Saturday, 15 June 2013 09:55

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ማንኛውም ሠው እንዲጠይቀው ተፈቀደ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ቀርቦበት የ18 ዓመት እስራት የተፈረደበት እና ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ማንኛውም ሠው እንዲጠይቀው መደረጉን ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሠርካለም ፋሲል ለአዲስ አድማስ ገለፀች፡፡ ላለፉት 22 ወራት ከአራት ሰዎች በስተቀር ማንም እንዳይጠይቀው ተከልክሎ እንደነበር የገለፀችው ሰርካለም፤ “አሁን ተመስገን ነው ልዩ ጠባቂም የተከለለ ቦታም ሳይዘጋጅ ረጅም ሠዓት ማዋራትና መጠየቅ ችያለሁ” ስትል ደስታዋን ገልፃለች፡፡

ከ10 ቀናት በፊት ሀሙስ ማለዳ ልትጠይቀው ስትሄድ በግምት 40 ሠዎች ብቻ በሚኖሩበት ዞን ሶስት እንደተለመደው ለ10 ደቂቃ አይታው መመለሷን የገለፀችው ሰርካለም፣ ቅዳሜ ዕለት ለ30 ደቂቃ የተፈቀደውን የመጠየቂያ ሰዓት ጠብቃ 4፡30 ስትደርስ “እስክንድር እዚህ የለም” ሲሏንመባሏንና ድንጋጤ ላይ መውደቋን ፣ በኋላ ከ170 በላይ የተለያዩ እስረኞች ወዳሉበት ዞን ሁለት መዛወሩን ሠምታ በመሄድ ያለ ልዩ ጠባቂ በነፃነት ለረጅም ሠዓት አዋርታው መመለሷንና፣ ይህን የሠሙ አንዳንድ ወዳጅ ዘመዶች መጠየቅ መጀመራቸውን በደስታ ገልፃለች፡፡

“ከዚህ በፊት እኔ፣ እናቴ፣ አክስቱና የአክስቱ ባል ነበርን የምንጠይቀው፣ ልንጠይቀው ስንሄድም አምስተኛው ሰው ፖሊስ ነው፤ አብሮን ተቀምጦ የምናወራውን ይሠማል፣ለብቻው የተከለለ ቦታም ነበር ስናስጠራው የሚመጣው” ያለችው የእስክንድር ባለቤት፣ “እንዴት እንደሆነ ባላወቅነው ሁኔታ አሁን እንደማንኛውም እስረኛ በነፃነት እየጠየቅነው ነው፡፡ በዚህም ደስተኛ ሆኛለሁ” ስትል ተናግራለች፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ሠዓት በነፃነት መጠየቅ ብንጀምርም ጉዳዩ ወደፊት ቀጣይነት ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ጋዜጠኛ ሠርካለም ለአዲስ አድማስ ጨምራ ገልፃለች፡

Read 10387 times