Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Saturday, 08 June 2013 08:37

እንጀራ ፈላጊ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(5 votes)

ጋዜጣ አዟሪ ነኝ፡፡ ካዛንቺስ፣ ሃናን ዳቦ ቤት አካባቢ ጋዜጦችን ታቅፌ ስዞር የምውል ጋዜጣ አዟሪ፡፡ ጋዜጦችን እሸጣለሁ፡፡ ጋዜጦችን አከራያለሁ፡፡ በመደዳ ከተሰደሩት ካፌዎች በረንዳ ላይ ቁጭ ብለው ሻይ ቡና ለሚሉ ተስተናጋጆች ጋዜጦችን አቀርባለሁ፡፡ አንዳንዶች ይገዙኛል። አንዳንዶች ገለጥ ገለጥ አድርገው አንብበው ሽልንግም፣ አንድ ብርም ይሰጡኛል፡፡ እርግጥ ጋዜጣ ማዞር ብቻ አይደለም ስራዬ፡፡ እግረ መንገዴንም ተስተናጋጆችን የሚነዘንዙ ለማኞች ወደ ካፌዎቹ ድርሽ እንዳይሉ እጠብቃለሁ፡፡ ትናንት ማለዳ አንድ ገገማ ለማኝ አጋጠመኝ፡፡ ዴንቨር ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለው ጋዜጣ ከሚያነቡ ሽማግሌ ደንበኛዬ ፊት ቆሞ ሲለምን አገኘሁት፡፡ “ስማ ወንድሜ… ይሄ የስራ ቦታ ነው” አልኩት ጠጋ ብዬ፡፡ ለማኙ መልስ አልሰጠኝም፡፡

ጋዜጣ ወደሚያነቡት ሽማግሌ ጠጋ ብሎ መለመኑን ቀጠለ፡፡ ሽማግሌው ቀና ብለው አዩት፡፡ ለማኙ ሳያሳዝናቸው አልቀረም፡፡ እኔን ግን አናዶኛል፡፡ ምክንያቱም ስራዬን እያበላሸ ነው፡፡ ሽማግሌው እንኳን እንዲህ ጣልቃ እየገባ ንባባቸውን የሚያቋርጣቸው ሰው ኖሮ፣ ድሮም ጋዜጣ ቶሎ አንብበው መመለስ አይወዱም፡፡ ወደ ለማኙ ተጠግቼ ቆጣ ብዬ ተናገርኩ፡፡ “እየነገርኩህ እኮ ነው! እዚህ ጋ መለመን አይቻልም!” አልኩት፡፡ ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም ብሎኝ ከሽማግሌው ፊት ተገተረ፡፡ ዝምታውን ከንቀት ውጭ ትርጉም ልሰጠው አልችልም፡፡ በህይወቴ ደግሞ፣ እንደመናቅ የሚያበሳጨኝ ነገር የለም፡፡ “ሲነግሩህ አትሰማም እንዴ?” ብዬ ጮህኩበት። ዘወር ብሎ በትህትና አይን አየኝና ወደ ሽማግሌው ተመልሶ እጁን ዘረጋ፡፡ ከዚህ በላይ ልታገሰው አልችልም፡፡

ጋዜጣዎቼን አስቀምጬ ልገፈትረው ስዘጋጅ፣ ሽማግሌው የሳንቲሙን አንድ ብር ለማኙ እጅ ላይ አስቀመጡለት፡፡ የማይሰማ ምርቃት ሰንዝሮ ፊቱን ወደ እኔ መለሰ፡፡ በንቀቱ ተናድጄ የምለው ጠፍቶኝ እንደቆምኩ ለማኙ ወደ እኔ ቀረበ። ሳንቲሟን ወደ እኔ ሰንዝሮ፣ በእቅፌ ከያዝኳቸው ጋዜጦች ወደ አንዱ ጠቆመኝ፡፡ ግራ ተጋብቼ ዝም አልኩ፡፡ “ይቺን ልስጥህና ላንብብ?” አለኝ ለማኙ በትህትና፡፡ “ዘወር በል ከፊቴ፣ ስራ እንጂ ቀልድ አይደለም የያዝኩት!” አልኩና አፈጠጥኩበት፡፡ ምንም ሳይናገር ፊቱን አዙሮ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ይህ ከሆነ ከደቂቃዎች በኋላ … ያንኑ ለማኝ ከሃናን ዳቦ ቤት በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ አየሁት፡፡ ጭኖቹ ላይ ጋዜጣ ዘርግቶ ያነባል። እያነበበ በቅዳጅ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ይፅፋል፡፡ ጠጋ ብዬ የሚያነበውን ጋዜጣ ገፅ አየሁት፡፡

የሟቾች የ40ና የሙት ዓመት መታሰቢያ የሚቀርብበት ገፅ ነው፡፡ ለማኙ ቅዳጅ ወረቀቷን ወደ ኪሱ ከትቶ ብድግ አለ፡፡ ጋዜጣውን አጠፈና ዞር ዞር ብሎ የሆነ ሰው መፈለግ ጀመረ፡፡ ከኋላው ስለነበርኩ አላየኝም። ወዲያው ጓደኛዬ ወደሆነ ሌላ ጋዜጣ አዟሪ ሄደ፡፡ ጋዜጣውንና ሽማግሌው የሰጡትን ሳንቲም ለአዟሪው ሰጥቶ፣ ወደ ኡራኤል አቅጣጫ ፈጠን ብሎ ሲጓዝ አየሁት፡፡ ወደ አዟሪው ሄጄ ስለ ለማኙ ጠየቅኩት፡፡ ደንበኛው እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ለማኙ ስራ ፈላጊ ነው፡፡ ስራ የሚፈልገው ግን፣ ከክፍት ቦታ ማስታወቂያ ሳይሆን ከሙታን መታሰቢያ ገፅ ላይ ነው፡፡ የትኛው ቤተክርስቲያን የማን ተዝካር፣ በምን ቀን እንደሚወጣ ያነብና ወደዚያው ሄዶ በመረጃ የተመሰረተ የልመና ስራውን ያከናውናል፡፡

Read 2587 times