Saturday, 08 June 2013 08:30

“በእጅ የሚሮጠው ወጣት” አስገራሚ ታሪክ!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ወደቅሁ፤ ተጋጋጥኩ፤ ግን ተሳካልኝ

ስምህ ትርጉም ያለው ይመስላል--- ስወለድ አፈጣጠሬ የሚያስደንቅ ስለነበረ ፈቃዱ ዘገዬ አሉኝ፡፡ “እሱ እንደፈቀደ፣ እንደፈጠረው የሚያደርገውን ያድርገው” ለማለት ይመስለኛል፡፡ ታምሩ የሚለው ግን የቆሎ ት/ቤት እያለሁ የወጣልኝ ስም ነው፡፡ ይሄም ተመሳሳይ ትርጉም አለው፡፡ አፈጣጠሬ የሚያስደንቅ ስትል--- ሁለቱም እግሮቼ ስወለድ ወደ ኋላ ተቆልምመው ነው የተወለድኩት፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ ማለት ነው። የት ነው የተወለድከው--- ከላሊበላ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለች የገጠር ሰፈር (ምዢ ማርያም በምትባል ቦታ) ነው። እናቴ፤ አያቴ ቤት በቤት ሠራተኝነት ታገለግል ነበር። እኔ የተረገዝኩት አባቴ ከእናቴ ጋር በነበረው የምስጢር ግንኙነት ነው፡፡ አባቴ ሊዳር ሁለት ወር ሲቀረው እኔ ተወለድኩ።

ስትወለድ በቤት ውስጥ የነበረው ስሜት እንዴት ነበር፤ ካደግህ በኋላ ስትሰማ--- ለእናቴም ለእኔም መጥፎ እንደነበር ዛሬ ዛሬ እሰማለሁ፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ በመወለዴ የአባቴ ቤተሰቦች ‹‹ይሄ ልጅ ከእኛ ዘር አይደለም፤ ዘር አሰዳቢ ነው›› ይሉ ነበር፡፡ እናቴ መረራትና ጥላኝ ጠፋች፡፡ ለ3 ወር ብቻ ጡት አጥብታኝና ከተማ ገባች፡፡ ሴት አያቴ ደረቅ ጡቷን ታጠባኝ ነበር። እናቴ ካደግሁ በኋላ አልፎ አልፎ ቤተሰብ ለመጠየቅ ትመጣ ነበር፡፡ እኔን ያሳደገኝ አያቴ ነው። እስከ አምስት አመቴ ድረስ ከቤት መውጣት አልችልም ነበር፡፡ አፈና ተደርጐብኝ ሳይሆን በቃ መራመድ አልችልም፡፡ እንደ እባብ ነበር የምሳበው፤ በእጄ እየተራመድኩ፣ እጄን እንደ እግር እየተጠቀምኩ ማለት ነው፡፡ ሰው ስለሚያገለኝ ብቻዬን አወራለሁ፤ ብቻዬን እጫወታለሁ፡፡

አያቴ ቄስ ትምህርት ቤት እንድማር ይፈልግ ነበር…ያኔ በየደብሩ ቄስ ትምህርት ቤት አለ፡፡ እኔ ግን ፍላጐቴ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ በእጄ እየተሳብኩ …በሩጫም እንኳን የሚቀድመኝ አልነበረም፡፡ አያቴ የትምህርት ፍላጐት እንደሌለኝ ሲረዳ ከብት ጠባቂ አደረገኝ፡፡ እንዴት? እረኝነት አልከበደህም…ከአካል ጉዳተኝነትህ አንፃር ማለቴ ነው--- አያቴ በአካባቢው አሉ ከሚባሉ ሃብታሞች አንዱ ነበር፡፡ እንደ እግር እንድጠቀምበት አንዲት ነጭ ፈረስ ሰጠኝ፡፡ ከፈረሷ ጋር የሰው ያህል የሚያግባባን ንግግርና የምልክት ቋንቋ ነበረን። እረኝነት እንደ እኔ የተዋጣለት ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ጠዋት ፈረሷ ላይ ጉብ እልና ከብቶቹን ከበረታቸው አውጥቼ መስክ እወጣለሁ። ማምሻውን ወደ ቤት እመልሳቸዋለሁ፡፡ ፈረሷን ጠዋት የተጫንኳት ማታ ነበር የምወርደው፡፡ ከእኔ ጋር በጣም ተላምዳ ነበር። ባይንቀሳቀስም ጠንካራ ነበር፡፡ ከብቶች የሰው እርሻ እየገቡ አትቸገርም? የምጠብቀው ፍየሎች፣ ላሞች፣ አህዮች… ነበር። የዘር ወቅት ሲሆን ከሰው ማሳ ይገቡብኝ ነበር። ፈረሷ እንደፈለግሁት ላትሆንልኝ ትችላለች።

