Print this page
Saturday, 01 June 2013 13:38

የመግደል ጥበብ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(3 votes)

ምዕራፍ አንድ፡- በሬ ከአራጁ ይውላል ‘You are a murderer whether you know it or not’ ይህን አረፍተ ነገር ያገኘሁት አንድ ለዳጄ ያዋሠኝ መፅሐፍ ላይ ነው፡፡ መፅሐፉ ለኢ-ልብ ወለድ ፀሐፊዎች እና አንባቢዎች የተፃፈ ነው፤ The Art of Non Fiction ይላል (የፅሁፌን ርእስ ያስተውሏል፤ የመግደል ጥበብ ነው የሚለው፤ The Art of Homicide እንደማለት ነው)፡፡ መፅሐፉ የቲዎሪ፣ የጋዜጣ እና በሁለቱ መካከል ላይ የ middle range መጣጥፎችን በጥሩ ሁኔታ ለመፃፍ እና እነዚህን ፅሑፎች በጥሩ ሁኔታ ለማንበብ ተብሎ የተፃፈ ነው፡፡ የመፅሐፉ ፀሐፊ ይህን አረፍተ ነገር እንደ ምሳሌ የጠቀሰችው፣ የመጣጥፍ መግቢያ ላይ እንዲህ አይነት አረፍተ ነገር ብንጠቀም እንዴት አትኩሮት መሳብ እንደምንችል ለማሳየት ነው፡፡ በርግጥም አትኩሮት ይስባል፤ “አወቃችሁትም አላወቃችሁትም ሁላችሁም ነፍስ አጥፊዎች ናችሁ፡፡”

ሲባል የማን ቀልብ ነው የማይሳብ? የገዳይንም፤ የህይወት አፍቃሪ እና አክባሪንም፣ ቀልብ እኩል ይስባል፡፡ በተለይ የገዳይን ሳይሆን የህይወት አፍቃሪ እና አክባሪን ቀልብ የበለጠ ይስባል፡፡ ንፁህ ሠው አውቀህም ሆነ ሳታውቅ ነብስ አጥፊ ነህ ሲባል … ግልፅ ነው፤ ቀልቡ ይሳባል ብቻ ሳይሆን ይደነግጣል፡፡ ገዳይ ያው ገዳይ ነው “መግደል” የሚባል ነገር ያለበት ነገር ሁሉ አትኩሮቱን ይስበዋል፡፡ እኔ ግን ‘You are a murderer whether you know it or not’ የሚለውን እንደመግቢያ የተጠቀምኩበት አትኩሮት ለመሳብ ብዬ አይደለም። ሠው ገድዬ ነው፡፡ ይህን ፅሑፍ የፃፍኩት ከቀብር መልስ ነው፡፡ ሰውየውን የገደልኩት እኔ ነኝ፤ አገዳደሌ ግን ረቀቅ ያለ ስለሆነ እኔ ነኝ የገደልኩት ብዬ ለፖሊስ እጄን ብሰጥ ይስቁብኛል፤ እብድ ነው ብለው ይሳለቁብኛል፤ ስለዚህ ልብ-ወለድ ነው ብዬ መጻፍን መረጥኩ፡፡ በሬ ከአራጁ ይውላል ያልኩለትን ሠውዬ የተዋወቅሁት እሱ የ67 አመት እኔ የ37 ዓመት ሠዎች ሆነን ነው፡፡ ፀጉሩ ሙሉ ነጭ ነው፡፡ አይኖቹ የህፃን ልጅ ይመስላሉ፡፡ ቀጫጫ ነው፡፡ እድሜው አልታየኝም ነበር፡፡ ሠውየውን የወደድኩት ገና እንዳየሁት ነበር፡፡ እጅግ ውስብስብ በሆነ ሁኔታ ከስራ ተባርሬአለሁ፡፡

