Print this page
Saturday, 08 June 2013 08:05

የወንደ-ላጤውና የሰራተኛዋ “ሜሞ”

Written by  ቢኒያም ሐብታሙ
Rate this item
(8 votes)

ይህች ጽሑፍ በአንድ ወቅት በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት አብሮኝ ይሰራ ስለነበር ናሆም የተባለ ወንደ ላጤና ስለሰራተኛው ገበያነሽ (ጋቢ) የምንጨዋወትባት አሪፍ ወግ ናት፤ ዘና በሉ… ቅድመ - ወግ ናሆም እድሜው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ምርጥ ልጅ ነው፤ በቃ ሙድ የገባው፣ የአራዳ ልጅ የምትሉት አይነት … ተቆራርጣ የምትደርሰው የወር ደሞዙ ባለ አራት ዲጂት ልትሆን ትንሽ የቀራት … በዛችው ደሞዙ ቤት ተከራይቶ ተመላላሽ ሰራተኛ ቀጥሮ የሚኖር … “እቺን ደሞዝ በምን አይነት ብልሃት ነው የምታብቃቃት?” ሲባል “በአስማት” የሚል፣ ኑሮን ቀለል አድርጎ የሚኖር ምርጥ ልጅ … ገበያነሽ፣ እንደ ናሆም ሁሉ ሙድ የገባት ስትሆን፣ ጎበዝ፣ የ10ኛ ክፍል የማታ ተማሪ ናት፡፡ ናሆም ጨምሮ ወደ አምስት የሚደርሱ ወንደ-ላጤዎች ጋር በመስራት ራሷን የምታስተዳድር ሁለገብ ፍሪ-ላንሰርም ነች … ጋቢ በጠዋት ተነስታ የሁለት ወንደ-ላጤ ቤቶችን ስራ አቀለጣጥፋ ጨርሳ፣ ናሆም ቤት ወደ አራት ሰዓት ገደማ ትደርሳለች፡፡

ናሆም ደግሞ ከእሁድ በስተቀር ከሁለት ሰዓት በፊት ከቤቱ ስለሚወጣ ከጋቢ ጋር የሚገናኙት በ “ሜሞ” (አጭር የፅሁፍ ማስታወሻ) ነው፡፡ የናሆምና የጋቢ ሜሞዎች ትዕዛዝና መረጃ ከመለዋወጫነት በዘለለ ስለ ብዙ ጉዳዮች በስፋት የሚያወጉበት፣ የሚቀላለዱበት፣ የሚበሻሸቁበት፣ የሚደናነቁበት … ወዘተ ነው፡፡ እነዚህ ብጫቂ ወረቀቶች በሁለቱ መካከል ያለውን ንፁህ እህታዊና ወንድማዊ ግንኙነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ሲሆኑ፤ ስነፅሁፋዊ ይዘታቸዉም የሚናቅ አይደለም፡፡ ሜሞዎቹን ሲያሻቸው በእንግሊዝኛ፣ አልያም በአራዳ ቋንቋ ስለሚፅፏቸው አንዳንድ ጊዜ ከፅሁፍ ይልቅ ወሬ ቢመስሉም ስርዓተ-ነጥብን ሳይቀር በአግባቡ ያካተቱና አንዱ ከሌላው በቅርፅም በይዘትም የማይገናኙ ናቸው፡፡ አስቂኝ ወሬ ወይም ተረባ በመሃከል ካለ የሳቅ ድምፃቸውን ሁሉ ሳያስቀሩ ያስገባሉ፤ ናሆም - ካካካካ … ጋቢ - ቂቂቂቂ … እያለች፡፡ ደስ ብሏቸው ይፃፃፋሉ … አንዱ የሌላውን ለማንበብ ይቸኩላል … እንኳን እነሱ እኛም ሳንቀር የቢሮ ስራችንን የምንጀምረው በእኒህ አዝናኛ ፅሁፎች ነበር፡፡