አንዴ ከብቶች የሰው ማሳ ገብተው እጭድ አድርገው በሉና ለአያቴ ክስ መጣበት…አይኔ እያየ እኮ ነው ማሳውን የበሉት…ግን ፈረሷን እንዴት አድርጌ ይዤያት ልግባ… ታጥሯል፡፡ ብቻዬን ያለ ረዳት ከመስኩ መሃል ስጯጯህ አመሸሁ፡፡ ቤት ስገባ ተገረፍኩ። አምስት ዓመት ሙሉ በእረኝነት ሰርቻለሁ፤ ፈረስ ላይ ቁጭ ብዬ፡፡ ከዚያ በኋላስ-- እግሬን ተነጠቅሁ - ፈረሴን፡፡ ከፈረሷ ጋር ብዙ ነገር አሳልፌያለሁ፡፡ አብረን ወድቀን ተነስተናል፡፡ ከሞት ሁሉ የዳንኩበት ሁኔታ አለ፡፡ ይዛኝ እየሄደች ድንገት ከወደቅሁ ዞር ብላ አይታኝ ትመለሳለች፡፡ ዛሬ ሳስባት ልክ የሰው ያህል …የእናት የአባት ፍቅር የምትሰጠኝ ፈረሴ ነበረች…እሷን ሳጣ አምርሬ ነበር ያለቀስኩት፡፡ አያቴ ግን ራቅ ወደ አለ ደብር ወሰደኝ። ለምንድነው ደብር የተወሰድከው--- ወለም ዘለም ሳልል እዛው ቁጭ ብዬ የቤተክርስቲያን ትምህርት እንድማር ነበር፡፡ ግን ለስድስት ወር እንደተማርኩ ‹‹ጐርሚጥ›› የሚባል በሽታ ያዘኝ፡፡ በሽታው አጥንት ይቦረቡራል…ትል ይፈጥራል፣ በጣም ሽታ አለው…ሰው መጠጋት አይቻልም፡፡ ቤተሰቦቼም ዞር ብለው ስላላዩኝና ህመሜም ስለበረታ ክሊኒክ ሄጄ መታከም ነበረብኝ። እየተጐተትኩ ወደ ክሊኒክ ሌላ የቄስ ተማሪ ነበር፤ አካል ጉዳተኛ ነው፡፡

እሱ ግን ማንከስ ብቻ ነው። ከእርሱ ጋር ተያይዘን እኔ እየተጐተትኩኝ ወደ ከተማ ሄድን፡፡ መንገዱ ለጤነኛ ሰው አራት ሰዓት ይፈጅበታል፡፡ እኔ ግን እየተጐተትኩኝ ስለሆነ ሁለት ቀን ፈጀብን፡፡ በህይወቴ አስከፊ ከምላቸውና ከማልረሳቸው ቀናቶች አንዱ ነበር…እንደ ኤሊ ነበር የምጐተተው፡፡ የሚያሳድረን ሁሉ አጥተን ነበር፡፡ ሲያዩኝ ይዘገንናቸዋል፤ ቁስሉም ስለሚሸት የሚጠጋኝም አልነበረም፡፡ መልካም ሰው ገጠመንና አሳደሩን፡፡ “አስከተማ” የተባለ ቦታ ነበር የምንሄደው፡፡ እዚያ ጤና ጣቢያ እንዳለ ሰምተን ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ሲያዩኝ ግን ‹‹እዚህ ልናክምህ አንችልም፤ መቆረጥ ስላለብህ ወደ ሌላ ሆስፒታል ሂድ” አሉኝ፡፡ በዛ ጊዜ ከህመሜ የተነሳ..ተቆረጠ አልተቆረጠ አይገደኝም ነበር፡፡ በጣም እየታመምኩ ስለነበር ባለፍንበት ጫካ ሁሉ እጽዋቱን፣ ሳሩን ቅጠሉን እየሸመጠጥኩና በእጄ እየጨመቅሁ ቁስሌ ላይ አፈስስ ነበር፡፡ ያገኘሁትን ቅጥላ ቅጠል እኮ ነው… ያብሰውም፣ ያድነውም በቃ ዝም ብዬ….. ብታምኝም ባታምኝም ግን ቁስሉ ዳነ፡፡ የሚፀጽተኝ የትኛው እጽዋት እንዳዳነልኝ አለማወቄ ነው፡፡ ግን ይቆረጥ የተባለው እግሬ ዳነ። (እግሩን ገልጦ አሳየኝ፡፡ ቁስሉ ጥሎት የሄደው ጠባሳ ይታያል) ከዳንክ በኋላ ወደ ደብሩ ተመለስክ? ወደ አያቴ ቤት ነው የተመለስኩት፡፡ ሲያየኝ “ወይኔ ልጄ በድየሃለሁ” ብሎ ተፀፀተ፡፡ እናትና አባትህስ? አይተውኝ አያውቁም፡፡