ተቀማጭ ገንዘብ ስለሌለኝ እና ጠጪ ስለነበርኩ፣ በአንድ ጊዜ ነው ከትልልቆቹ መደብር ወደ አረቄ መንደር የወረድኩት፤ እና የመጀመሪያውን አረቄ ስቀምስ እና ሠውየውን ቀና ብዬ ሳየው የሆነ ምስጢራዊ ስሜት ተሠማኝ፡፡ ከሠውየው ጋር እንደ ተያየን ደንግጠናል፤ ተዋደናል፤ እንደተዋደድን ሁለታችንም አውቀናል፡፡ ለመነጋገር ብዙ ጊዜ ወሰደብን፡፡ ሁልጊዜ ግን ሳናወራ እናወራ ነበር፡፡ ሠውየው ለምሳሌ እንዲህ ይላል፡፡ “እኔ እኮ አብዲሳ …” ስሙን ማንም ሳይነግረኝ አወቅሁት፡፡ (ስሙን አስተዋወቀኝ) ሲያወሩ ብዙ ጊዜ ‘እኔ እኮ እከሌ…’ እንደሚሉት አይነት ሰዎች አይደለም፡፡ የራሱን ስም ሲጠራ ራሱ አፉ ላይ ባዕድ ይሆንበታል፡፡ እራሳቸውን ደጋግመው እንደሚጠሩ እና እንደሚያደንቁ አይነት አይደለም፡፡ ያኔ “እኔ እኮ አብዲሳ…” ሲል የነበረው ስሙን እኔ እንዳውቅለት ነበር፡፡ ሠውየው አረቄ ቤት ስንት ሠዓት እንደሚመጣ፣ ስንት አረቄ እንደሚጠጣ፣ ስንት ሠዓት እንደሚወጣ አውቃለሁ፡፡ እሱም የእኔን እንደሚያውቅ ያስታውቅበታል፡፡

ምዕራፍ ሁለት፡- “ለምንድነው የምትወደኝ?” አንድ ቀን ስካር አድሮብኝ በጠዋት አረቄ ቤት ሄድኩ፡፡ ቁርስ አልበላሁም ነበር፤ እንቀጠቀጥም ነበር፡፡ የመጀመሪያውን መለኪያ ስጠጣ መረጋጋት ጀመርኩ፡፡ “ይኸውላችሁ ልጆች ሠው አትናቁ” አለ ሽማግሌው ለሌላ ሠው እያወራ ያለ ይመስላል፤ ግን እኔን ነበር የሚያየው፤ ወይም እኔን እያየ ለሌላ ሠው የሚያወራ ነበር የሚመስለው፤ ሀቁ ግን እኔን እያየ ለእኔ ነበር የሚያወራው፡፡ አየሁት እና ከት ብዬ ሳቅሁ፡፡ ሁሉም አፈጠጡብኝ፡፡ ሁሉም ሠካራሞች በጠዋት ተስፋ በቆረጡ እና በሚያስቆርጡ የሠካራም አይኖቻቸው አፈጠጡብኝ፡፡ ድንገተኛ፣ ደባሪ ፀጥታ ሠፈነ፡፡ “ምን ያስቅሃል?” አለኝ ሽማግሌው፡፡ “ሠው አልንቅም እኔ!” “ሠው ትንቃለህ ማን አለህ?” “አብዲሳ” “ስሜን ማን ነገረህ?” “አንተ፤ ማለቴ እራሶት” (አንተ፣ አንቱ ስል ድምፄ ውስጥ ማመንታት የለም፤ አማራጭ ነው ያለው፤ የቱን ልበልህ አንተ ወይስ አንቱ ነው፡፡) “መቼ? መቼ ቀን ነገርኩህ?” “ሀምሌ አስራ አንድ ቀን” “ጎበዝ ልጅ፡፡ እኔም አስታውሳለሁ፡፡

