Saturday, 15 June 2013 09:52

ነባር የቤት ተመዝጋቢዎች “በምዝገባ ቁጥራችን ሌሎች ቤት ወስደዋል” አሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(5 votes)

አዲሱን የቤቶች ምዝገባን ተከትሎ የነባር ቤቶች ተመዝጋቢዎች ስማችን ኮምፒተር ውስጥ እንደሌለና፣ በእኛ ቁጥር የሌሎች ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ ተነግሮናል በማለት ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ወ/ሮ መሠረት ጐሌ በ1997 ዓ.ም በቤት ፈላጊነት ሲመዘገቡ በተሰጣቸው ቢጫ ካርድ ላይ ስማቸውና የምዝገባ ቁጥራቸው በትክክል መስፈሩን ይናገራሉ፡፡ እስካሁን ግን ቤት ስላልደረሳቸው አዲሱን የቤቶች ምዝገባ እድል ለመጠቀም በነባር ተመዝጋቢዎች ዘርፍ ለመመዝገብ ሲጠይቁ፣ ስማቸው ኮምፒውተር ውስጥ አለመኖሩ እንደተነገራቸው ይገልፃሉ፡፡ በተሰጣቸው ቁጥርም የእሳቸው ስም ሳይሆን የሌላ ግለሰብ ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝና ግለሰቡም ቤቱን መረከባቸውን ወ/ሮ መሠረት ይናገራሉ፡፡

ምናልባት ቁጥሩ ተሳስቶ ይሆናል በሚል በስማቸው ቢፈለግም የእሳቸውን ምዝገባ የሚጠቁም መረጃ አለመገኘቱን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ “ይሄ በጣም ተንኮል ያለበት አሠራር ነው፤ ያልተመዘገበ ሰው ቤት ወሰደ ሲባል አላምንም ነበር” በማለት አቤቱታቸውን ለበላይ ሃላፊ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ታምራት ከበደ እንዲሁ በራሳቸውና በመጀመሪያ ልጃቸው ስም በቤት ፈላጊነት ተመዝግበው እንደነበርና በእነሱ የምዝገባ ቁጥር ሌሎች ሰዎች ቤት መውሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡ “በወቅቱ መዝጋቢዎቹ ካርዱን ከጣላችሁ ቤቱን አታገኙም፤ ቁጥራችሁን ያዙ እያሉ ስለነገሩን ቁጥሩን በማስታወሻ ደብተር በመፃፍ ይዤው ነበር” የሚሉት አቶ ታምራት፤ አሁን ግን ከእነአካቴው ስማችን እንደሌለ ተነግሮናል ብለዋል፡፡

በእሳቸው እና በልጃቸው ስም ምትክም የሁለት ሌሎች ግለሰቦች ስም መገኘቱንና ሁለቱም ቤቱን መረከባቸውን ተናግረዋል፡፡ “እንዴት በእኛ ምዝገባ ቁጥር የሌሎች ግለሰቦች ስም ተመዘገበ?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ታምራት፤ ነገሩ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ገልፀዋል፡፡ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የሄዱ ነባር ተመዝጋቢዎች፣ ቅሬታቸውን በየወረዳና ክ/ከተማ ጽ/ቤት እንዲያቀርቡ ተነግሮናል ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግስቱ፤ በ1997 ዓ.ም በተደረገው የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ የቁጥሮች መተራመስ መፈጠሩንና ቁጥሮቹ እንደ አዲስ (ከ01-453ሺ ድረስ) መስተካከላቸውን ጠቁመው፤ በዚህም ምክንያት የተመዝጋቢዎቹ የምዝገባ ቁጥርና ስማቸው ተለያይቷል ብለዋል፡፡ ዋጋ ያለው የያዙት ካርድ ሳይሆን ስማቸው በኮምፒውተር ላይ መኖሩ ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ ከተመዘገቡ ስማቸው የማይኖርበት ምክንያት የለም ይላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ቅሬታዎች በተደጋጋሚ እንደቀረበላቸው በመግለጽም ትክክለኛ ማስረጃ ያላቸውን አጣርተን በነባር ምዝገባ እንዲካተቱ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ማስረጃ ሳይኖራቸው ቅሬታ የሚያቀርቡ ግለሰቦች ግን ጊዜው ሳያልፍባቸው እንደ አዲስ እንዲመዘገቡ አሳስበዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የ10/90 እና የ20/80 ተመዝጋቢዎች ቁጥር 200ሺህ እንደደረሰ ለማወቅ ችለናል፡፡

Read 9317 times