ብቻዬን ነኝ፤ ማን ይፈልገኛል፡፡ አንድ “ባለእጅ” ነበር፡፡ እኛ አካባቢ “ቀጥቃጭ” ነው የሚባለው፡፡ ማታ ማታ ወደ ጅብነት ይቀየራል ይሉታል፡፡ ይሄ ሰው “ወደ ሰቆጣ ይዤህ ልሂድ” … “እዛ ትለወጣለህ፣ ትምህርትም ትማራለህ… ከአሁን በኋላ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አናይም” ብሎ ጉዟችንን ጀመርን… ጉዞው እንዴት ነበር? የሰሜን መሬት ታውቂው እንደሆነ ወጣ ገባ ነው፤ በጣም ጠንካራ፤ ሻርክ ነው፡፡ እጄን አየሽው እሾህ ወጋግቶኝ… እጄ እንደ እግር ያገለገለች ስለነበረ እንዴት ጠንካራ እንደሆነ አልነግርሽም። አጥቢያ ላይ ዶሮ ሊጮህ ሲል ተነስተን ወደ ሰቆጣ ጉዞ ጀመርን፡፡ በእጄ ስለሆነ የምሄደው ይደክመኝና እቆማለሁ፡፡ ይሸከመኛል፡፡ ከዛ “ጉምራቅ” የተባለ ቦታ አደርን፡፡ በጣም ቀዝቃዛ ነው አገሩ፡፡ መኪና በህይወቴ አይቼ አላውቅም ተሳፍረን ስንሄድ መንገዱ ዚግዛግ ነው፤ አዋራው ይጨሳል…‹‹እመለሳለሁ ወደ አገሬ… አልፈልግም›› ብዬ አለቀስኩ…መኪናው የሚባላ ነገር ነበር የመሰለኝ፡፡ “ኧረ እባክህ ሰው ነው የሚነዳው” ቢሉኝ አሻፈረኝ አልኩ፡፡ ዕድሜህ ስንት ይሆናል ያን ጊዜ? አሥራ አንድ ዓመት ቢሆነኝ ነው፡፡ እንደምንም አሳምነውኝ ከተማ ገባን…ማታ ደግሞ ፓውዛውን መብራት ሳይ ፍርሃት ለቀቀብኝ…ጅብ እና ሌላ አውሬ እኮ አልፈራም፡፡ ይዞኝ የሄደውን ልጅ በጣም ፈራሁት፤ በረንዳ ነው ያደርነው፡፡

