Wednesday, 12 June 2013 15:37

የአዲስ አበባ የመንገድ ጉድጓዶች የሞትና የአካል ጉዳት እያደረሱ ነው በዘጠኝ ወር ብቻ 22 ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ሞተዋል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(6 votes)

በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች በግለሰቦችና በመንግስት ተቋማት ለተለያዩ ስራዎች የሚቆጠፈሩና ያለ አግባብ ተከፍተው የሚተዉ ጉድጓዶች፣ በነዋሪዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ እያደረሱ ሲሆን ዘንድሮ ብቻ ከ22 ሰዎች በላይ ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ፣ አስር ሰዎችም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በጉድጓዶች ውስጥ ገብቶ ህይወቱ ለሚያልፍና የአካል ጉዳት ለሚደርስበት ኃላፊነት የሚወስድና ካሣ የሚከፈልበት አሰራር አለመኖሩም ተገልጿል፡፡ በከተማዋ ለመንገድ ግንባታ፣ ለኮንስትራክሽን ስራና ለመሳሰሉት ስራዎች ተብለው በሚቆፈሩ ጉድጓዶች በአንድ ሳምንት ብቻ በሁለት ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ እንደሚያጋጥም የጠቆሙት የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ፤ የድረሱልን ጥሪ ጥቆማውን ተከትሎ ሰራተኞች በቦታው ሲደርሱ ተከፍቶ በሚተወው ጉድጓድ ውሃ ስለሚሞላ ተጎጂውን ከእነህይወቱ ማግኘት እንደማይቻል ነው የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ የጠቀሱት፡፡

የመንግስት ተቋማቱ፤ ቴሌ፣ መብራት ሃይል፣ ውሃ ልማት፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የአካባቢ ጥበቃ መ/ቤት እና ግለሰቦች ለሚደርሰው አደጋ ተጠያቂዎች ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች፤ ቦሌ ቡልቡላ፣ ሃና ማሪያም፣ ቀራኒዮ፣ ሚኪሌላንድ አካባቢዎች ከፍተኛው የሞትና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች በከተማዋ በየአምስት ሜትሩ ርቀት ጉድጓድ እንዳለና ጥልቀቱም ከሰው ቁመት በላይ በመሆኑ እንዳባባሰውም ተነግሯል፡፡ ለተለያዩ ስራዎች የሚቆፈሩ ጉድጓዶች ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ መልሰው የማይደፈኑ፣ የማይታጠሩ፣ ውሃ የሚሞላባቸው፣ ከፊት ለፊት ጉድጓድ መኖሩን የሚያመላክት ነገር ባለመኖሩ፣ ሰዎች መንገድ እየመሰላቸው ገብተው እንደሚሞቱና ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ተገልጿል፡፡በአለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ሰላሳ አራት ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡

Read 10519 times