Saturday, 08 June 2013 08:22

የመግደል ጥበብ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(4 votes)

ካለፈው የቀጠለ

ምዕራፍ አራት፡

- የድብርት ቀን አንድ ቀን አመመኝ ብዬ ከትምህርት ቀርቻለሁ፡፡ ማመም ሳይሆን በቃ የዚያን ቀን እንዲሁ ደብሮኛል። ያው እናቴ ነገሮችን ያለ ምክንያት እንደማላደርግ ስለምታውቅ እንድቀር ፈቀደችልኝ፡፡ “ግን ምንህን ነው ያመመህ?” አለችኝ፤ ሻሿን እያሰረች፡፡ “እውነቱን ልንገርሽ ጆርጌ?” እናቴን በስሟ ነው የምጠራት፤ ጆርጌ የእናቴ ስም ነው፤ ጆርጌ ማለት በኦሮሚኛ ዘንጣፋ ማለት ነው፤ እናቴ በጣም ዘንጣፋ ናት፡፡ ቤተሰቦቿ ስሟን ያወጡላት ካደገች በኋላ ሳይሆን አይቀርም፤ አለበለዚያ አራስ እያለች እንዲህ ዘንጣፋ መሆኗን እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? “እውነቱን ንገረኝ” “አላመመኝም” “እና?” “ደብሮኝ ነው” “ደብሮኝ ነው ማለት?” “በቃ ቀፈፈኝ ትምህርት ቤት መሄድ” “እንዳሻህ፤ ግን ሰኞም፣ እሮብም፣ አርብም እየተነሳህ ደበረኝ እንዳትል” “እንደማልል ታውቂያለሽ” “አውቃለሁ” “እንደምታውቂ አውቃለሁ” “ወሬኛ፤ በል ና ሳመኝ” “ምንሽን?” “አፍንጫዬን” ፊቷን ሁሉ ሣምኩት፡፡

እናቴ የሸቀጥ ሱቅ አላት፤ በሷ ነው የምንተዳደረው፡፡ ብዙ ተርፎንም፣ በጣም ጎሎብንም አያውቅም፡፡ ከትምህርት የቀረው ቀን የሰፈር ልጆች ስላልነበሩ ሱቃችን አጠገብ እየተጫወትኩ ነበር፡፡ ሱቃችን ላይ ብዙ ጊዜ ቆሞ የሚያጨስ ሰው መጣ፡፡ ከወሬ እንደምሰማው፣ ብዙ ጊዜ እኔ በሌለሁበት እኛ ቤት ይመጣል፡፡ ዛሬ መጣ፡፡ ሲያየኝ ደስ አላለውም። “ጎረምሳው!” ሰባት አመቴ ነው፤ ይሄ ነገር ፍለጋ ነው፡፡ ቀና ብዬ አየሁት፡፡ “ትምህርት የለም እንዴ?” “አለ” “እና?” “እና ምን?!” “እዚህ ምን ታደርጋለህ?” “እዚህ እየተጫወትኩ ነው” “እንዴት፣ እንዴት ነው የሚያወራው ባካችሁ?! ለምን ከትምህርት ቀረህ?!” “ደብሮኝ” “ምን?” አሁን አኳሃኑ፤ አነጋገሩ ደሜን አፈላው፡፡ “ቆይ ግን አንተ ምን አገባህ?!” አልኩት በንዴት። ከምጫወትበት ተነሳሁ፤ ሲቀርበኝ፣ ሳፈገፍግ፣ ሲቀርበኝ፣ ሳፈገፍግ … እናቴ አየችን፡፡ “ሠው ጤፉ ምንድነው? አንተስ ምንድነው?” አለችን ሁለታችንም፡፡ አይታኝ ስሜቴን በደንብ ታውቃለች፡፡ መናደዴ ገብቷታል፡፡ ሰውየው እየቀረበኝ ነው፡፡ ቢያንስ ኩርኩም ሊያቀምሰኝ እንደከጀለ ያስታውቅበታል፡፡ “ማነው ያለችህ እናትህ?” “ሠው ጤፉ” “ምን ማለት ነው?” “ቆይ በጆሮህ እነግርሀለው” ቱር አልኩኝ፣ ከእጄ የሚተርፍ ድንጋይ አንስቼ ዥው አደረኩኝ፡፡ እናቴ ጩኸቷን አቀለጠችው። ሠውዬው ደሙን እያዝረከረከ አባረረኝ፤ አልያዘኝም፡፡ የመንደሩ ሰው ግልብጥ ብሎ ወጣ፡፡ ራቅ ብዬ የሚሆነውን እያየሁ ነበር፡፡ “ና ላስታጥብህ” አለችው እናቴ፡፡ የሆነ ነገር አላት፡፡