‹‹ባለ እጅ ነው፣ ቡዳ ስለሆነ ሌሊት ሌሊት ወደ ጅብነት ይቀየራሉ›› ስለሚባል ተጨነቅሁ፡፡ ሌሊት ከአሁን አሁን ጅብ ሆኖ ተቀይሮ በላኝ… በሚል ስጋት፡፡ ሌላ ታሪክ ለማውራት የማወራ አስመስዬ ስለ ቡዳ ማውራት ስጀምር ‹‹እናንተ እኛን ሰው ይበላሉ ትላላችሁ›› ብሎ አስደነገጠኝ፡፡ ባየው ባየው ግን አልነካኝም፡፡ ሰቆጣ ገባችሁ…ከዛስ? በጠዋት ገስግሰን ሰቆጣ መድሃኒያለም ደረስን። ለቄስ ት/ቤት ፈትነው አስገቡን፡፡ በየመንደሩ እየዞርን ‹‹በእንተ ስለማርያም›› እንላለን፡፡ ሁሉም ከንፈሩን እየመጠጠ ሳንቲም ይሰጠኛል፡፡ ‹‹ለምንድነው ሰው ሳንቲም የሚሰጠኝ›› እል ነበር፡፡ ቤተሰብ ፍለጋ አልመጣም? አንቺ ደግሞ እኔንማ ማንም አይፈልገኝም። የጓደኞዬ ቤተሰቦች ግን መጥተው አዩት፡፡ ወደ አገሩ ሲሄድ…ሰልባጅ አለባብሼው ዝንጥ አድርጌ ላኩት፡፡ እኔም ሳንቲም አገኝ ስለነበረ፣ ዘንጬ … “ማንነቴን ማሳየት አለብኝ” አልኩና… ወደ ሃሙሲት ገበያ አመራሁ፡፡ እዛ ገበያ ውስጥ አባቴን አገኘሁት፤ ለሸመታ ወጥቶ ነው፡፡ አህያ ይዞ መጥቶ ስለነበር በአህያ ተጭኜ ወደ አያቴ አገር ሄድኩኝ፡፡ የተወሰነ ገንዘብ ይዤ ስለነበር፣ አያቴንና አባቴን ጠላ ጋብዤ፣ ለአያቴ ገንዘብ ሰጥቼ ተመለስኩ፡፡ በመሃል ብዙ ውጣውረድ ደረሰብኝ፡፡ ረሃብ ችግር ብዙ ነገር።

መሄድ የለመደ ልብ ሆነና…ስለ ላሊበላ እሰማ ስለነበር ለጉዞ ተነሳሁ፡፡ በወቅቱ የነበረው ሁኔታም ሰርቼ ስለማልበላ በቤተሰቦቼ የምሬትና የንቀት ፊት ስላየሁ …ስለሰየቹን ሌት ተቀን በእንኩትት(በእጄ እየተንፏቀቅኩ) አንድ ቀን ከተጓዝኩ በኋላ “መሪ” የሚባል ወንዝ ደረስኩ…አካባቢው በሽፍታ የታወቀ ነበር፡፡ አንድ የታወቀ ሽፍታ ከርቀት ሲያየኝ በሆዱ እየተሳበ የሚሄድ አውሬ መስዬው አነጣጥሮ ሊገለኝ ነበር፡፡ ተጠግቶ ሲያየኝ ጐስቆልቆል ብያለሁ፡፡ ‹‹ሃጢያት ውስጥ አስገብተኸኝ ነበር›› አለና አንስቶ ምግብ አበላኝና ተሸክሞ የተወሰነ ስፍራ ድረስ ከሸኘኝ በኋላ ‹‹አይዞህ በርታ›› ብሎ ተመለሰ፡፡ ምን ብትሰማ ነው ወደ ላሊበላ ለመሄድ የተነሳሳኸው? እኔ በላሊበላ አድርጌ በጌምድር ለመድረስ ነው ያሰብኩት፡፡ ዋናው ፍላጐቴ የማጂክ ትምህርት ለመማር ነበር፣ ‹‹መተት›› የሚባለውን ነገር፡፡ ለምን መሰለሽ ይህን ጥበብ ለመማር የተነሳሳሁት? ሰዎች ይበድሉኝ ነበር፡፡ ‹‹ቆማጣ፣ ጐልዳማ፣ አንካሳ›› እያሉ ይሰድቡኛል፡፡ የበደሉኝን በመተት ማጥፋት እፈልግ ነበር፡፡ እንደውም ሰዎች ሰብሰብ ብለው ቁጭ ካሉበት ሄጄ መደባደብ ነበር ስራዬ፡፡ በአፌ ዱላ ይዤ እጋጠማቸዋለሁ - ተንኮለኛ ነበርኩ፡፡ ብቻዬን ነው ቦታ እየጠየቅሁኝ የምጓዘው፡፡ “ብልባለ” የተባለ ቦታ ደረስኩ፡፡ ሱር ኮንስትራክሽን ከብልባለ ላሊበላ መንገድ ይሰሩ ነበር፡፡ እነሱ ጭነው ላሊበላ ወሰዱኝ…እዚያ ግን የሚያሳድረኝ አጣሁ፤ ተንከራተትኩ፡፡ በመጨረሻ አንዲት ልጅ አሳዝኛት አስጠጋችኝ… እኔ እንግዲህ ሊቃውንት ምሁራን ወደአሉበት አካባቢ ሄጄ ጥበብ፣ ዕውቀት መቅሰም ነው ፍላጐቴ፡፡