እንደውም፣ እነዚህን ፅሁፎች ማሳተም አለብህ እያልኩ እወተውተው ነበር፡፡ ወደፊት “የወንደ-ላጤናውና የሰራተኛዋ ሜሞ” በሚል ርዕስ እንደሚያሳትማቸው ከልብ እየተመኘሁ ከሜሞዎቹ በጥቂቱ እነሆ … ፅሁፎቹ እንደወረዱ የቀረቡ ናቸው፡፡ ቀን፡ 10/4/2001 ዓ.ም ይድረስ፡- ለገበያነሽ (Arrive: for Marketing) ካካካካ … ጋቢዬ፣ ዛሬ ጓደኛዬን እቤት ምሳ ስለጋበዝኩት ቤቷን ሰንደል ጨስ አድርጊባትና አሪፍ ምሳ አዘጋጂልን፣ አራት ድንችና ሶስት ራስ ሽንኩርት አለ፡፡ በሱ አሪፍ፣ ጣት የሚያስቆረጥም ጥብስ ፍርፍር ስሪልን … ካካካካ … ለማንኛውም ለእንጀራና ሌላ መግዛት የምትፈልጊው ነገር ካለ ብዬ ኮመዲኖው ላይ ሃያ አምስት ብር አስቀምጬልሻለሁ፡፡ መልስ ካለ እዛው አስቀምጪልኝ፣ በተረፈ መልካም ፈተና፡፡ ናሆም፣ ከማይነበብ ፊርማ ጋር ቀን፡ 10/4/2001 ዓ.ም ይድረስ፡ ለናሆም … ኡኡቴ! አንተን ብሎ ምሳ ጋባዥ … ቂቂቂቂ … ለማንኛውም አራቱ ድንቾች ትንንሽ ስለሆኑ ግማሽ ኪሎ ድንች ገዝቻለሁ፤ ከዛ ውጪ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና እንጀራ ገዝቼ የተረፈውን 1 ብር ከ50 ኮመዲኖው ላይ ላስቀምጠው ብዬ እናቴ “ለታላቅ አይመለስም” ትል የነበረው ትዝ ሲለኝ ይዤው ሄጃለሁ … ቂቂቂቂ … በተረፈ በአራት ድንችና በሶስት ሽንኩርት የሚሰራ ጥብስ ፍርፍር ስለማልችልበት አልጫ ድንች፣ ወጥና … ጥብስ … አምሮህ እንዳይቀር ብዬ … ጥብስ ቅጠል ያለው ፍርፍር ሰርቼልሃለሁ … ቂቂቂቂ … ያው ወጡ ከቀዘቀዘባችሁ አሙቃችሁ ብሉ … ዘይት ስለጨረስኩ ለነገ ብር አስቀምጥልኝ፡፡

