ከ1983-2000 ዓ.ም በርካታ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት የመዝሙሩን ፍሬ ሃሣብ ሣይገነዘቡ አብረው ቆመው ዘምረዋል የሚሉት አቶ አብዲ፤ በኋላ እውነታው ወጥቶ ከኦብነግ ርዝራዦች ከክልሉ ተጠራርጐ መጥፋት ጋር አብሮ መክሠሙን አስረድተዋል። አሁን ስለ ክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ የሚዘረዝረው መዝሙርም ከሚያዝያ 4 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ እንደዋለ ተመልክቷል፡፡ ክልሉን ከኦብነግ ይፋዊ “ፋኖ ተሠማራ” አዋጅ በኋላ ተረክቦ ሲያስተዳድር የነበረው የሶማሌ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ሶዴፓ)ም ከጐሣ አመለካከትና ከኦብነግ አስተሣሠብ የፀዳ አልነበረም፡፡ በውስጡ የነበሩ በርካታ አመራሮች በሁለት ቢላዋ የሚበሉ ነበሩ፡፡ በአንድ በኩል ህገመንግስቱን የተቀበሉ በማስመሠል ከፌደራል መንግስት ጋር ተባብረው ሲሠሩ፣ በሌላ በኩል ጫካ ለሚገኘው ኦብነግ ስንቅ በማቀበልና የጥቃት በሮችን በመክፈት ይተባበሩ ነበር፡፡

ከፌደራል መንግስት የሚላከው በጀት ሣይቀር ጫካ ለሚገኙት የኦብነግ ታጣቂዎች በደሞዝ መልክ ጫካ ድረስ ተወስዶላቸው ፈርመው ይቀበሉ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የኋላ ኋላ ኦብነግ እየተጠናከረ መጥቶ ራስ ምታት ለመሆን የመቻሉ ምስጢር አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ኦብነግ እንዴት ተጠናከረ? በዘውዳዊው ስርአትና በደርግ ጊዜ የክልሉ ማህበረሠብ የሁለተኛ ዜግነት ማዕረግ እንዲኖረው መደረጉና ከሌላው የሃገሪቱ ማህበረሠብ የተለየ ተደርጐ መቆጠሩ፣ ህዝቡ ነፃ እናወጣሃለን ለሚሉት ልቡ እንዲያደላ አድርጓል፡፡ ኢህአዴግ ከመጣ በኋላም ይህ አስተሣሠብ ባለመቀየሩ የበለጠ ለኦብነግ ፕሮፓጋንዳ አመቺ ሆነ፡፡ ኦብነግ ለህዝቡ በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች “አማርኛ የሚናገር ደርግ ሄዶ ትግርኛ የሚናገር ደርግ መጣ” ይል ነበር፡፡ በዚህ የህዝቡን በተለይም በማህበረሠቡ ትልቅ ቦታ የሚሠጣቸውን የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችን ቀልብ መግዛት ቻለ፡፡ ድጋፍም በሠፊው አገኘ፡፡ በትጥቅ፣ በኢኮኖሚ፣ በኔትወርክ (ግንኙነት) በደንብ ተጠናከረ፡፡ በርካታ የክልሉን ዞኖችና ወረዳዎችም በእጁ አስገብቶ ያስተዳድር ነበር፡፡

በጅጅጋ፣ በጐዴ ከሚገኙ አራት ካምፖች በስተቀር ሁሉም ወታደራዊ ካምፖች በቁጥጥሩ ስር ነበሩ - እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ፡፡ ይህን እንቅስቃሴያቸውን ደግሞ ከኢህአዴግ ጐን በአጋርነት ተሠልፎ ይመራ የነበረው የወቅቱ አስተዳደር ይደግፍ ነበር፡፡ የክልሉ አመራሮች ስድስት ወር ህዝቡን ቤተመንግሥት ሆነው ይመራሉ፤ ስድስት ወር ይዋጋሉ፡፡ የኢፌዲሪ የመከላከያ ሠራዊትም በጦርነት ይማርክ የነበረው ዋናዎቹን ተዋጊዎች አልነበረም፡፡ እነሡ ቀን ተዋግተው ማታ ከከተማው ነዋሪ ጋር ተመሣስለው ይኖሩ ነበር፡፡ ሌላው ለኦብነግ የማታ ማታ መጠናከር አስተዋፅኦ ያበረከተው “ጅሃዲስት” ነኝ የሚለው አስተሣሠቡ ነው፡፡ ለማህበረሠቡ የሃይማኖት አባቶችና ሼካዎች “ከክርስቲያን መንግስት ጋር ነው የምዋጋው” እያለ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ይጠይቃል፡፡