ሠው እንደማትንቅ ይህ ብቻ በቂ ነው፡፡ የዚያን እለት ለሀምሌ ሚካኤል አጥቢያ አስሬ አብዲሳ ስል የነበረው አንተ ስሜን እንድታውቅ ስለፈልግሁ ነበር፤ የዚያን እለት ስታየኝ አስተያየትህ ‘ስምህ ማነው?’ የምትል ይመስል ነበር፡፡ አብዲሳ ማለት ተስፋዬ ማለት ነው፡፡” “አውቃለሁ” “ማን ነገረህ?” “አንተ በለኝ፤ አጠራጠረህ እና አስተያየትህ ውስጥ ክብር ስለለ እሱ ይበቃል” “አመሰግናለሁ አብዲሳ” “በል ተነስ አሁን፤ ቁርስ ስላልበላህ ቁርስ ልግዛልህ” ተያይዘን ቁርስ ልንበላ ወጣን፡፡ ሰንጋ ተራ ቶታል ጋ ያለው ምግብ ቤት ሄድን፡፡ “ቁርስ ምን ልግዛልህ?” “’ምን ልግዛልህ’ አይባልም፤ ልጋብዝህ ነው የሚባለው” “አንተ እራስህ ነህ ይህን አባባል የምትጠቀመው፤ ካንተ ነው የተማርኩት፡፡ አረቄ ቤት ሰው ስትጋብዝ ‘አረቄ ልግዛልህ ወይ?’ ነው የምትለው፤ ልጋብዝህ አትልም” አስተናጋጁ መጥቶ አጠገባችን ዣንጥላ ሆኖ ቆመ፡፡ “ጋሽ አብዲሳ ምን ላምጣ?” “ለኔ የተለመደውን፤ ለዚህ ሠውዬ የሚፈልገውን ጠይቀው” “እሺ?” አለኝ አስተናጋጁ፡፡ “አብዲሳ የለመደውን አምጣልኝ” “ላንተ አይሆንም” አለ አብዲሳ፡፡

“እንዴት?” “የእንቁላል አለርጂ አለብህ” “እንዴት አወቅህ?” “ስታወራ ሰምቼ ነው፤ ከአሁን በኋላ እንዴት አወቅህ የሚለውን እንተወው” ሳናወራ እያወራን ነበር የኖርነው፡፡ ትንሽ ዝም ከተባባልን በኋላ፡- “አንድ ነገር ልጠይቅህ፤ የሚጠየቅ አይደለም፤ ግን ልጠይቅህ” አለኝ ሽማግሌው፡፡ “መልካም” “እንደምትወደኝ አውቃለሁ፤ ማወቅ የፈለግሁት ለምን እንደሆነ ነው፡፡ ለምንድነው የምትወደኝ?” “እኔ ሠው ወድጄ አላውቅም” “እኔን ግን ትወደኛለህ አይደል?” “አዎ” “ለምን?” “ፊትህ በጣም ይገርማል፤ ሀጢአት የምታውቅ አትመስልም፤ ፀፀት የለበትም ፊትህ፤ ፀፀት ብቻ ሣይሆን ሥጋትም የለበትም፤ ይገርማል፤ እንዲህ አይነት ፊት ያላቸው ሰዎች የሉም፡፡ አይንህን ሳየው ሁሌ እረጋጋለሁ፡፡ እንደ አንተ አይነት ንፁህ አይኖች አይቼ አላውቅም፡፡” “ስለኔ ሳይሆን ስለ ራስህ የምታወራ ነው የሚመስለው” “ለዚያ አይመስልህም ታዲያ የምወድህ?” “ስለ አይን ስታወራ አስደገነጥከኝ፤ አይኔ ውስጥ ጭካኔ አለ?” “የለም፤ ሙቀት ነው ያለው” “ያንተ አይን ውስጥ ግን አለ፤ ጭካኔ አለ” “ጭካኔ አይደለም” አልኩ በእርግጠኝነት፡፡

“አዎ፤ ጭካኔ አይደለም፤ ግራ ይገባል፤ ጭካኔ ይመስላል ግን ያስፈራል፤ ሠው ስታይ ታስፈራለህ” “አውቃለሁ፤ አስራ አንደኛ ክፍል እያለሁ ጌታቸው የሚባል እንግሊዝኛ አስተማሪያችን ስታየኝ ስለማልወድ እኔ ክፍል ውስጥ አትግባ ብሎ ለምኖኝ፣ እኔ እሱ ክፍል ላልገባ እሱ ጥሩ ውጤት ሊሰጠኝ ተስማምተን አድርገነዋል፡፡ ኮሌጅ እያለሁ፣ ነፍሱን ይማረውና ኤፍሬም የሚባል ሲቪክስ አስተማሪያችን ‘ምናባህ ታፈጥብኛለህ፤ የምፈራህ መሰለህ?!’ ብሎ ተማሪ ሁሉ እስኪታዘበው ጮኋል፡፡ ሰዎች ሳያቸው ይረበሻሉ” ለረዥም ጊዜ ዝም አልን፡፡ በዝምታችን ቆይታ፣ ሽማግሌው እያየሁት ፀዳሉ ፈካ፡፡

