Print this page
Wednesday, 12 June 2013 14:53

ዋልያዎቹ በ2 የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ከሜዳ ውጭ እና በሜዳቸው ይፈተናሉ

                   በ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ አንድን በሰባት ነጥብ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ ከቦትስዋና ጋር ከሜዳው ውጭ በሚያደርገው የ4ኛ ዙር ጨዋታ ውጤታማ ሆኖ መሪነቱን ለማጠናከር እንደሚችል ግምት አገኘ፡፡ በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ብሄራዊ ቡድኑን ለመሸኘት በተካሄደ ስነስርዓት ዋልያዎቹ ኢትዮጵያን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ካበቁ ለእያንዳንዱ የቡድኑ አባላት የመኪና ሽልማት እንደሚሰጥ ፌደሬሽኑ ቃል ገብቷል፡፡ ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው የምድብ ማጣርያ በ4ኛ እና 5ኛ ዙር ሲቀጥል ዋልያዎቹ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ዛሬ ከሜዳ ውጭ እና ከሳምንት በኋላ ደግሞ በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ወሳኝ ግጥሚያዎች ይፈተናሉ፡፡

በምድብ 1 ኢትዮጵያ በ3 ዙር ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ እና 3 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ እየመራች ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ በ4ኛ ዙር ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ሎባታሴ በተባለች ከተማ ከቦትስዋና ጋር ሲገናኝ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ማቀዱ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሳምንት በኋላ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በ5ኛ ዙር ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን የሚያስተናግድ ሲሆን ይህን ጨዋታ ድል ማድረግ ከቻለ መሪነቱን ሳይነጠቅ የምድብ ማጣርያውን ሊጨርስ ይችላል፡፡ ዋልያዎቹ ከሜዳ ውጭ እና በሜዳቸው ለሚያደርጓቸው ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች ዝግጅታቸውን የጀመሩት ከ2 ሳምንት በፊት ሲሆን በዚሁ ጊዜ እንደ አቋም መፈተሻ በሚታይ ግጥሚያ ሱዳንን 2ለ0 በማሸነፍ ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል መታሰቢያ ዋንጫን በመውሰድ ተነቃቅተዋል፡፡

የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት የሚያደርገውን ዝግጅት በካምፕ በመሰባሰብ ለ2 ሳምንት የሰራ ሲሆን ሰሞኑን ከግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ አንድ እኩል አቻ ተለያይቷል፡፡ ሌሎቹ የምድብ 1 ተፋላሚዎች መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ እና ደቡብ አፍሪካ በገለልተኛ ሜዳ በ4ኛ ዙር ጨዋታ በካሜሮኗ ያውንዴ ከተማ ይጫወታሉ፡፡ የሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ባለው አለመረጋጋት በተያያዘ በካሜሮኗ ከተማ እንዲደረግ ካፍ እና ፊፋ የጋራ ውሳኔ እንዳሳለፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሳምንት በኋላ በ5ኛው ዙር የምድብ 1 ፉክክር ሲቀጥል ቦትስዋና እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ይገናኛሉ፡፡ በዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያዎች በምድብ 1 ከተደለደሉት ቡድኖች ምንም ተስፋ የሌላት በዋና ከተማዋ ባንጉዊ በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች ያለችው መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ስትሆን በአገሪቱ አለመረጋጋት ሳቢያ ብሄራዊ ቡድኑ በመካከለኛው ምስራቅ ሊያደርግ የነበረውን ዝግጅት እንደሰረዘ ታውቋል፡፡

በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ እንደቅደምተከተላቸው የሚገኙት 5 ነጥብ እና 2 የግብ እዳ ያላት ደቡብ አፍሪካ እና 3 ነጥብ እና 2 የግብ እዳ ያስመዘገበችው ቦትስዋና በፉክክሩ ለመቆየት በቀሪዎቹ የ3 ዙር ግጥሚያች ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካው አሰልጣኝ ጎርደን ሌጀሰንድ ቡድናቸው በሚያደርጋቸው ሁለት ወሳኝ የምድብ ማጣርያ ፍልሚያዎች ከፍተኛውን የነጥብ ውጤት በመሰብሰብ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ተስፋን ለማለምለም እንዳቀዱ ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ በገለልተኛ ሜዳ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ከሚያደርጉት ጨዋታ ይልቅ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሚኖራቸው ጨዋታ ከፍተኛውን ትኩረት ሲሰጡ፤ ይህን ግጥሚያ የሚያሸንፉበትን ስትራቴጂ ዋልያዎቹ በቦትስዋና የሚያሳያቱን አቋም በመገምገም ለመንደፍ አስበዋል፡፡ ዜብራዎቹ የሚባለው የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስታንሊ ትሶሆኔ በሳምንት ልዩነት የሚያደርጉት ጨዋታ ለተጨዋቾቻቸው የስነልቦና ጥንካሬ እና የአካል ብቃት ወሳኝ ልምድ የሚገኝበት መሆኑን ትኩረት ሰጥተንበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቡድናቸው የአራተኛ እና የአምስተኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎችን ካሸነፈ ደግሞ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣርያ ምእራፍ ለመብቃት እድል የሚፈጥርልን ይሆናልም ብለዋል፡፡ ከ3 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ በነበረው 19ኛው ዓለም ዋንጫ ስሎቫኪያ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ በቅታ ነበር፡፡ በ2006 እኤአ ጀርመን አስተናግዳ በነበረው 18ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ደግሞ 6 አገራት ትሪንዳድ ኤንድ ቶቤጎ፤ አይቬሪኮስት፤ አንጎላ፤ ጋና፤ ቶጎ እና ዩክሬን ለመጀመርያ ጊዜ ሊሳተፉ ችለዋል፡፡ በ2002 እኤአ ላይ ደቡብ ኮርያና ጃፓን በጣምራ ባዘጋጁት 17ኛው ዓለም ዋንጫም አራት አገራት ቻይና፤ ኤኳዶር፤ ሴኔጋልና ስሎቪንያ በታሪክ የመጀመርያ ተሳትፏቸውን አግኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ዓለም ዋንጫ በታሪኩ በየአራት አመቱ አንድ አዲስ ብሄራዊ ቡድን በማሳተፍ የሚታወቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡በመላው ዓለም በ5 አህጉራዊ ዞኖች ተከፋፍሎ ሲካሄድ በቆየው የዓለም ዋንጫው ማጣርያ አዘጋጇ ብራዚል እና ከኤስያ ዞን ጃፓን ብቻ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ለቀሪዎቹ የ30 ብሄራዊ ቡድኖች ኮታ በመላው ዓለም የሚደረገው ትንቅንቅ ይቀጥላል፡፡ ከዓመት በኋላ በዚሁ የዓለም ዋንጫ ላይ እንደተለመደው በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳትፏቸውን የሚያደርጉ 7 ብሄራዊ ቡድኖች ይኖራሉ በሚል ግምቱን የሰነዘረው ቢልቸርስፖርት የተባለ ድረገፅ ነው፡፡

ቢልቸር ስፖርት በማጣርያው ያላቸውን አያያዝ በማገናዘብ በዓለም ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ የመሳተፍ እድል ይዘዋል ያላቸው 7 አገራት የኢትዮጵያ፤ የኮንጎ፤ የሞንቴኔግሮ፤ቦስኒያ ሄርዞጎቪኒያ፤ የፓናማ፤ የኡዝቢኬስታንና የቬንዝዋላ ብሄራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ ለ2014 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከቅድመ ማጣርያው ጀምሮ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን አባል ከሆኑ 53 አገራት 52 ያህሉ ተሳትፈዋል፡፡ እስከ 3ኛው ዙር የምድብ ማጣርያ በነበረው ጉዞ 13 አገራት ከውድድሩ ውጭ ሲሆኑ 39 አገራት በየምድቦቻቸው የማለፍ ተስፋ እንደያዙ ናቸው፡፡ እስከ ሶስተኛ ዙር በተደረጉ ጨዋታዎች በምድብ 1 ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ፤ በምድብ 2 ቱኒዚያ በ9 ነጥብ፤ በምድብ 3 አይቬሪኮስት በ7 ነጥብ፤ በምድብ 4 ዛምቢያ በ7 ነጥብ፤ በምድብ 5 ኮንጎ በ9 ነጥብ፤ በምድብ 6 ናይጄርያ በ8 ነጥብ፤ በምድብ 7 ግብፅ በ9 ነጥብ፤ በምድብ 8 አልጄርያ በ6 ነጥብ፤ በምድብ 9 ካሜሮን በ6 ነጥብ እንዲሁም በምድብ 10 ሴኔጋል በ4 ነጥብ መሪነታቸውን ይዘዋል፡፡ ከአስሩ ምድቦች መሪ በመሆን የሚጨርሱት 10 ብሄራዊ ቡድኖች ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ 5 አገራት ለመለየት በሚደረገው የመጨረሻ ዙር የደርሶ መልስ የማጣርያ ጨዋታ ለመሳተፍ ይበቃሉ፡፡

Read 3880 times