Saturday, 08 June 2013 08:19

አዝናኝ ትዝታ

Written by  ከመድኃኔ ከዛርያስ pinued@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

አስገራሚ ሠርግ በ50ኛው ዓመት የአፍሪካ ህብረት ክብረ - በዓል ጉያ
በወርሃ ግንቦት፤ በ24ኛው ቀን፤ በ2005 ዓ.ም፤ አምስት ኪሎ ድህረ ምረቃ አዳራሽ የተፈፀመ የሰርግ ገጠመኝ ነበር የጽሑፌ መነሻ፡፡ ከዚያ በፊት ግን በቀጥታ ወደ “ገደለው” ሳንዘልቅ መግቢያ ነገር እናብጅ፡፡
ሠርግ የደስታውን ያህል ጣጣው ብዙ ነው፤ በየሠርጉ ውስጥ ብዙ ጉድ አለ፡፡ ሚዜዎቹ የጠፉበት ሠርግ ብዙ ነው፡፡ ሙሽሪትና ሙሽራው ተጣልተው የጠርሙስና የብርጭቆ መወራወር የተከሰተበት ቀውጢ ሠርግ ነበር፡፡ ድንኳን ላያቸው ላይ የወደቀባቸው ሙሽሮች፤ ነብሰ-ጡር ሙሽሪት ፍስስ ልፍስፍስ ብላ (fainting) የወደቀችበት ወዘተ. ብዙ አስደንጋጭ ገጠመኞች ታይተዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ አዝናኝ ናቸው ያልኳቸውን ጥቂት አጋጣሚዎች በየመልኩ ላቋድሳችሁ፡፡

የሰላም እርግብ ሰላም አጣች!
በአንድ ራሰ በራ፤ ፀጉሩ በጂሌት ምላጭ ሳይሆን በፕላስተር የተነሳ የሚመስል፤ ሙሽራ ሰርግ ላይ፣ አናቱ ላይ የሆነች እርግብ ለማስቀመጥ የመጡ አስተናጋጆች፤ በላብ የወዛው የሙሽራው ትኩስ መላጣ እያዳለጣት በሰላም መቆም ባለመቻሏ በጥፍሯ ቆንጥጣ ለመቆም በምታደርገው ጥረት ህመሙ የበረታበት ሙሽራ፣ በሰርጉ ቀን ለቅሶ ለቅሶ ሲለው ታይቷል፡፡

የእነቶሎ ቶሎ ቤት - ግድግዳው ሰንበሌጥ!
በሆነ ሰርግ ላይ ደግሞ ጥንዶቹ ኬክ ለመቁረስ የቆሙበት መድረክ በአልባሌ ብረት የተሰራ ሳንቃ ኖሮ ደልደል ያሉት ሙሽሪትና ሙሽራው ገና ሲቆሙበት ከእነ ኬካቸው ተከንብለው አፈር ቅመው ተነሱ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን አስደምሞኝ የነበረው የቪዲዮ ባለሙያው፣ ምንም ድንጋጤ ሳይስተዋልበት ሚዜዎችና እንግዶች ሙሽሪትና ሙሽራውን ለማንሳት ሲያደርጉት የነበረውን ርኩቻ አንድ ሳይቀረው ሪከርድ አድርጐ ማኖሩ ነበር፡፡

“በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት!”
በአንድ የሰርግ ስነስርአት ላይ ደግሞ የተጠራው እድምተኛና አዳራሹ የማይመጣጠን ሆኖ ወንበር ያጣ እንግዳ መተላለፊያው ላይ ተደርድሮ በመቆሙ ሙሽሮች ምግብ ለማንሳት መተላለፊያ አጡ፡፡ ፊታቸው ጠቆረ፡፡ እንግዶቹ ከሙሽሪትና ሙሽራው ትይዩ ቆመው በልባቸው “እናንተ ብሎ ጠሪ፤ እኛ ብሎ እድምተኞች” ያሉ መሰሉ በሆዳቸው፡፡