“ታውቃለህ…” አለኝ አለመጠን ተደስቶ እና ኮርቶ፡- “ታውቃለህ አሁን አይደለም የመጣልኝ፤ አይንህ ውስጥ ስላለው ነገር ካየሁህ ቀን ጀምሮ ነበር አስብ የነበረው፤ ሁሌ አስብ ነበር፤ ብታምንም ባታምንም በህልሜ አይኖችህን ብቻ አይ ነበር፤ አይኖችህን ብቻ፤ አሁን ደረስኩበት፤ አይኖችህ ውስጥ ምን እንዳለ ታውቃለህ?” “አውቃለሁ” ምን እንደሆነ ሳልነግረው ተሽቀዳድሞ “ቆይ እኔ ነኝ እምነግርህ፤ የሚገርምህ ግኝት ነው፤ አይኖችህ ውስጥ ያለው እርግጠኛነት ነው፤ ታይቶ የማይታወቅ እርግጠኝነት አይኖችህ ውስጥ አለ” “በትክክል ተመልሷል” ማስታወሻ የመያዝ ልማድ አለኝ፤ ሁሌ ከእጄ የማይጠፋ አፈርማ ቀለም ያለው ማስታወሻ ደብተር አለኝ፡፡ በጣም አጠር ያለ ማስታወሻ ስለምወስድ ይህ ማስታወሻ ደብተር እጄ ላይ ከርሟል፤ ገና ይከርማል፡፡ አሁን ከሽማግሌው ጋር ያወራናቸውን እና የማረኩኝን አንዳንድ ነገሮች ማስታወሻዬ ላይ አሰፈርኩ፡፡ እንደጨረስኩ ሽማግሌው፡- “ይህቺ ነገር ከእጅህ አትጠፋምና!” አለኝ፡፡

“አዎ፤ ላስታውሳቸው የምፈልጋቸውን ነገሮች እከትብብታለሁ” አልኩት፡፡ ምዕራፍ ሶስት፡- “ሠው ጤፉ” እኔ እና ጤፍ ኢትዮጵያዊ እና እንጀራ ተመጋቢ ከመሆነ የዘለለ ቅርርብ አለን፤ “ሠው-ጤፉ” እየተባልኩ ነው ያደግሁት፡፡ እናቴ ጎረቤቶቿ ተፅእኖ የሚያሳርፉባት አይነት ሴት አልነበረችም፡፡ ቡና ከጎረቤት ጋር አትጠራራም፤ ማህበር (ፅዋ) አትጠጣም፤ እቁብ አትሰበሰብም፣ አትጥልም ነበር፡፡ እድር ውስጥ የነበረችውም ግድ ሆኖባት ነው፡፡ እናቴ ለተፅእኖ አትመችም፡፡ ልጅ ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር ስጫወትም (ከምወደው ልጅ ጋር እጫወታለሁ፤ ከማልወደው ጋር አልጫወትም) ሆነ ስጣላ ከቁብ የማስገባው ልጆቹን እና አቅሜን ነው፡፡ ልጆቹ ነገር ከፈለጉኝ ቤተሰቦቻቸውን ፈርቼ አልተዋቸውም፤ እላቸዋለሁ። ስጣላ ታዲያ ከፍተኛ ፀብ ነው የሚሆነው፡፡ በእድሜ እና በጥንካሬ የሚበልጡኝን ከቅርብ ከሆነ እናከሳለሁ፤ ከሩቅ ከሆነ፤ እፈናከታለሁ፡፡ እኩዮቼን በቦክስ እና በጠረባ እዘርራለሁ፡፡