አልሰማሁትም፡፡ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ ሳቀ፡፡ ደሙን እያዘራ ሄደ፡፡ በነጋታው እናቴ ከቤት ጠፍታ ዋለች፡፡ በሚቀጥለው ቀን ሰፈር ቀየርን፡፡ ምዕራፍ አምስት፡- “ለምን ከሥራ ተባረርክ?!” አንድ ቀን ሽማግሌው እየጠጣን፡- “ይኼም የሚጠየቅ አይደለም፤ ግን ልጠይቅህ፤ ለምንድነው ከአንድም፤ ሁለት፣ ሶስቴ ከሥራ የተባረርከው፣ … ማለቴ የለቀቅከው?” “አይኔ ውስጥ ምንድነው እንኳ አለ የተባባልነው?” “እርግጠኝነት” “በዚያ ሳቢያ ነው ከሥራ የተባረርኩት” “እንዴት?” “በቃ አለቆችም፣ ምንዝሮችም እርግጠኝነቴን አይወዱትም” “እና ታዲያ አንተ ለምን አትተወውም?” “ምኑን?” “እርግጠኛ መሆኑን እና ከሥራ መባረርን” “እርግጠኛ አለመሆን አይቻልም፤ ለኔ” አይን ለአይን ተያየን፡፡ ምዕራፍ ስድስት፡- ሌላ የድብርት ቀን አንድ ቀንም ልክ ከሠላሳ አመት በፊት እንደሆነው አብሮኝ ከእንቅልፌ ተነሳሁ፡፡ እንደተለመደው ቁርሴን ሳልበላ ማስታወሻ ደብተሬን ይዤ አረቄ ቤት ሄድኩኝ፡፡ … የሆነ ነገር እየታወቀኝ ነው፤ የቀፈፈኝ ነገር እየታወቀኝ አይታወቀኝም ነበር፡፡ … ብቻ ወደ አረቄ ቤት ሄድኩኝ፡፡ ሽማግሌው ቀድሞ ጠብቆኛል፡፡ እንደ ወትሮው በስነ-ሥርዓት ሠላም አላልኩትም፡፡ ቤቱ ውስጥ ያሉትን በጅምላ ሰላም ብዬ ቁጭ አልኩኝ፡፡ አንደኛውን መለኪያ በተለመደው ፍጥነት ጨለጥኩት፡ ቀና ብዬ ስመለከት ሽማግሌው ፁጉሩን ተስተካክሏል፡፡ ከዚያ በፊት አይቻት የማላውቃትን ግንባሩ ፀጉር መጀመሪያ ላይ የምትጀምር እና ወደ ኋላ የምትሄድ ፍንክት፣ ጠባሳ አየሁበት፡፡ የሚገርመው እሷን እየፈለግኋት ነበር፤ ይገርማል፡፡

“አብዲሳ?” “እዚህ ጋ ምን ሆነህ ነው?” “ከሰላሳ አመት በፊት ነው … “ፊትህ ፀፀት የለውም ብለኸኝ ነበር … ይኼ ከተከሰተ ቀን ጀምሮ ሁሌ ፀፀት ይሰማኛል” “ምን ተከሰተ?” “አንድ ልጅ ፈነከተኝ” “ለምን?” “እእ … የሚነገር አይደለም” “መልካም” አወቅሁ፤ ይኼ ሠውዬ ነው ለካ ከሰላሳ አመት በፊት እናቴን እና እኔን ከሰፈራችን ያፈናቀለን፡፡ በደለኛ እሡ ነበር፤ ለዚህ ነው የሚፀፀተው፡፡ ግድ የለም ከፀፀቱ እገላግለዋለሁ፡፡ ምዕራፍ ሰባት፡- የመግደል ጥበብ “ኪያ?” አለኝ ሽማግሌው፡፡ ኪያ ስሜ ነው፤ እናቴ ያወጣችልኝ ስም ነው፤ ኪያ በኦሮሚኛ የኔ ማለት ነው፡፡ “አቤት?” “ለምን ጠየከኝ ስለፍንክቱ?” “ችግር አለው ስለፍንክቱ መጠየቅ?” “የለውም፤ግን አይኖችህ ልክ አይደሉም፤ ጥሩ አይደሉም፡፡” “አዎ ልክ አይደለሁም፤ ለዚያ ነው” ማስታወሻ ደብተሬን አንስቼ አዲስ ገፅ ገልጬ ይህን አረፍት ነገር ፃፍኩ፡፡ “አብዲሳ በቅርቡ ስለሚሞት ብዙ አትቅረበው” በጣም ጉልህ በሆኑ ፊደላት ነው የፃፍኩት፡፡