“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ!”
አንድ ጊዜ ደግሞ ጊዮን ሆቴል መናፈሻ ላይ በነበረ የፎቶ ፕሮግራም ከሞቅታም አልፎ ወደ ስካር የገቡ የሚመስሉ ዲያስፖራ ሙሽሪትና ሙሽራ፣ የሚዜና የአጃቢ ነገር ቁብ ሳይሰጣቸው እንዴት ከልባቸው ሲጨማጨሙ፣ ሥር-የሰደደ ስሞሽ (deep-kiss) ደረጃ ሲደርሱ ታዩ፡፡ ቀድሞ ነገርስ “በዚያች ቀን ያልታበደ መቼ ይታበዳል?” ያሉ ይመስላሉ፡፡ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ!!
ለጊዜው የእኔ ገጠመኞችን እዚህ ላይ ገታ አድርገን ከእኔ በተሻለ ሊያዝናኑ የሚችሉ ትዝታዎችን እንደሚያስታውሱአችሁ ግን ተማምነን ወደ ዛሬው ጽሑፍ ልውሰዳችሁ፡፡
50ኛው የአፍሪካ ህብረት በአሉታ ወይም በአዎንታ ጥሎት የሄደው ትዝታ ለመኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ መንገዶች እየተዘጉ ስንቱን ፀጉር አስነጭተዋል፡፡ አሁን የተከፈተው መንገድ ከአንድ ማስታወቂያ ቆይታ በኋላ እንመለሳለን የተባለ ይመስል ይዘጋል፡፡ ቤቶች ለ50ኛው መንገድ ሲባል ፈርሰዋል - ሆኖም አሪፍ አሪፍ መንገድ አግኝተናል፤ “ፈጣን ልማት” አይተናል፡፡ ዱሮ ለማኞች ይታፈሱና እሥር ቤት ይታጐሩ ነበር፣ ቆሻሻ በአሮጌ ቆርቆሮ አጥር ይከለል ነበር፡፡ (በአአድ ሰሞን)…ወዘተ
ለነገሩ እንደ እኔ እምነት የድህረ ምረቃው አዳራሽ ገጠመኝ ከአዝናኝነቱ ባለፈም ታሪካዊ ፋይዳው የሚጐላ መስሎ ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም ይህን የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት ክብረ በአል በተከበረበት ሳምንት የተደገሰው ሰርጋቸውን አስታክኮ የሙሽሪትና የሙሽራው ዘለአለማዊ ዝክር በሚሆነው በቪዲዮና በፎቶ ታሪካዊ ማስታወሻ ለማኖር ሃሳቡን ያፈለቀውንና በተግባር ያዋለውን ግለሰብ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡
ጥንዶቹ እንደ ቀደሙት አባትና እናቶቻችን ሙሽራዎች እፍረትና መሽኮርመም የማያውቃቸው ስለነበሩ ወደ አዳራሹ በመጡባት ክፍት ዳፕ መኪና ህዝበ አዳምን በየአደባባዩና በየመንገዱ ሰላም እያሉና እየደነሱ፣ ከዚያም ከመኪና ወርደው ወደ አዳራሹ ባደረጉት ጉዞ ዘና፤ ፈታ ብለው እየጨፈሩ የሚጓዙ ዓይነት ናቸው፡፡
የምግብ መስተንግዶና፤ ጭፈራው፤ ሌላም ሌላም ፕሮግራም በአዳራሹ ውስጥ ተካሄደ፡፡ ከዛም ዲጄው “የኬክ መቁረስ ስነ ስርአት ከአዳራሹ ውጭ በክፍት አየር ላይ ይካሄዳል” ሲል አወጀ፡፡
“ከአዳራሽ ውጭ ኬክ ቆረሳ ምን ሊፈይድ ይሆን?” ሳልል አልቀረሁም፡፡ የሆነው ሆኖ ዲጄውም ማጫወቻዎቹን አዘጋጀ፤ የፎቶና የቪዲዮ ባለሙያዎች መብራቶቻቸውን አምቦግቡገው ካሜራዎቻቸውን ወድረው በመጠባበቅ ጀመሩ። ኬክ አዘጋጆች ኬካቸውን አዘጋጅተው ሲቀርቡ የሁሉም እድምተኛ ትኩረት ኬኩ ላይ ሆነ፡፡ በሚገርም ሁኔታ ኬኩ በአፍሪካ ካርታ ቅርጽ የተሰራ ሆኖ ሙሉ በሙሉ በአረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለም የተዋበ ሲሆን ዙሪያውን ቁራጭ ኬኮች ተዘጋጅተው የሃምሳ ሁለቱ (52ቱ) የአፍሪካ ሀገራት ባንዲራ ተሰክቶባቸዋል፡፡ አስደማሚ ትእይንት ነበር!!
ሙሽሪትና ሙሽራው ወደ መድረኩ ለመውጣት ሲዘጋጁ ዲጄው፤ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ካቀረቡት ንግግር በፊቸሪንግ በማስገባት፣ በቀጣይም አፍሪካ ነክ ሙዚቃዎችን በማከታተል ካሰማ በኋላ የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር ለቀቀ፡፡ ሁለቱ ሙሽሮች ወታደራዊ ሰላምታ እንደሚያቀርብ ወታደር በተጠንቀቅ ቆመው መዝሙሩ ተዘመረ። ከዛም ባንዲራ የተሰካበትን ኬክ ተራ በተራ እንድንወስድ ተደርጐ ሁላችንም እጆቻችንን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ በአፍሪካ ሙዚቃዎች ጭፈራና ዳንስ ተከተለ፡፡

