Wednesday, 12 June 2013 14:49

ሞስኮ ለ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተዘጋጅታለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

14ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሁለት ወራት በኋላ የምታስተናግደው የራሽያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች ታወቀ፡፡ በዚሁ የዓለም ሻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ምርጫ ከወር በኋላ ሊታወቅ ይችላል፡፡ በሻምፒዮናው የኢትዮጵያ ቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች የተሰባሰቡበትና 69 አባላት ያሉትን ጊዜያው የልዑካን ቡድን ዝርዝር ሰሞኑን ይፋ አድርጋለች፡፡ 14ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ ከ7 ዓመታት በፊት ከራሽያዋ ሞስኮ ጋር የስፔኗ ባርሴሎና፤ የአውስትራሊያዋ ብሪስባኔና የስዊድኗ ጉተንበርግ ማመልከቻ በማስገባት ተፎካክረው ነበር፡፡

ለዓለም ሻምፒዮናው አጠቃላይ መሰናዶ 5.1 ሚሊዮን ዶላር በጀት ያንቀሳቀሰችው ሞስኮ በውድድሩ ወቅት ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ እንደሚኖራት ስታሳውቅ ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ከ25 ሺ በላይ ስፖርተኞች፤ የአይኤኤኤፍ አባል አገራት የሆኑ የ207 ፌደሬሽን ልዑካኖች እንደምታስተናግድ ተጠብቋል፡፡ በ1980 አኤአ ላይ ምሩፅ ይፍጠር በ10ሺ እና በ5ሺ ድርብ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደበትን ኦሎምፒክን ለማስተናገድ የቻለችው ሞስኮ፤ በ2006 እኤአ ላይ የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮናን በተሳካ መንገድ ለማዘጋጀት ከመቻሏም በላይ በ2018 እኤአ ላይ ደግሞ የ21ኛው ዓለም ዋንጫ መክፈቻ እና መዝጊያ የምታስተናግድ ከተማ ናት፡፡ 14ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሞስኮ የሚገኘውና የኦሎምፒክ ደረጃ ያለው ሉዝኒስኪ ስታድዬም ያስተናግዳል፡፡

78ሺ ስፖርት አፍቃሪ የሚይዘው ስታድዬሙ ለዓለም ሻምፒዮናው በሚመች ሁኔታ ለማሰናዳት፤ አዲስ ትራክ ለማንጠፍ እና ለሜዳ ላይ ስፖርቶች ምቹ መወዳደርያ በማዘጋጀት እድሳት ሲደረግለት ቆይቷል፡፡ ሉዝኒስኪ ስታድዬም በ2008 እኤአ ላይ በማንችስተር ዩናይትድ እና በቼልሲ መካከል የተደረገውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ፍልሚያ እንዳስተናገደ ሲታወስ ቶርፒዶ እና ስፓርታክ ሞስኮ የተባሉ ሁለት የራሽያ ክለቦች ሜዳ በመሆንም ያገለግላል፡፡ ስታድዬሙ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 67 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚካፈለው የኢትዮጵያ ቡድን ከወዲሁ የመመረጥ እድል ያላቸው በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ጥሩ ሰዓት እና ብቃት ያሳዩ አትሌቶች ናቸው፡፡ ከእነሱም መካከል በ5ሺ ሜትር ወንዶች ሃጎስ ገብረህይወትና ደጀን ገብረመስቀል፤ በ5ሺ ሜትር ሴቶች ገንዘቤ ዲባባ እና የርቀቱ ኦሎምፒክ ሻምፒዮን መሰረት ደፋር እንዲሁም በ800 ሜትር ወንዶች መሃመድ አማን ይጠቀሳሉ። በዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ በ1500 ሜትር ወንዶች እና በ3ሺ ሜትር መሰናክል እየተሳተፉ ያሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ለዓለም ሻምፒዮናው ቡድን የመመረጥ እድል ይኖራቸዋል፡፡

በውድድር ዘመኑ በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች በማሸነፍ በሁለቱም ፆታዎች የተሳካላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊ ማራቶኒስቶች መኖራቸውም በውድድር አይነቱ ምርጥ አትሌቶችን ለመምረጥ ከባድ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚያሳትፈውን ሚኒማ ለማምጣት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውስን በሆኑ ውድድሮች መፎካከር ግድ ይሆንባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውድድሮች መካከል የመጀመርያው ከሳምንት በፊት የተካሄደው የዩጂን ፐሮፎንታይኔ ክላሲክስ ውድድር ነበር፡፡ ባለፉት ሶስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የኢትዮጵያን የበላይነት በከፍተኛ ደረጃ መቀናቀን የጀመረችው ኬንያ ለሞስኮው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የምትልከው ልዑካኗን ሙሉ ዝርዝር በሚቀጥለው ወር እንደምታሳውቅ ተጠብቋል፡፡ በጊዜያዊነት ይፋ የሆነው የኬንያ አትሌቶች ዝርዝር 3 የዓለም ሻምፒዮን አትሌቶች የሚጠቀሱ ሲሆን በ800 ሜትር ዴቪድ ሩዲሻ ፤ አዝቤል ኪፕሮፕ በ1500 ሜትር እንዲሁም በ3ሺ መሰናክል እዝቄል ኬምቦሚ ናቸው፡፡

በተያያዘ ግን ሁለት የኬንያ ምርጥ ሴት አትሌቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ለዓለም ሻምፒዮናው እንደማይደርሱ ታውቋል፡፡ ሁለቱ አትሌቶች ከ2 ዓመት በፊት በኮርያ ዳጉ በተደረገው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ እና 10ሺ ሴቶች ድርብ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ቪቪያን ቼሮይት እና የዘንድሮውን የዓለም 5 ትልልቅ ማራቶኖች ሊግ ያሸነፈችው ማሪ ኪታኒ ናቸው፡፡ ቪቪያን ቼሮይት በ29 ዓመቷ የመጀመርያ ልጇን ለመውለድ መድረሷ በጣም እንዳጓጓት ከሰሞኑ ስትናገር በዘንድሮ የውድድር ዘመን ጥሩ እረፍት አድርጋ በ2015 በሙሉ ብቃት ወደ ውድድር እንደምትመለስ አስታውቃለች፡፡ በጊዜያዊነት በተመለመለው የኬንያ ቡድን ከ2 ዓመት በዳጉ በተደረገው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ የወሰዱ ምርጥ አትሌቶች ይገኛሉ፡፡

ጊዜያዊ ቡድኑ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ከናይሮቢ ከተማ 25.3 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው ፕሪዘን ስታፍ ትሬኒንግ ኮሌጅ በመግባት መለስተኛ ልምምድ የጀመሩ ሲሆን በአጠቃላይ ለ2 ሳምንት ሲዘጋጁ ከቆዩ በኋላ እረፍት አድርገው በሁለተኛ ጥሪ ወደ ካምፑ ተመልሶ በመግባት የመጨረሻውን ቡድን ለመምረጥ ከወር በኋላ ለሚደረገው ብሄራዊ ሻምፒዮና በሚደረግ ዝግጅት መስራት እንደሚቀጥሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከትራክ አትሌቶች በተጨማሪ ከሁለቱም ፆታዎች ከ20 በላይ ምርጥ የማራቶን አትሌቶች ተቀማጭነታቸውን በኤልዶሬት በማድረግ በዓለም ሻምፒዮናው የሚሳተፉ 3 ወንድ እና ሶስት ሴት ማራቶኒስቶች ከመካከላቸው ለመምረጥ መታሰቡንም የኬንያ አትሌቲክስ መግለጫ አመልክቷል፡፡

Read 3376 times