ግን ሳላስበው ሁለት ዓመት ላሊበላ ተቀመጥኩ፡፡ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ዜማ፣ ቅኔ ተምሬ ጨረስኩ፡፡ የላሊበላ ህዝብ ደግ ህዝብ ነው። በኋላ ላይ ውስልትና መጣች፡፡ ምን ወሰለትክ? በትምህርቴ ግዴለሽነት አመጣሁ፡፡ የድብርትና ተንኮል ለመማር የመሄድ አሳቤን፣ አላማዬን አስረሳኝ የላሊበላ ቆይታዬ፡፡ በእጄ እሮጥ ነበር። ላሊበላ ላይ የምታወቀው “በእጁ የሚሮጠው›› እየተባለ ነው፡፡ ብዙ ህዝብ እያወቀኝ መጣ፡፡ አንድ ልጅ ግን መከረኝ ‹‹ፈረንጅ ስታይ በእጅህ እየሮጥክ ሂድ..›› ብሎ፡፡ ፈረንጅ ባየሁ ቁጥር በእጅ መሮጥ ሆነ፤ ፈረንጆቹ በጣም ይደነቁ ነበር፡፡ ገንዘብ በገንዘብ ሆንኩኝ… ጠላ፣ ጠጅ፣ አረቄ፣ መጠጣት ጀመርኩ፡፡ የቄስ ትምህርቱን ትውት አደረግሁት። ሊስትሮ ገዛሁና ጫማ መጥረግ ጀመርኩ፡፡ ሊስትሮዬን በትከሻዬ አዝዬ እየተንኳተትኩ መዞር ነው፡፡ ፈረንጆችን ሳይ ደግሞ ‹‹ትርዒት ላሳያችሁ›› እያልኩ በእጄ እሮጣለሁ… እንግሊዝኛ እንዴት ነው… ዘመናዊ ትምህርት አልተማርክም… አልተማርኩም፡፡ ግን ልጆች “እንደዚህ ብለህ ተናገር ይሉኝ ነበር፡፡ ከዚያ ላሊበላ የማሳየውን ትርዒትና የሊስትሮነት ስራ ትቼ ወልድያ ሄድኩ፡፡ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ሰቆጣ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ… በሊስትሮነት ሥራ አገሩን አዳረስኩት፡፡ ከዚያ ተመልሼ ወደላሊላ ሄድኩ፡፡ እዚያ የገጠመኝ ነገር ነው ለዛሬ ማንነቴ ያበቃኝ፡፡ ሁለት አሜሪካኖችን አገኘሁ፤ ባልና ሚስት፡፡ ባልየው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ስፔሻሊስት ነው፡፡

ዶ/ር ሞራስ ይባላል፡፡ ከአሜሪካ ለአጭር ጊዜ የበጐ አድራጐት ስራ የመጡ ናቸው፡፡ ላሊበላ እንዴት አገኘኻቸው? ለጉብኝት መጥተው ነው፡፡ ምርር፣ ድብር ትክዝ ብዬ ተቀምጬ አገኙኝ…እግሬን አገላብጠው ካዩት በኋላ “ይሄ ልጅ ቢታከም መዳን ይችላል…ወጪውን ሸፍኖ አዲስ አበባ ድረስ የሚያመጣው ቢገኝ” ሲሉ ለአንድ የቱርጋይድ ነገሩት፡፡ ከዚያ አንድ ብር ሰጡኝና ሄዱ፡፡ እርቦኝ ስለነበር…አምባሻ ገዝቼ በላሁበት፡፡ እድሜ ዘላለሜን እግሬን ታክሜ ይድናል የሚል ህልም ኖሮኝ አያውቅም፡፡ በጣም አሰብኩ፤ “እኔ ቆሜ ልሄድ ….. በፍፁም” አልኩ ለራሴ፡፡ የላሊበላ ህዝብ ሁሉ ያውቀኝ ስለነበር፣ ነገሩ በከተማው ተወራ፡፡ አዲስ አበባን ማለም ጀመርኩ። ገንዘብ ተዋጣ … የአውሮፕላን ትኬት ያኔ መቶ ስልሳ ብር ነበር፡፡ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፈረንጆቹ ሲያዩኝ አጨበጨቡ፡፡ ተደሰቱ። ቅዳሜ ገብቼ ማክሰኞ ኦፕሬሽኑ ተጀመረ። ኦፕሬሽኑ በጣም ከባድ ነበር፡፡ አሜሪካኖቹ ካከሙኝ በኋላ ሃላፊነቱን ዶ/ር ተመስገን ለሚባል የአጥንት ስፔሻሊስት ሰጥተው ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ በአጠቃላይ አራት ጊዜ ከባድ ኦፕራሲዮን አደረግሁ። ምን ያህል ጊዜ ፈጀ? አራት ወር፤ ግን በሆስፒታሉ በትክክል የተኛሁት አንድ ወር ብቻ ነው፡፡ ትልቁ ነገር ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ… እግርሽ፣ እጅሽ፣ አይንሽ፣ ቢታመም ምንም አይደለም፡፡ ትልቁ ነገር የአእምሮ ጨዋታ ነው፡፡ ቆሜ ለመሄድ ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ፡፡ ገና እግሬ ተሰርቶ ሳያልቅ ለመሄድ እሞክር ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በእግርህ መጓዝ ስትጀምር የተሰማህን ስሜት ታስታውሳለህ? መጀመሪያ በዊልቸር ነበር፡፡ ከዚያ ጐንና ጐን መደገፊያ ባለው ጐማ በሚመስል ነገር መንሸራተት ጀመርኩ፡፡ ቆሜ ስሄድ ዶክተሬ አላመነም፡፡ ቆሜ እየተራመድኩ የሄድኩት እሱ ቢሮ ነበር፡፡ ሲያየኝ ጭንቅላቱን ያዘ…ደስ አለውና አበረታታኝ። በጣም ይወደኝ ነበር፡፡

