Saturday, 08 June 2013 08:48

ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እስከ ፊንፊኔ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(4 votes)

ረቡዕ ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ነው፡፡ በሒልተን ሆቴል በኩል ወደ መስቀል አደባባይ በእግር በመጓዝ ላይ ሳለሁ፤ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መግቢያ በር ላይ ትኩረቴን የሚስብ ክስተት አስተዋልኩ፡፡ ወደ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግቢ የሚገቡ መኪኖች ጥብቅ ቁጥጥር አልፈው ነው ወደ ውስጥ የሚዘልቁት። ሁሉም ባለ መኪና የመግቢያ መታወቂያውን በር ላይ ለሚቆጣጠሩት የጥበቃ ሠራተኞች የማሳየት ግዴታ አለባቸው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ መኪኖቹ በልዩ የመፈተሻ መሣሪያ ዙሪያቸው ሊመረመርም ይችላል፡፡ እንደ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ልዩ ሞገስ ካላቸው የጥበቃ ሠራተኞች አንዷ፤ 10 ዓመት ከሚሆናት አንዲት ሕፃን ልጅ ጋር ቆመው ያወራሉ፡፡ የደንብ ልብሷን ቀድጄ ካልወጣሁ የሚል ወፍራም ሰውነት ያላት የጥበቃ ሠራተኛዋ ከሕፃኗ ጋር ሲታዩ ግንኙነታቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ ጉጉት ይፈጥራል፡፡

ወላጇ ልትሆን እንደማትችል ግን ገምቻለሁ፡፡ ልዩነታቸው የጐላ ነውና፡፡ ልጅቱ ያደፈ ጉርድ ቀሚስ ለብሳለች፡፡ ወገቡ ሰፍቶባት በመርፌ ቁልፍ ሸብ የተደረገው ቀሚሷ፤ ከታሰረበት ጫፍ የተረፈው በስተቀኝ በኩል ተንጠልጥሏል፡፡ ከላይ የነተበ ካኒቴሪና ሹራብ ለብሳለች፡፡ ጫማን የማያውቁ የሚመስሉት እግሮቿ ውሃ ካዩ የሰነበቱ ይመስላል፡፡ የትከሻ ማንገቻ ያለውና በአሮጌ ጨርቅ የተሰራ ከረጢት በግራ ትከሻዋ አንጠልጥላለች፡፡ በእግሯ ላይ በቅርቡ የደረሰባት ጉዳት ሳይኖር አይቀርም፤ ስትራመድ ትንሽ እንደማነከስ ያደርጋታል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የጥበቃ ሠራተኛና ትንሿ ልጅ ምን እንዳወሩ አላውቅም፡፡

ልጅቱ ጥበቃዋን ተሰናብታ ወደ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን አቅጣጫ ስታመራ ከኋላ ደርሼባት ላናግራት ሞከርኩ፡፡ ሥሟ ሀና መሆኑን፤ አባቷ ቤት ተከራይቶ በግሉ እንደሚኖር፤ እናቷ በአሮጌ ቄራ (ሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት) የላስቲክ ቤት ሠርታ እንደምትኖር፤ እሷም ከእናቷ ጋር እንደሆነች፤ በፊንፊኔ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዜሮ ክፍል ተማሪ መሆኗን ነገረችኝ፡፡ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን በስተጀርባ የሚገኘው ፊንፊኔ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1954 ዓ.ም ነው የተቋቋመው፡፡ በአካባቢው የነበሩ መኖሪያ ቤቶች ለዳግም ልማት በመፍረሳቸው ምክንያት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ቁጥር በግማሽ ቀንሶ፣ አሁን 300 ያህል ተማሪዎች እያስተማረ ሲሆን ሀና ከእነዚህ ተማሪዎች አንዷ ናት፡፡ ቀልቤን ከሳበችው ሀና ጋር እያወራሁ እራሴን በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ አገኘሁት፡፡ የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር ወ/ሮ ዘውዴ መኮንን አፈላልጌ በሀና ዙሪያ አንድ ዘገባ ለመሥራት ማቀዴን ስነግራቸው፣ ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ብዙ ልጆች በትምህርት ቤቱ እንዳሉ ገልፀው፤ ዝርዝር መረጃ የሚሰጡኝን ሰዎች አገናኙኝ፡፡