በዚህም ህዝቡ በየአመቱ በዘካ መልክ ገንዘብ እንዲሠጥ ተገደደ፣ የክልሉን በጀት የሚቆጣጠሩት እነሡ በመሆናቸውም የኢኮኖሚ አቅማቸው ፈረጠመ፡፡ ከተለያዩ የአረብ መንግስታት ጋርም ግንኙነት ፈጠረ፡፡ ከምዕራባውያን ጋር ሲገናኝም “ናሽናሊስት” (ብሄርተኛ) ነኝ ብሎ እርዳታ ይቀበላል፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉለት ከነበሩት ውስጥ የቀድሞው የሊቢያው መሪ መሃመድ ጋዳፊ በዋናነት ይጠቅሳሉ፡፡ ጋዳፊ በሡማሌ ክልል ለሚንቀሣቀሡ ታጣቂ ሃይሎች ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ሠጥተዋል፡፡ ኳታርና ግብፅም ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ ነበር፡፡ የውጭ ሃገር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በተረጂዎች ስም እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ያመጡትን እርዳታ ለኦብነግ ያስረክቡ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ሚስጥር የፌደራል መንግስት አመራሮች አብጠርጥረው የተረዱት በ1999 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ በጉዳዩ ላይ ሠፋ ያለ ትንታኔ ያለው ፅሁፍ አዘጋጅተው እንደነበር አቶ አብዲ ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ በተደረገው የተሃድሶ ጉባኤም የማጥራት እርምጃዎች ተወስደው በርካታ በሁለት ቢላዋ የሚበሉ አባላትና አመራሮች እንዲወገዱ ተደረገ፡፡ የፌዴራል መንግስት አስቀድሞ ችግሩን ባለመረዳቱ፣ ይህ ሁሉ የክልሉ የውስጥ ትግል ሲካሄድ ብዙም ድጋፍ አላደረገም ነበር፡፡

በ1999 ዓ.ም ግን አቶ መለስ ራሣቸው ዋነኛ ተሣታፊ በመሆን፣ የክልሉ ቀደምት ችግሮችን በመፍታት ትልቁን ድርሻ መወጣታቸውን አቶ አብዲ ገልፀዋል፡፡ በአሁን ወቅት ክልሉን የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እየመራው ሲሆን ፕሬዚዳንቱም አቶ አብዲ መሃመድ ናቸው፡፡ ከሐምሌ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮም ቀደም ሲል “የሶማሌ ክልላዊ መንግስት” የሚለው ስያሜ በአዲስ መልክ “የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት” ወደሚል ተቀይሮ በዚሁ ስያሜ እየተጠራ ይገኛል፡፡ ሌሎች የክልሉ አስተዳደር ቢሮዎችም “የኢትዮጵያ ሶማሌ” በሚል መነሻ ስያሜ እንዲጠሩ ተደርጓል፡፡ ክልሉ በመጪው ዓመት ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም 8ኛውን የብሄር ብሄረሠቦች በአል ለማዘጋጀት መመረጡ የሚታወስ ነው፡፡ የዚህ በአል አከባበር አካል የሆነው የመጀመሪያው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት “የምስራቅ ኢትዮጵያን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል ባለፈው ሰሞን የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የሚዲያ ሠዎች እንዲሁም ፖለቲከኞች ወደ ክልሉ የተጓዙ ሲሆን አንፃራዊ ሠላም የሠፈነበት ክልሉ በአሉን ለየት ባለ መልኩ ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡

Read 3784 times