አስምሬበታለሁ፡፡ ለሽንት ብዬ ወጣሁ፡፡ ሽማግሌው ሁሌ እንደሚያደርገው ማስታወሻ ደብተሬን አንስቶ እንደሚያነብ እርግጠኛ ነበርኩ፤ በተለይ ዛሬ ያነበዋል፡፡ ከሽንት ተመልሼ ስገባ ሽማግሌው ተመሳቅሎ ጠበቀኝ፤ የሰው ፊት በፍርሃት እንዲህ ተረብሾ አይቼ አላውቅም፡፡ ሽማግሌው ያለ ወትሮው ቶሎ ቶሎ፣ ብዙ ብዙ ይጠጣ ነበር፡፡ በንጋታው ሽማግሌውን አረቄ ቤት አላገኘሁትም፡፡ በሚቀጥለውም ቀን አልመጣም፡፡ በኋላ ታሞ መተኛቱን ነገሩኝ፡፡ ማስታወሻ ደብተሬን ይዤ ልጠይቀው ሄድኩኝ፡፡ “አብዲሳ ምን ሆነህ ነው?” “ታምሜያለሁ” “ምንህን?” በዝምታና በፍርሃት እጄ ላይ ያለችውን ማስታወሻ ደብተር አያት፡፡ ብዙ ሳልቆይ፣ ብዙም ሳልናገር “እግዜር ይማርህ” ብዬ ወጣሁ፡፡ በር ላይ እንደደረስኩ “ኪያ” የሚል ድምጽ ሰማሁ፤ ሽማግሌው ነው፡፡ “አቤት” “ማስታወሻህ ላይ የፃፍከው …” ዝም ብዬ አየሁት፤ አንገቱን ደፋ፤ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ምዕራፍ ስምንት፡- የማይደገም ስድብ እናቴን ቀብር ላይ አይቻት ነበር፡፡ እዚያ ሳያት ገርሞኛል፤ ግን ብዙ አይደለም፡፡ ማታ እቤት ስገባ እስከዛሬ አይቼባት በማላውቅ አስተያየት አየችኝ፤ በጥርጣሬ እና በፍርሃት፡፡

“ሰውየውን እንዳገኘሁት እና እንደአወቅሁት እንዴት አወቅሽ?” “ሰሞኑን በእንቅልፍ ልብህ ስሙን እየጠራህ ስታቃዥ ነበር” “እና?” “ተከታተልኩህ፤ አረቀ ቤት ድረስ” “ለምን?” እንደምትገድለው አውቅ ነበር፤ ጆርጌ እኮ ነኝ፤ እናትህ እኮ ነኝ፤ አውቅሀለሁ” “እንደምታውቂኝ አውቃለሁ፤ መሞቱን ማን ነገረሽ?” “እጄ ላይ ነው የሞተው፤ እቅፌ ላይ፡፡ እንዴት አድርገህ ገደልኸው ግን?” “አይገባሽም” “አንድ ነገር ልንገርህ?” “ንገሪኝ” “አብዲሳ አባትህ ነበር፡፡” የምጠራው በአያቴ፣ በእናቴ አባት ስም ነበር፡፡ ጅል ልጅ ስላልነበርኩ አባቴ ማነው ገለመሌ ብዬ አላውቅም ነበር፡፡ እናቴ ለኔ ከብዙ በላይ ናት፡፡ አሁንም አልገረመኝም፡፡ “አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ?” “ጠይቀኝ” “ያኔ ምን ነበር ያለሽ? ከሰላሳ አመት በፊት ምን ነበር ያለሽ?” “አልነግርህም” አለች በእርግጠኝነት፡፡ አሁን ገረመኝ፡፡ ከሰላሳ አመት በኋላ የማይደገም ስድብ ምን አይነት ቢሆን ነው? እናቴ መቼም አትነግረኝም፡፡ ሠው ሁለቴ አይገደል ነገር? የታባቱንስና፡፡ ቅዠት የሌለው እንቅልፍ ተኛሁ፡፡

Read 2518 times