23 መምህራን ያሉት የፊኒፊኒ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ በ1999 ዓ.ም በመማር ማስተማሩ ሂደት የገጠመውን ችግር ለመቅረፍ የቀየሰው ዘዴ፤ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በከፊል ለመፍታት አስችሎታል፡፡ በወቅቱ መምህራኑ በተማሪዎቻቸው ዙሪያ ካዩት ችግሮች መሐል ትምህርታቸውን በአትኩሮት የመከታተል ፍላጎት ማጣት፣ በክፍል ውስጥ ማዛጋትና መንጠራራት፣ ዴስክ ተደግፎ መተኛት፣ በድንገት በክፍል ውስጥ ማስመለስ … የመሳሰሉት ነበሩ፡፡ ከመምህራኑ ስምንቱ የችግሩን ምክንያት ሊያጠኑና ከቻሉም መፍትሔ ሊዘይዱ ተስማምተው ኮሚቴ አዋቀሩ፡፡ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን በትኩረት እንዳይከታተሉ ያደረጋቸውን ምክንያት ሲመረምሩ የችግሩ ተጠቂዎች፤ ወላጆቻቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ አካል ጉዳተኞችና፣ መኖሪያ ቤት አልባ ድሆች … መሆናቸውን ይረዳሉ፡፡ ልጆቹ በቂ ምግብና እንክብካቤ አለማግኘታቸው፣ በክፍል ውስጥ ለሚታይባቸው ችግር መከሰት መነሻ መሆኑንም ደረሱበት፡፡ ኮሚቴው ለችግሩ መፍትሔ ሲያፈላልግ በመጀመሪያ የራሱን አቅም መጠቀም እንዳለበት ተገነዘበ፡፡

ስምንቱ የኮሚቴ አባላት አንዳቸው በርበሬ፣ ሌላኛቸው ሽሮ … እያሉ ያላቸውን ከየቤታቸው በማምጣት፣ በትምህርት ቤቱ ማዕድ ቤት አብስለው ለችግረኛ ልጆች ምግብ ማቅረብ ቻሉ፡፡ 20 ችግረኛ ልጆችን በመርዳት ነበር ሥራውን የጀመሩት፡፡ ከመማር ማስተማር ኃላፊነታቸው ወጣ በማለት፣ የአገርና የሕብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ በጋራ መንቀሳቀስ የጀመሩት የኮሚቴ አባላትና የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች፤ የተጀመረው መልካም ተግባር እንዳይቋረጥና ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከማሰብ አልቦዘኑም፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተጀመረው መልካም ተግባር እንዲቀጥል ያቅማቸውን ያህል ዕርዳታ የሚሰጡ ሰዎች አፈላልገው አገኙ፡፡ ነዋሪነታቸውን በውጭ አገር ያደረጉት አቶ አሊፍ ድጋፍ በማድረግ ቀዳሚው ናቸው፡፡ የትምህርት ቤቱ ኮሚቴ፤ በአለፍ አገደም ዕርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ትብብር ብቻውን የበጎ አድራጎት ሥራውን ለማስቀጠል እንደማይችል ተረድቷል፡፡ እናም በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ሻይ ቤት አቋቋመ፡፡ ሠራተኞችም ተቀጠሩ፡፡ መምህራኑ ለተረጂ ልጆች በየዕለቱ ምግብ ለማዘጋጀት ወደ ማዕድ ቤት መመላለሳቸው ቀረ፡፡ ተረጂ ተማሪዎች ምግባቸውን ከሻይ ቤቱ ማግኘት ቻሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ከሻይ ቤቱ የሚገኘው ትርፍ ልጆቹን በዘላቂነት ለመርዳት የሚያስችል ተስፋን ፈነጠቀ። ይሄኔ ነው በፊኒፊኔ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጀመረው መልካም ተግባር ያስደሰተው “USAID” የተባለ የአሜሪካ በጐ አድራጐት ድርጅት የሻይ ማፍያ ማሽንና ጠረጴዛዎችን የለገሰው፡፡