ቻው፣ ገበያነሽ ቀን 11/4/2001 ዓ.ም ይድረስ ለጋቢያንስ ኧረ ጋቢያችን! ጨዋታ ጨምረሽ የለ እንዴ? የትላንቱ ተረብሽን አልቻልኩትም፣ ልቤ እስኪፈርስ ነው ያሳቅሽኝ … ወጡም በጣም አሪፍ ነበር፣ እኔ እምልሽ፣ ቅቤ ደግሞ ከየት አምጥተሽ ነው? ከሼባው ወንደላጤ ቤት ቋ አድርገሽ እንዳይሆን? ቤተሰብ አደረግሽን እኮ … ካካካካ … በነገራችን ላይ፣ ቤት ውስጥ ምንም አስቤዛ በሌለበት ምግብ የምትፈጥሪው ነገር ብዙም አይገባኝም፣ ለነገሩ እንዲገባኝ አልፈልግም፣ በአስማትም ይሁን በፀሎት ዋናው ቁም ነገር የሚበላ ነገር መኖሩ ነው፡፡ የትም ፍጪው … (Where crash bring my ash) አይደል የሚባለው … ካካካካ … መቼም ባንቺ መላ ባይሆን ኖሮ ይቺ ደሞዜ ሁለት ሳምንት እንኳን በቅጡ እንደማታዘልቀኝ ታውቂዋለሽ፡፡ ለማንኛውም በድጋሚ አመሰግናለሁ፣ የኔ አስማተኛ … ካካካካ … የዘይት ብር ኮመዲኖው ላይ አስቀምጬልሻለሁ፡፡ ፒስ ባይ - ናሆም ቀን 11/4/2001 ዓ.ም ለ፡ እርሶ አንተ ነገረኛ! እንደው ምን ይሻልሃል … ለማንኛውም ወጡ ቅቤ አለው ምናምን ያልከውን ወሬ ቅቤ ያለው እስኪመስል ይጣፍጣል ለማለት ከሆነ ከአንገቴ ሰበር፣ ከወገቤ ጎንበስ ብዬ ተቀብዬዋለሁ … ይህቺ የፈጠርካት ታሪክ ግን ብዙም አልተመቸችኝም፤ እኔኮ ፕሮፌሽናል ነኝ! እንዴት ከአንዱ ቤት ወስጄ ለሌላው እሰራለሁ፣ ከአስራ ሁለት የስነ ምግባር መርሆች መካከል አንዱ ታማኝነት እንደሆነ ረሳኸው? ቂቂቂቂ … ለማንኛውም ሀሳብህን በመርህ ደረጃ ተቀብዬዋለሁ፡፡

ባይሆን ሚስጥሩን ልንገርህ፣ አንዳንድ ጊዜ ምንም አስቤዛ ሳይኖር ምግብ የምሰራልህ ከራሴ ቤት እያመጣሁ ነው፤ ምክንያቱም ስለምታሳዝነኝና ስለምታዝናናኝ … በዛ ላይ ልክ እንደ ወንድሜ ስለማይህ ነው፡፡ በል አሪፍ ምስር ወጥ ሰርቼልሃለሁ፤ አሙቀህ ብላ … ያጠብኳቸውን ልብሶች አልጋው ላይ አጣጥፌ አስቀምጬልሃለው … ብር ስላልነበረኝ እንጀራ አልገዛውልህም፡፡ እደር፣ ጋቢ ይህች ቀጣይዋን ሜሞ ኖሆም በጋቢ የምግብ ዘይት አጠቃቀም በጣም ቅር በመሰኘቱ የፃፋት ናት፡፡ ለአንድ ወር የሚገዛትን አንድ ሊትር ከግማሽ ዘይት እሷ በሁለት ሳምንት ጭጭ ስለምታደርጋት እንዲህ ሲል ፅፎላታል … ለተከበሩ … ጋቢሽካ፣ የትላንቱ ምስር ወጥ በጣም አሪፍ ነበር፤ ነገር ግን ቅባት በጣም ስለበዛበት ነው መሰለኝ ጨጓራዬ ሲነድ ነው የዋለው፡፡ ሌላ ነገር ይሆናል እንዳልል ውጪ አልመገብም፣ ባለፈው ሳምንትም የሰራሽልኝን ድንች ወጥ ቅባቱን እየፈራሁ በልቼው በቃ ምን አለፋሽ፣ አንቆራረጠጠኝ … ስቃጠል ነው የዋልኩት … ለማንኛውም ካሁን በኋላ የምትሰሪልኝ ወጦች ላይ ዘይት በጣም አትጠቀሚ፡፡