ከደፋርነቴ እና ከዘደኝነቴ ሁሉ ልቆ ያስከበረኝ ቂመኝነቴ ነው፤ ቂም አልረሳም፡፡ ልጆች ብዙ ጊዜ ትምሕርት ቤት ተጣልተው ‘ቆይ ሰኔ ሰላሳ ላግኝህ’ ሲሉ ዝም ብለው ማስፈራራታቸው ነው፤ የአፍ-ልማድ ሆኖባቸው፤ የምራቸውን አይደለም፡፡ እኔ ግን ‘ሰኔ ሰላሳ ላግኝህ’ ካልኩ በቃ እንዲያ ማለቴ ነው፡፡ ሰኔ ሰላሳ ብዙ ጊዜ ቢዚ ነበርኩ፡፡ ታላቅ ወንድም አለኝ ብሎ ወይም በቤተሰቦቹ ተመክቶ የሚጣላኝ ብዙ የለም፡፡ ለዚያ እናቴ አለች። ማን እንደ ነገራት፣ እንዴት እንደ ደረሰችበት ባላውቅም ያለ ምክንያት ወይም በሰንካላ ምክንያት እንደማልጣላ ታውቃለች፡፡ የጎረቤት እናቶች እና አባቶች አባብለውም ተቆጥተውም አይልኩኝም፤ መቼ ሰምቻቸው። ታላቅ ለምን እንደሚከበር አይገባኝም ነበር፤ ብዙዎቹ የሚከበሩ አልነበሩም፡፡ ሲልኩኝ እምቢ ስል ከመቱኝ እማታለሁ፤ ከተቆጡኝ አንጓጥጣለሁ፤ ከሰደቡኝ ጆሮዋቸው ሞልቶ እስኪፈስ ብዙ ነገር እላቸዋለሁ፤ ስድብ አይደለም፤ አልሰድባቸውም፤ ለኔ እንደሚመስሉኝ እነግራቸዋለሁ፤ ብዙ ጊዜ ልክ ነበርኩ፡፡ ‘ሠው-ጤፉ’ የሚለው ስም የወጣልኝ ያኔ ነው፡፡

መጀመሪያ ማን እንዲያ እንዳለኝ አስታውሳለሁ፡፡ ወ/ሮ አበበች ነበሩ። (ሊልኩኝ ፈልገው አመናጭቀው በንቀት ሲጣሩ በጣቴ ምልክት ሰደብኳቸው፡፡ በጣም የተከበሩ ሴት ነበሩ፤ ቴሌቪዥን ነበራቸው፤ ሁሉም ልጅ ሳይጠሩት ሊላካቸው ይፈልጋል፤ እናም ሁሌም የኔ ኩራት፣ አለመታዘዝ ከሁሉም በላይ ያናድዳቸው ነበር፡፡) ከዚያ በኋላ ስሜ ሆኖ ቀረ፡፡ እናቴም ደስ ሲላት “ሠው-ጤፉ” ትለኝ ነበር እየሳቀች፤ አናቴን እየዳበሰች፡፡ አቤት ደስ ሲለኝ፣ እሷ እንዲያ ብላ ስትጠራኝ፡፡ “ሠው ጤፉ” ብሎ ፈሊጥ ይገርመኛል፡፡ ሌላ ቦታ፣ ከሌላ ሠው ሠምቼው አላውቅም፤ የትም ቦታ አንብቤው አላውቅም፡፡ ሁሌ እንጀራ ስለምበላ ሁሌ ትዝ ይለኛል፤ ሁሌ ፈገግ እላለሁ፡፡ “ሠው-ጤፉ” የሚገርም ንፅፅር ነው፤ የጤፍ ቅንጣት እና የበቆሎ ፍሬ እራሱ ከባድ ንፅፅር ነው፡፡ ለዚያውም ለሰባት ዓመት ልጅ የዋለ ንፅፅር ሲሆን ይገዝፋል፡፡ ወይዘሮ አበበችን አሁን አከበርኳቸው፡፡ (ይቀጥላል)

Read 2849 times