በኋላ ላይ ብረት ያለው ጫማ ተሰራልኝ፡፡ እሱንም በራሴ ጊዜ አውጥቼ ጥዬ ኖርማል ጫማ አደረግሁ፡፡ የብረት ጫማውን እስከአሁን ማድረግ ነበረብኝ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ግን ቁስለት ነገር ይሰማኝ አጥንቴና አጥንቴ የተያያዘበት ብረት መውጣት ነበረበት፡፡ ያ ማመርቀዝ ጀመረ፡፡ አስራ ሶስት ዓመት አብሮኝ ነበር፡፡ ይደማል ይመግላል፤ እኔ ግን አያስጨንቀኝም ነበር፡፡ ብረቱን ያወጣሁት የዛሬ ሁለት ዓመት ነው፡፡ አንደኛው እግሬ በጠቅላላ ሰላሳ አምስት ሴንቲ ሜትር ብረት አለው፡፡ እስከ አሁን ወደ ዘጠኝ ጊዜ ኦፕራሲዮን አድርጌያለሁ፡፡ እነዛ አሜሪካኖች አሁን ያለህበትን ያውቃሉ? ዶ/ር ተመስገንስ? ዶ/ር ተመስገን ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ አሜሪካ ሄደ፡፡ ለአሜሪካኖቹ “የቀለም ትምህርት መጀመር እፈልጋለሁ” ብዬ መልዕክት ልኬላቸው ነበር፡፡ በ16 ዓመቴ አንደኛ ክፍል ገባሁ፡፡ ሰዎቹ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለች አንዲት ፈረንጅ ጋር አገናኙኝ፡፡ እሷ ትረዳኝ ጀመር፡፡ 5ኛ ክፍል ሆኜ ቆሜ እንድሄድ የረዱኝ ፈረንጆች እኔን ለማየት ከአሜሪካ መጡ። ደስ አላቸው፡፡ አዝናኑኝ፡፡ ተመልሰው ሲሄዱ በየወሩ ብዙ ብር ይቆርጡልኝ ጀመር፡፡ ቤት ተከራይቼ ራሴን ማስተዳደር ጀመርኩ፡፡ ከዚያማ መጨፈር፣ ፓርቲ መውጣት ሽርሽር ሆነ፡፡ የከተማ ልጅ ሆንክ ማለት ነው… ታዲያስ! በአዲስ አበባ ያሉ ፓርቲ ቤቶችን፣ ዳንስ ቤቶችን ከጓደኞቼ ጋር ተንሸራሸርኩባቸው። ስፖርት እሰራለሁ፤ ክብደት አነሳ ነበር፡፡ በእጄ ደረጃ መውረድ ጂምናስቲክ ጀመርኩ፡፡ አንዲት ሙስሊም ወድጄ በፍቅር ልብሴን ሁሉ አስጣለችኝ።