ታሪካዊ ፋይዳው
…እስቲ በምናብ መርከብ 50 ዓመታት ወደፊት እንቅዘፍና እ.ኤ.አ 2063 ላይ ደርሰናል እንበል። አፍሪካ እንደ ምኞቷ አንድ የመሆን ህልሟ ተሳክቶ በአንድ የገንዘብ ኖት፤ በአንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በመሳሰሉት ጉዳዮች መጠቀም ጀምራለች። ኢትዮጵያም ድህነትን ታሪክ አድርጋ የላቀ የኢኮኖሚ እድገት ተቀዳጅታለች፡፡ እንዲሁም የአፍሪካ መዲና መቀመጫ በመሆኗ ለህብረቱ ያላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የዛሬዎቹ ሙሽራዎች ቢያንስ የ80 አመት አዛውንት ይሆናሉ፤ ካደላቸውም አባት እልፍ ሲልም አያት ሆነው ይህን ፊልም ከልጅና ልጅ ልጆቻቸው ጋር ይመለከቱታል። ያኔ የዛሬው ትውልድ ከባለፉት ትውልድ የሃገር ፍቅርንም ሆነ ፓን አፍሪካኒዝምን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ሲያካሂድ የነበረውን ትግል ጐልቶ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ የዚያን ዘመን ተረካቢ ትውልድም ይማርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
የሙሽሮቹ ቤተሰብና መጻኢ ልጆቻቸው ይቅርና እኔ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢና ሌሎች ካሜራና ሞባይላቸውን አውጥተው ታሪክ ለማስቀረት ሲጣደፉ የነበሩ እድምተኞችን ያስደመመው ይህ ትዕይንት ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የጥቁር አፍሪካዊ ስሜትን አጉልቶ ያሳያል። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ድል አለ?

እንደመሰናበቻ
ያው የአፍሪካ ባንዲራ የተሰካበት ኬክ ሲከፋፈል፤
እኔ ለኬክ ቆራሹ፡ “ለእኔ የደረሰኝ ኬክ ባንዲራ የማን ሀገር ይሆን?”
ኬክ ቆራሹ፡ “የአፍጋኒስታን” አለኝ፤ ኬኩን ወደ እጄ እያቀበለ፡፡
ቸር ሰንብቱ!!!

Read 6671 times Last modified on Saturday, 08 June 2013 08:37