Saturday, 08 June 2013 07:51

መንግስት የህዝብን ጥያቄ በ3 ወር ውስጥ እንዲመልስ ሰማያዊ ፓርቲ ጠየቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

ሰማያዊ ፓርቲ ዋና ዋና ያላቸውን አራት የህዝብ ጥያቄዎች በመያዝ ባለፈው ግንቦት 25 ያካሄደውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሠልፍ፣ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት እና የመንግስት ተወካዮች “የሀይማኖት አክራሪነት አጀንዳ” ነው ማለታቸው ተልካሻ አስተያየት ነው ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ተቃወመ፡፡ “መንግስት ሠማያዊ ፓርቲ ህጋዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ ባደረገባቸው የህዝብ ጥያቄዎች ላይ ተልካሻ ምክንያቶችን እያቀረበ ከመፈረጅ ይልቅ በሶስት ወራት ውስጥ የህዝቡ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በድጋሚ እንጠይቃለን” ብሏል በመግለጫው፡፡ ፓርቲው በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ሠማያዊ ፓርቲ ከመንግስትም ሆነ ከገዢው ፓርቲ በሚሰጥ የትኛውም ማስፈራሪያ ከጀመረው ሰላማዊ ትግል ፍፁም ወደ ኋላ እንደማይል ገልፆ፤ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ እስኪመልስ ትግሉን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው አስፍሯል፡፡

ፓርቲው አክሎም፤ መንግስትና ገዢው ፓርቲ በሰጡት አስተያየት፤ “የሀይማኖት አክራሪነትን አጀንዳው አድርጐ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ዛሬ በጠራው ሰልፍ ድብቅ አጀንዳው ገሀድ ወጣ” በማለት የሰጡት አስተያየት፤ ፓርቲውን ለማንቋሸሽና ለማራከስ የተደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል አጣጥሏል፡፡ “በህጋዊ መንገድ ተጠይቆና ራሱ መንግስት አምኖበት ይሁንታ የሠጠውን እጅግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተካሄደ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ፣ ውጭ አገር የሚገኙ ሀይሎች ተላላኪ አድርጐ ማቅረብ “የአብዬን ወደ እምዬ” አይነት ማላከክ ነው ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መልክ ዕውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀሰውን ፓርቲያችንን መንግስት እንዳልተቀበለው ተገንዝበናል ብሏል ፓርቲው፡፡ “መንግስት በፓርቲው ላይ እያደረሠ ያለው አጉል ፍረጃ የገዢው ፓርቲ አባላት ለንግግራቸው ሚዛን እንደሌላቸው ያሳያል” ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ከፍርጃ ውጭ ሰማያዊ ፓርቲ ከሽብርተኝነት ጋር የሚያገናኘውን አንዳችም ነገር አልጠቀሱም ሲል ተችቷ፡፡

ፓርቲው ቀደም ሲል በሰጣቸው መግለጫዎች በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደረገውን ጣልቃ ገብነት መቃወሙን አስታውሶ፣ ይህንኑ ጥያቄ በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ወደ አደባባይ ይዞ መውጣቱ ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከባለስልጣኑ የተሰጠው አስተያየት፣ የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ ዜጐች በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ወደ ሽብርተኝነት ፍረጃ ለመክተት የሚያደርገው ጥረት ፓርቲውን በእጅጉ ማስቆጣቱን በመግለጫው አካትቷል፡፡ የትኛውም ፍረጃና ከመንግስት የሚመጣ ማስፈራሪያ ከሰላማዊ ትግሉ እንደማያግደው የጠቀሰው ሰማያዊ ፓርቲ፤ መንግስት በሙስና፣ በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት፣ በኑሮ ውድነትና በዜጐች ማፈናቀል ዙሪያ ከህዝቡ የተነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በሶስት ወራት ውስጥ ምላሽ እንዲሠጥ ጠይቋል፡፡

Read 4975 times