የተዋወቅነው እንግሊዝኛ ቋንቋ በምማርበት ት/ቤት ውስጥ ነበር…እብድ አልኩላት፡፡ እሷ ደግሞ ካናዳ ሌላ ጓደኛ ነበራት፤ ጥላኝ ሄደች፡፡ አስረኛ ክፍል እያለሁ ማለት ነው፡፡ እስከ አስረኛ ክፍል አንደኛ እወጣ የነበርኩት ልጅ፣ በእሷ ፍቅር አቅሌን ስቼ ከስልሳ አንድ ተማሪ ስልሳኛ ወጣሁ፡፡ ጥላኝ ስትሄድ እንደማበድ አደረገኝ፤ ራሴን ለማጥፋት ተነሳሳሁ፡፡ የፍልስፍና መጽሐፍት ማንበብ ጀመርኩ በቃአጓጉል ሆንኩ፡፡ ፀጉሬን ሁሉ አሳድጌ ነበር፡፡ በኋላ ራሴን በራሴ መክሬ አገገምኩ፡፡ እንጦጦ አጠቃላይ ቴክኒክና ሞያ ገብቼ፣ በእልህ አንደኛ ወጣሁ፡፡ በጥሩ ውጤት ዲፕሎማዬን ይዤ ወጣሁና የራሴን ቢዝነስ ለመጀመር አሰብኩ። ስድስት ኪሎ አካባቢ ኢንተርኔት ቤት ከፈትኩ፡፡ ገንዘብ አጠራቅም ነበር። አይቲዬን እያጧጧፍኩ የሜንቴናንስ ስልጠና ወስጄ ጨረስኩ፡፡ አንድ ጓደኛዬ ሱዳን ይኖር ነበር፡፡ እየደወለ ‹‹ወደ አውሮፓ ልሻገር ነው ለምን አትመጣም?›› እያለ አነሳሳኝ፡፡ ሁለት ሰራተኛ ቀጥሬ እያሰራሁ ነበር፡፡ ከሞቀ የንግድ ስራዬ ተፈናቅዬ ያለኝን ሻሽጬ ሱዳን ገባሁ፡፡ በእግር ነው በአውሮፕላን? መጀመሪያ በህጋዊ መንገድ ኤምባሲ ስንጠይቅ አልተቀበሉንም፡፡ በህገወጥ መንገድ በመተማ አድርገን መሄድ አለብን ብለን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመኪና ጐንደር ደረስን፡፡ ጐንደር ላይ ተጨፈረ። አስረሽ ምችው ነበር፡፡ መተማም እንደዚሁ ጉዞ በእግር ተጀመረ፡፡ ከእኛ መካከል አንደኛው አጭበርባሪ ነበር፡፡

አረብኛ ቋንቋ ይችላል፡፡ እሱ መውጣት አይፈልግም፡፡ ሱዳን ጠረፍ ከደረስን በኋላ፣ የሱዳን ገበሬዎችን “ድንበር ጠባቂዎች በየት በኩል ናቸው” እያለ እነሱ ባሉበት ቦታ ወስዶ አስያዘን፡፡ ገንዘባችንንና የያዝነውን ሁሉ ቀምተውን ተመለሰን፡፡ አሁንም በእግራችሁ? ያውም እግሬ እየደማ፡፡ ግን ህልም አለኝ። ራሴን፤ ራዕዬን ስለማውቅ አውሮፓ በእግሬ ተጉዤ ገብቼ፣ ረጅም ፎቅ በክራንች ወጥቼ ወርጄ፣ ውጤት ማስመዝገብ ….የሆነ ሪኮርድ መስበር፣ ያለኝን ታለንት ማውጣት እፈልግ ነበር፡፡ ሱዳኖች ለኢትዮጵያ ወታደር አሳልፈው ሰጡን፡፡ ጐንደር መለሱን፡፡ እንደገና በሁመራ በኩል ሞከርን፡፡ ሁለት ሶስት ቦታ ተያዝን፡፡ አልሆነልንም፡፡ አስር ቀን ታስረን ለቀቁን። “ማይካድ ራት” የምትባል ከተማ ሄድን፡፡ ገዳሪፍ ገባን፡፡ ገዳሪፍ የተወሰነ ተሰባስበን ቀን ተጠራቅመን፤ ሱዳን ሄድን፡፡ ሱዳን ሁለት ወር ቆየሁ፡፡ ምን እየሰራህ? በሊቢያ አድርጐ ለመሻገር ወቅት ስላለው፣ ሱዳን ውስጥ ቆይተን በእግራችን ለመጓዝን ተነሳን። ግን ሊቢያ ድንበር ላይ ተያዝን፡፡ እየቀጠቀጡ እስር ቤት አስገቡን፤ ከዚያም በካርጐ መኪና አጭቀው ለሱዳን አስከረቡን፡፡ እዚያ ታሰርን፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሊሴ ፓሴ ሰጠኝና ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ።