በ1999 ዓ.ም በስምንት መምህራን የተጀመረው የበጎ አድራጎት ሥራ በአንድ በኩል ፈተና በሌላ በኩል ተስፋ እያስተናገደ ለዛሬ ደርሷል፡፡ በቅርቡ ወ/ሮ ሠናይትና ወ/ሮ መዓዛ የሚባሉ በጎ አድራጊዎች በየቀኑ ለ27 ተማሪዎች ቁርስና ምሳ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በዓመት ሁለት ጊዜ ደብተርና በዓመት አንድ ጊዜ ልብስ የሚሰጡ በጎ አድራጊዎችም አሉ፡፡ በት/ቤቱ የተማሪዎችን ችግሮች ለማቃለል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም ሌሎች ትኩረት የሚሹ ፈተናዎች አልጠፉም፡፡ ማየት የተሳናቸው ወላጆች ያሏቸው ተማሪዎች፤ እነሱን ወደ ሚለምኑበት ቦታ ስለሚያመላልሱ ብዙ ጊዜ በትምህርት ገበታ ላይ አይገኙም፡፡ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ በቅርቡ በእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ደጅ ከወላጁ ጋር በተኛበት በጅብ ተወስዶ የተበላው ልጅ የፊኒፊኔ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር፡፡ ለችግረኛ ልጆቹ ምግብ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ውጤታቸውን እንዲያሻሽሉ በትምህርት ቤቱ ኮሚቴ ልዩ ክትትል ቢደረግላቸውም ተመልሰው የሚሄዱበት የመኖሪያ አካባቢያቸው የሚያሳድርባቸዉ ተጽዕኖ እንደሚያሸነፋቸው መምህራን ይናገራሉ፡፡ ወላጆች በልጆቻቸው ጉዳይ ወደ ትምህርት ቤት ሲጠሩ በአብዛኛው ለመምጣት ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ከሚውሉ ከእነሱ ጋር የአካባቢው ችግር ተካፋይ ቢሆኑ ይመርጣሉ፡፡

“መንግሥት ትምህርት ቤቶችን ሠርቷል፤ አስተማሪዎችን ቀጥሯል፤ ለመማር ማስተማሩ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሊያሟላ እየሞከረ ነው” የሚሉት የትምህርት ቤቱ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ አባላት፤ ሕብረተሰቡ አላየም ወይም አልሰማም እንጂ ወገኑን ለመርዳት ፍላጎት እንዳለው እኛን ሊረዱ የመጡ አካላት ማሳያ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የዓለም አቀፍ ድርጅት ቢሮዎችን የሚጎራበቱ ጎስቋላ የአገር ተቋማት፤ በትላልቅ ኢንዱስትሪና የቢዝነስ ማዕከላት አጠገብ የሚገኙ የደከሙ የመኖሪያ መንደሮች፤ በትላልቅ የመኖሪያ ቪላዎች ዙሪያ በየጥጋጥጉ የሚኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች … በብዛት ይገኛሉ፡፡ “ይህንን ልዩነት ማጥበብ የሚቻልበት ዕድልና ዘመን ይመጣ ይሆን?” ብለው የሚጠይቁ ወገኖች ጥቂት አይደሉም። የአገርና የሕብረተሰቡን ችግር አይተው በጋራ በመንቀሳቀስ ለውጥ ለማምጣት እየጣሩ ያሉት የፊኒፊኒ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ተግባር ግን ምስጋና ሊቸረው ይገባል፡፡

Read 2037 times