በዛ ላይ ደግሞ የልብ በሽታ እንዳለብኝ ነግሬሻለሁ አይደል? በዘር ነው መሰለኝ እኛ ቤት ሁሉም የልብ በሽታ ታማሚ ስለሆነ ለዘይት የሚደረገው ጥንቃቄ ለየት ያለ ነው፡፡ ሰሞኑን ደረጃ ስወጣ ሁሉ ልቤ ድው ድው እያለች ነው፡፡ እናም … ባጭሩ … እንዳልጭርብሽ ለማለት ያህል ነው! ካካካካ … በነገራችን ላይ ሶስቱን የፊዚክስ ጥያቄዎች በትክክል ሰርተሻቸዋል፤ የሆነ የተሳሳትሽው ስቴፕ ነበረ፤ እሱን ምልክት አድርጌበታለሁ፡፡ በደንብ እይው፡፡ ቻው! ናሆም ለ፡ እርሶነቶ … ናሆሜ ለምንድን ነው እስከ ዛሬ ድረስ ያልነገርከኝ! እኔ እኮ ላንተ ማሰቤ ነበር፤ ጣፍጦህ እንድትበላ ብዬ ነው ቅባት የማበዛው፡፡

ለማንኛውም ከአሁን በኋላ አስተካክላለሁ፡፡ አይዞህ! አትጭርም … ቂቂቂቂ … ለልብ በሽታህ ደግሞ ጠዋት ጠዋት ትንሽ ዱብ ዱብ በልባት … ሰሞኑን ብር ሳታስቀምጥልኝ እየወጣህ ስለሆነ ምንም ነገር አልገዛሁልህም፤ ሽሮም የመጨረሻዋን ዱቄት አራግፌ ነው የሰራሁልህ … ለነገ ምን እንደምሰራልህ አሳውቀኝ … ደህና እደር፣ ጋቢ ጋቢ ከተጫዋችነቷና ከምስኪንነቷ ባሻገር የዋህ ቢጤ ናት፤ የነገሯትን ሁሉ አምና የምትቀበል … ከቅርበታቸው የተነሳ ስለ ዘይቱ የፃፈውን ሜሞ አንብባ “በግልፅ ዘይቴን አትጨርሺ አትልም…” ብላ ኩም የምታደርገው መስሎት ነበር፤ ነገር ግን ልጅቷ ጋቢ ናት … አምና ተቀብላዋለች፡፡

በነገራችን ላይ ምንም እንኳን በመሃከላቸው ጥሩ ቅርርብና ግልፅነት ቢኖርም የዘይት ቅነሳውን እውነተኛ ምክንያት ለምን እንዳልነገራት ናሆምን ስጠይቀው እንዲህ ነበር ያለኝ … “ባክህ! እሷ ምስኪን ስለሆነች እንደዛ ካልኳት፣ ዘይት ከራሷ ቤት እያመጣች ልትሰራልኝ ትችላለች፤ ያን ደግሞ እኔ አልፈለግሁም …” የናሆምና የጋቢ መተሳሰብና መዋደድ በጣም የሚያስቀና፣ የሚያዝናና … ብዙ ብዙ የሚባልለት ነው … እስኪ በመጨረሻ ጋቢ ከላይ ለፃፈችው ሜሞ፣ ናሆም የፃፈላትን መልስ አስነብቤያችሁ ወጌን ላብቃ … ለ፡ ጋቢሻ … ጋቢቾ! ፒስ ነው አይደል? ጠፋህ ነው ያልሽው? አንቺ ምን አለብሽ … አምስት ደሞዝ እየበላሽ … ካካካካ … ለማንኛውም የጠፋሁት … ያው እንደምታውቂው አራተኛው ሳምንት አይደል፤ እናም ብር ኔፕ ሆኜ ነው … ለአስቤዣ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስለሌለኝ ለእራት የሆነች ነገር ይዤ እገባለሁ፡፡ ባይሆን “ምን ሰርቼ ልሂድ?” ላልሽው፣ ምንም ሳትሰሪ ከምትመለሺ ፑሻፕ ሰርተሽ ሂጂ … የቻልሽውን ያህል … ካካካካ … ሰራሁልሽ … ካካካካ … ናሆም፣ ቻው!

Read 8105 times