ግን ባዶ እጅህን ነው… ሱዳንም ሄድኩ ሊቢያ ብቻ ኢንተርኔት በማገኝበት ቦታ ሁሉ ከሚረዱኝ ሰዎች ጋር ግንኙነቴን አላቋረጥኩም፡፡ ኢትዮጵያ ስደርስ ወደ 15ሺ ብር አካባቢ ላኩልኝ፡፡ ላይን ቱሪዝም ኢትዮጵያ ኮሌጅ በቱር ጋይድነት ተመዘገብኩና ለ2 ዓመት ተምሬ አጠናቀቅሁ፡፡ ክረምት ላይ ሰርከስ ጀመርኩ፡፡ ከማን ጋር ምን አላማ ሰንቀህ? ብቻዬን፡፡ አንድ ጓደኛዬ ነበር፤ ያየኛል፤ አብሮኝም ይሰራል፡፡ የማልሞክረው ነገር የለም። ኦፕራሲዮን አድርጌ በክራንች ነበር የምሄደው፡፡ ስለዚህ ለምን ተዘቅዝቄ በክራንች በእጄ አልሄድም ብዬ ተነሳሁ፡፡ በኢንተርኔት ላይ እንደዚህ ዓይነት ሪከርድ ያስመዘገበ የለም፡፡ በዚህ መንገድ ለምን ራሴን አላወጣም ብዬ ጀመርኩ፡፡ ወደቅሁ፣ ተነሳሁ፣ ተጋጋጥኩ፡፡ አሁን ከመቶ ሜትር በላይ እሄዳለሁ፡፡ የሚፈለገው በአንድ ደቂቃ ውስጥ ምን ያህል ሜትር ይኬዳል የሚለው ነገር ነው፡፡ በዓለም ላይ እንደዚህ ዓይነት ጅምናስቲክ የሚሰራ አለ? የለም፡፡ ተዘቅዝቆ በክራንች ላይ በእጅ በመሄድ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ቆየሁና ለምን በክራንች ላይ ሆኜ ደረጃ አልወርድም አልኩና ልምምድ ጀመርኩ፡፡

በተደጋጋሚ ወደቅሁ፤ ተጋጋጥኩ ግን አደረግሁት፡፡ ሪኮርዱ ተሳካልህ ወይስ? በአንድ ደቂቃ ከ76 ሜትር በላይ ተዘቅዝቆ በክራንች ላይ በእጅ በመሄድ ሶስት ድርጅቶች እውቅና ሰጥተውኛል፡፡ “ወርልድ ሪኮርድ አካዳሚ”፣ “ወርልድ ሪኮርድ ሴተር”፣ እና “ወርልድ ኦቶራይዝ›› ናቸው፡፡ የእነዚህ ሪከርዶች ባለቤት ነኝ፡፡ ሁለቱ ሪከርዶች ያገኘሁት በክራንች በመሄድ ነው፡፡ የራሴን ስም አስጠርቼ አገሬን ማስጠራት ነበር የምፈልገው፡፡ ይሄው ተሳካልኝ፡፡ ጊነስ ወርልድ ሪከርድ በዚህ ወር እውቅና ይሰጠኛል፡፡ ትርዒትህን ለማቅረብ ወደ ውጭ አገራት ሄደሃል? አሁን የምሰራበት “ሰርከስ ደብረብርሃን” ይባላል፡፡ አምስት ወር ይሆነኛል ከገባሁ፡፡ ነሐሴ ላይ ትርኢት ለማሳየት ወደ ስዊድን እንሄዳለን፡፡ በህይወቴ የተማርኩት ነገር ቢኖር ማንም ሰው ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት ነው፡፡ በተለይ አካል ጉዳተኞች፡፡ ምስጢሩ አካል ላይ ሳይሆን አእምሮ ላይ ነው፡፡ እዚህ ለመድረስ ያበቃኝ “እችላለሁ” ብዬ የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን መድፈሬ ነው፡፡ ብዙ እቅድ አለኝ፡፡ ነገን ነው የማስበው፡፡

Read 6213 times Last modified on Wednesday, 12 June 2013 15:43